አቶ ንጉሤ ቶዬ፣ የአዲስ አበባ የአስጎብኚ ድርጅቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት
የአዲስ አበባ የአስጎብኚ ድርጅቶች ማኅበር ከተመሠረተ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ 36 አስጎብኚ ድርጅቶችን በሥሩ የያዘው ማኅበሩ፣ በቱሪዝም ዘርፍ ከሚንቀሳቀሱ የግል ማኅበሮች አንዱ ነው፡፡ በቅርቡ የማኅበሩ አባላት በሆኑ አስጎብኚዎች የተነሱ ፎቶግራፎች ዓውደ ርዕይ በብሔራዊ ሙዝየም ተዘጋጅቷል፡፡ ስለ ማኅበሩ እንቅስቃሴ እንዲሁም ስለ ዓውደ ርዕዩ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ንጉሤ ቶዬን ምሕረተሥላሴ መኰንን አነጋግራቸዋለች፡፡
ሪፖርተር፡- ስለ ድርጅቱ አመሠራረትና ስለምታደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ቢገልጹልን?
አቶ ንጉሤ፡- ማኅበራችን የተመሠረተው መስከረም 29 ቀን 2004 ዓ.ም. ነው፡፡ ሲመሠረት የኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪን አንድ ዕርምጃ ለማራመድ ነው፡፡ ሁሉም አባላቱ ማለት ይቻላል ከቱሪዝም ኮሌጅና ከዩኒቨርሲቲ በቱሪዝም የተመረቁና ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ወደ 80 በመቶ የሚሆኑት አባሎች ወጣቶች ናቸው፡፡ አንደኛው የማኅበሩ ዓላማ የአባላትን ጥቅም ማስከበር ነው፡፡ ከብቃት ማረጋገጫና ከመዳረሻ ልማት ጋር ተያይዞም ከመንግሥት ጋር መወያየት ሌላው ነው፡፡ ዓላማችን ብዙ ቢሆንም ለአባላት በተለያየ የቱሪዝም ዘርፍ ሥልጠና መስጠት ይገኝበታል፡፡ እንደ በርድ ዋቺንግና ዋይልድ ላይፍ የመሰሉትን እንዲያውቁ ስለጉዳዩ ዕውቀት ያላቸው አባሎች ለሌሎች አባላት ሥልጠና ይሰጣሉ፡፡ እንደ ባለድርሻ አካልነታችን በኢትዮጵያ ቱሪዝም የሚጠበቅብንን ለማድረግ ከመንግሥት ጋር በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ አብረን እንሠራለን፡፡ በየጊዜው አስፈላጊ በሆኑ ሐሳቦች ዙሪያ ከክልልና የፌዴራል ቢሮ ጋርም አብረን እንሠራለን፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ ያዘጋጃችሁት የፎቶግራፍ ዓውደ ርዕይ የቱሪስት መስህብ አካባቢዎችን በማሳየት የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን ለመሳብ ያለመ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ አለመሠራቱ በተደጋጋሚ ይጠቀሳልና ዓውደ ርዕዩ ምን ያህል ለውጥ ያመጣል ብለው ያምናሉ?
አቶ ንጉሤ፡- እኛ የምናስጎበኘውና ለአገሪቱም የውጪ ምንዛሬ የምናስገባው ከውጪ ገበያ በማምጣት ነው፡፡ ወደ አገር ውስጥ ስንመለስ ግን ሕዝባችን ያለውን የቱሪዝም ሀብት ብዙ አያውቀውም፡፡ የዓውደ ርዕዩም ዓላማ ኅብረተሰቡ ስለቱሪዝም ሀብቱ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ ነው፡፡ እያንዳንዱ አካባቢ ተደራሽ ሆኖ ሕዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆንና ስለመንከባከብም ግንዛቤ እንዲወስድ ነው፡፡ ከዐውደ ርዕዩ በጣም ትልቅ ነገር አግኝተናል፡፡ መቶ በመቶ ባይባልም የመጣው ሕዝብ አድንቆታል፡፡ ብዙ አስተያየት መጻፊያ አጀንዳ አልቋል፡፡ በዐውደ ርዕዩ ሰው ቁጭት እንዲሰማውና አገሩን ለማወቅ እንዲነሳሳ አድርገናል፡፡ ቀድሞ ዝም ብለው የሚያዩዋቸው ወፎች የቱሪስት መስህብ ስለመሆናቸው ግንዛቤ አስጨብጠናል ብዬ እገምታለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- አስጎብኚዎችን በተለያየ ዘርፍ እንደምታሠለጥኑ ገልጸውልናል፡፡ አስጎብኚዎች ስለቱሪስት መዳረሻዎች ያላቸው መረጃ ላይ ጥያቄ የሚያነሱም አሉ፡፡ በማኅበሩ የምትሰጡት ሥልጠና የመረጃ ክፍተትን በማጥበብ ረገድ ፋይዳው ምንድነው?
አቶ ንጉሤ፡- በቅርቡ የምንጀምረው ሥልጠና አስጎብኚዎቹን ወደማያውቁት ቦታ በመውሰድ ይሆናል፡፡ ወደ ሰሜን ሸዋ እስከ ጋቸኒ፣ አንኰበርና መልካ ጀብዱ በመሄድ ከቦታዎቹ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶች ጋር ማስተዋወቅ ነው፡፡ ብዙ አባሎቻችን በተፈጥሮ ቱሪዝም በተለይም በርድ ዋቺንግ ብቻ ይሠራሉ፡፡ ሌሎች ድርጅቶችም ስለዚህ ቱሪዝም ዕውቀት መጨበጥ አለባቸው፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሙላት በሚመጣው ወር 15 ለሚሆኑ የድርጅት ባለቤቶች ማለትም ቱር ኦፕሬተሮች የአሥር ቀን የመስክ ሥልጠና ይሰጣል፡፡ ምን አላችሁ ቢባል ይህ መረጃ አለን ብለው መናገር መቻል አለባቸው፡፡ ቱሪዝሙ በታሪካዊና በብሔር ብሔረሰቦች ባህል ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮ ዘርፍም መሆን አለበት፡፡ ያለውን ክፍተት ለማጥበብ በታሪክ፣ በባህልና ሌሎችም ዘርፎች ብቃት ያላቸው ባለሙያዎች ሥልጠናውን ይሰጣሉ፡፡ ሁሉም አባሎች የአስጎብኚ ድርጅቶች ባለቤት ይሁኑ እንጂ፣ አስጎብኚዎች የነበሩ ናቸው፡፡ መስክ ላይ ሥልጠና ከሚሰጡ አባላት አንዱም እኔ ነኝ፡፡ አባላቱ ለሥልጠናው ምንም አይከፍሉም፡፡ የየዕለቱን የራሳቸውን ወጪ ብቻ ይችላሉ፡፡ በአንድ ጊዜ ማሠልጠን ስለማይቻል በሁለት ከፍለን እንሰጣለን፡፡
ሪፖርተር፡- ቱሪዝም ዘርፈ ብዙ ኢንዱስትሪ በመሆኑ ስፖርት፣ ኮንፈረንስና ሌሎችም ክንውኖችን መሠረት ያደረገ ሥራ መሥራት ይቻላል፡፡ በአገራችን ያለው አካሄድ የተለያዩ አማራጮችን ከመከተል በአንድ ዘርፍ የተወሰነ ይመስላል?
አቶ ንጉሤ፡- አንድ ሰው ከሚኖርበት ከ24 ሰዓት በላይ ከሄደ ወይም እስከ አንድ ዓመት በሄደበት ቦታ ከቆየ ቱሪስት ይባላል፡፡ ቱሪዝምን በብዙ መልኩ ማስኬድ ቢቻልም እኛ በባህላዊ፣ ታሪካዊና የተፈጥሮ ቱሪዝም ውስን ነገሮች ላይ አተኩረናል፡፡ በስፖርት፣ በኮንፈረንስና በብዙ መልኮች ቱሪስትን መሳብ ይቻላል፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ ጎብኚዎች ኢትዮጵያን ለአክሱም፣ ለጎንደር፣ ላሊበላ፣ ለሰሜን ፓርክ፣ ለባሌ፣ ለቀይ ቀበሮ፣ ለጭላዳና ለብሔር ብሔረሰቦች ብለው በመምጣት ተወስነዋል፡፡ እዚህ ላይ የእኛ የባለሙያዎቹ ድክመት ይመስለኛል፡፡ የተገኘችውን ብቻ ይዘን ስለምንሄድ ስህተቱን ራሳችንን በመውቀስ መቀበል አለብን፡፡ እኛ ያለንን አላስተዋወቅንም፡፡ ከእኛ ቀጥሎ ደግሞ በዚህ መንገድ ሂዱ በማለት አቅጣጫ ማሳየት ያለበት ኢንዱስትሪውን የሚመራው አካል ሌላውን ድርሻ ይወስዳል፡፡
ሪፖርተር፡- ከማኅበሩ ግቦች አንዱ የአባላቱን ማለትም የአስጎብኚዎችን ጥቅም ማስጠበቅ እንደመሆኑ አስጎብኚዎች የሚገጥሟቸውን ችግሮች የምትፈቱት በምን መንገድ ነው?
አቶ ንጉሤ፡- በብዛት የሚፈትነን ከመንሥት ጋር ያለው ቢሮክራሲ ነው፡፡ ሌላው መስክ ላይ የሚገጥመውና አስጎብኚዎች በግላቸው የሚወጡት ችግር ነው፡፡ ከመንግሥት ጋር በተያያዘ ከብቃት፣ የንግድ ፈቃድ ዕድሳት ጋር የሚገናኙ ነገሮች አሉ፡፡ እንግዶች ላይ የሆነ ችግር ቢጠፈር ወይም ቱሪስቶች ላይ አንዳች ጉዳት ቢከሰት እነዚህን ከመንግሥት ጋር እናወራለን፡፡ ዘርፉ የተረጋጋ እንዲሆን አስጎብኚዎች ስለችግሮቻቸው በተናጠል ከሚጠይቁ በማኅበር ቢሆን ይመረጣል፡፡ በየመዳረሻው ሰላማዊ የሆነ የቱሪስት ፍሰት እንዲኖር እንዲሁም ቱሪዝም ነክ መረጃዎች ከመንግሥት ወደታች እንዲወርዱ በማድረግ እንሠራለን፡፡ በማኅበር ከምንጠይቃቸው አንዱ ከቀረጥ ነጻ የሚገቡ ነገሮች ናቸው፡፡ የማኅበራችን አባል የሆኑ ድጋፍ እንዲደረግላቸው እንጠይቃለን፡፡ ማነቆ ስለሆኑ ነገሮችን ለመወያየት 36 ድርጅት ከሚሄዱ የነሱን ድምፅ የሚያስተጋባና መብታቸውን የሚያስጠብቅ ተቋም ያስፈልጋል፡፡ ለእነሱ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ዕድገት ተብሎ በሚሠራው ሥራ ብዙ ችግሮች ቀርፈናል ማለት እችላለሁ፡፡ ቀድሞ ከመንግሥት ጋር መገናኘት አስቸጋሪ ነበር፡፡ ዛሬ ከሚኒስትሮች ጋር እኩል ቁጭ ብለን ስለ አገር እናወራለን፡፡ የምንሰጣቸው ሐሳቦች እንደ አንድ ግብዓት ይቆጠራሉ፡፡ ብዙ የተስተካከሉ እንዳሉ ሁሉ፣ የሚቀሩም አሉ፡፡ ከአገሪቱ ዕድገትና ከቱሪዝም ልማት ጋር በሒደት የሚቀረፉ ችግሮች ይኖራሉ፡፡ አንዳንዴ የሚመደበው ሰው በተቀያየረ ቁጥር ግብ የሚላቸው ነገሮች ቢቀያየሩም፣ ከዛሬ አሥር ዓመት ወዲህ የመጡት ኃላፊዎች ብዙ ነገር ስላወቁ በተለሳለሰ መንገድ እየሄደ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች የመሠረተ ልማት ዝርጋታ አለመሟላት ዘርፉን ከሚፈታተኑ ችግሮች አንዱ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
አቶ ንጉሤ፡- ከትንሹ ችግር ስንጀምር የዛሬ 17 እና 18 ዓመት ሌላው ቀርቶ የፕላስቲክ ውኃ ሳይቀር እዚህ ስለሌለ ከውጪ ይመጣ ነበር፡፡ መንገዶችም አልነበሩም፡፡ ዛሬ በቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች በአብዛኛው የሚያስደስቱ ለውጦች አሉ፡፡ ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶች ተሠርተዋል፡፡ ድሮ መኪና ቢበላሽ ሌላ መኪና ለማግኘት ሌላ ከተማ ይኬድ ነበር፡፡ ዛሬ በእጅ ባለ ስልክ ያሉበት ቦታ ድረስ መኪና ይመጣል፡፡ ቀድሞ በየቦታው ሆቴሎች አልነበሩም፡፡ ዛሬ አንድም ቢሆን ሁለት ሆቴሎች እየተሠሩ ነው፡፡ አሁንም ግን የሚሠሩት ሎጆችና ሆቴሎች በቂ አይደሉም፡፡ ወደ ደቡብ ምሥራቅ ለምሳሌ ወደ ነገሌ ቦረና ለበርድ ዋቺንግ ቢኬድ ሆቴል አለመኖሩ ያስቸግራል፡፡ ራቅ ያለ ቦታ የሚገነቡት ደግሞ የምግብ ችግር አለባቸው፡፡ ጥሩ አብሳይ የላቸውም፡፡ ችግሮቹ በሒደት ይቀረፋሉ በሚል ነው እንጂ አሁን ባለው መልክ የቱሪስት ፍሰቱ ከቀጠለ ችግር ይፈጠራል፡፡ በተለይ በደቡብ ምሥራቅና ምዕራብ በተወሰነ መልኩ ችግር አለ፡፡ አንዳንዴ ያሉት ሆቴሎችም የማስተወቂያ ብቻ ይሆናሉ፡፡ አንዳንድ ሎጆች ሆቴል ተብለው ብዙ እየተከፈለባቸው ሰፈር ውስጥ እንዳለ ቦታ ይሆናሉ፡፡ ሲሠሩ ደረጃቸውን የጠበቁ ስለመሆናቸው ቁጥጥር ያስፈልጋል፡፡ የሰው ኃይል ችግር ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ የቤቶቹ ባለቤቶች በኩል በአነስተኛ ወጪ ሠርቶ ከፍተኛ ገቢ የማግኘት ነገር አለ፡፡ እስከተከፈለ ድረስ ጥሩ አገልግሎት መገኘት አለበት፡፡ ችግሮቹ ካልታሰበባቸው ትላንት ስናወራ እንደነበረው ለወደፊትም የምናወራበት ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- በመዳረሻ ቦታዎች ያለውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ በማድረግ እንዲሁም የየአካባቢውን ባህላዊና ተፈጥሯዊ ሀብት እንዲጠበቅ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ በምን መንገድ መስተካከል ይችላል?
አቶ ንጉሤ፡- ትክክል ነው፡፡ አንዳንድ ቦታ ትልቁ ችግር የባህል ወረራ ነው፡፡ አንዳንድ አገሮች የቱሪስት ፍሰትን ቁጥር ይወስናሉ፡፡ ምክንያቱም ለታሪካቸውና ለተፈጥሮ ሀብታቸው ጥንቃቄ በመውሰድ ነው፡፡ ኖርዝ ፖል አካባቢ ያለችው ቡታን የምትባል አገር ውስን ቱሪስት ብቻ ትቀበላለች፡፡ የሰው እግር የተፈጥሮ ሀብት ይዘቱን ስለሚያበላሽ በዓመት የምትቀበለው ሰው ይወስናል፡፡ በኪሊማንጃሮ ተራራም ተመሳሳይ ነገር አለ፡፡ የሰው ኮቴ አፈር እንዳይሸረሽርና በአካባቢው ያሉ አትክልቶችን ሰው ሲታከክ እንዳይጎዱ ለመከላከል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች አንጻር ስትታይ የቱሪስት ፍሰቱ እንደዚህ አልበዛም፡፡ በመዳረሻ ቦታዎች የነበረው ማኅበረሰብ ቀድሞ በስፋት ተጠቃሚ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ አሁን በየትኛውም መዳረሻ ያለው ማኅበረሰብ በአስጎብኚነት ይሠራል፡፡ የስጦታ ዕቃ በመሸጥ፣ እንደሰሜንና ባሌ ፓርክ በመሰሉት ደግሞ ፈረስ ጫኝ፣ አከራይ፣ ስካውትና አስጎብኚዎችም በማኅበር ተደራጅተው ይጠቀማሉ፡፡ ገቢው ለማኅበራቸው ይሆናል፡፡ የተወሰነ ፐርሰንት ደግሞ የግል አበል ይሆናል፡፡ ከዚህ በፊት ለምሳሌ ቦረና ሲኬድ ሊቦን ላርክ የምትባል ወፍ ለማየት አይከፈልም ነበር፡፡ ዛሬ ግን የዛ አካባቢ ሰዎች በማኅበር ተደራጅተው በበርድ ላይፍ ኢንተርናሽናል ሠልጥነው ወፏን በመፈለግና ከብቶች እዛ አካባቢ እንዳይግጡ በመጠበቅ ይሠራሉ፡፡ በመኪና 25 ብር በሰው 50 ብር እያስከፈሉ ባንክ ያስቀምጣሉ፡፡ ገንዘቡን መከፋፈል ሳይሆን ሱቅ በመክፈት ወይም በሌላ መንገድ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ከዛ በኋላ ድርቅ ወይም ሌላ ችግር በሚመጣበት ጊዜ ድርጅቱ ይጠቀሙበታል፡፡ ለወርቅ አውጪዎች ማኅበርም አንዳንድ ዕርዳታ ያደርጋሉ፡፡ ከ21 ዓመት በፊት ሳይከፈልባቸው የማውቃቸው ቦታዎች ዛሬ ኅብረተሰቡ ይብዛም ይነስም እያስከፈለ ተጠቃሚ እየሆነ ነው፡፡ ትልቁ ችግር ከእኛ ጋር የመረጃ ልውውጥ አለማድረጋቸው ነው፡፡ ለአንድ አካባቢ ጉብኝት ማስከፈል ሲጀምሩ በደብዳቤ ወይም በስልክ አያሳውቁንም፡፡ አስጎብኚዎችን በምንልክበት ጊዜ የሚሰጣቸው ገንዘብና እዛ የሚጠየቁት ገንዘብ ሳይመጣጠን ይቀራል፡፡ ክፍያ መጀመሩ ጥሩ ቢሆንም መረጃ መሰጠት አለበት፡፡ ገንዘብ የሚከፈልባቸው ቦታዎች ላይ ማኅበረሰቡ ተፈጥሯዊ ሀብቱንም ይጠብቃል፡፡ አሁን አደጋ እያመጣ ያለው የተጥሮ ሀብት መጥፋት ነው፡፡ ለደን እንክብካቤ አለማድረግ የሚታይባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ አንዳንድ ቦታዎች የምንከፍለው የተፈጥሮ ሀብቶቹን ከጠበቁ ብቻ ስለሆነ፣ ለውጥ አላቸው፡፡ እየተከፈለም ሰው እንክብካቤ ያጎደለባቸው ቦታዎችም አሉ፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንሞክራለን፡፡ ጎብኚና አስጎብኚም ተመልሶ የሚመጣው ሀብቶቹ እስካሉ ድረስ በመሆኑ ጠብቁ የሚል መልዕክት እናስተላልፋለን፡፡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኢንዲስትሪ ትልቁ ክፍተት የተፈጥሮ ቱሪዝሙ በጣም እየሞተ መሆኑ ነው፡፡ አካባቢዎች በሙሉ ወደ ግጦሽና እርሻ መሬትነት እየተቀየሩ ነው፡፡ ኅብረተሰቡና መንግሥትም ቆም ብሎ ከደን ጭፍጨፋ መታቀብ አለበት፡፡ ልማትም ሲስፋፋ ለተፈጥሮ ሀብት ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ዝም ብሎ ከተለጠጠ ነገ ምንድንነው የሚመጣው? የዓለም ሙቀት መጨመር ከካርቦን ልቀትና ከደን መጥፋት የመጣ ነው፡፡ ይህ ወደፊት ለኢትዮጵያም አደጋ ያለው ይመስለኛል፡፡ በአንዳንድ ፓርኮቻችን ሕዝቡ ገቢው ወደእኔ ስለማይመጣ ምን አገባኝ የሚል ነገር አለው፡፡ አዋሽ፣ አቢያታና ነጭ ሳር ችግር ያለባቸው ፓርኮች ናቸው፡፡ ስለዚህ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ በማድረግ መጠበቅ ይቻላል፡፡ የመጠበቁ ነገር ላይ ጅማሮዎች ቢኖሩም ገና ብዙ ይቀራል፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም መለዮ ‹‹ላንድ ኦፍ ኦሪጅንስ›› ተብሏል፡፡ ምን ያህል አገሪቷን ገላጭና ቱሪስት ሳቢ ነው?
አቶ ንጉሤ፡- ‹‹ላንድ ኦፍ ኦሪጅንስ›› የኢትዮጵያን ተፈጥሮ፣ ባህልና ታሪክ ሦስቱን በአንድ ለመግለጽ ነው፡፡ የሉሲ፣ የቡና የራሷ ፊደል እንዲሁም ብዙ ለየት ያለ ነገር ያላት መሆኗን ያሳያል፡፡ መለዮው ገላጭ ነው፡፡ ለቱሪዝሙ አንድ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ምክንያቱም ስናስተዋውቅ የነበረው እነዚህን ሀብቶች በመሆኑ፣ መለዮው ተጨማሪ አስተዋዋቂ ይሆናል እላለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበራችሁ በቅርብ ርቀት ያከናውናቸዋል የሚሉትን ዕቅዶች ቢገልጹልን?
አቶ ንጉሤ፡- ለወደፊት አባላት በቱሪዝም ልማት ከኅብረተሰቡ ጋር የተቀናጀ እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው ማድረግ እንፈልጋለን፡፡ አባላትን በመወከል እንደ አንድ ድምፅ በቱሪዝም ልማት ላይ መንቀሳቀስና ለአባላት ምቹ የገበያ ሁኔታ መፍጠርም ይገኝበታል፡፡ አባላት የመንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት በሚያዘጋጇቸው ከቱሪዝም ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እናበረታታለን፡፡ በየጊዜው ለአባላት ሥልጠና በመስጠት ለአገራችን ቱሪዝም የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ማስቻል ለሚቀጥሉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የያዝነው ዕቅድ ነው፡፡ በየጊዜው ከአገሪቷ ዕድገት ጋር እነዚህ ዓላማዎች ይዳሰሳሉ፡፡