Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሕጋዊ ውጤቱን የተነፈገው የጋብቻ ማስረጃ

ሕጋዊ ውጤቱን የተነፈገው የጋብቻ ማስረጃ

ቀን:

የካ ክፍለ ከተማ ውልና ጋብቻ ምዝገባ አገልግሎት፣ አገልግሎት መስጫ መስኮት ላይ ሁለት ተገልጋዮ ውስጥ ካሉ ሠራተኞች ጋር ይጨቃጨቃሉ፡፡ ጭቅጭቁ የተፈጠረው ተገልጋዩ በሃይማኖት ሥርዓት መሠረት የፈጸምኩት ጋብቻ ተመዝግቦ ማስረጃ ይሰጠኝ ሲሉ፣ ከሠራተኞቹ አንዷ ማስመዝገብ እንደሚችሉ፣ ከቤተክርስቲያን ያመጡት የጋብቻ ማስረጃ ዋና ቅጂ ደግሞ በሚከፈትላቸው ፋይል ተያይዞ እንደሚቀር በመናገሯ ነው፡፡ ጋብቻቸውን ለማስመዝገብ ወደ መዝጋቢ አካል የሄዱት ባለጉዳይ ግን፣ ከማስመዝገብ ባለፈ በመጀመሪያ የተጋቡበትን ዋና ቅጂ መነጠቃቸውንም እንደሚቃወሙ ጐላ ባለ ድምፅ ይናገራሉ፡፡

የሃይማኖት የጋብቻ ማስረጃቸውን ለማስመዝገብ ሾላ ገበያ አካባቢ ወደሚገኘው የካ ክፍለ ከተማ ውልና ጋብቻ ምዝገባ አገልግሎት ያቀኑት ባል፣ ባለቤታቸውን፣ ሦስት ሦስት ፎቶ ግራፍ፣ የታደሰ የቀበሌ መታወቂያ ብቻ (የታደሰ ፓስፖርትና መንጃ ፍቃድ አይቻልም) በባልና በሚስት ወገን ሁለት ሁለት ምስክር ይዘው መቅረብ እንዳለባቸውም በተጨማሪ ይነገራቸዋል፡፡

‹‹በ2000 ዓ.ም. በቤተክርስቲያን ሥርዓት የፈጸምኩትን ጋብቻ እንድትመዘግቡ እንጂ ዳግም ጋብቻ ልፈጽም አልመጣሁም›› ቢሉም ከሠራተኞች የተሰጣቸው መልስ ‹‹እሱን ሐሳብ መስጫ ሳጥን ውስጥ አስገቡ፤ እኛ የታዘዝነውን ነው የምንፈጽመው፤›› የሚል ነበር፡፡

‹‹ማስመዝገብ›› የተባለውን አካሄድ እንደተመለከትነውም፣ የቤተክርስቲያን የጋብቻ ሰርተፍኬቱ ላይ ያለው መረጃ ትክክል ነው ብሎ አረጋግጦ፣ መመዝገቡን የሚገልጽ ማስረጃ መስጠት ሳይሆን፣ የቤተክርስቲያኒቷን የጋብቻ ሰርተፍኬት በጥንዶቹ ስም በሚከፈተው ፋይል አያይዞ ለባለትዳሮቹ አዲስና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በውልና ክብር መዝገብ ማስረጃ አገልግሎት በሚሰጠው የጋብቻ ማስረጃ መተካት ነው፡፡ ሒደቱም ከጋብቻ ማስረጃቸው ግርጌ ከሚጻፈው ልዩነት በስተቀር፣ እንደ አዲስ ተጋቢዎች ነው፡፡ በዚህ ሒደት በ2000 ዓ.ም. የጋብቻ ሥነ ሥርዓታቸውን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የፈጸሙት ባለትዳሮች እንደ አዲስ ተጋቢ ምስክር በግራና በቀኝ አቁመውና እንደሙሽራ የሙሽራ ወንበር ላይ ተቀምጣችሁ ካልተፈራረማችሁ አገልግሎት አታገኙም ተብለው፣ባለትዳር ቢሆኑም የሙሽራውና የሙሽሪት ፊርማ በሚለው ሥር መፈራረማቸውን ይቃወማሉ፡፡

ባለትዳሮቹ እንደሚሉት፣ በሃይማኖት ሥርዓት የፈጸሙት ጋብቻ በአስተዳደሩ የክብር መዝገብ መስፈሩ ላይ ተቃውሞ የላቸውም፡፡ ሆኖም በቤተክርስቲያን የተጋቡበት የጋብቻ ምስክር ወረቀት መወሰዱ፣ እንደ አዲስ ተጋቢ ምስክር ቆጥራችሁ ተፈራረሙ መባሉ፣ በእምነታቸው መሠረት ያደረጉትን ጋብቻ የሚያስረዳው ማስረጃ ተወስዶ በአስተዳደሩ ማስረጃ መቀየሩ፣ በሕገ መንግሥቱም ሆነ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ መሠረት በሃይማኖት ስለመጋባት የተሰጠው መብትና ጥቅም መገፈፍ ከሁሉም በላይ ደግሞ በሃይማኖታዊው ሥርዓት የሚከናወነውን ሥርዓተ ተክሊል የሚገልጽ የጋብቻ ማስረጃቸው በማስመዝገብ ስም ሕጋዊ አገልግሎቱ መሸፈኑ አግባብ እንዳልሆነ ያመለክታሉ፡፡

‹‹ጋብቻችንን በቤተክርስቲያን ስንፈጽም የቤተክርስቲያን ሕግ፣ ሥርዓትና ሚስጥራት አሟልተን፣ ከየምንኖርበት ቀበሌ ያላገባ የሚል የምስክር ወረቀት ለቤተክርስቲያን አስተገብተን፣ ምስክር አቁመን፣ የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪ በተገኙበትና በኋላም በተሰጠን ምስክር ወረቀት ላይ ፈርመውበትና ማኅተም ተደርጎበት ጋብቻ ከፈጸምን ስምንት ዓመት ሆኖናል፡፡ ለማስመዝገብ በሄድንበት ወቅት ደግሞ ሃይማኖቴ ከሚፈቅደው ሥርዓትና ድባብ ውጭ በሆነ መንገድ ዳግም እንድንፈራረም፣ ቤክርስቲያኒቷ የሰጠችኝ የጋብቻ ምስክር ወረቀት ዋናው ተወስዶ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በውልና ክብር መዝገብ ማስረጃ አገልግሎት ተመዝግቦ የአስተዳደሩ የጋብቻ ማስረጃ ተሰጥቶኛል፤›› ይላሉ፡፡

ጥንዶቹ የጋብቻ ማስረጃቸውን ለማስመዝገብ መዝጋቢው አካል ጋር የተገኙበት ምክንያት የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ቅርንጫፍ ሦስት ጽሕፈት ቤት ለሌላ ወገን ንብረት መሸጣቸውን ለማሳወቅ ሲሄዱ ዴስኩ ላይ አገልግሎት ከሚሰጡ ሠራተኞች ባለትዳር ከሆኑ የጋብቻ ሰርተፍኬታቸውንና ባለቤታቸውን ይዘው እንዲመጡ፣ ካላገቡ ያላገባ ሰርተፍኬት እንዲያመጡ ስለተነገራቸው ነበር፡፡

ባለጉዳዩ ባለቤታቸው የጋብቻ ሰርተፍኬቱን ይዘው እንዲመጡ በስልክ ይነግሯቸዋል፡፡ ከሰዓታት ቆይታ በኋላ ባለቤትየው ይዘው የመጡትን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት የተጋቡትን የጋብቻ ማስረጃ፣ ዴስኩ ላይ ላሉት ሠራተኞች ይሰጣሉ፡፡ ወዲያው የተሰጣቸው መልስ ግን በቤተክርስቲያኒቱ የጋብቻ ምስክር ወረቀት መስተናገድ እንደማይችሉ፣ ማስታወቂያ ሰሌዳ ቦርዱ ላይ የተጻፈውን እንዲያነቡና አሟልተው እንዲመጡ ነበር፡፡ የሃይማኖት ጋብቻ በኢትዮጵያ ሕግ ተቀባይነት አለው የሚል መከራከሪያ ቢያቀርቡም ከመጨቃጨቅ ውጭ የመጣ መፍትሔ አልነበረም፡፡

በጽሕፈት ቤቱ የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ የተለጠፈው መግለጫም፣ ‹‹አገልግሎት ለማግኘት በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ 1992 አንቀጽ 28 መሠረት (ሀ)  የጋራ የሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት ለመሸጥ፣ ለመለወጥ፣ ለማከራየት፣ በመያዣ ወይም በዋስትና ለመስጠት ወይም በሌላ በማንኛውም ሁኔታ በዚህ ንብረት ላይ ሌሎች ሰዎች መብት እንዲያገኙ ለማድረግ (ለ) ዋጋቸው ከብር 500 በላይ ለሆኑ የሚንቀሳቀሱ የጋራ ንብረቶች ወይም የገንዘብ ሰነዶች ለመሸጥ፣ ለመለወጥ፣ በመያዣ ወይም በዋስትና ለመስጠት ወይም በማንኛውም ሁኔታ ለማስተላለፍ ወይም ለመበደር ወይም ለሌላ ሰው ዋስ ለመሆን (ሐ) ከብር 100 በላይ ያለው የጋራ ንብረት ወይም ገንዘብ ለሌላ ሰው  በስጦታ ለማስተላለፍ ደንበኞቻችን ወደ ጽሕፈት ቤታችን ስትመጡ የተጋቢዎች ስምምነት አስፈላጊ በመሆኑ፣ በተራ ቁጥር (2) ባልና ሚስት በአካል ከቀረቡ የጋብቻ ሰርተፍኬታቸውን ይዘው መቅረብ እንዳለባቸውና በጋራ ፈርመው እንዲገለገሉ ይደረጋል ይልና፣ ለዚህም በተራ ቁጥር 4 የጋብቻ ሰርተፍኬቱን በተመለከተ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ 1992 አንቀጽ 28 ጋብቻን ስለማስመዝገብ በሚለው፣ ጋብቻው የተፈጸመው በማንኛውም የጋብቻ አፈጻጸም ሥርዓት ቢሆንም አግባብ ባለው የክብር መዝገብ ሹም መመዝገብ አለበት ስለሚል፣ ይዛችሁ የምትመጡት የጋብቻ ሰርተፍኬት የክብር መዝገብ ሹም የመዘገበው መሆኑን ማረጋገጥ አለባችሁ፤›› ይላል፡፡

ጥንዶቹ ከአስተዳደሩ ባገኙት የጋብቻ ማስረጃ በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ቅርንጫፍ ሦስት ጽሕፈት ቤት  የተስተናገዱ ቢሆንም፣ ቤተክርስቲያኒቷ ሰጥታቸው የነበረው የጋብቻ ማስረጃ ጥቅም ማጣቱን ይቃወማሉ፡፡

      በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሥርዓት ጋብቻ የፈጸሙት ባልና ሚስቶችም ቤት ለመግዛት በነበራቸው ሒደት ቤተክርስቲያኒቷ የሰጠቻቸው የጋብቻ ምስክር ወረቀት ዋጋ እንዳልነበረውና፣ ለማስመዝገብ በሄዱበት ወቅት እንደ አዲስ ተጋቢ ተደርገው የነበራቸው ዋና የጋብቻ ማስረጃ ተወስዶ በአስተዳሩ እንደተተካ ይናገራሉ፡፡

      በየካ ክፍለ ከተማ ውልና ማስረጃ ምዝገባ አገልግሎት ያገኘናቸው ሌላው አባት አሠራሩ ሁሉ ግራ እንዳጋባቸው ይናገራሉ፡፡ ጋብቻቸውን በባህላዊ መንገድ የፈጸሙት በ1961 ዓ.ም. ሲሆን፣ በጋብቻ በቆዩባቸው ባለፉት 47 ዓመታትም ሰባት ልጆችን እንዳፈሩ፣ የልጅ ልጆችን እንዳዩ ይናገራሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ ወደምትገኘው ልጃቸው ለመሄድ ስለፈለጉ በባህላዊ መንገድ የፈጸሙት ጋብቻ ተመዝግቦ ማስረጃ እንዲሰጣቸው በሥፍራው ቢገኙም፣ ባለቤታቸውንና ከሁለቱም ወገን ሁለት ሁለት ምስክሮች ይዘው እንዲገኙ መደረጉንም፣ ዳግም እንደ አዲስ ሙሽራ መፈራረማቸውንም ይቃወማሉ፡፡

‹‹ከ47 ዓመታት በፊት ከሁለታችን ወገን ሁለት ሁለት ምስክርና አንድ አንድ የነገር አባት አድርገን ተጋብተናል፡፡ ዛሬ ላይ ገሚሱ ምስክሮቻችን በሕይወት የሉም፡፡ እንደዛሬው የዕድሜ እኩያ ወይም በዕድሜ የሚያንሰኝ ሰው ሳይሆን ሽማግሌዎችና በዕድሜ የበሰሉ ነበሩ ሽማግሌ ሆነው ያፈራረሙን፡፡ ዛሬ የልጆቼን ባልና ዘመዶቼን እንደምስክር ቆጥሬ እንደ አዲስ በሙሽራ ወንበር ላይ ተቀምጨ ተፈራርሜያለሁ፤›› ሲሉ አሠራሩ ትክክል አለመሆኑን ይነቅፋሉ፡፡

የሃይማኖት ተቋማት ምን ይላሉ?

በጉዳዩ ዙሪያ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶች አሠራሩ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 11 ላይ የተቀመጠውን መንግሥት በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ ጣልቃ አይገባም ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም የሚለውን መርሕ የሚፃረር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

‹‹ቤተክርስቲያኗ ሕጋዊ ሰውነት አላት፡፡ በመሆኑም ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው ተቋማት ያሏቸው የተለያዩ መብቶችና ጥቅማ ጥቅሞች አሏት፡፡ ከነዚህ መብቶች መካከልም የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ማስፈጸም አንዱ ነው፤›› ያሉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የሕግ አገልግሎት መምሪያ ኃላፊ አፈ መምህር አባ ገብረሥላሴ ጌትነት ናቸው፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ ቤተክርስቲያኗ የምትሰጠውን የጋብቻ ማስረጃ እንደገና እንዲመዘገብ ማድረግ ሕገ መንግሥቱ የሰጣትን መብት ከመግፈፍ አይተናነስም፡፡ በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ አብያተክርስቲያናት ውስጥ አንዱ በዓመት ቢያንስ እስከ 30 የሚደርሱ ጋብቻዎችን ያስፈጽማል፡፡ በመመዝገብ ሰበብ ቤተክርስቲያኒቷ የምትሰጠውን የጋብቻ ማስረጃ መዝጋቢው የሚወስድ ከሆነም አግባብ አይደለም ይላሉ፡፡

በእስልምና ሃይማኖት የሚፈጸመው የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ኒካ በመባል ይታወቃል፡፡ ጋብቻውን ለመፈጸም ከሴቷ በኩል አባት ወይም ወንድም፣ ከወንዱ በኩል እንደዚሁ ሁለት ሰዎች ለምስክርነት መቅረብ አለባቸው፡፡ ጋብቻውን የሚያስፈጽሙ ደግሞ የሃይማኖት መሪዎች ቃዲዎች ይሆናሉ፡፡ ቃዲዎቹ ለጋብቻው መፈጸም የሚያስፈልጉ መሥፈርቶች መሟላታቸውን ካረጋገጡ በኋላ ተጋቢዎቹ መጋባታቸውን የሚመሰክር ፎርም እንዲሞሉ ይደረጋል፡፡ ይህም ፎርም እንደ ጋብቻ ምስክር ወረቀት ሆኖ ያገለግላል፡፡ የጋብቻ ምስክር ወረቀት የሚያስፈልጋቸው እንደ ሃጂ ጉዞ የመሳሰሉ አጋጣሚዎች ሲኖርም፣ ሲጋቡ የሞሉትን ፎርም ለሸሪአ ፍርድ ቤት በማሳየት ማረጋገጫ ያገኛሉ፡፡ ‹‹በዚህ መልኩ ሲሠራ ዓመታት ተቆጥረዋል፤›› የሚሉት በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳይ ጠቅላይ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሼክ ኡመር ኢማም ጋብቻን ማስመዝገብ ብቻ በቂ ነው ይላሉ፡፡

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ምክትል ጠቅላይ ጸሐፊ ዶክተር አባ ሥዩም ፍራንስዋ፣ ቤተክርስቲያኒቷ ከምትከተላቸው ሰባቱ ሚስጥራት አንዱ ሚስጥረ ተክሊል መሆኑን ጠቅሰው፣ ተጋቢዎች ከጋብቻቸው በፊት የሚስጥራት ዝግጅት እንደሚያደርጉ፣ ጋብቻ ሁሌም የፀና እንደሚሆንና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ትምህርት እንደሚሰጥ፣ ያላገቡ መሆናቸው እንደሚረጋገጥ፣ ጋብቻው ከመፈጸሙ በፊትም ስለተጋቢዎች በየአብያተ ክርስቲያናቱ ማስረጃ እንደሚለጠፍና ተቃውሞ ያለው እንዲቀርብ እንደሚጠየቅ ይናገራሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ላለፉት ተጋቢዎች የሚሰጠው የጋብቻ ማስረጃም ማኅተም የተደረገበትና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ነው፡፡

ዶክተር አባ ሥዩም እንደሚሉት፣ እስካሁን ድረስ የጋብቻ ሰርተፍኬት በማስመዝገብ ሒደት ቤተክርስቲያኒቷ የምትሰጠውን ዋናው ኮፒ ተወሰደብን ብለው የመጡ ባይኖሩም፤ በመመዝገቡ ሒደት ዋናው ኮፒ የሚወሰድ ከሆነ፣ የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ ካለማወቅ የመነጨ ነው ብለው እንደሚወስዱት፣ የቤተክርስቲያን ጋብቻም ቤተሰብን በማነጽ ረገድ ለመንግሥት ትልቅ ድጋፍ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

 የሃይማኖት አባቶቹ ስለ ጉዳዩ አለመስማታቸውን፣ ቅሬታ ወደ እነሱ የወሰዱ ጥንዶች አለመኖራቸውን፣ ነገር ግን አሠራሩ በሃይማኖት ተቋማቱ ተቀባይነት እንደሌለውና በጉዳዩ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቶ መፍትሔ ለመስጠት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ሕጉ ምን ይላል?

ለቤተሰብ መሠረት የሆነው ጋብቻ በተለያዩ መንገዶችና ሥርዓቶች ይፈጸማል፡፡ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ስለጋብቻ አፈጻጸም ባሰፈረው ድንጋጌ አንቀጽ አንድ ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት፣ ጋብቻ በአንድ የክብር መዝገብ ሹም ፊት ሊፈጸም ይችላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ጋብቻ ጥንዶቹ የክብር መዝገብ ሹሙ ፊት በመቅረብ ለመጋባት ፈቃደኛ መሆናቸውን ሲገልጹ የሚከናወን ይሆናል፡፡ በአንቀጽ 2 እና በአንቀጽ 3 እንደተገለጸው፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ የጋብቻ ሥርዓቶችም አሉ፡፡

በተለያዩ መንገዶች የሚፈጸሙ ጋብቻዎችም ተጋቢዎቹ ነፃና ሙሉ ፈቃዳቸውን ሲሰጡ፣ አስቸጋሪ ነገር ካላጋጠመ በስተቀር ተጋቢዎቹ 18 ዓመት ከሆናቸው፣ የሥጋና የጋብቻ ዝምድና ከሌላቸው ከጥንዶቹ አንዱ ሌላ ጋብቻ ከሌለው መሠረታዊ ስህተት ካልተፈጸመ የተጋቢዎቹ ጋብቻ የጸና ይሆናል፡፡

ጥንዶቹ በአብሮነታቸው የሚያፈሯቸው ንብረቶች የጋራ ሀብት እንደሆኑም ይቆጠራል፡፡ ይኽም ሁለቱም እኩል መብት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ሲሆን፣ ምናልባት ቢለያዩ፣ በጋራ ያፈሩትን ንብረት እኩል ይከፋፈላሉ፣ ወይም አንድ ንብረት ለመሸጥ ወይም በስጦታ ለሌላ ሦስተኛ ሰው ለማስተላለፍ የሁለቱንም ፈቃደኝነት ይጠየቃል፡፡

‹‹ከ500 ብር በላይ የሚገመቱ ንብረቶችን ለመሸጥ የጥንዶቹ የጋራ ስምምነት አስፈላጊ ነው፤›› የሚሉት በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ቅርንጫፍ ሦስት ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ የማኅበራት ሰነዶች ባለሙያ አቶ ዮሐንስ ማለደ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ የቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ሽያጭ በጥንዶቹ የጋራ ፍቃድ ላይ እንዲመሠረት እየተደረገ ነው፡፡ ባልና ሚስት ነን በማለት ንብረት ለመሸጥ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ትክክለኛ ስለመሆኑ ተጋቢዎቹ የተመዘገበ የጋብቻ ማስረጃ እንዲያቀርቡ እየተደረገም ነው፡፡ ይህ የተጀመረው ኅዳር 2008 ዓ.ም. ላይ በወጣ መመርያ መሠረት ሲሆን፣ አሠራሩ ከግንቦት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. በኋላ ሙሉ ለሙሉ ተፈጻሚነት አግኝቶ እየተሠራበት ይገኛል፡፡

‹‹የሀብት ሁኔታን ስንመለከት ሀብት የሚገኘው በአብዛኛው በወንዶች እጅ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በሴቶች ላይ ትልቅ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድር ነበር፤›› የሚሉት አቶ ዮሐንስ፣ መመርያው ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ ከፍተኛ ለውጥ መመዝገቡን ይናገራሉ፡፡

ይህ ይበል የሚያሰኝ ውጤት ቢሆንም፣ የጋብቻ ማስረጃ ከማቅረብ ጋር እንዲሟሉ የሚጠየቁ መስፈርቶችና በሚስተዋሉ አሠራሮች አግባብነት የላቸውም ሲሉ ጋብቻቸውን በሃይማኖታዊና በባህላዊ መንገድ የፈጸሙ ጥንዶች ይናገራሉ፡፡ ጋብቻቸው መመዝገቡ ባይከፋም ጋብቻቸውን በፈጸሙበት ዕለት የተሰጣቸውን የምስክር ወረቀት ገቢ አድርገው በምትኩ ሌላ የጋብቻ ማስረጃ እንዲወስዱ መደረጉ እያስመዘገቡ ያለበት መንገድም፣ ማስመዝገብ ሳይሆን ዳግም ጋብቻ የመፈጸም ያህል እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ምዝገባውን ለማድረግ የሚጠየቁት መስፈርቶች በአብዛኛው ጋብቻቸውን በሃይማኖት ሲፈጽሙ ያከናወኗቸው ያህል መሆኑን ይናገራሉ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንቃተ ሕግና የምክር መስጠት የሕግ ኤክስፐርቶች የሆኑት አቶ ብሩክ ትዕዛዙና አቶ ልሳኑ ክብሩ፣ ጋብቻንና ቤተሰብን በተመለከተ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 34 ላይ የተቀመጠውን፣ ዝርዝሩ በሌላ ሕግ እንደሚደነገግ በወሰነውና በ1992 በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ መሠረት፣ በክብር መዝገብ ሹም ፊት የሚፈጸም ጋብቻ፣ በሃይማኖት ሥርዓት የሚፈጸምና በባህል ሥርዓት የሚፈጸም ጋብቻ ጸንቶ ባለው ሕግ ተቀባይነት አላቸው፡፡

የቤተሰብ ሕጉ በሦስቱ መንገድ የተፈጸሙ ጋብቻዎች ሕጋዊነታቸው የፀና ነው ቢልም፣ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች የቤተሰብ ሕጉን አንቀጽ 28 በመጥቀስ ጋብቻው በክብር መዝገብ ሹም መመዝገብ አለበት በሚል በሃይማኖትና በሽምግልና የፀኑ ጋብቻዎችን ለሚሰጧቸው አገልግሎቶች በማስረጃነት አይቀበሏቸውም፡፡ ሆኖም ባለሙያዎቹ በክብር መዝገብ ሹም፣ በሃይማትና በባህል የተፈጸሙ ጋብቻዎች ሕጋዊ ውጤታቸው ተመሳሳይ እንደሆነና ምንም ዓይነት ልዩነት እንደሌላቸው በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 40 መደንገጉን ይናገራሉ፡፡

‹‹ውጤት›› የሚለውን ሲገልጹ፣ ጋብቻዎቹ በሕግ ፊት ዕውቅና እስከተሰጣቸው ሕጋዊ መሆናቸው የተረጋገጠ ነው ለማለት ነው፡፡ ለመሸጥ፣ ለመለወጥ፣ ለመደበርም ሆነ ማንኛውንም ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ሲያከናውኑ የሃይማቱን አልቀበልም፣ በመንግሥት የሚከናወነውን እቀበላለሁ የሚሉ ዓይነት ጥያቄች እንዳይነሱ ለማረጋገጥ ‹‹ሕጋዊ ውጤት አላቸው፤›› ተብሎ ተቀምጧል ይላሉ፡፡

በጽሕፈት ቤቶቹ በኩል የቤተሰበ ሕጉ ‹‹ማንኛውም ጋብቻ በመዝገብ ሹም መመዝገብ›› አለበት ስለሚል ነው የሚል ማስታወቂያ ቢለጠፍም፣ የሕግ ባለሙያዎች የጋብቻ ማስረጃን ማስመዝገብና ከሦስቱ የጋብቻ ዓይነቶች የምቀበለው አንዱን ነው ማለት እንደሚለያይ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ጋብቻ ተፈጸመ የሚባለው መቼ ነው? ሲባል ከሥርዓቶቹ ባንዱ ጋብቻ የተፈጸመበት ዕለት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ አዲስ የጋብቻ ማስረጃም አያስፈልግም፡፡ በየትኛውም ሥርዓት የተፈጸመ ጋብቻ ግን መመዝገብ አለበት፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡ አንድ የሃይማኖት ተቋምም እነዚህን ሰዎች አጋብቻለሁ የሚል የምስክር ወረቀት ከሰጠ፣ የምስክር ወረቀቱን ይዞ የሄደ ሰው ጥያቄ ካልተነሳበት በስተቀር የክብር መዝገብ ሹሙ መመዝገብ አለበት፡፡ መመዝገብ ያስፈለገውም አንዱን በአንዱ ለመተካት ሳይሆን ውልደት፣ ሞትና ጋብቻ ለአንድ አገር ስታትስቲክስ አስፈላጊ ስለሆኑ ይህንኑ ለማጠናከርና ለመረጃ ዓላማ ነው፡፡

ችግሩ የተፈጠረው የሕጉ አረዳድ ላይ ነው ሲሉም ይጠቅሳሉ፡፡  የጋብቻውን ዋናውን ቅጂ ለራሳቸው አስቀርተው አስተዳደሩ የሚሰጠውን ማስረጃ መስጠታቸውም አግባብነት እንደሌለው ያብራራሉ፡፡ አዲሱ የወሳኝ ኩነቶች መመርያም ቢሆን ይህንን አይልም፡፡

ማንኛውም ተቋምም ከሦስቱ ሥርዓቶች በአንዱ የተጋቡ ጥንዶች የሚያቀርቡትን ማስረጃ በተቋማቸው አገልግሎት አይሰጥም ብለው መመለስ አይችሉም፡፡ ባለሙያዎቹ እንደሚሉትም፣ እንዲህ የሚያደርጉ ተቋማት አገሪቷ ካወጣችው ሕግና በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 40 ከተቀመጠው በተቃራኒ የሚሠሩ ናቸው፡፡

ሕጉ በግልጽ እንዳስቀመጠው፣ በሦስቱም ዓይነት የተፈጸሙ ጋብቻዎች ሕጋዊ ውጤት ያላቸው ቢሆንም፣ በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ኤጀንሲ ጽሕፈት ቤቶች የባህልና የሃይማኖት ተቋማት የጋብቻ ማስረጃዎች ተቀባይነት አጥተዋል፡፡ በቤተሰብ ሕጉ ጋብቻን ማስመዝገብ የሚለውም በመዝጋቢው አካል ሲከናወን፣ በባህልና በሃይማኖት ተቋማት የተሰጡ ማስረጃዎች ዋና ቅጂው ተወስዶ አስተዳደሩ በሚሰጠው መተካቱ አግባብ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ቀለበት ከማድረግና ያላገባ የሚል ማስረጃ ከማቅረብ ውጭ አዲስ ሙሽራ ሲጋባ የሚያስፈልገውን ሒደት በሙሉ እንዲያልፉ መገደዱ፣ የቤተሰብ ሕጉ ከሚለው ውጪ ነው፡፡

ኩነቶችን የማስመዝገብ ፋይዳ

በተለያዩ መንገዶች የሚፈጸሙ ጋብቻዎች ከተፈጸሙበት ቀን ጀምሮ ውጤት አላቸው፡፡ ነገር ግን ጋብቻውን በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ እንዲመዘገቡ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ የኮሙዩኒኬሽን የሥራ ሒደት መሪ ማኅደር ንጉሴ እንደምትለው፣ ጋብቻን ማስመዝገብ የተለየ አገራዊ ፋይዳ አለው፡፡ የተጋቢዎችን ቁጥር መመዝገብ የሚወለዱ ሕፃናትን ቁጥር ለመገመት ይረዳል፡፡ በጥንዶቹ ሕይወት ላይም እንደዚሁ የተለየ ሚና ይጫወታል፡፡ የውርስ፣ ልጅነትን የመቀበልና የንብረት ባለቤትነትን በተመለከተ የሚያጋጥሙ ጉዳዮችን በቀላሉ ለመፍታት ይረዳል፡፡

ይሁንና ወሳኝ ኩነቶችን የማስመዝገብ ባህሉ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ጋብቻን የማስመዝገብ ባህሉ እየተሻሻለ ቢመጣም፣ አሁንም ብዙ ይቀረዋል፡፡ በ2005 ዓ.ም. የተመዘገቡ ጋብቻዎች ከ27,578 አይበልጡም፡፡ በ2006 ዓ.ም. የማሽቆልቆል ነገር ታይቷል፡፡ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ የተመዘገቡ ጋብቻዎች 19,835 ናቸው፡፡ በ2007 የተመዝጋቢዎች ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በልጦ ነበር፡፡ 30,813 ጋብቻዎች መመዝገብ ችለዋል፡፡ 2008 ዓ.ም. ከገባ በወራት ውስጥ 15,703 ጋብቻዎች ተመዝግበዋል፡፡ ተመዝጋቢዎቹ ከ1970ዎቹ ጀምሮ ተጋብተው የሚኖሩ ጥንዶች ሲሆኑ፣ ጋብቻቸውን የሚያስመዘግቡትም በፈቃደኝነት ሳይሆን በአጋጣሚዎች ተገደው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዋ እንደምትለው፣ ጋብቻዎቹን ለማስመዝገብ የተጋቢዎቹ መታወቂያ ያስፈልጋል፡፡ መታወቂያ ካልተገኘ ደግሞ ፓስፖርትና መንጃ ፈቃድ ማሳየት በቂ ነው፡፡ ምስክሮችና የተጋቢዎች ፎቶግራፍ ያስፈልጋሉ፡፡ ከሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ሁሉም ኩነቶች በአስገዳጅ ሁኔታ እንዲመዘገቡ ይደረጋል፡፡ በየክፍለ ከተሞቹ የሚገኙ 117 ወረዳዎችም አገልግሎቱን እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ በምዝገባ ሒደቱ ላይ የሚስተዋሉ አንዳንድ ክፍተቶችንም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በመሥራት ለመሙላት ታስቧል፡፡

በሃይማኖት ተቋማት የሚሰጡ የጋብቻ ማስረጃዎችን በምዝገባ ሒደት ለምን ዋናው ኮፒ እንደሚወሰድ ሲጠየቁም፣ ከመመለስ ተቆጥበዋል፡፡

ምሕረት ሞገስ እና ሻሂዳ ሁሴን

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ