ኢትዮጵያ ውስጥ ዓይናችን የሚያየው ዕድገት፣ ተስፋ ሰጪ ለውጥና አበረታች የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን አለ፡፡ በዚያው ልክ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግጭት፣ አለመግባባት፣ የሰው ሕይወትና የንብረት ውድመት እየተከሰተ ነው፡፡ ፖለቲካው ተረጋግቶ ከርሟል ሊባል አይችልም፡፡ ይልቁንም በበርካታ አካባቢዎች ነውጦች በስፋት ታይተዋል፡፡
በቅርቡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የተጣራ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጉዳይ ሪፖርት ብቻ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ከ300 በላይ ያልታጠቁ ዜጎች ሕይወት አልፏል፡፡ ከአሥር በላይ የፀጥታ ኃይል አባላት ሕይወትም እንዲሁ፡፡ በአካል ጉድለት፣ በንብረት ውድመት የሚጋለጠው ችግርም ከተለመደው ጊዜ የባሰ ነው፡፡ መደማመጥ ጠፍቶ ግጭት በነገሠበት በዚህ ወቅት መፍትሔ ካልተፈለገ አያያዛችን አያምርም፡፡
በዚሁ ዓመት በጋምቤላ ክልል፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቡለን አካባቢ፣ በደቡብ ክልል በኮንሶ ልዩ ዞን የተከሰቱ ሌሎች ግጭቶች የሰው ሕይወት አጥፍተዋል፡፡ ቀላል የማይባል የንብረት ውድመትን፣ የዜጎችን መደናገጥና መፈናቀልን አስከትለዋል፡፡
ይኼው አደጋ አሁንም አልበረደም፡፡ ከሰሞኑ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ጎንደር፣ ደባርቅና ዳባት ከተሞች ላይ ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል፡፡ በተለይ በጎንደር ከተማ የዜጎችንና የፀጥታ ኃይሎችን ሕይወት የቀጠፈ ግጭት ተከስቷል፡፡ ከሁሉም በላይ በማንነታቸውና በብሔራቸው ምክንያት የግጭቱ ሰለባ የሆኑ የአገሪቱ ዜጎች ንብረት ወድሟል፡፡ ተዘርፍል፡፡ ይህ ከፍተኛ ሊባል የሚችል የማንቂያ ደወል ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያንን ምንን ይነግራል? ተብሎ በጥልቀት ምክክር ካልተጀመረበት ከፍተኛ አደጋ ከፊታችን መደቀኑ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ መነሻውን አንዳንድ በአንድ መመልከት ያስፈልጋል፡፡
ፌዴራሊዝሙ ለጥላቻ አቀጣጣዮች እየዋለ ነው
አስከፊው የደርግ አምባገነናዊ ሥርዓት ከተወገደ በኋላ ሥልጣን የያዘው ኢሕአዴግ መራሽ መንግሥት ፌደራላዊ ሥርዓትን ለማስፈን ሞክሯል፡፡ ይሁንና ይህ ሥርዓት ብሔርና ቋንቋን መሠረት አድርጎ የተገነባ እንደመሆኑ በአገሪቱ አንድነት ላይ የፈጠረው ጫና አለ የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ለዘመናት በአሀዳዊ ሥርዓት ታስረው የቆዩትን ብሔር ብሔረሰቦች የእኩልነት መብት ይበልጥ አጎናጽፎአቸዋል የሚሉም ይገኙበታል፡፡
እውነታው ግን ከዚህ ፌደራል ሥርዓት ትግበራ በኋላ የብሔር ብሔረሰቦች መፋጠጥና መጠራጠር ያለጥርጥር ተባብሷል፡፡ በቅርቡ አንድ ታዋቂ ብሎገር ‹‹አካሄዳችንን በጊዜ ስላላረምነው ምድራችን ሩዋንዳ ሩዋንዳ ስላለመሽተቷ ምን ዋስትና አለን?›› ማለቱን ያጤኑዋል፡፡
በአንድ በኩል በብዙ መስዋዕትነትና ትግል ይህን የአገሪቱ የለውጥ ተስፋ በግንባር ቀደምነት ያመጣው የትግራይ ሕዝብ በጅምላ ‹‹ወያኔ›› እየተባለ ነው፡፡ ጉዳቱ ስም ስለወጣለት አይደለም፡፡ ይልቁንም ከሥርዓቱ ዋነኛ ተጠቃሚ እንደሆነ ከመደረጉ ባሻገር፣ የሌላውን ሕዝብ ጥቅምና ሀብት በልዩነት እንደሚወስድ ተደርጎ ፕሮፓጋንዳ ይነዛበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋነኞቹ አቀንቃኞች ከሥርዓቱ ጋር የመረረ ፀብ አለን የሚሉ ፅንፈኛ ወገኖች ናቸው፡፡ አንድን ሕዝብ ለይቶ በጠላትነት መፈረጅ ፀረ ዴሞክራሲ አመለካከት ከመሆኑም በላይ፣ ኃላፊነት የማይሰማቸው ግብዞች ተግባር ነው፡፡
በሌላ በኩል በፌደራል ሥርዓቱ ‹‹መብትህን አስከብርልሃለሁ›› ቅስቀሳ ስም፣ የቀድሞዎቹ ሥርዓቶች የወጡበት ማኅበረሰብ የጥላቻ ቅስቀሳ ተካሂዶበታል፡፡ በተለይ አንዳንድ በመንግሥትና በገዥው ፓርቲ ውስጥ ተወሽቀው ‹‹አማራ›› እና ‹‹ነፍጠኛ›› የሚባለውን መገለጫ እያቀለቀሉ በንፁኃን ዜጎች ላይ ሳይቀር ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉት ያልተቋረጠ ቅስቀሳ ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏል፡፡
በደቡብ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ለሚነሳው ግጭት መንስዔውም ‹‹ማንነት›› እና ጥቅም ነው፡፡ ሲዳማው ከወላይታው፣ ኮንሶው ከጋሞው የሚገናኝበት ቤተሰባዊ ገመድ እየላላ በሥልጣን፣ በኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ሒሳቡን ሲያወራርድ ማየት በእጅጉ አስከፊና አሳዛኝ ነው፡፡
ከዚህ አንፃር አሁን ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌደራላዊ ሥርዓት በሁለት መንገዶች ችግር ላይ ወድቋል፡፡ በአንድ በኩል ሥርዓቱን የተቃወሙ ያሉ የውስጥም ሆኑ የውጭ ኃይሎች ጠባብነትን ዋነኛ የፖለቲካ መሣሪያ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ይህ ከዚህ ቀደም በአሀዳዊነትና ‹‹ትምክህት›› ሲወቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች (ኅብረ ብሔራዊ አደረጃጀቶችን) ሳይቀር እየሳበ ሲመስል ይበልጥ ያስደነግጣል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ››ን አስቀድመው ብዙ የደከሙትን ሁሉ የብሔር ካባን ደርበው እንዲባዝኑ ማድረጉ በራሱ የሚፈጥረው ነገር አለ፡፡
በሌላ በኩል ራሱ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ከብሔራዊና አገራዊ ይልቅ አካባቢያዊና ብሔረሰባዊ ትርጉሙ ላይ ለ25 ዓመታት የዘለቀበት መንገድ ችግር ላይ ወድቋል፡፡ ማንነትና ብሔር ይጨፍለቅ እንኳን ባይባል አገር ከምትባለው የጋራ ሀብት በላይ መቀንቀኑ፣ በማንነት ላይ የተመሠረተ የብሔራዊ መገለጫ መሰጠቱ፣ ከዕድርና ከማኅበር አንስቶ ባንኩ፣ ፓርቲው፣ አክሲዮኑ፣ ደብሩና አጥቢያው ሁሉ ብሔር ተኮር መሆኑ ቀስ በቀስ እየፈጠረ ያለው ፍጥጫ ከፍተኛ ነው፡፡
ከዚህ አንፃር የፌደራል ሥርዓቱ የቆመበት መሠረት በጥልቀት ከልብ መፈተሽ አለበት፡፡ ዛሬ በሕዝብም ይባል በፖለቲካ ፓርቲዎች ደረጃ የሚታየው የመነጣጠልና የጥላቻ ዝንባሌ ነገ በክልል መንግሥታት ደረጃ ዕውቅና ቢሰጠውስ? በራሱ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ባሉ አካላት የሐሳብ ክፍፍል ቢያስነሳስ? እነዚህ ሁሉ መተንበይ ያለባቸው ክስተቶች ናቸው፡፡ ዛሬ እንደ ዋዛና ቀላል የሚመስሉ ጉዳዮች ሁሉ ነገ በተለያዩ አገሮች እንደታዩ አስከፊ ክስተቶች መነሻ እንዳይሆኑም መሥጋት ተገቢ ነው፡፡
ከእነዚህ እውነታዎች አንፃር የፌደራል ሥርዓቱን እንከኖች መፈተሽ ተገቢ ነው፡፡ የጠባብነትና የትምክህት ዝንባሌውን መርምሮ መግደልም ተገቢ ይሆናል፡፡ ከሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በአገራዊ ጉዳይ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምክክር መጀመርም ያስፈልጋል፡፡ ከሁሉ በላይ የሕዝቡን የመቻቻልና የኑሮ አንድነት መጠገን ተገቢና አስፈላጊ ነው፡፡ ለነገ የሚባል ሥራም አይደለም፡፡
የሕዝብ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ይፈልጋሉ
በመላው አገራችን በተለያዩ መንገዶች የሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎች በተለያዩ ምክንያቶች እንደሚነሱ ይታወቃል፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመመለስና ዘላቂ መፍትሔ የመስጠት (በተቻለ መጠን) ጉዳይ ደግሞ፣ የመንግሥትና የገዥው ፓርቲ ዋነኛ ኃላፊነት ነው፡፡ የሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችና የምሁራን ቀዳሚ አጀንዳ መሆን አለበት፡፡
ከዚህ አንፃር ባሳለፍነው በጀት ዓመት በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ‹‹ከዳር ዳር›› በሚባል ደረጃ የተነሳ የሕዝብ ጥያቄ በቂ መልስ አላገኘም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከሞላ ጎደል በክልሉ ምንም እንኳን ሁከትና አመፅ ጋብ ቢልም፣ የአዲስ አበባና (ፊንፊኔ) የአጎራባች ከተሞች ማስተር ፕላን፣ የባለሀብቶች የኢንቨስትመንት የመሬት ሊዝና የካሳ ጉዳይ አሁንም ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡
ከዚህ ጥያቄ ጋር በተያያዘ በተነሳ ሁከትም ይባል በሕዝባዊ እምቢተኝነት የተሳተፉ ዜጎች (በተለይ ወጣቶች) እንደታሰሩም ይታወቃል፡፡ እነዚህን ኃይሎች በሆደ ሰፊነት አስተምሮና መክሮ በጊዜ መፍታት ይገባል፡፡ በግርግሩ ለሞቱና ለተጐዱ ዜጎችም የፖለቲካ መጠቀሚያ እንዳይሆኑ የሚያደርግ የማነጋገርና የማካካስ ሥራ ያስፈልጋል፡፡ ይገባልም፡፡ ከሰሞኑ የቆሻሻ አወጋገድ ጋር እየተሰማ ያለው ችግርም በዴሞክራሲያዊ መንገድ መፍትሔ ያስፈልገዋል፡፡
የአማራና የትግራይ ብሔራዊ ክልል መንግሥታትና ያደናገረውና ሕዝቡንም ወደ ፍጥጫ እያስገባ ያለው ‹‹የወልቃይት የማንነት ጥያቄ›› ግልጽና የማያሻማ መፍትሔ ማግኘት ይኖርበታል፡፡ በተለይ የማንነት ጥያቄን በቀላሉ ለመመለስ የሚችለውና እየፈጸመ ለመጣው ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ጉዳዩ የሚከብደው ሊሆን አይገባም፡፡
በአንድ በኩል ማንነትን ከሥልጣን፣ መሬትን ከመሰል ሀብት ጋር ማያያዝ ሊኖር ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ለዘመናት አብሮ በኖረ ሕዝብ መሀል ሲቀነቀን የከረመው ብሔር ተኮር ቅስቀሳ ሰው ማንነቱን እንዲሻ ክፉኛ ሊገፋው እንደሚችል መታመን አለበት፡፡ ስለዚህ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያም ሆነ በደቡብ ክልሎች የሚነሱ የሕዝብ የማንነት ጥያቄዎች መልስ የሚያገኙበት አልያም ጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲፈጠር ሥራው ከወዲሁ መጀመር አለበት፡፡
ምላሽ የሚሹት ጥያቄዎች ግን እነዚህ ብቻ አይመስሉም፡፡ ከዚህም በላይ ናቸው፡፡ በተለይ ከፖለቲካና ከዴሞክራሲ ምኅዳር ማስፋት ጀምሮ በፖለቲካ መዘዝ የታሰሩ ዜጎች፣ የተሰደዱና የተፈናቀሉ ሁሉ በአገራቸው ጉዳይ ያገባናል የሚሉበት መንገድም መከፈት አለበት፡፡ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ ውስጥ እየተጫወተ ያለውን ጉልህ ሚና ማስመር የሚችለውም በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡
ግለሰቦች፣ ተቃዋሚዎችና ትክክልም ይሁንም አይሁንም ፕሮፓጋንዲስቶች ስህተት ሊፈጽሙ ይችላሉ፡፡ አክራሪና ጽንፈኛ ወይም አፍራሽ የሚባል አስተሳሰብም ሊያራምዱ ይችላሉ፡፡ መንግሥት ግን የሕዝብና የአገር ኃላፊነት አለበትና ሆደ ሰፊ፣ አስተዋይና አስታራቂ ሊሆን ይገባል፡፡ ለውይይት፣ ለድርድርና ሰጥቶ ለመቀበል በሩን ክፍት ማድረግም ኃጢያት ሊሆን አይገባም፡፡
ኢትዮጵያ በዚሁ መንግሥት ጥረት ዓለም አቀፍ ተሰሚነትን ይበልጥ አግኝታለች፡፡ ዲፕሎማሲያዊ ተቀባይነት ብቻ ሳይሆን ከሁሉም የውጭ ኃይሎች ጋር ለመደራደርና ለመወያየት የሚያስችሉ መርሆዎችንም አጥብቃ እንደያዘች ይታመናል፡፡ ይህንን ለአገሪቷ ሕዝቦች ጥያቄ ወይም ለኢትዮጵያዊያን ፖለቲከኞች ሐሳብ አለማዋል ግን ‹‹የውጭ አልጋ የውስጥ ቀጋ›› ሲባሉ የነበሩትን የቀደምት አገዛዞች ስያሜ የሚያላብስ ነው፡፡
የሕዝብ ጥያቄ በሁሉም ደረጃ ምላሽ ማግኘት አለበት ሲባልም ግጭት ስለተነሳና የአድማ ጥያቄ ስለሆነ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም የእያንዳንዱን ዜጋ ቅሬታ መንግሥት ሊመልስ ይገባል በማለት የሚቀርቡ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የሰላም ጥያቄዎች ምላሽ ይፈልጋሉ፡፡ ባለሀብቱ በየትኛውም የአገሪቱ ጫፍ ዋስትናን ይሻል፡፡ ዜጎች ተንቀሳቅሰውና ሠርተው የመለወጥ መብታቸው ሊከበር ግድ ይላል፡፡
በአጠቃላይ አገራችን የሁላችንም ቤት ነች፡፡ በዘር፣ በቋንቋና በፖለቲካ አመለካከት እየተባላን መልሰን ወደ አዘቅት እንድንገባ አያስፈልግም፡፡ ከሁሉም በላይ ዜጎች የሚገለሉበት (Marginalization) እና የሚሸሹባት፣ አንዳንዶችም እንደፈለጉ የሚፈነጩባት አገር እንዳትሆን መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ጊዜው ረፈደ ሊባል አይችልም፡፡ ሁሉም በጋራና በትጋት መነሳት ይጠበቅበታል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን እዚህ አገር ዴሞክራሲያዊ ውይይት ሊለመድ ይገባል፡፡ እያቆጠቆጡ ያሉ ግጭቶች የሚቆሙት ዴሞክራሲያዊ ውይይቶች ሲለመዱ ብቻ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊዋን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡