Tuesday, September 27, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ኪንና ባህልኢትዮጵያ በሪዮ ባህላዊ ኦሊምፒክ አትሳተፍም

  ኢትዮጵያ በሪዮ ባህላዊ ኦሊምፒክ አትሳተፍም

  ቀን:

  ተናፋቂውና ተወዳጁ ኦሊምፒክ የአራት ዓመት ቀጠሮውን አጠናቆ ካለፈው የለንደን ኦሊምፒክ አርማ የተቀበለችው የላቲን አሜሪካዋ ብራዚል መዲና ሪዮ ዲጄኔሮ የዘንድሮውን 31ኛ ኦሊምፒያድ ለመክፈት ሦስት ቀናት፣ 72 ሰዓታት ብቻ ቀርቷታል፡፡ የዓለምን ሕዝብ ያላንዳች ልዩነት የሚያስተሳስረውና በባህላዊ መድረክ የሚታጀበው የኦሊምፒክ ጨዋታ ከ207 አገሮች የተውጣጡ 10 ሺ አትሌቶች ከነባህላዊ መገለጫዎቻቸው ጋር ይገኛሉ፡፡ ሪዮን በባህላዊ ገጽታ ጠቢባኑ (አርቲስቶች) በኦሊምፒኩ ብቻ ሳይሆን በፓራሊምፒክ ጭምር ለማድመቅ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል፡፡ ብራዚል በዓለም የምትታወቅበት ሳምባ ዳንኪራዋን ጨምሮ በልዩ ልዩ መገለጫዎቿ ኦሊምፒኩን እንደምታደምቅ ይጠበቃል፡፡

  ቢቢሲ ሬዲዮ 4 በድረ ገጹ ከሳምንት በፊት እንደዘገበው፣ የባህል ኦሊምፒያዱ ይዘት ‹‹ምሥጢራዊ›› ሆኗል ብሏል፡፡ ምን ምን ባህላዊ ኩነቶች እንደሚኖሩ በቅጡ ማወቅ አልተቻለም፡፡ የሪዮ ኦሊምፒክ አዘጋጆች ግን እንደ ለንደን ኦሊምፒክ ዓይነት ባህላዊ ኦሊምፒያድ እንደሚኖርና የተለያዩ ሥነ ጥበባዊ ኩነቶች እንደሚኖር ቃል ገብተዋል፡፡ ‹‹በድረ ገጽ ምንም ዓይነት መረጃ ይፋዊ ፕሮግራምም አልተለቀቀም›› ብሏል ቢቢሲ ሬዲዮ 4፡፡

  የባህላዊ ኦሊምፒያድ ዳይሬክተሯ ካርላ ካሙሪቲ፣ በየትኛውም ቦታ ሆነ በድረ ገጽ መረጃዎች ያለመለቀቃቸው ‹‹አስደናቂና አስገራሚ ሁነቶችን ለመፍጠር ስለሆነ አስቀድሞ ማስተዋወቅ አላስፈለገም፡፡ በድንገት በዐውራ ጎዳናዎች የሚታዩ ይሆናል›› ብለዋል፡፡

  ተካፋይ አገሮች በኦሊምፒኩ መንደር የየራሳቸው ባህላዊ መገለጫዎች እንደሚያቀርቡም እየተናገረ ነው፡፡

  ዘ ሪዮ ታይምስ እንደዘገበው፣ ሠላሳ የኦሊምፒክ ባህላዊ መሰናዶ ቤቶች በመዲናይቱ ምርጥ ቦታዎች የተዘጋጁ ሲሆን አገሮች ባህላቸውን፣ ምግባቸውን፣ ሙዚቃውንና የዘንድሮውን ኦሊምፒክ ስኬታቸውን በተስፋ የሚያከብሩበት ይሆናል፡፡

  አምስት ቢሊዮን የዓለም ሕዝብ የሪዮ ኦሊምፒክን ቴሌቪዥን ጨምሮ በልዩ ልዩ መንገዶች የሚከታተል ቢሆንም ዕድለኞቹ የሪዮን ምድር የሚረግጡት ጎብኚዎች ከኦሊምፒክ የመስተንግዶ ቤቶች የሚያጣጥሙት ሁነት ያህል አይሆንም፡፡ የአፍሪካ አህጉር ጨምሮ ሠላሳ አገሮች የራሳቸው ቤት እንደሚኖራቸው አረጋግጠዋል፡፡ ባህላቸውንና ታሪካቸውን መስህቦቻቸውንም ጭምር ያስተዋውቁበታል፡፡

  ቤቶቹ የኦሊምፒክ የክብር አካል ሆነው መከሰት የጀመሩት በቤጂንግና ቀጥሎም በለንደን ኦሊምፒክ ጊዜ ነበር፡፡ ቤቶቹ እንግዶችን እንደቤታቸው የሚቆጥሩበት ዓይነት ምቾትን ያጎናፅፋቸዋል፡፡

  እንግዶች የየአገሩን ባህላዊ ምግብ የሚያጣጥሙበት፣ በየሙዚቃው ዘና የሚሉበት በዐውደ ርዕይ ልምድ የሚለዋወጡበት፣ እንደየአገሩ አቀራረብ የተለያዩ ጨዋታዎች ውድድሮች የሚፈጠሩበት እንደሚሆን ተጠብቋል፡፡

  ኢትዮጵያ የማትገኝበት ባህላዊ ኦሊምፒያድ

  ኢትዮጵያ ዘንድሮ ራሷን የምታስተዋውቅበት አዲስ መለያ (ብራንድ) አስቀድማ በጀርመን፣ ቆይታም በአዲስ አበባ ይፋ አድርጋለች፡፡ በአማርኛ በይፋ የሚታወቅ መጠርያ ባይኖራትም በእንግሊዝኛው “Land of Origins” (ላንድ ኦፍ ኦሪጅንስ) መለያዬ ነው ብላለች፡፡ የመብቀያዎቹ ምድር እንደማለት ነው፡፡  

  ይህን አዲሱን መለያዋንና ሌሎች ጓዞቿን በኦሊምፒክ መንደር በ‹‹አፍሪካ ቤት›› (Africa House) ለማስተዋወቅ አልታደለችም፡፡ ከአራት ዓመት በፊት ለንደን ባዘጋጀችው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች፣ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አጋፋሪነት በባህላዊ ኦሊምፒክ ተሳትፋ ራሷንም አስተዋውቃ ነበር፡፡ አፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የራሷ ጎጆ ተዘጋጅቶላት ከተሳተፉት አገሮች መካከል የኢትዮጵያ መቀመጫ በርካታ ተመልካችና ልዩ አድናቆት ማግኘቱ ተዘግቦ ነበር፡፡ በወቅቱ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዐቃቤ ንዋይ የነበሩት አቶ ገበያው ታከለ እንደገለጹት፣ በኦሊምፒክ መንደር ውስጥ የኢትዮጵያ ቀን በታላቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡

  በአፍሪካ ሐውስ የኢትዮጵያ መቀመጫም ልዩ አድናቆትና ተመልካች አግኝቷል፡፡ በኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩልም አትሌቶችን የማስተዋወቅ የባህልና የሙዚቃ ሥራ ቀርቧል፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ የልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ መካነ መቃብር በመጎብኘትና ማንነትን በማሳወቅ ረገድ ልዩ ልዩ ሥነ ሥርዓቶች ተካሂደዋል፡፡

  በኢትዮጵያ ኤምባሲ በሃይድ ፓርክ በተዘጋጀው የኢትዮጵያ ቀን፣ ባህላዊ ምግብና የቡና ሥነ ሥርዓት፣ ሙዚቃና ዳንስ ያካተተ የምሳ መሰናዶ እንዲሁም በገናናው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥነው ‹‹ጽናት›› ፊልም ለዕይታ በቅቶ ነበር፡፡

  የዘንድሮው የሪዮ ኦሊምፒክ በዓለም በቡና ምርት ቀዳሚ የሆነችው ብራዚል የሚካሄድ ከመሆኑ አንፃር የቡና መገኛዋ ኢትዮጵያ የቡና ሥነ ሥርዓቱን ጨምራ ልዩ ልዩ ባህላዊና ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊም መገለጫዎቿን በአፍሪካ ጎጆ ውስጥ ለማዘጋጀት ለምን ተሳናት?

  ሪፖርተር ያነጋገራቸው የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዳንኤል አበበ እንደገለጹት፣ ወጪው ከፍተኛ በመሆኑ ለመሳተፍ አገሪቱንም ለማስተዋወቅ አልተቻለም፡፡ በመድረኩ አስቀድመው ይሳተፋሉ ተብለው የተጠበቁት ኩባንያዎች ፈቃደኛ ሆነው አልተገኙም፡፡                  

    

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...