Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ባለፈው ሰሞን የምሣ ሰዓት ደርሶ ወደ ወትሮው የመመገቢያ ቤት ሳመራ ስልኬ ጮኸ፡፡ የደወለው ጓደኛዬ ነው፡፡ ‹‹አዲስ የተከፈተ ምርጥ ሬስቶራንት ስለምወስድህ ጠብቀኝ፤›› ብሎ ዘጋው፡፡ ከቢሮዬ ወጥቼ የተወሰነ ርቀት ሄጄ ስለነበር ወደኋላ መመለስ ግድ ሆነብኝ፡፡ እሱ እስኪመጣ ጫማዬን ለማስቦረሽ ወደ ሊስትሮዎቹ አመራሁ፡፡ በዚህ መሀል አንዲት ሴት በፍጥነት የሚጓዝ አነስተኛ የቤት መኪና ውስጥ ሆና፣ ‹‹አድኑኝ! አድኑኝ!›› እያለች ስትጮህ እኔን ጨምሮ ሌሎች በአካባቢው የነበሩ ሰዎችን ትኩረት ሳበች፡፡ ይኼኔ ሊስትሮዎቹና የሚገነባ አዲስ ሕንፃ ላይ የሚሠሩ የቀን ሠራተኞች በጩኸት አካባቢውን እያደበላለቁ መኪናውን ተከተሉት፡፡ አካባቢው በአንድ ጊዜ ተረባበሸ፡፡

ይኼንን ድንገተኛና የተረባበሸ ክስተት በአርምሞ እየተመለከትኩ ሳለ ጓደኛዬ ደረሰ፡፡ የጓደኛዬ መኪና ውስጥ ገብቼ ጉዞ ጀመርን፡፡ ከሁለት ደቂቃዎች የማይበልጥ ጉዞ እንዳደረግን ያ በፍጥነት ይሽከረከር የነበረ መኪናና በርካታ ሰዎች ያሉበት ሥፍራ ደረስን፡፡ በግምት ዕድሜው ከ25 የማይበልጥ ወጣትና ሃምሳ ዓመት የሚጠጋት ሴት በሰዎች ተከበው ሲጨቃጨቁ፣ ዙሪያቸውን የከበበው አዳማቂ ቴአትር እንደሚመለከት በፅሞና ያዳምጣቸዋል፡፡ ያቺ ‹‹አድኑኝ! አድኑኝ!›› እያለች ስትጮህ የነበረች ሴት የወጣቱ እናት እንጂ፣ በኃይል ተገዳ ወይም ጥቃት ተፈጽሞባት የምትጓዝ አትመስልም፡፡ ከሴትዮዋ አነጋገር እንደተረዳሁት በወጣቱ ፍቅር በመነደፍዋ ምክንያት ወፈፍ ያደረጋት ናት፡፡ ወጣቱ ደግሞ በሴትዮዋ አላስፈላጊ የፍቅር ጥያቄ በመበሳጨት፣ ቤቷ አድርሷት ለመገላገል በፍጥነት ማሽከርከሩን ሲናገር ሰማነው፡፡ ለፈራጅ ያስቸገረ ነገር፡፡  

የሁለቱን ንትርክ ስንሰማ የተረዳነው በድንገት በተፈጠረ መቀራረብ ተላምደዋል፡፡ ሴትዮዋ በዚህ መላመድ ፍቅር ይዟታል፡፡ ወጣቱ ደግሞ በፍቅር ለመቀጠል በፍፁም ፍላጎት የለውም፡፡ ሁለት በዕድሜ የማይገናኙ ሰዎች በመሀላቸው የተፈጠረው ጭቅጭቅ አደባባይ ላይ ተዘርግፎ ዙሪያቸውን ለከበቡ ሰዎች ምፀትና ነቀፋ ቢዳርጋቸውም፣ አንዳንዶች በተፈጠረው ነገር ሐዘናቸውን መግለጻቸው አልቀረም፡፡ እኛ ከዚህ በላይ ያንን አሳዛኝ ትዕይንት መታደም ስላልፈለግን ወደ ምሣችን አመራን፡፡ ጓደኛዬ አሳይሃለሁ ያለኝ አዲሱ ዘመናዊ ሬስቶራንት ቦሌ ውስጥ የከተመ በመሆኑ፣ የወረት እንግዶች ሞልተውታል፡፡ የተስተናጋጆች ቁጥር ከመብዛቱ የተነሳ ማቆሚያ ፍለጋ ያባከንነው ጊዜ የምሣ ሰዓታችንን በዕጅጉ ተሻምቶናል፡፡

- Advertisement -

የሬስቶራንቱ ግርማ ሞገስ ከምድረ ግቢው ይጀምራል፡፡ ሰፊ፣ የተንጣለለ፣ ንፁኅ፣ በአትክልት የተከበበና የሚያምር ግቢ መሀል እኔ ነኝ ያለ ትልቅ ቪላ ጉብ ብሏል፡፡ ከወደ ጎን ደግሞ በዘመናዊ ድንኳን መሳይ ጎጆ (Canopy) የተሠራ ልዩ አዳራሽ ተሰይሟል፡፡ ቪላው በመሙላቱ ድንኳን መሳዩ ጎጆ ውስጥ ስንገባ አዲስ አበባችንን አንቱ የሚያሰኝ ልዩና ውብ ሬስቶራንት አገኘን፡፡ በአስተናጋጁ መሪነት አንድ ያልተያዘ ጠረጴዛ ተሰጠን፡፡ አረፍ ካልን በኋላ የምግብ ዝርዝር የያዘ ሜኑ ቀረበልን፡፡ የምግቡ ዓይነት ዝርዝር ከመብዛቱ የተነሳ ሜኑው እንደ መጽሔት ይገለጻል፡፡ የዋጋ ነገር ከተነሳ ደግሞ ለምሳሌ ጥብስ 175 ብር፣ ላዛኛ 180 ብር፣ የዶሮ አሮስቶ 480 ብር፣ ወዘተ እያለ ይቀጥላል፡፡ ይኼ ሬስቶራንት የላይኛው መደብ አባላት ስለሆነ ብዙም መነጋገር አያስፈልግም፡፡ ያለ ቦታችን እየሄድን በዋጋ መማረር ጨጓራ ከማቃጠል ውጪ ምንም ጥቅም የለውም፡፡

እዚህ ሬስቶራንት የጋበዘኝ ጓደኛዬ አዲስ ነገር ማየት ስለሚወድ እንጂ የዘወትር ደንበኛ አይደለም፡፡ አቅሙን አውቀዋለሁ፡፡ ይልቅስ ዓይኖቼ ዙሪያ ገባውን እያማተሩ የዘመኑን ከበርቴዎች ሲፈልጉ በእርግጥም የደላቸውና በቅንጦት የሚኖሩ የሚመስሉ ሰዎች በብዛት ይታያሉ፡፡ ምግቡ እስኪመጣ ከጓደኛዬ ጋር ስለዚህ ጉዳይ እየተነጋገርን ሳለ ከኋላችን ያለ ጠረጴዛ ተለቀቀ፡፡ በብርሃን ፍጥነት ማለት ይቻላል ፈጣኑ አስተናጋጅ አፀዳድቶት በሚገባ ካዘጋጀው በኋላ ሁለት ሰዎችን ይዞ መጣ፡፡ አንዲት በ40ዎቹ ውስጥ ያለች ምቾት ያጥለቀለቃት ሴት ወይዘሮና በሃያዎቹ መጀመሪያ ላይ ያለ መለሎ ወጣት፡፡ እነዚህ ከቅላታቸውና ከሁኔታቸው በእርግጥም እናትና ልጅ ይመስላሉ፡፡ አስተናጋጁ ትዕዛዛቸውን ተቀብሎ ሄደ፡፡ የእኛም ምግብ መጥቶ መብላት ጀመርን፡፡ ከቆይታ በኋላ የእነሱም ምግብ መጣ፡፡ እነሱም መብላት ጀመሩ፡፡

በዚህ ሁኔታ ላይ እያለን አንዳንድ ሰዎች የኃፍረትና የመገረም ስሜት እያሳዩ ወደኛ አቅጣጫ እየደጋገሙ ሲያዩ አየኋቸው፡፡ ጓደኛዬ አንገቱን ዞር አድርጎ ከኋላችን ያለው ጠረጴዛ ላይ ዓይኖቹን ሲልክና ሲደነግጥ አየሁት፡፡ ምን ሆኖ ነው ብዬ እኔም ዞር ስል በድንጋጤ ደርቄ ቀረሁ፡፡ እናትና ልጅ የመሰሉኝ ሁለቱ ጥንዶች ምግቡን ትተው፣ ያሉበትን ቦታ ረስተው ተቃቅፈው ይሳሳማሉ፡፡ ሴት ወይዘሮዋ ወጣቱን እንቅ አድርጋ አቅፋ አቅሏን ስታ ስትስመውና ስትቃትት ላያት ከመደንገጥ በላይ ያሳቅቃል፡፡ አስተናጋጆቹ ጨንቋቸው ግራ በመጋባት ከላይ ታች ቢሉም ማን ነገሬ ብሏቸው፡፡ በዚህ መሀል ነበር የሬስቶራንቱ ሥራ አስኪያጅ በጥድፊያ መጥቶ ፍፁም ትህትና በሞላው አቀራረብ፣ ‹‹ይቅርታ! እባካችሁ የቀረበውን ገበታ ተስተናገዱ…›› በማለት ማሳሰቢያ ያቀረበው፡፡ ምንም ዓይነት ይሉኝታ ያልፈጠረባት ሴት ወይዘሮ፣ ‹‹የምን ማፍጠጥ ነው? ዞር በል ከዚህ …›› ብላ ስታመናጭቀው ብዙዎቻችን ኩምሽሽ አልን፡፡

ሴትዮዋ እንደዚያ እያበደች ወጣቱ እንድትረጋጋ ቢሞክርም፣ አሁንም ላዩ ላይ ተጠመጠመችበት፡፡ ይኼን ጊዜ ሥራ አስኪያጁ ሁለት የጥበቃ ሠራተኞችን አስመጥቶ ከምግብ አዳራሹ እንዲወጡ አደረገ፡፡ በጥበቃ ሠራተኞች ከአዳራሹ እየወጡ እያሉ የሴትዮዋ ስድብ ለጆሮ የሚዘገንን ነበር፡፡ በኋላ እንደተረዳነው ወጣቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሲሆን፣ ሴትዮዋ በንግድ ሥራ የምትተዳደር ናት፡፡ እንዲህ ዓይነት በደመነፍስ የሚመራ ስሜት ፍቅር ሳይሆን ጋጠወጥነት ካልሆነ በስተቀር ምን ይባላል? አቅልን እየሳቱ በአደባባይ ገመናን ማጋለጥ ምን የሚሉት አጉራ ዘለልነት ነው? የዕድሜ አለመመጣጠን ተጨምሮበት በዘፈቀደ የሚፈጸም ግንኙነትስ ለማን ይጠቅማል? ይጠቅማል ቢባል እንኳ ገመናን መሸፈን ማንን ገደለ? በዕለቱ በገጠሙን ድንገተኛ ጉዳዮች ላይ በመገረም ስንነጋገር ጓደኛዬ፣ ‹‹እዚህ አገር ውስጥ በጣም የሚገራርሙ ጉዳዮች በብዛት እየተከሰቱ ነው፡፡ ግን ምን እየሆንን ነው? ወዴትስ እየተጓዝን ነው?›› ያለው የእኔም ጥያቄ ነበር፡፡ በእርግጥም ምን እየሆንን ነው? (ንጋቱ ይታየው፣ ከለገጣፎ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...