Saturday, September 23, 2023

‹‹የአንድነት መንግሥቱ››ን አደጋ ላይ የጣለው የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ዕርምጃ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

መቶ በመቶ ሊባል በሚችል ድምፅ ከእናት አገሯ ከሱዳን ከተገነጠለች አምስተኛ ዓመቷን አስቆጥራለች፡፡ ሁለት ዓመታት ገደማ ግን በራሷ ፖለቲከኞች የውስጥ አለመግባባት የተነሳ በጦርነትና በሁከት ለማሳለፍ ተገዳለች፡፡

በደቡብ ሱዳን ቀውስ ላይ ጎረቤት አገሮችና ኃያላን አገሮች ጣልቃ ለመግባት ተገደዋል፡፡ እስካሁን በአንፃራዊነት ፍሬያማ የተባለለት ውጤት ያስገኘው በኢትዮጵያ ፊታውራሪነት የሚመራው የኢጋድ የዕርቅና የሽምግልና ሒደት ነበር፡፡

ለረዥም ዓመታት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን ያገለገሉትና በአሁኑ ወቅት ደግሞ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው በመሥራት ላይ የሚገኙት አቶ ሥዩም መስፍን በልዩ ልዑክነት የሚመሩት የኢጋድ ሸምጋይ ቡድን፣ ሁለቱን ተፋላሚ ወገኖችን ለማስታረቅ ከዓመት በላይ ያለሰለሰ ጥረት ያደረገ በመሆኑ ‹‹የጋራ መንግሥት›› ቅርፅ ያለው አካል እስከ መፍጠር ደርሰው ነበር፡፡

የቀውሱ መነሻ በተለያየ መንገድ የሚገለጽ ቢሆንም በአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና በምክትላቸው ዶ/ር ሪክ ማቻር መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ዋነኛው ነው፡፡ ይህ ለአንድ ዓመት የቆየው የሽምግልና ሒደት ብዙ ውጣ ውረድ የገጠመው ቢሆንም፣ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ውስጥ የተፈረመው ስምምነት ግን በብዙዎች ዘንድ ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡ አሁን ግን ያንን ስምምነት አደጋ ላይ ይጥላል የተባለለት ምክትል ፕሬዚዳንቱን በሌላ ሰው የመተካት ዕርምጃ ተወስዷል፡፡

ስምምነቱ ሁለቱም መሪዎች ከምንም ዓይነት ግጭትና ትንኮሳ እንዲታቀቡ፣ የፌደራል ገጽታ ያለው መንግሥት እንዲዋቀር፣ የአገሪቱ የጦር ኃይልም በአንድ አመራር ጥላ ሥር እንዲሆን የሚሉ ነጥቦች ተግባራዊ እንዲደረጉ ይደነግጋል፡፡

ዋናው አጨቃጫቂ ጉዳይ ከሥልጣን ክፍፍል ጋር የተያያዘው አለመግባባት ነው፡፡ የፕሬዚዳንቱ ሥልጣን ተቀንሶ ለምክትላቸው እንዲሰጥና የሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ሚዛን እንዲጠበቅ ማድረግ ለትግበራ እጅግ አስቸጋሪ የሆነ ሐሳብ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ከአገራቸው ውጪ (ብዙ ጊዜ አዲስ አበባ ነበሩ) የቆዩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ዶ/ር ማቻር፣ የቀድሞ ሥልጣናቸውን እንዲይዙ ፕሬዚዳንቱም በያዙት ቦታ ላይ እንዲቀጥሉ ነው በመጨረሻ ስምምነት ላይ የተደረሰው፡፡  

የስምምነቱ ዋና የመሠረት ድንጋይም ጁባ ላይ የጋራ የአንድነት መንግሥት መመሥረት ሲሆን፣ ስምምነቱ ከተፈረመ ዘጠኝ ወራት ቆይቶም ቢሆን ተግባራዊ ለማድረግ ተሞክሮ ነበር፡፡ ባለፈው መጋቢት ወር ላይ ዶ/ር ማቻር በስደት ከቆዩበት ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ ዋና ከተማዋ ጁባ በመጓዝ የተሰጣቸውን ሹመት ተቀብለው እነሆ ለሁለት ወራት ያህል ቦታው ላይ ቆይተው ነበር፡፡

ከአንድ ወር በፊት ግን በሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች መካከል (ማን እንደጀመረው ማረጋገጥ አልተቻለም) ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ፕሬዚዳንቱ ያልተገባ ዕርምጃ ወስደዋል ተብለው እየተወቀሱ ይገኛሉ፡፡ ሳልቫ ኪር ተቀናቃኛቸውን ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ማቻርን ከቦታቸው አንስተው ቦታው ላይ ሌላ ሰው ማስቀመጣቸውን ያወጁ ሲሆን፣ በአደራደሪዎችም ሆነ ከድርድሩ ጀርባ ባለችው ኢትዮጵያም ዕርምጃው አሳሳቢ እንደሆነ እየተገለጸ ነው፡፡

‹‹ሕገወጥ ዕርምጃ››

በሁለቱም የፀጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ ዶ/ር ማቻር በመኖሪያቸው ላይ ጥቃት እንደተሰነዘረ ገልጸው ነበር፡፡ ሁለቱም መሪዎች ችግሩን ለማቀዝቀዝ ተኩስ እንዲቆም መግለጫ ሰጥተውም ነበር፡፡ ሆኖም ዶ/ር ማቻር ረዘም ላለ ጊዜ ወደ ሥራ ቦታቸው ሳይመለሱ የቆዩ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንቱ ምክትላቸውን ወደ ቤታቸው ተመልሰው እንዲገቡ አሳስበዋል፡፡ ያስቀመጡት ቀነ ገደብም አልፏል፡፡ ከዚህ በኋላ ሳልቫ ኪር ምክትላቸውን አንስተው አዲስ ሰው (ታባን ዴንግ ጋይ የተባሉ ጄኔራል) ቦታው ላይ ማስቀመጣቸውን በማወጃቸው፣ ዕርምጃቸው ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተቃውሞ እየገጠመው ይገኛል፡፡

ዶ/ር ማቻር ጁባ ከተማን ለቀው መውጣታቸው የተዘገበ ቢሆንም፣ በስልክ ለአልጄዚራ እንደገለጹት ግን ጁባ ውስጥ ናቸው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ማናቸውም ከሥልጣን የማውረድም ሆነ አዲስ ሰው የመሾም እንቅስቃሴ በሁለቱም ወገኖች የተፈረመውን ስምምነት የጣሰ እንዳይሆን አስጠንቅቋል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ቃል አቀባይ እንደሚሉት ማቻር ወደ ቀድሞ ቦታቸው እንዲመለሱ የቀረበላቸው ቀነ ገደብ ካለፈ በኋላ በቦታቸው ላይ አዲስ ሰው የተካው በራሳቸው በማቻር ሊቀመንበርነት የሚመራው ተቃዋሚ ድርጅት (SPLM-IO) ነው፡፡

በስምምነቱ መሠረት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ከዚሁ ተቃዋሚ ፓርቲ እንዲመረጥ የሚደረግ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንቱ ያፀደቁት ሹመት የፓርቲውን ውሳኔ መሠረት ያደረገ ነው ብለዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ቃል አቀባይ አታኒ ዌክ አታኒ የዶ/ር ማቻር ድርጅት አዲሱን ተሿሚ ያቀረበ በመሆኑ፣ የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ጉዳይ ካላቸው በፓርቲያቸው ውስጥ እንዲጨርሱ አሳስበዋል፡፡ ‹‹በነገራችን ላይ ደቡብ ሱዳን በጄኔራል ታባንና በሳልቫ ኪር ስትመራ የተሻለ ሰላም እንደምታገኝ ላረጋግጥላችሁ እችላለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ዶ/ር ማቻር ግን ከተደበቁበት በመሆን ለአልጄዚራ በስልክ ሲናገሩ፣ ‹‹አዲሱ ሹመት ሕገወጥ ነው፡፡ ‹‹ምክንያቱም የተሾመው ግለሰብ ከድርጅታችን አፈንግጦ በፕሬዚዳንቱ ድርጅት ውስጥ ያለ ሰው ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹አንድ አፈንጋጭ በእኔ ቦታ ለመሾም አይችልም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ ‹‹ዛሬም ድረስ የደቡብ ሱዳን የመጀመርያው ምክትል ፕሬዚዳንት ነኝ፤›› ያሉት ዶ/ር ማቻር፣ ወደ ሥራ ገበታቸው ተመልሰው መግባት የሚችሉት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጣልቃ ሲገባ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የደኅንነት ሥጋት እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህንን የማያደርግ ከሆነ ግን በቅርቡ የጦር ኃይላቸውን ይዘው ወደ ጁባ ለማምራት እንደሚገደዱ አስጠንቅቀዋል፡፡

‹‹ያበቃለት ስምምነት››

ከተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ የነበሩት ላም አኮል የተባሉ የተቃዋሚ አመራር በበኩላቸው፣ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የተፈረመውን ስምምነት በተደጋጋሚ ሲጥሱት መቆየታቸውን ገልጸው፣ ‹‹ዛሬ ግን ለመጨረሻ ጊዜ ገድለውታል፤›› ብለዋል፡፡

አኮል ከአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ጋር ባደረጉት በዚሁ ቃለ ምልልስ፣ ‹‹ካቢኔ ውስጥ የገባሁት ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ነው፡፡ ስምምነቱ ካበቃለት ግን በዚህ መንግሥት ውስጥ የምቀጥልበት ምክንያት አይኖርም፤›› ብለዋል፡፡

አኮል የስምምነቱን አፈጻጸም የሚከታተል ኮሚሽን አባልና የአገሪቱ የግብርና ሚኒስትር የነበሩ ሲሆን፣ ከፓርቲውም ሆነ ከመንግሥት ኃላፊነታቸው በራሳቸው ፈቃድ መልቀቃቸውን አሳውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉት ኃላፊ የኢትዮጵያ መንግሥት ጁባ ውስጥ የተከሰተው ቀውስ የሚያሳስበው መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸው፣ እስካሁን የተያዘ አቋም እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ በቅርቡ እንደሚነጋገርበትም ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ ከሪፓርተር ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የአካባቢው የፖለቲካ ተንታኝ ፕሮፌሰር አሌክስ ዲዋል ስምምነቱ የቀውሱ ዋነኛ ችግሮችን ግምት ውስጥ ያስገባ እንዳልሆነ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ፕሮፌሰሩ በተለይ የጦር ኃይሉ በጎሳ የተከፋፈሉ ኃይሎች ስብስብ በመሆኑ፣ ይህንን በአንድ ዕዝ ሥር ለማድረግ ሳይቻል የሥልጣን ክፍፍል ብቻ ማድረግ ችግሩ ባለበት እንዲቆይ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡       

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -