Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትአምባገነንትን የጠቀመ ዴሞክራሲን ያዘገየ ቁልፍ ችግራችን

አምባገነንትን የጠቀመ ዴሞክራሲን ያዘገየ ቁልፍ ችግራችን

ቀን:

በሲሳይ ገላው

አንድ የበጀት ዓመት አልቆ ሌላው ሲመጣ አሮጌው ዓመት አልፎ አዲሱ ዓመት ሲጠባ፣ እንዲሁም በዚሁ ውስጥ የሕዝብ ንቅናቄዎችና የፓርቲ ምሥረታ ወዘተ. የመሳሰሉት ‹‹አነጋጋሪ› ክበረ በዓላት በመጡ ቁጥር፣ ሁሌም የተለመደ ምናልባትም ያሰለቸ ‹‹ግምገማ›› መስማታችን አልቀረም፡፡ በደርግ ዘመን አብዮቱ ከፈነዳበት፣ በግብታዊነት ከፈነዳበት ከየካቲት 1966 ዓ.ም. ጀምሮ እየተባለ ሁሌም በየዓመቱ አብዮታችን የደረሰበት የዕድገት ደረጃ ይነገረናል፡፡ ኢሕአዴግም ከየካቲት 1967 ዓ.ም. ጀምሮ በግንቦት በ1983 ዓ.ም. በኩል አድርጎ የ25 ዓመታት ‹‹አበረታች›› ጉዞውን ከቀድሞው በለጥኩ እያለ ቁጥር እያሰላ ሲነግረን ኖሯል፡፡

ዴሞክራሲያችን የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ በእውነት ማሳየት የፈለገ መመዘኛ መጀመርያ መመለስ ያለበት አምባገነንነት አይዞህ ባይ ማጣቱን፣ አድራጊ ፈጣሪነት ሕዝብን መፍራት መጀመሩን በማስመስከር ነው፡፡ በኢትዮጵያችን ዛሬም አምባገነንነትን ዋልታና ማገር ሆነው ደግፈው የያዙ ዴሞክራሲን የሚያዘገዩ በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን ዴሞክራሲ መሰል አምባገነንነት መምራትም ሆነ መፈንገል (ትግሉ ሁሉ ሰለማዊና ሕጋዊ ነው) ቀላል አይደለም፡፡ የአምባገነንቱን መቀጠል የሚደግፉና ነባሩ ቢሄድ ሌላ አምባገነንነትን የሚጠሩ ችግሮች ብዙ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱና ምናልባትም ከመነጋገርና ከውይይት በላይ ሆኖ ራሱን ዕርም ያደረገ ጉዳይ አለ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች በዕድገት ኋላቀር መሆን፣ በተፈጥሮ ሀብት ሥርጭት፣ በሕዝቦች ስብጥር፣ በባህልና በታሪክ ያላቸው ቁርኝት እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ያላቸው ሥፍራና የጥቅም ግንኙነት ሰላማቸውን አስጠብቀው፣ በዕድገት የመጓዝ ዕድላቸውን አብሮ በመኖራቸው ላይ የተንጠለጠለ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በዚህ ላይ የአፍሪካ ቀንድ ጦርነትና አለመረጋጋት፣ አክራሪነትና ሽብርተኝነት ሁሉ ያለበት ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያ በቀንዱ ውስጥ የበረሃማነት ግፊት የታከለባት፣ የውኃ፣ የግዛትና የወሰን ውዝግብ እንዲሁም ከዚህ ጋር በተያያዘ የጎረቤት ቂም በቀል (ጠላትነት) ያለባት ናት፡፡ አልፎም ኢትዮጵያ የሙስሊምና የክርስትያኖች አገር ሆና ሳለ በጎረቤቶቿ ሙስሊም አገሮች ዘንድ የክርስቲያን አገር መንግሥት ተደርጋ መቆጠር ገና ያልቀረለት፣ ለአሜሪካና ለእስራኤል ያጋደለች ተደርጋ የምትታይ መሆኗ ሳያንስ ጥንቃቄ የጎደለው መንግሥታዊ አቋም ጭምር በፀረ እስራኤል አሸባሪ እንቅስቃሴ ውስጥ እንድትጠመድ አድርጓታል፡፡   

ይህ ሃይማኖት ለባስ አሸባሪነትም በዛሬው ወቅት፣ ቀውስና ግርግር ብቅ ባለበት በጣም ፈጥኖ በመዝለቅ መጥፊያ የሌለው ሥርዓት አልባነትና መጨፋጨፍን አንድ ባህልና ሃይማት ባላቸው አገሮች ሳይቀር የማራበት አቅም እንዳለው፣ በሩቅና በቅርብ ጎረቤት አገሮች ከዚያም ባሻገር በማያጠራጥር ሁኔታ የተረጋገጠ ነው፡፡ የአክራሪነትና የአሸባሪነት ሙከራዎችም ሊሰረስሩን እየተጣጣሩ መሆኑ ሚስጥር አይደለም፡፡ የዚህ ዓይነት እንቅስቃሴና የጎረቤት ጠላትነት ውስጣዊ የግርግር ቀዳዳ አግኝቶ ቢስፋፋና ከክፍልፋይነትና ከጥላቻ ዝንባሌዎች ጋር ቢገናኝ ሊፈጥረው የሚችለው መተላለቅና መበጣጠስ አርቆ ላስተዋለው ይዘገንናል፡፡ ሰላማዊ ህልውናና ዕድገት ድራሻቸው ጠፍቶ ወደ ህልምነት ከመለወጣቸውም በላይ ከስህተት ለመማር ደግሞ ዕድል ለመገኘቱም እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡

ይህን የመጥፊያ አዘቅት ማስተዋልና ፈጥኖ አደጋውንም ለማምከን ደግሞ የአገሪቱ ሕዝቦች በብሔርም ሆነ በሃይማኖት የመሸካከር ስንጥቃት ሳያሳዩ ወይም በሌላ የፖለቲካ ቀርቁስ ሳይታመሱ፣ በአገራዊ የጋራ ደኅንነታቸው ላይ አንድ ልብ ሆነው እንዲቆሙ ማስቻል እንቅልፍ የማያስወስድ ተግባር ሆኖ ሳለ፣ የኛ ፖለቲከኞች ግን ሌላ ዓለም ውስጥ ናቸው፡፡ ገዥው ቡድንና ተቃዋሚዎች በጭራሽ የሚቀራረቡ አይደሉም፡፡ አይመስሉም፡፡ ተቃዋሚዎች በተቃውሟቸው ይህን ተሰባስቦ የማሰባሰብ ኃላፊነት ለመወጣት የሚበቁ አልሆኑም፡፡ በዚህ ረገድ የሚደረገው ሙከራ ሁሉ ከመጠንከርና ከመስፋፋት ይልቅ ተወሻሽሎ የሚፈረካከስ ነው፡፡ እጅግ አስገራሚው ምፀት ደግሞ አንድ የመራራቂያና የመፋረሻ ምክንያት ‹‹የብሔረሰቦች መፈቃቀድ››› እና ‹‹እስከ መገንጠል›› የሚባል መብት መሆኑ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱም ሰፍሯል፡፡

ብሔርተኛና ኅብረ ብሔራዊ የፖለቲካ ድርጅቶችን ለመቀራረብ በሞከሩ ቁጥር፣ የመግባባትና የመተማመን መሰናከል የሚሆነው ምርጫ በመጣ ቁጥርም ዋናው መጨቃጨቂያ ሆኖ የሚገኘው ይኸው ነው፡፡ እውነታውን ከጭቅጭቃቸው ፋይዳ ጋር ላገናዘበ ፖለቲከኞቹ  ነሁልለዋል ወይ? የሚያሰኝ ነው፡፡ ላስረዳ!

አንደኛ የመፈቃቀድ አመለካከት እውነታዊ አይደለም፡፡ ሁለተኛ ነገር ከመፈቃቀድ በላይ የሆነ የህልውና ግድን ከልሎ የሚያደናግር ነው፡፡ እያንዳንዱ ብሔረሰብ፣ ትንሹም ትልቁም ሰላምና ዕድገት ያለው ሉዓላዊ አገር ለመሆን የመቻሉ ነገር ተጨባጭ ዕድል ሳይሆን ተምኔት ነው፡፡ የመገነጣጠል ፍላጎት ከዓለም የትስስር ጉዞና ከአፍሪካ ቀንድ ሁኔታ ጋር የሚጋጭና ማለቂያ ወደሌለው መጠፋፋት የሚወስድ መሆኑን ማየት ለፈለገ ወለል ብሎ ይታያል፡፡ የተሻለ የተፈጥሮ ሀብት አለኝ፣ ወይም የተሻለ አቅም አደራጅቻለሁ ብሎ ለመገንጠል የሚደረግ ሙከራ አምባገነናዊ ቅጥቀጣን ከማራዘም ወይም ጭራሽ በሥርዓተ አልባነት መንኮታኮት የሚመጣበትን ቀን ከማቅረብ የተሻለ ውጤት የማያመጣ መሆኑ እየታወቀ፣ ሰላማችንና ወደ ብልፅግና የመግባት ዕድላችን ግድ የሚለው አማራጭ በመላ አገሪቱ ያለውን የማቴሪያል፣ የዕውቀትና የችሎታ ሀብት በፍትሐዊነት ተጠቀሞና እኩል ተያይዞ ማደግ ሆኖ ሳለ ‹‹ብሔር ብሔረሰቦች ሉዓላዊ ናቸው. . . የማይታጠፍ የመገንጠል መብታቸው እንደተጠቀበ ሆኖ በመፈቃቀድ ኢትዮጵያን  ፈጥረዋል፡፡ . . . ቅሬታ ያለው ተበደልኩ የሚል በሕጋዊ አግባብ መለየት ይችላል፤›› በሚል አስተሳሰብ ውስጥ መሽከርከርና ዛሬ ያለውን አከላለል ከአስተዳደራዊ ይዞታነት ባሻገር የየአገር መለያ ድንበር አድርጎ በመውሰድ፣ ሁብቴ/ሀብትህ እያሉ መናቆር ተጨፍኖ በእሳት ከመጫወት አይለይም፡፡ እዚህ ላይ ‹‹መፈቃቀድ››ን ስንተች ‹‹ኢትዮጵያ ግዛቷ አይቆራረስም፤›› የሚል አስተሳሰብ ያላቸው ወገኖች ክርክሩን ወደ ራሳቸው ፍላጎት ሊወስዱት ይሞክሩ ይሆናል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ጭንቀት ግን የግዛት አንድነት ማስከበር ሳይሆን የሕዝቦች ሰላምና ዕድገት ህልውና አግኘቶ በዚያው የመዝለቅ ጉዳይ ነው፡፡

የአንድ ብሔረሰብ የመነጠል ጉዳይ የራሱን ብሔር ዕድል የመወሰን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎችም ብሔረሰቦች ዕድልና ሕልውና ላይ የመወሰን ጉዳይ ጭምር ነው፡፡ የሌሎችን አብሮ የመኖር ፍላጎት የማሳጣት ብቻ ሳይሆን በቅንጣትነት ቆርጦ የማስቀረት፣ ትልቅ ሆኖ የማደግና ደኅንነትና ሰላምን የማስጠበቅ አቅም ማሳጣትን የሚያስከትል ይህንን የህልውናን ጥቅም ላለማጣትም ቅዋሜ የሚነሳበት ነው፡፡

ዛሬ ‹‹ሉዓላዊነት ሲባል የሕዝብ ወሳኝነት ማለት ነው፣ ዋናው ሕዝብ ነው፣ ተራራና ወንዝ አይደለም፤›› ማለት የጊዜው ‹‹ሳይንሳዊ የማይታበል›› ሀቅ ሆኗል፡፡ እውነቱ ግን ሌላ ነው፡፡ እነዚህ ተራ የማጭበርበሪያ ቃላት ናቸው፡፡ የሕዝብ መኖሪያው፣ የሚበላው፣ የሚተነፍሰው፣ ዕድገቱና ልማቱ ሁሉ ከመሬቱ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

ተራራና ወንዝ የማያስጨንቅ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያዊ የሚባለውን የድንበር ሕዝብ ወደ ኢትዮጵያ አምጥቶና ባድመንና ዛላንበሳን ለሻዕቢያ ይኼውልህ ማለት ቀላል በሆነ ነበር፡፡ በተለይ መሪዎቻችን ‹‹ዋናው ሕዝብ ነው›› ለማለት የሚችሉት በምን አፋቸው? ሕዝቦችን ማለትም ትግርኛ ተናጋሪውን ሕዝብ ጨምሮ አፋሮችን ከሻዕቢያ ጋር ሆነው በቅኝ ግዛት ይዞታ መሠረት የሰነጠቁ እነሱው አልነበሩ? ከጥንት ጀምሮ የኖረ የረዥም ዘመን የሕዝብ ዝምድና ታሪክ ውስጥ ጣልቃ የገባ አጭር የቅኝ ግዛት ምዕራፍ የሠራውን ወሰን ከሕዝቦች ወጥነትና የጋራ ህልውና አብልጦ መቀበል፣ በኤርትራም በኢትዮጵያም ሕዝቦች የጋራ ዕድገትና ሰላም ላይ የመፍረድ ውሳኔ ነበር፡፡ አቀያይሟልም፡፡ የኤርትራ የዛሬ ካርታ እንደ ቅኝ ዘመኑ ጊዜ ኢትዮጵያን የወደብ መውጫ ለማሳጣት የተዘረጋ አጥርም ሆኖ ከመታየት አላመለጠም፡፡

በፌዴሬሽኑ መፍረስ የተጀመረው ጦርነት ለ30 ዓመታት ደቁሶ ለሌላ ጦርነት አስረከበን፡፡ ከ1991 እስከ 1992 ዓ.ም. የፊት ለፊት ጦርነት ቢቆምም ተቃዋሚዎች ላይ የተቸከለ የሁለቱ መንግሥታት ጦርነት ቀጥሏል፡፡ የአሁኑ ጦርነት ደግሞ የሻዕቢያና የኢሕአዴግ ገዥነት ሲቀር ይቀራል የሚል ‹‹ተስፋ›› የሚደረግበትም አይደለም፡፡ ወደብ ማግኘት ተፈጥሯዊ መብታችን ነው የሚልና ሌላም የሌላ ጦርነቱ መነሻ ሊሆን የሚችል ጥያቄ ፈትሉን ከጀመረ ቆይቷል፡፡

በሌላ በኩል ሁለቱም አገሮች አካባቢያዊ ሰላምና ዕድገታቸው ከጦርነት ከመላቀቅም በላይ፣ ኢኮኖሚያቸውን ማስተሳሰርና ንፋስ የማይገባቸው አገሮች መሆንን ይጠይቃቸዋል፡፡ ይህን እስካልተገነዘቡ ‹‹ኤርትራ›› ቅኝ በተያዘች ጊዜም ሆነ ቅኝ አገዛዙ ወደታች በሰፋ ጊዜ፣  በጋራ የጥቃት ቁጭታቸው የተንፀባረቀውን በኋላም የሁለት በኩል ተሳትፎ ለታየበት የአርበኝነት ትግልና ድኅረ ድል የውህደት እንቅስቃሴ መሠረት የነበረውን፣ በከፋ ቀን ያልተበገረ የአንድ ቤት ልጆች ዝምድና መልሰው እስካልገነቡና የወደብ ጉዳይን ለሌሎች ጥቅሞቻቸው ሁሉ መሰናክል እንዳይሆን እስካልፈቱት ድረስ ተጣምረው እርስ በርስ መቋሰላቸው አይቀርም፡፡ ሁለቱ አገሮች እጅና ጓንት ሆነው እንኳን ራሳቸውን ለአካባቢያቸውም የሚተርፍ ልማት ሊያመጡ የሚችሉበትን ሰፊ ዕድል ማጤን ከቻሉ ግን ወደብ በጣም ቀላል ነገር መሆኑን ይረዱታል፡፡

ሌሎችም የኢትዮጵያ ሕዝቦችን እንወክላለን የሚሉ ፖለቲከኞች ከኢትዮ ኤርትራ ጠባሳ ተምረው ‹‹የብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል ድረስ›› በሚል ምኞታዊ የጠባብ ሥልጣን መፈክር ተሳስተው ከማሳሳት እስካልወጡ ድረስ እሳት ውስጥ የመግባት አደጋ አይወገድም፡፡ የብሔር የመገንጠል መብት ሳያባላ ሊከናወን የሚችልበት ዕድል ወደፊት ቢገኝ እንኳ፣ ያንን ዕድል የሚያስገኘው የኢኮኖሚ ግስጋሴና የዴሞክራሲ ባህል በሁሉም ቦታ መሳካት ብቻ ነው፡፡ ጥቅምና ህልውናዬ አደጋ ላይ ይወድቃል የሚል የእርስ በርስ ትንቅቅ የማይኖረው የዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲሟላ ነው፡፡ ይህ በሌለበት በዛሬው እውነታ የራስን ዕድል በራስ መወሰን የሚባል ነገር ቢያንስ በጋራ ተባብሮ መቆምና መሥራት አማራጭ የለሽ መሆኑን ማሳየት አለበት፡፡

ሰላማችንን አስጠብቀን በዕድገት የመጓዝ ዕድላችን አብሮ በመኖራችን ላይ እንዲንጠለጠል ያደረገ ነባራዊ ሁኔታ አለብን፡፡ በዚህም ምክንያት የመነጠል ትግልና አምባገነንት ይጠቃቀማሉ፡፡ ከመነጠል ዴሞክራሲንም፣ ሰላምንም፣ ዕድገትንም መጨበጥ አስቸጋሪ በሆነበት በዛሬው ጊዜ እውነታ፣ ሕዝቡን በመነጠል ትልግ ውስጥ መጎተት ወይም አብሮ በመኖርም ሆነ በመለየት ላይ ሕዝቡ ፍላጎቱን በሪፈረንደም ይግለጽ የሚል እንቅስቃሴ ማካሄድ መድረሻው ጥፋት ነው፡፡ የ1966 ዓ.ም. አብዮትን በወታደራዊ ሥልጣን እንዲጠናቀቅ ከዚያ በኋላም ወታደራዊው መንግሥት አፈር ልሶ አፈራርሶ እየተነሳ 17 ዓመታት እንዲጓዝ ካስቻሉት ምክንያቶች አንዱ፣ በአገሪቱ ውስጥ በጊዜው የነበረው የመነጠል (የመገንጠል) ትግል እንደነበር ሁሉ ዛሬም የሚካሄድ የመነጠል ትግል የአገሪቱ የዴሞክራሲ ደጋፊ በዚሁ ሥጋት እንዲከፋፈልና ገዥው ቡድን በመተላለቅ እያስፈራራ ዕድሜውን እንዲያረዝም ከመጥቀም አያመልጥም እየጠቀመም ነው፡፡

የሱዳንና የደቡብ ሱዳንን ሁኔታ ከአገራችን ጋር አስተያይቶ መከራከሪያ ለማድረግ የሚሞክር ካለ ጭፍን ወይም እውነታዊነት የራቀው መሆን አለበት፡፡ በደቡብ ሱዳን ቁልጭ ካሉ የሃይማኖቶችና የባህል ልዩነቶች በተጨማሪ የልማቱ ሁሉ ተጠቃሚ በሆነውና ዓረብነት አለኝ በሚለው የሰሜን ሱዳን የበላይነት ሥር ለድህነት፣ ለድንቁርናና ለችጋር  ተትቶ የቆየ የሱዳን ግዛት ተብሎ ከመቆጠር በቀር የአንድ አገር አካል የሚያስብል ሌላ ተዛምዶ የሌለውን፣ በዚህና በስሜት ሃይማኖታዊ ጫና ምክንያቶች የብረት ትግል ውስጥ የገባ ሕዝብ ነው፡፡

እንዲህ ያለና የለየለት ሁኔታ በኢትዮጵያ ፈጽሞ የለም፡፡ በኤርትራ መነጠል ጊዜም አልነበረም፡፡ የኤርትራ መገንጠል የአንድ ጥንታዊ ሥልጣኔ አካባቢን ለሁለት የቆረጠ ነበር፡፡ ከዚህም በላይ ሻዕቢያ የአሰብ አስተዳደርን ሁሉ ጠቅሎ የእኔ ነው ሲል፣ ‹‹ይችን ይወዳል››  የሚል ተቀናቃኝ ዘመቻ ያልመጣበት በኢትዮጵያ ሥልጣን ላይ (ለዚያውም ጊዜያዊ ሥልጣን ላይ) ተቀምጦ የነበረው መንግሥት የዓላማው ሸሪክ ስለነበር ነው፡፡ ሸሪኩም በግልበጣና በተቃውሞ ያልተጠናው ነባሩን ሠራዊት በትኖ በራሱ ሠራዊት የሚሠራ ስለነበር ነው፡፡ ያኔ መቀጣጠል ያልቻለው ጣጣ ግን ይኸው ጊዜውን ጠብቆ ተደጋግሞ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

አሁን አሁን ኦነግን በተመለከተ እስከዛሬ እገነጠላሁ ብሎ አያውቅም እስከማለት ተደርሷል፡፡ ተብሏል? አልተባለም? የሚል ክርክር ውስጥም አንገባም፡፡ ይሁን እንጂ ሕዝብ ይወስን የሚል ጥያቄ ራሱን ችሎ የቆመ እንዳልሆነ መሳት የለብንም፡፡ አብሮ በመኖር ላይ ወይም በመለየት ላይ ውሳኔ የመስጠት ነገር ዝም ብሎ ከመሬት አይነሳም፡፡ ለዚህ ጥያቄ መምጣት መነሻ የሚሆነው ከበስተኋላ የመነጠል እንቅስቃሴ መኖሩ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ውሳኔ ሕዝብ ወይም ‹‹የሕዝብ ውሳኔ›› ዋና ጥያቄ ሳይሆን የጥያቄ መፍቻ ዘዴ ነው፡፡ ማተኮሪያ መሆን ያለበትም ሕዝብ ይወስን ባይነት ሳይሆን፣

  1. ከዚህ ጀርባ ቡድኖች ይበጃል ብለው የሚከራከሩበት አቋም ምንድነው? የሚለው ነው፡፡
  2. በአብሮ መኖር አለመኖር ላይ የመወሰን መብት በራሱ ሰላምን፣ ዴሞክራሲንና ፍትሕን ያቀዳጃል ወይ? ወደ እርስ በርስ ጦርነት የመግባትን ዕድል የሚያስቀረው የቱ መንገድ ነው? ያሉት ገዥዎች ወርደው የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ቢፈጠር እንኳን ተባብሮ ያንን ዴሞክራሲ ዘላቂ መሠረት እንዲይዝ ለማድረግ በመረባረብ ፈንታ በሽግግር ወቅት ቶሎ አዋክቦ ለመነጠል ጥያቄ ሕዝበ ውሳኔያዊ መልሶ ለማስገኘት ግፊት ቢኖር ወይም ውሳኔ ሕዝብ የማስደረግ ክንዋኔ ቢጀመር፣ በመከራ የተገኘች የዴሞክራሲ ጭላንጭል በወታደራዊ ግልበጣ እንድትቀለበስና ሌላ የተራዘመ አምባገነንነት እንዲዘረጋ ወይም እዚያም እዚያም በሚነሳ ተፃፃራሪ አመፅ ተለግቶ ፍጅት እንዲመጣ መንገድ መስጠት አይሆንም ወይ?

እነዚህን ለመሳሰሉ ህልውናን ለሚወስኑ ጥያቄዎች የማያሻማ መልስ መስጠት የማይዘለል ኃላፊነት ነው፡፡ ከዚህ ኃላፊነት ውጪ ሆኖ ‹‹ሕዝብ ይወስን›› በሚል አቋም ውስጥ መድበስበስ የአፈናን ዕድሜ የሚያሳጥር የዴሞክራሲ ትግል ለመገንባት አያስችልም፡፡

የመገንጠል ጥያቄን በማያነሱ እንዲያውም የማያዋጣና ከፋፍሎ የሚያስጠቃ መሆኑን አነሰም በዛም እንደ መገንዘብ ባሉ ቡድኖች ዘንድ የሚታይ የባሰ የፖለቲካ ጅልነት ደግሞ አለ፡፡ በአንድ በኩል የብሔረሰቦች እኩልነትና ሙሉ መብት በሕገ መንግሥት የተጻፈና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሰበከ ይሁን እንጂ በተግባር እየሠራ እንዳልሆነ፣ የብሔር የበላይነት ዛሬም እንደቀጠለና ፌዴራላዊ የሚባለው አወቃቀር የአንድ ፓርቲ አገዛዝ እንደሆነ እየተናገሩ (ባለው አገዛዝ ሥር አንቀጽ 39ን ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር የትም እንደማያደርስ እያወቁ) አንቀጽ 39ን ሙጥኝ አትንኩብን የሚሉ ብሔርተኞችን እናገኛለን፡፡ እነዚህ ሰዎች አንቀጽ 39ን በፕሮግራማቸው አስፍረው የአንቀጹ ጠበቃ ስለሆኑ ምንም ጠብ እንደማይል፣ ብሔረሰባዊ አድልኦን አሽቀንጥሮ እኩልነትንና ነፃነትን ማረጋገጫው የጭቆናውን ምንጭ ተባብሮ ታግሎ ዴሞክራሲን መዘርጋት እንደሆነ የኩቤክን ሕዝብ ከአንዴም ሁለቴ ሪፈረንደም ለማካሄድ ያበቃው ‹‹የመነጠል መብት›› አንቀጽ ሳይሆን፣ የዴሞክራሲ መገንባት እንደነበር መረዳትና መቃኘት ተራራ እንደ መግፋት ከብዷቸዋል፡፡

የብሔረሰብ እስከ መገንጠል የሚባል መብት በቻርተሩም ጊዜ ሆነ ከዚያ በኋላ ለአንዱ ማስፈራሪያ ለሌላው ማሞኛ ከመሆንና ከመነታሪከያነት ያለፈ እርባና አልነበረውም፡፡ ‹‹መነጠል አይበጀንም፣ ፍላጎቱም የለንም፤›› እያሉ ‹‹ኢትዮጵያ በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተች ነች . . . ቅር ያለው የመነጠል መብት አለው፤›› የሚል ቅብጥርጥር ውስጥ መግባት፣ ከዚያም አልፎ የመተባበር ጥያቄ ሲመጣ እስከ መገንጠል ያለመ መብትን ትቀበላላችሁ የሚል ጥያቄና ክርክር ማንሳት ሳንተማመንና ሳንቀራረብ እንረገጥ እያሉ ከመስበክ የማይለይ የመጨረሻ እንዝላልነት ነው፡፡ ይህ እንዝላልነት መሰባሰብን ከልክሏል፡፡ በመነጠል መብት ላይ እየተናቆሩ፣ መለያየትን ተሻግሮ በትግል መያያዝ እንደሚያስፈልግ በገባቸው ላይ ተፅዕኖው በቀላሉ የሚለቅ አልሆነም፡፡ መነጠል መብት ነው የሚባል ነገር አይበጅም ከሚሉ ወገኖች ጋር ግንባር መግጠም የብሔር መብትን አሳልፎ እንደመስጠት ሆኖ የሚተናነቃቸው፣ ከዚህም ቢያልፍ (እስከ መገንጠል የሚባል መብት ከብሔር ብሔረሰብነት ጋር የተጣበቀና የማይደፈር ተጨባጭ መብት እስኪመስል ድረስ በመስበክና ብሔርንም መወከል በየብሔር እየተቧደኑ ይህንኑ መብት ማነብነብ ሆኖ በመለመዱ የተነሳ) ብሔራችንን የካድን ተደርገን እንቆጠራለን ወይም ዘመቻ ይከፈትብናል የሚለው ሥጋት ይታገላቸዋል፡፡

ኅብረ ብሔር ነን በሚሉት በኩልም በብሔረሰብ ከተሰባሰበና ‹‹እስከ መገንጠል›› የሚል መብትን በፕሮግራሙ ካሰፈረ ቡድን ጋር ግንባር መግጠም ዓላማን እንደመሳትና ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እንደ መስማማት የሚቆጠረውና በዚህ አስተሳሰብ የሚምታታው ቁጥሩ ቀላል አይደለም፡፡ ‹‹ተፈቃቅደን›› ባይነት ከ70 እስከ 80 ብሔረሰባዊ አገሮች መሆን በተጨባጭ እንችላለን ብሎ የምር የሚያምን አለመሆኑና የሚያምን ካለም ብቻውን የሚቀር ወፈፌ ከመሆን በቀር፣ ምንም ያለማምጣቱ (የተናጠል ትግል የትም ያለማድረሱ) እናም ዛሬ የተፈጠረ መቀራረብ በሒደት ብዙ መልካም ነገሮችን ይዞ የመምጣቱ እውነትነት ጠንካራ ግንዛቤ አልፈጠረም፡፡

የትኛውንም የብሔር የበላይነት የሻረና እኩልነትን ያረጋገጠ የዴሞክራሲ ሥርዓት እስከተዘረጋ ድረስ አብሮ መኖር ችግር አለመሆኑን፣ እንዲያውም ዴሞክራሲ ቢጎድል እንኳን ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ይበልጥ የሚከብደው ከአብሮ መኖር ይልቅ መለያየት መሆኑን፣ ትግሉ ተሳክቶ ዴሞክራሲ ከተገነባ በኋላም የመነጠል ጥያቄ ቢኖር ጦርነትና ብጥብጥ በማይኖርበት ሁኔታ ምላሽ የመስጠትን ዕድል ራሱ የዴሞክራሲ ሥርዓትና ባህል ይዞት የሚመጣ መሆኑን ያስተዋለ ብልህ ትግል እስከተገመደ ድረስ፣ ጥርጣሬ እየጠፋ ‹‹አንድነት›› ባይና ‹‹ብሔር›› ባይ ድርጅታዊ ልዩነት እየፈረሰ፣ መዋሀድ መምጣቱ የማይቀር ነው፡፡ ዛሬ የሚያስፈልገውም ይህንን አሻግሮ ማየትና ማሳየት የሚችል በኅብረትና በግንባር መልኩ እያደገ የሚሄድ ኅብረ ብሔራዊ የእንቅስቃሴ አስኳል ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዕድገትና ሰላም ከአገርም አልፎ አካባቢያዊ የመደጋገፍና የመግባባት አድማሱን የሚሻ ሆኖ ሳለ አያሌ የብሔር ብሔረሰብ ቡድኖች ተፈጥረው የመሬት፣ የሀብት፣ የሥልጣን፣ የሥራ፣ የፌዴራላዊ ልማትና የተቋማት ድርሻን ከመተሳሰብ በላይ መትረክረካቸው እንደ ቀላል የማይታይ ችግር ነው፡፡ የአገሪቱን የተፈጥሮ፣ የሰው ኃይልና የዕውቀት ሀብት የብሔር ወይም ክልል አጥር ውስጥ ሸንሽኖ የደሃና የሀብታም ክልል ማነፃፀሪያ አድርጎ ማየትና የ‹‹ሀ›› ብሔር አባል የሆነ ሰው በያዘው ገንዘብና ጥበብ በቅድሚያ የ‹‹ሀ›› ብሔርን መጥቀም ያለበት አድርጎ ማሰብ፣ እኩል የልማት ዕድልን እየታገለ ነው፡፡ የአገሪቱ ሁሉ አቀፍ የዕውቀትና የማቴሪያል ሀብት የሁሉንም አካባቢ የልማት አቅም ለማውጣትና ለማሳደግ የመዋሉ መብትነት ገና በአግባቡ መሬት አልቆነጠጠም፡፡ ክልልተኛና ጎሰኛ ዕይታ የአካባቢው ተወላጅ ያልሆነውን አልሚ ሀብት ሊቦጠቡጥ እንደመጣ አድርጎ ይጠረጥራል፣ ያንጓልላል፡፡ ተንጋላዩም ባዕድ ቦታ እንዳለ እያሰበ ልማት ከማስፋፋት ይልቅ ትርፍ ወደ ሌላ የማሸሽ ችግር ውስጥ ይገባል፡፡ የዚህ ዓይነቱ ችግር አድሮና ከርሞ አሳፋሪ በቀልና መፈናቀልን ሊዘረግፍ የሚችል መሆኑ ይህንን አጥፊ አዝማሚያ ለማሸነፍም ሆነ ላልተዛባ የሀብትና የልማት ሥርጭት ከሽፋን ያለፈ ኅብረ ብሔራዊ የባለቤትነት ስብጥር ያላቸው የኢንቨስትመንት ኩባንያዎችን መፍጠርና ማበረታታት ተገቢና ብልህ መሆኑ በባለሀብቱም ሆነ በመንግሥታት በኩል ገና አልተጤነም፡፡ ሚድሮክ በኦሮሚያ ተጨማሪ የወርቅ ማዕድን መሬት ሲሰጠው በልማትና በአካባቢ ጥበቃ ስም የተደረገው ቅዋሜ (2002) እውነተኛ ይዘት፣ ሀብታችንን ተዘረፈ ነበር፡፡ ቢጂአይ  (BGI) የሚባለው የፈረንጅ ኩባንያ የቢራ ውጤቶችን (ለአገር ውስጥ ኩባንያ የማድላት ችግር ሳይገጥመው) እንደ ልቡ ሲቸበችብ ዳሸን ቢራ ግን በውስጣዊ ኩርፊያ የመጠመዱ አንዱ ምክንያት ይኸው ነው፡፡

ሐረሪን ከመሰለ ትንሽ (ሚጢጢ) ክልል አንስቶ እንደ ኦሮሚያ ያለ ከአንድ ጫፍ እስከ ሌላ ጫፍ የተዘረጋ ግዙፍ ክልል የሚገኙበትና የተወሰኑ ክልሎች በስተኋላ ወደ አንድ የተጠቃለሉበት መዋቅር፣ ለክልሎች ከሚሰጠው ድጎማ ጋር በተያያዘ ጥቅም የጠባብ ሩጫዎች መፍለቂያነቱ ማቆሚያ አጥቷል፡፡ ከእኛ ያነሰ የሕዝብ ቁጥርና የቦታ ስፋት ያለው ክልልም ሆኖ ቀጥታ ድጎማ ሲያገኝ እኛ ብቻ በአንድ ላይ የምንታጨቀው በምን አንሰን ነው? እነ እከሌ ልዩ ወረዳ ሲባሉ እኛ ለምን አንባልም? እኛ የራሳችን መለያ ያለን ራሳችንን የቻልን ብሔረሰብ ሆነን ለምን በአንድ ስያሜ ከሌላው ጋር እንጠራለን? ለምንስ እንዳበላለን? የእኛ አካባቢ ራሱን የቻለ አስተዳደር ባለመሆኑ በልማት ተዘነጋን . . . እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎች የሚነገርባቸውና ድል እስኪገኝ ድረስ ትግል የሚደረግባቸው ዓላማዎች እየሆኑ ናቸው፡፡ ለእንዲህ ዓይነቶቹ ጥያቄዎች መፍለቂያ የማይሆን ማስተካከያ እስካልተደረገና ክፍልፋይነትን ሰፊ አመለካከት እስካላሸፈነው ድረስ፣ ሁሉም ብሔረሰብና ‹‹ጎሳ›› ክልል እስኪሆን ድረስ ችግሩ ማቆሚያ አይኖረውም፡፡

የእነዚህ ዓይነቶችን ትንንሽ ሩጫዎች የሚፈታ መልስ የሚሰጥ ዴሞክራሲያዊ ማዕቀፍ በሌለበት ሁኔታ ወይም እነሱን ያኮመሸሸ የሕዝብ አጠቃላይ ትግል ከመፍጠሩ በፊት፣ አሁን የተዘረጋው ጥርነፋ ተሰብሮ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ቢከፈት ክልል ነኝ የማለት ሩጫ፣ ተዘረፍኩኝ/ተበደልኩ ባይነትና የተጠራቀመ ድፍርስ ሰሜቶች የሚፈጥሩት ትርምስና በየአደባባዩ የሚንጋጋ የጥያቄ ውጥንቅጥ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታውን የ15 ቀናት ዕድሜ ሳያገኝ በአጭር እንዲቀጭ፣ አፈና እንዲሰፍን ሊያደርግ እንደሚችል ከወዲሁ ቢሠጋ አጉል ማጋነን አይሆንም፡፡

በነገራችን ላይ አሁን ያለው አከላለል ሲተች ወይም ይሻሻል ሲባል ልዩ ልዩ ሕዝብ እንዳይኖር፣ ሁሉም አንድ ሕዝብ እንዲሆን ተፈልጎ ነው የሚል ክርክር ይቀርባል፡፡ በታሪክ ሒደት የማይቀረው መዘማመድም ክፉ ጉዳት ሆኖ ይቀርባል፡፡ እንዲህ ያለውን ክርክር ትቶ በደቡብ ክልልም በሌሎችም በትልልቅ ክልሎች ዘንድ ያሉ በአካባቢ ያሉ የልማት ተዛነፎችንና ቅሬታዎችን በወጉ ማድመጥና ለልማትና ለአስተዳደር ቅልጥፍና አመቺነትን ከቋንቋ ያለፈ የባህልና የኢኮኖሚ መወራረስን ከሕዝብ ፍላጎት ጋር የሚያግባቡ ማሻሻያዎች ለማድረግ ቢሠራ ለሁሉ ይበጃል፡፡

ብሔርተኛ ስንጥርጣሪነት ወይም በብሔረሰብ ውስጥ የታጠረ ትግል ለዴሞክራሲያዊ ትግል ያለውን ሌላ ገጽታም እንደመልክት፡፡ ብሔረሰባዊ ወገንተኝነትን መሠረት አድርጎ የሚፈጠሩ ስብስቦች ሕዝብ የተሻለ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አማራጭ ያለው የቱ ነው? በሚል ሚዛን ፓርቲዎች ከመለካት ፈንታ በየብሔር ወገንነታቸው እንዲመርጧቸው የሚያጥር ነው፡፡ በብሔር መደራጀት እንደተጠበቀ ሆኖ ብሔረሰቦች ፓርቲዎችን ባላቸው አማራጭ ለማበላለጥ ዕድል ሊያገኙ የሚችሉት ለየብሔሩ ከአንድ  የበለጡ ፓርቲዎች (ያውም የፖለቲካ ኢኮኖሚ ዓላማን የልዩነት መሠረት ያደረጉ) ከተፈጠሩ ብቻ ነው፡፡ ይህ ማለት ለኢትዮጵያ ቢያንስ ወደ 160 አካባቢ ፓርቲዎች ያስፈልጋሉ እንደማለት ነው፡፡ ይኼም ቢሆን ብሔረ ብዙ ስብጥር ባለበት አካባቢ ወይም በአገራዊ ሁኔታ የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ ድሬዳዋ ከተማ ውስጥ ከአንድ የበለጡ የሐረሪ፣ የኦሮሚያ፣ የሶማሌ፣ የአማራ፣ ወዘተ. ፓርቲዎች የምርጫ ውድድር ቢያደርጉ ዞሮ ዞሮ ብሔረሰባዊ የአደረጃጀት አጥሩ ሁሉም በየብሔሩ ካሉ አማራጮች ውስጥ ከማማረጥ እንዳይወጣ ያደርገዋል፡፡

የትልቁም ሆነ የትንሹ ብሔረሰብ ብሔርተኛነት ከማንም ቅድሚያ በራሱ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ በብሔርተኛ አመለካከት መደራጀት ምንም ቢሆን የራሱን ብሔር የማስቀደምና ሌላውን የማንጓለል ፈተና ውስጥ ይጥላል፡፡ በብሔረሰባዊ አደረጃጀት ሥልጣን ሲያዝም የአድሏዊነት ችግሩ አብሮ ይወጣና ሁለተኛ ዜጋ ሆንኩ የሚል ቅሬታ መፈጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህ ለመላቀቅና የሁሉንም ጥቅም ለማገናዘብ የሚያስችለው መፍትሔ ኅብረ ብሔራዊ አደረጃጀት ነው፡፡ ኅብረ ብሔራዊ አደረጃጀት ከዴሞክራሲ ጋር ሲገናኝና የብሔረሰብ መብት በዴሞክራሲ እኩልነት ውስጥ ሲስተናገድ የብዙኃንም ሆነ የአናሳዎች መብት የመቻቻል ዕድል ያገኛል፡፡

በአጠቃላይ አምባገነንነትን ከሚጠቅሙ ዴሞክራሲን ከሚያዘገዩ ችግሮቻችን መካከል አንደኛው አቦዳደናችን ነው፡፡ የብሔር ወይም ብሔረሰቦችን እውነት መካድ ይህ ባይቻል ጎሳ በሚል አጠራር እውነታውን ማሳነስ የለመደበት የትግሉ ሥልት ክፉኛ ቢሸፈንም፣ ኢትዮጵያ ባለብዙ ማኅበረሰቦች መሆኗን ተቀብሎ ይህንን እውነታ ከአገራዊ ትስስር ጋር የሚያግባባ ዴሞክራሲያዊ አመለካከት ይዞ ወደ ሕዝብ መቅረብና ሕዝብን መምራት ዛሬም ችግር መሆኑ እንደቀጠለ ነው፡፡ ስለዚህም የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ ዕውንና እውነት መሆኑን አውቆ ይህ ጥያቄ ግን የኢትዮጵያ ሕዝቦች አጠቃላይ የዴሞክራሲ ጥያቄ አካል እንጂ፣ በተገላቢጦችሽ የሁሉም ነገር መፍቻ አለመሆኑን ተረድቶ አያያዛችንን ከጅምሩ ማስተካከል አለብን፡፡ እስከዛሬም ድረስ አምባነገንነትን የጠቀመ ዴሞክራሲን ያዘገየ ቁልፍ ችግራችን ይኸው ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...