አዲስ አበባችንንና ነዋሪዎቿን ከሚፈትኑ ወደፊትም እየተናነቋት ከሚዘልቁ መሠረታዊ ፍላጐቶች መካከል አንዱ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ነው፡፡ የመኖሪያ ቤት ፍላጐት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ነው፡፡ አሁንም አብዛኛው የከተማው ነዋሪ መኖሪያ ቤት የለውም፡፡ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋውም አልቀመስ እያለ ነው፡፡ በሚፈለገው ደረጃ የመኖሪያ ቤት ፍላጐትን ማሟላት አልተቻለም፡፡
በተፈለገው ብዛትና ጥራት እየተገነባም ባይሆን መንግሥት የሚገነባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሊፈጠር የሚችለውን ከፍተኛ ቀውስ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን አርግበዋል፡፡ ምንም እንኳ ቤት ለማግኘት የሚጠባበቀው ሕዝብ ብዛት ከ900 ሺሕ በላይ ቢሆንም፣ መንግሥት ከአሥር ዓመት በላይ ባካሄደው የቤት ግንባታ ከ120 ሺሕ ያነሱ ዕድለኞች ቤት አግኝተዋል፡፡
ቤቶቹ አነሰም በዛ ባይገነቡ ኑሮ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የተንሰራፋው የመኖሪያ ቤት ችግር አሁን ካለውም እጅግ የከፋ ይሆን እንደነበር ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ በፍላጐቱና በአቅርቦቱ መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት ለማጥበብ ብዙ መሠራት፣ ሌሎች አማራጮችን ማየት ይፈልጋል፡፡ ምክንያታዊ ያልሆነ የቤት ኪራይ ዋጋ ንረትን ለመከላከል የመኖሪያ ቤቶችን የሚያስተዳድር አካል መመሥረት ሳያሻን አይቀርም፡፡
ሰሞኑን እንደሰማነው የአዲስ አበባ አስተዳደር ከጋራ ቤቶች ግንባታ ጐን ለጐን የመኖሪያ ቤቶችን እያስገነባ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማከራየት ያስባል፡፡ ቤት አከራይነቴ አይቀሬ ስለመሆኑ ለማረጋገጥም በቅርቡ በተደረገ ቆጠራ ሰው ያልነበረባቸውና ከአንድ ሺሕ በላይ የኮንዶሚኒየም ቤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ አከራያለሁ ብሎ ማስታወቁ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አስተዳደሩ መኖሪያ ቤት ገንብቶ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማከራየት ያለውን ውጥን ከግብ ለማድረስ መቁረጡን ያሳየ ይመስላል፡፡
የአስተዳደሩን ውጥን ስኬታማነት ለመተቸትና ፍርድ ለመስጠት መቸኮል ባያስፈልግም፣ የከተማዋን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ አማራጮችን መመልከቱ ግን አይናቅም፡፡ ከዚህ የተሻሉ አማራጮች የሉም ወይ የሚል ጥያቄም ሊነሳ ይችላል፡፡ ለማንኛውም የከተማዋን የቤት እጥረት ብሎም የኪራይ ዋጋ ንረትን ለማርገብ አማራጮችን መጠቀሙ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እስካሁን ለባለዕድለኞች የተላለፉና ሰሞኑን ይተላለፋሉ ተብለው የሚጠበቁ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የኪራይ ዋጋን ምን ያህል አረጋግተዋል? የሚል ጥያቄ እንዳነሳ አስገድዶኛል፡፡ ምክንያቱም የጋራ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት መተግበር ከጀመረ ወዲህ ለባለዕድለኞች የሚተላለፉ ቤቶች ቁጥር ከ110 ሺሕ በላይ መድረሱ ተነግሯል፡፡ እነዚህ ቤቶች የከተማዋን የቤት ኪራይ ዋጋ ምን ያህል እንደታደጉ ሳስብ ግን ብዥታ ይፈጥርብኛል፡፡
በእርግጥ በሚፈለገው ብዛት ባይገነቡም እነዚህ ቤቶች ግን የኪራይ ዋጋን በተወሰነ ደረጃ ጋብ ማድረግ በተገባቸው ነበር፡፡ የከተማዋን የቤት እጥረት መቅረፍ በጋራ ቤቶች ፕሮጀክት ትከሻ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ አይደለም፡፡ በአራቱም የከተማው ክፍሎች የሪል ስቴት አልሚዎች የሚገነቧቸውና በግልም እየተገነቡ ካሉት ቤቶች ቁጥር አንፃር ገበያው ባይቀንስ እንኳ አንድ ቦታ ላይ መጠነኛ ለውጥ ሊያሳይ በተገባው ነበር፡፡
በእርግጥ አዲስ አበባችን በየጊዜው የምትቀበላቸው ነዋሪዎች ስለሚጨምር፣ ፍላጐቱም ማቆሚያ ስለሌላው የቱንም ያህል ቢገነባ የኪራይ ዋጋውን ማሻቀብ ለመግታት አልተቻለም የሚል ሙግት ይኖራል፡፡ ይህ እውነትነት ያለው እንዳለው እገነዘባለሁ፡፡
ነገር ግን በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ጐጆዎች ከተቀለሱ፣ ወደ አዳዲስ ጐጆዎች የሚገቡት ዜጐች የቀድሞ መኖሪያቸውን ይለቃሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ ቀደምቶቹ የሚለቁትን ቤት ያላገኙት ሰዎች በቀድሞቹ ቦታ እየገቡ በሚመጣቸው ሽግሽግ ምክንያት ለውጥ መታየት እንደነበረበት ይታመናል፡፡
ወደ አዲሶቹ ቤቶች የሚገቡት ዕድለኞችም ሆኑ በሌላ መንገድ የራሳቸው ቤት ባለቤት የሆኑ ዜጐች፣ ወደየቤቶቻቸው ሲያቀኑ፣ በኪራይ ሲጠቀሙባቸው የነበሩ ቤቶች ይለቀቃሉ ማለት ነው፡፡ ይህ ዑደት ካለ የኪራይ ዋጋ ሽቅብ ከመውጣት ይልቅ መለሳለስ የለበትም እንዴ?
በቀጣዩ ሳምንት እንኳ 40 ሺሕ ዜጐች የቤት ዕድል ስለሚያገኙ ቀድመው ይኖሩበትን ቤት ይለቃሉ፡፡ ስለዚህ ሊከራዩ የሚችሉ በርካታ ቤቶች ይኖራሉ ማለት ነው፡፡ 40 ሺሕ ባይሆን እንኳ በርካታ ቤቶች መኖር አለባቸው፡፡ ይህ ግን ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ለውጥ የማይታይበት፣ ዋጋ የማይረጋጋበት ምክንያቶች በርካታ ቢሆኑም፣ በዚህ ወቅት የኪራይ ዋጋ እንዳይወርድ ትልቁን ሚና የሚጫወቱት ደላሎች ናቸው፡፡ የሚለቀቁ ቤቶችን እያሰሱ ከገበያ ዋጋ ውጭ እየቆለሉና አከራዮችን እያማለሉ የቤት ኪራይ ተመኑን ያንራሉ፡፡ ይህ አደገኛ አካሄድ የቤት ኪራይ ዋጋ እንዳይቀንስ ብቻም ሳይሆን የሕዝብን የኑሮ ሁኔታ እያናጋ ነው፡፡ በጥቅል ሲታይ የጨዋታው ካርድ ደላሎች ጋር እንዳለ መገመት ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የመንግሥት ድካም መና ይከተዋል፡፡ የመንግሥት መዋቅርንም ጥርጣሬ ላይ ይጥለዋል፡፡ ከደላላ የማያስጥል አስተዳደር ያለበት ከተማ ሆኖ እስከመቼ ይዘልቃል የሚለው የብዙዎቻችን ሥጋት ነው፡፡
ስለዚህ ስንትና ስንት ዓመታት ተለፍቶባቸው፣ ስንትና ስንት ገንዘብ ተከስክሶባቸው የተገነቡ ቤቶችን ከማስተላለፍ ባሻገር፣ የጋራ የመኖሪያ ቤቶች የሚተዳደሩበት፣ የሚከራዩ ከሆነም ተገቢው ሕግ ያስፈልጋቸዋል፡፡ መንግሥት የመኖሪያ ቤቶች ኪራይ ሲጀምር ይህ የኪራይ ዋጋ መነሻ መሆን አለበት፡፡ የመኖሪያ ቤት ጉዳይ መሠረታዊ ስለሆነ በተለይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኪራይ ዋጋ ሊወሰንለት ይገባል፡፡ ደላሎችም ከዚህ ቢዝነስ እንዲወጡ መደረግ አለበት፡፡ መንግሥትም ቢሆን ዛሬ ከራሱ ቤት ይልቅ በኪራይ የሚኖረው ዜጋ እየጨመረ መሆኑን በመረዳት በአግባቡ ግብር ቢሰበስብ ከቤት ኪራይ ብቻ የሚገኘው ገቢ ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ዋጋውንም በቀላሉ መቆጣጠር ያስችላል፡፡