Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አሰልቺ ምኞቶች

ሰላም! ሰላም! ‘ዮፎዎች በሰማይ ሲያይሽ ዋሉ …’ እያሉ አገሬን ሲያምታቷት የሰነበቱት ሰዎች ዓላማቸው ምን እንደሆነ እንጃ። ከዓለም ሥልጣኔና ዕውቀት ተነጥሎ ለሺሕ ዓመታት የኖረ ሕዝብ እያለላቸው እነሱ ራሳቸው ይህን ያህል ‘በዩፎ ቲዎሪ’ መመሰጣቸው አንዳንዴ አይገባኝም። እዚህ እንደ ልባችን የምንረግጠውን የምንኖርበትን ዓለም በደንብ አጥርተን አውቀን ያልጨረስን ሰዎች፣ ካልታወቀ ዓለም የሚመጡ ያልታወቁ በራሪ አካላት እያልን የምንሸበረው ለምን ይሆን? ስል ሰነበትኩ። ኧረ የሚያምታታን በዛ ምን ይሻላል ጎበዝ! ታዲያ ከሁሉ ነገር በላይ ሐበሻ መሆኔ የሚያኮራኝና የሚያስደስተኝ ለክፉም ለደግም ለአዲስ ነገር ያለመበገር ፅኑ መንፈሴ ነው። በመጠየፍና በማጣጣል ጎዳና ፈረንጅ ላይቀድመን ትተነው መሄዳችንን እንጃ መቼ እንደሚያውቀው። እና ‘ላሊበላ አናት ላይ ያልታወቁ በራሪ አካላት ሲበሩ ታዩ’ በሚል ሰበብ ታላቁን የላሊበላ የሥነ ሕንፃ ቅርስ ላይ ‘ቲዮሪ’ መቀመሩን የባሻዬ ልጅ ነገረኝ።

እንደምታውቁት ሕንፃው የተገነባው ቀን ቀን በሥጋ ለባሾች፣ ሌት ሌት በመላዕክትን ነው የሚል ዘመናትን የተሻገረ ታሪክ አለ። ታዲያ ይህንን አስታውሰው ‘ዩፎዎች’ ከስንትና ስንት ዓመታት በኋላ በላሊበላ ሰማይ ላይ ዘለግ ያለ የሻይ ሰዓት የወሰዱት ሥራቸው በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ለማጤን ነው ዓይነት አንድምታ ያለው ነገር መለፈፋቸውን ሰማሁ። አይገርማችሁም? ትናንት እንዲህ ተምታቶብን ስንምታታ ኖርን፡፡ በእጆቻችን መፍጠር የምንችለውን ተዓምር ለአማልዕክቱና ለተመሩጡ ሰዎች ብቻ ሰጥተን በድህነት ተኮራምተን ሳለን ኋላቀሮች፣ ሞኞች፣ ጅሎች ሲሉን ኖረው ዛሬ ‘የእግዜርን ለእግዜር፣ የሰውን ለሰው’ ብለን በዕውቀታችን፣ በወኔያችን፣ በእጆቻችን እንሠራለን ብለን ስንነሳ የለም ትላንት ነበራችሁ ልክ ዛሬ እየተሳሳታችሁ ነው ሊሉን ያምራቸዋል። እንዲህ በቀላል ድራማ የሐበሻ ወኔ የሚከዳ ቢሆን ኖሮ እንደ ጣሊያን ያለ ቴአትረኛ አይጥለንም ነበር ያለኝ ማን ነበር በፈጠራችሁ?

እናላችሁ በሰርክ መሰባሰቢያችን ካፍቴሪያ ስለገበያው፣ ኑሮው፣ ወቅታዊ የልዩ ልዩ አውቶሞቢሎች ተመን ‘አፕዴት’ የምንደራረግባት ካፌ አለችን። ታዲያ ይኼ የሰሞኑን የዩፎ ቅኝት ዜና ተነሳና ወዳጆቼ አስተያየት መስጠት ጀመሩ። አንዱ ጀመረ፣ ‹‹እኔ እውነት ከእኛ ውጪ ሌላ በዓለም ላይ ፍጡር አለ ብዬ አላምንም። እነዚህንም ዩፎ የሚባሉ ወፈፌ ነገሮች ሳስብ የሚመስለኝ የምዕራባውያን የስለላ መንገድ ነው፣ አስቡት። ያልታወቁ በራሪ አካላት እያሉ በተለየ አቋምና መልክ ሮቦት አበጅተው ያለጠያቂና ኩርፊያ የፈለጉት አገር ገብተው የፈለጉትን ዓይተው ለመውጣት ይኼን ከመሰለ ዘዴ ሌላ ምን አለ? ባይሆን እንኳ የጌታ ምፅዓትን ለማመቻቸት በቅድሚያ የተላኩ የስለላ መንኮራኩሮች ሳይሆኑ አይቀሩም፤›› ብሎ ይምል ይገዘት ጀመር።

‹‹ኧረ በፈጠራችሁ አሁን ይኼን ወሬ ብለን ስናወራ ራሱ አናሳፍርም። እዚህ ከጎናችን ከአንድ አባት ከአንድ እናት ተወልደናቸው እንዳልተፈጠሩን፣ እንዳልተጎራበቱን፣ አብረውን እንዳልበሉ እንዳልጠጡ ባዕዳን ፍጥረታት የሚያሰቃዩን እያሉ፣ እስኪ አሁን ዮፎዎች ምን አደረጉን ብለነው እንዲህ ስናነሳ ስንጥላቸው የምንኖረው?›› ያለው ሌላኛው ወዳጃችን ነበር። ይገርማችኋል ኋላ ብቻዬን ሆኜ ያለውን እያስታወስኩ ከራሴ ጋር ሳወራ ትልቅ ነገር እንደተናገረ ገባኝ። አንዳንዶች ለምን እንደሆነ አላውቅም ሲለዩንና ሲያልፉን ነው የተናገሩት የሚገባን። በተለይ እዚህ አገርማ ሰውን መሬት ስትበላው ነው፣ ‘እሱ እኮ የሚናገረው አንዱ እንኳ መሬት ጠብ አይልም’ ይባልለታል። እናም ለራሴ እንዲህ ብዬ የሚል ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ ‹‹ማን ነው ዩፎው? ዩፎ አልበዘበዘን። ዩፎ ያለጉቦ ጉዳይ አላስጨርስም አላለን። ዩፎ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ፀር ሆኖብን አያውቅ። ኧረ እስኪ ልጠይቃችሁ . . . አንተዬ ኧረ ከዩፎ ምን አለን?››

በቀደም ደግሞ ውዷ ማንጠግቦሽ፣ ‹‹ጎርፍ ሳይበላኝ በፊት ዶሮ ወጥ አብላኝ፤›› ብላ ሰቅዛ ያዘችኝ። የ2004 ቢኤምደብሊዩ አውቶሞቢል እጄ ላይ ነበርና መጀመሪያ ትኩረቴን ወደ ድለላዬ አደረግኩ። ‹‹አንድ ዶሮ ለመግዛት ምነው ይኼን ያህል ጭንቅ?›› አለኝ አንድ ሆላንድ የሚኖር ዳያስፖራ ወዳጄ በቫይበር። ‹‹አንተ ምን አለብህ? በአርባ ስምንት ሰዓት ውስጥ ልጅነቱን፣ ጉርምስናውንና ጎልማሳነቱን የጨረሰ ዶሮ በዩሮ ገዝተህ ትበላለህ፤›› አልኩት እንዳየ ሰው። እኔ እኮ በግምት ነው። ‹‹በምን አወቅክ ዘጠኝ ዮሮ እንደሆነ?›› አይለኝም? እንግዲህ ዘጠኝ ጊዜ ሃያ አምስት ብላችሁ ስትመቱት 225 ብር ይመጣል። ‹‹ለነገሩ ያው ነው …›› ስለው ‹‹ተው! ተው! ያው ቢሆንማ ይኼን ያህል ዘመን ከአገሬ ወጥቼ እቀራለሁ?›› ብሎ በቀን በቀን ሙሉ ዶሮ በዚያው ዋጋ እየገዛ ቤቱ እንደሚገባ አጫወተኝ።

ወይ የአውሮፓና የአፍሪካ ልዩነት? ‹‹እዚያ የዶሮ የነፍስ ወከፍ ገቢ የእኛን የሰዎቹን በእጥፍ ይበልጠዋል እኮ ማለት ነው፤›› ስለው ለባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ቢሆንም እኛ ታርደን አንበላ . . .›› እንዳለ አፉን ከፍቶ ቀረ። ምናልባት ላይ ሲደርስ በዚህች ምስኪን ምድር ደሙ ደመ ከልብ ሆኖ የቀረው ሰው ቁጥር ትዝ ብሎት ይሆናል ብዬ እኔም ዝም አልኩት። እና እንዳልኳችሁ ካፌ ተፍ ብዬ ያቺን ቢኤም አሻሻጥኩና (ደግሞ ቢኤም ስል ጦር መሣሪያ መስሏችሁ እንዳትጠቁሙብኝ አደራ፣ ፍቅር ለራቀው ኅብረተሰብ ቁልምጫ ደባ ነው ሲሉ ሰምቼ እኮ ነው) ዶሮ ልገዛ ወደ ሰው ገበያ ሄድኩ። ዘንድሮ የሚገዛው ዶሮ የሚሸጠው ሰው ሆኗል ብዬ እኮ ነው። ጉድ ማለቂያ የለው!

ብታዩት ደረቱ እንደ ቅርፅ ተወዳዳሪ ጡንቸኛ ያበጠ ዶሮ ገዛሁና ወደ ቤቴ መጓዝ ጀመርኩ። መንገድ ላይ የሰሞኑን የማንጠግቦሽ ሁናቴ ትዝ እያለኝ አስባለሁ። ብታዩዋት ዕቃ ማጠቡን፣ ልብስ ማለቅለቁን፣ በብርጭቆ ቀድታ ውኃ መጠጣት ሳይቀር ደርታ ልትሞት ነው። በተለይ በያዝነው ክረምት አንድ ሚሊየን ገደማ ነዋሪዎች በጎርፍ ይጠቃሉ የሚል መርዶ ማን እንደነገራት አላውቅም። እኔማ ሚትዮሮሎጂ ደግ ደግ የአየር ጠባይ መተንበይ ሲሳነው ለማናችንም የማይቀርልንን በከፊል ወደ መተንበዩ ገባ እንዴ? እያልኩ ከባሻዬ ጋር አውርቻለሁ። ባሻዬ ከሁሉ ከሁሉ ስሙን ሲሰሙት ገና የዚህ ተቋም አቋቋም በሳቅ ጦሽ ያደርጋቸዋል። ረሃብ ጥጋቡን መተንበይ ባልቻለ አገር ለደመና ተንባይ ተቋም በጀት መመደቡ ያስገርማቸዋል። የሰውነታችን ሙቀትና ቅዝቃዜ መቆጣጠር የሚያስችል ጤናማ አኗኗር ሳንኖር፣ የተመጣጠነ አመጋገብ ሳንመገብ ነገ ይበርዳል እሳት ሙቁ፣ ነገ ይሞቃል ተገላለጡ የሚል ትንበያ እርባናው አይታያቸውም። ‹‹ያው ቢሞቅ ከልኩ፣ ቢበርድም ከልኩ በማያልፍ ተፈጥሮ ያደላት አገር …›› ይላሉ የሚሉት አያጡ።

እንግዲህ ይኼ የባሻዬ አመለካከትና አረዳድ ነው። ድንገት ባሻዬን እንዲህ እያስታወስኩ ገደድ ስል፣ ‹‹አትዘቅዝቀው እንጂ ቀና አድርገው፤›› ብሎ አንዱ ጆሮዬ ላይ ጮኸ። ዘወር ብዬ ሳየው እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ እኔ ላይ አፍጧል። ‹‹እኔን ነው?›› ስለው ክው ብዬ፣ ‹‹ታዲያ ማን ነው ይህንን ተናፋቂ ክቡር ነገር ዘቅዝቆ የያዘ?›› ብሎ ዶሮውን ጠቆመኝ። ይኼኔ እኮ ሰው ተዘቅዝቆ ቢያይ ትንፍሽ አይልም። ለነገሩም እኛም አንልም። ‹‹ምነው ባንተነፍስ አይደል እንዴ ዕድሜ የቀጠልነው? ስንት ዓይነት ሰው አለ …›› ብዬ ሳልፈው ደግሞ ከወዲያኛው አስፓልት አንዱ ወደ እኔ አቅጣጫ እየተሻገረ፣ ‹‹እናንተ ምን አለባችሁ? ብርዱ ቆዳችንን የዶሮ ቆዳ አስመስሎት ውለን እናድራለን እናንተ ቁርስ የዶሮ ፍርፍር፣ ምሳ የዶሮ ፍትፍት፣ ራት የዶሮ መረቅ ታማርጣላችሁ፤›› ብሎኝ አለፈ። ‘እናንተና እኛው’ እስኪ አሁን ቢቀርስ?!

በሉ እንሰነባበት። ከስንት ስድብና ግልምጫ በኋላ ቤቴ ስደርስ አላመንኩም። ደረታሙ አውራ ዶሮ ራሱ ያን ሁሉ ስድብና ሒስ ሲያዳምጥ ውሎ በቀላሉ የሚታረድልኝ አልመሰለኝም ነበር። ኧረ አፍ አውጥቶ ‘በሕግ አምላክ! እስራቴን ፍታ!’ ብሎ ቢጮህብኝ ኖሮስ? ዘንድሮ እኮ ከሰው መብት ይልቅ ለእንስሳት የሚያዳላው በልጧል። ካላመናችሁ ያን ሆላንድ የሚኖር ወዳጄን ስልክ እሰጣችሁና ታወሩታላችሁ። ‹‹ደቾች ከውሻ ጋር እጅግ የተለየ ቁርኝት አላቸው፤›› አለኝ በቀደም። ‹‹ምን ይገርማል ይኼ? ፈረንጅ ሲባል ለውሻ ልዩ ትኩረት አለው፤›› አልኩት ቀለል አድርጌ። ‹‹የለም! የለም! ለምሳሌ እዚህ አንድ የምታውቀው ደች ውሻው መሞቱን ሰምተህ እግዜር ያፅናህ ካላልከው በቃ ያንተና የእሱ መጨረሻ ተቆረጠ ማለት ነው። ከቻልክ የውሻው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘት አለብህ፤›› አይለኝም? እዚህ እኛ ማን ይቀብረኛል ማን አይቀብረኝም ይወዘውዘናል ያደላቸው ውሻ በሬሳ ሳጥን ይቀብራሉ። ባሻዬ የእኔን ልዩ መረጃ ስነግራቸው መሳቅም ማልቀስም ቸግሯቸው እንደ ሌሊን ሐውልት ወደ ግራ እንደ ዞሩ ቀሩ። ትርጉሙን እንጃ።

ኋላ ከዞሩበት ሲመለሱ፣ ‹‹የተመረቁት ለውሻ ለቅሶ አቆልቋይ ያደራጃሉ። አለን እንጂ እኛ መኖርም መቀበርም የማያምርብን፤›› ብለው ተቆጡ። እኔ ግራ ገባኝ። መኖሩንስ እሺ። ‹‹ግን እኮ ባሻዬ እኛ ኢትዮጵያውያንን የመሰለ የተዋጣለት አዛኝና አስተዛዛኝ የለም ነው የሚባለው፤ ስላቸው፣ ‹‹ሚስጥሩ ምን ይመስልሃል ታዲያ?›› መልሰው ጠየቁኝ። ‹‹እንጃ!›› ከማለቴ፣ ‹‹ወዬው ለራሴ ነው። የሐበሻ ሐዘን ወዮ ለራሴ ነው። ሐዘን ሲደምቅ ደረት ሲደቃ፣ ፊት ሲቧጠጥ ብታይ ወዮ ለራሴ ነው። ሰው ከሰው ተወልዶ የውሻን ያህል እንኳ ያለክብር፣ ያለመብት፣ ያለነፃነት፣ ያለዕውቀት ዘቅጦ ኖሮ ሲሞት ስታይ ባታውቀውም ታለቅሳለህ። ለምን?›› ሲሉኝ ቀለብ አድርጌ፣ ‹‹ወዮ ለራሴ!›› አልኳቸው። ‹‹ኤክዛክትሊ!›› ብለው ጨዋታውን ደመደሙት። በክብር ኖረን፣ መብት ጠብቀን፣ መብት አስጠብቀን፣ ግዴታ አሟልተን፣ እንዲያው በአጭሩ እንደ ሰው ኖረን እንደ ሰው ሟች ያድርገን ብያለሁ። ይኼ እንግዲህ ምኞት ነው፡፡ ምኞት አይከለከልም። የምኞት ነገር ሲነሳ ደግሞ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው የሚመስሉ ወሬዎች የበዙበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ እንደ ሰው የሚያኖሩና የሚያሳልፉ ሳይሆኑ፣ ከሰውነት ደረጃ የሚያወርዱ አሮጌ ድርሳናት በዝተዋል፡፡ በተረት ተረት የተጀቦኑ አሮጌ ታሪኮች፡፡ ሰው መሆንን ሳይሆን ከሰው በታች መሆንን የሚሰብኩ፡፡ በአዲስ መሸፈኛ ውስጥ የተደበቁ አሮጌ ሐሳቦች ይሰለቻሉ፡፡ አሰልቺ ምናቶች ለዘመኑ ትውልድ አይመጥኑም፡፡ መልካም ሰንበት!    

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት