እ.ኤ.አ. በ2016 ማብቂያ ግድም አሜሪካ በምታካሂደው ምርጫ ሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ፕሬዚዳንት ሆነው የቀረቡት ዶናልድ ትራምፕ፣ ‹‹ሙስሊሞች አሸባሪ ናቸው፣ ሽብር የሚፈጽሙትን እያወቁም አያጋልጡም፣ በመሆኑም አሜሪካ ከመግባት መታገድ አለባቸው፤›› በሚለው አቋማቸው፣ በተለይ ከዴሞክራት ፓርቲ በኩል ሲወቀሱና ሲተቹ ከርመዋል፡፡ በዚህ አቋማቸው ዓለምን እያነጋገሩ የሚገኙት ቢሊየነሩ ትራምፕ፣ ሰሞኑን ደግሞ ከፓርቲያቸው የሪፐብሊካን አባላትም ወቀሳ እየተሰነዘረባቸው ነው፡፡
እያንዳንዷን ንግግር ነቅሰው በሚዲያው አስተያየታቸውን የሚሰነዝሩት ትራምፕ፣ በዴሞክራቶች ፓርቲ ብሔራዊ ጉባዔ ማብቂያ ላይ ከፓኪስታን ተሰደው በአሜሪካ የሚኖሩ የአንድ ሙስሊም ቤተሰቦች፣ እ.ኤ.አ. በ2004 አሜሪካ በኢራቅ በነበራት ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት በ27 ዓመቱ መስዋዕት የሆነውን ወጣት ልጃቸውን አስመልክተው፣ ‹‹ሙስሊሞችም ለአሜሪካ ደኅንነት በመከላከያ ኃይሉ ውስጥ እየተሳተፉ እንደሆኑ፣ አገራቸውን እንደሚወዱና ኃላፊነት እንዳለባቸው . . .›› በመናገራቸው በጉባዔው አድናቆት የተቸራቸው ቢሆንም፣ በትራምፕ የመልስ ምት ግን ክብር ተነፍገዋል፡፡
በ27 ዓመቱ ለአሜሪካ መስዋዕት የሆነው ሻምበል ሁማዩን አባት ኪዚር ካህን፣ በዴሞክራቶች ጉባዔ ማብቂያ ላይ ‹‹ልጄ ሁማዩን መስዕዋት የሆነው አብረው የነበሩት ጓዶቹን ለማትረፍ ነው፡፡ እንደ ሚስተር ትራምፕ ቢሆን ልጄ በአሜሪካም አይገኝም ነበር፤›› ብለው መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ካህን ትራምፕን በጉባዔው ላይ ያወገዙ ሲሆን፣ ዋና መነጋገሪያ የሆነው ግን የትራምፕ መልስ ነው፡፡
ሚስተር ካህን ባደረጉት ንንግር ‹‹ትራምፕ የአሜሪካን ሕገ መንግሥት አንብቦት አያውቅም፣ ሁልጊዜም ስለሙስሊሞች የሚሰጠው አስተያየት አሉታዊ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ይህንን ተከትሎ የአፀፋ መልስ የሰጡት ትራምፕ፣ ‹‹የካን ባለቤት ጋዛላን ካን፣ በዴሞክራቶች ጉባዔ ላይ ከባሏ ጎን ሆና ከመናገር ታግዳለች፣ ለዚህም ነው ባሏ ብቻ ተናግሮ ከመድረኩ የወረደው፣ እስቲ እሷ አንድ ቃል ትናገር፤›› ሲሉም ሙስሊሞች ሴቶችን እንደሚጨቁኑ አመላክተዋል፡፡ የካህን ባለቤት በበኩላቸው በጉባዔው ላይ ንግግር ያላደረጉት በልጃቸው ሞት ክፉኛ በመጎዳታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
‹‹ካህን ልጁን በሞት ስላጣ ባዝንም ከዚህ ቀድሞ አግኘቶኝ አያውቅም፣ በሚሊዮኖች ፊት ቆሞም ትራምፕ ሕገ መንግሥቱን አላነበበም የማለት መብት የለውም፣ የተናገረውም ውሸት ነው፤›› ብለዋል፡፡
ካህን፣ ‹‹ትራምፕ ለአሜሪካ ምን አደረገ? ልጄ ለአሜሪካ መስዋዕት ሆኗል፤›› በማለታቸው ሳቢያም ትራምፕ፣ ‹‹ጠንክሬ ሠርቻለሁ፡፡ በሺዎች ለሚቆጠሩ የሥራ ዕድሎችንም ፈጥሬያለሁ፤›› ብለዋል፡፡
ትራምፕ የሟቹን ካህን ቤተሰቦች የወርቅ ኮከብ ሜዳሊያ ተሸላሚ በመሆናቸው በክብር መጥራት ሲገባቸው፣ በጦርነት ከሞቱ ቤተሰቦቻቸው የተረፉ ማለታቸውም ለወታደር ቤተሰቦች ያላቸው ክብር ዝቅተኛ ነው የሚል ቁጣ አስነስቶባቸዋል፡፡
ትራምፕ ለኤቢሲ የሰጡትን ቃለ መጠይቅ ተከትሎ ከዴሞክራቶችና ከሊበራሎች ትችት ቢሰነዘርባቸውም፣ እ.ኤ.አ. በ2016 ማብቂያ የሚካሄደው የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሊጭበረበር ይችላል ሲሉ አዲስ አጀንዳ ይዘው ብቅ ብለዋል፡፡
በኮሎምበስ ኦሃዩ በነበራቸው ቅስቀሳም ብዙዎቹ ሒደቶች ፍትሐዊ አልነበሩም ሲሉም በማስረጃ አስደግፈው ሳይሆን በደፈናው ተናግረዋል፡፡ ትራምፕ እየሰነዘሩ ባሉዋቸው አወዛጋቢ አስተያየቶች ሁሌም የሚነቅፏቸው የዴሞክራት ፓርቲ ተቀናቃኛቸው ሒላሪ ክሊንተንም፣ ‹‹ጤነኛ ዕጩ ፕሬዚዳንት አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
በሟች የወታደሩ ቤተሰቦች ላይ በሰነዘሩዋቸው የሚያንቋሽሹ ቃላት፣ እ.ኤ.አ. በ2008 በነበረው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለው ከኦባማ ጋር የተወዳደሩት ጆን ማክኬን ትራምፕን ከተቃወሙ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይገኙበታል፡፡ ‹‹ትራምፕ ከኛ ውስጥ ምርጥ የሆኑትን ለማንቋሸሽ አይችልም፤›› ሲሉ በሙስሊሞቹ የሟች ወታደር ቤተሰቦች ላይ የሰነዘሩትን ትችት ተቃውመዋል፡፡
ዴሞክራቱ ባራክ ኦባማም፣ ‹‹የወርቅ ኮከብ ተሸላሚ ከሆኑት ውጪ ለእኛ ማንም ነፃነትን ሊያጎናጽፈን አይችልም፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በቅድመ ምርጫ የትራምፕ ተቀናቃኝ የነበሩት የደቡብ ካሮላይና ሴናተር ሊንድሴይ ግርሃም፣ ‹‹ለመቀበልና ለመግለጽ የሚከብድ፤›› ብለዋል፡፡ አፈ ጉባዔ ፖል ሪያን ደግሞ የዶናልድ ትራምፕን ስም ሳይጠቅሱ፣ ‹‹ሙስሊሞችን ከሽብር ጋር በማያያዝ መውቀስን በአጠቃላይ ማውገዝ አለብን፤›› ብለዋል፡፡ የፍሎሪዳ የቀድሞ ገዥ የነበሩት ሪፐብሊካኑ ጄብ ቡሽ፣ ‹‹ለማመን የሚከብድ ክብር መንሳት፤›› ብለውታል የትራምፕን ንግግር፡፡
ትራምፕ ከግራም ከቀኝም ቢወገዙም ለጉዳዩ ቦታ አልሰጡትም፡፡ ይልቁንም ተፎካካሪያቸውን ሒላሪ ክሊንተን ‹‹ዲያቢሎስ›› ናት ብለዋል፡፡
በአሜሪካ ሙስሊሞች ቁጥራቸው አናሳ ቢሆንም በጦር ኃይሉ ውስጥ በመሳተፍ አብሮ በመቆም አገራቸውን ጠቅመዋል፣ መስዋዕት ሆነዋል፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከ15 ሺሕ በላይ ዓረብ አሜሪካውያን በጦርነቱ ተሳትፈዋል፡፡ በአፍጋኒስታንና በኢራቅም ከ3,500 በላይ ሙስሊሞች ወታደር ሆነው ተሳትፈዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2014 በፔው የጥናት ማዕከል የተሠራው የሃይማኖት ጥመርታ፣ 0.9 በመቶ የሚሆኑት አሜሪካውያን ጎልማሶች ራሳቸውን ሙስሊም ብለው እንደሚገልጹ አመላክቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2011 በሙስሊም አሜሪካውያን ላይ የተደረገ ጥናት ደግሞ፣ 1.8 ሚሊዮን ጎልማሳ ሙስሊሞች፣ በአጠቃላይ 2.75 ሚሊዮን ሙስሊሞች በአሜሪካ እንደሚገኙ፣ ከእነዚህ ውስጥ 63 በመቶ ያህሉ በስደት የገቡ መሆናቸውን አሳይቷል፡፡ የሥነ ሕዝብ ትንበያ ደግሞ እ.ኤ.አ. በ2050 በአሜሪካ የሚኖሩ ሙስሊሞች ብዛት 2.1 በመቶ እንደሚሆን አስታውቋል፡፡
ወደ አሜሪካ በተለይ በስደት መልክ የሚገቡ ሙስሊሞች ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩን፣ ሙስሊሞች አሸባሪዎች ናቸው በሚል አሜሪካ ለሙስሊም በሯን መዝጋት እንዳለባት ለሚከራከሩት ትራምፕ፣ ከሪፐብሊካኑ ትችት ቢሰነዘርም ትራምፕ መመረጥ የለበትም የሚል ንግግር ከፖለቲካ መሪዎቹ አልተንፀባረቀም፡፡
ትራምፕ በተለይ በሙስሊሞች ላይ ያላቸው አቋም በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ ከሆነ የሰነበተ ሲሆን፣ ከሒላሪ ክሊንተን ጋር በሚኖራቸው የፖለቲካ ክርክር ዋናው አጀንዳ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሆኖም ትራምፕ ከኤቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ከሒላሪ ክሊንተን ጋር የሚኖሯቸውን ሦስት የክርክር ፕሮግራሞች መታደማቸው ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው፣ ለዚህም ምክንያቱ ሒላሪ ክሊንተን ከሦስቱ የክርክር ፕሮግራሞች ሁለቱን የአሜሪካ የእግር ኳስ ጨዋታዎች በሚካሄዱበት ጊዜ አድርጋለች ብለው በማመናቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ትራምፕ፣ ‹‹ክርክሩን የሚያዳምጡ ሰዎች አናሳ ሊሆኑ ይችላሉ፣ የብሔራዊ እግር ኳስ ሊጉም ክርክሩን አስመልክቶ የቅሬታ ደብዳቤ ልኮልኛል፤›› ቢሉም ሊጉ ለትራምፕ ደብዳቤ አለመላኩንና የክርክሩ ጊዜ ከእግር ኳሱ ጨዋታ ጋር ግጭት እንደማይፈጥር አስታውቋል፡፡
በእነዚህና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ አወዛጋቢው ዶናልድ ትራምፕ እንግዳ ነገር መፍጠራቸውና ከሒላሪ ክሊንተን ጋር የሚኖራቸው ፉክክርም በበርካታ ክስተቶች እንደሚታጀብ የብዙዎች እምነት እየሆነ ነው፡፡