Thursday, May 30, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉየአገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታና የመፍትሔ ሐሳቦች

የአገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታና የመፍትሔ ሐሳቦች

ቀን:

በሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ

(ክፍል ሁለት)

ባለፈው ሳምንት ዕትም አገሪቱ ስላለችበት አጠቃላይ ፖለቲካዊ ሁኔታ፣ የፖለቲካዊ ሥርዓቱን አሳሳቢ ገጽታዎች፣ የኢኮኖሚ ሥርዓቱን ተግዳሮቶች፣ አገሪቱ አሁን ያለችበት ሁኔታ ውስጥ ለምን እንደገባች፣ በአጠቃላይ የተዘረዘሩት ጉዳዮች እርስ በርሳቸው እየተደጋገፉ በኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት በመሪነት ያፀደቀውን ሕገ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ የማይቻልበት ሁኔታ ላይ መደረሱ ተገልጿል፡፡ በዚህ የመጨረሻ ክፍል ተጨማሪ ችግሮችና የመፍትሔ ሐሳቦች  ተዳሰዋል፡፡

- Advertisement -

ሆኖም ይህ ከላይ የተገለጸው ሁኔታ ረጅም መቆየት ስለማይችል ኅብረተሰቡ ከሚሸከምው በላይ ስለሆነበት፣ የመንግሥት አስፈጻሚው አካል በኅብረተሰቡ ላይ የሚፈጽመው በደል ስለበዛበት፣ ከዚሁ ጋርም የኑሮ ውድነቱ፣ ሥራ አጥነቱ፣ ለችግሮቹ መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ግልጽ አቅጣጫዎች አለማየቱ ጋር ተቀላቅሎ የኢሕአዴግ መንግሥት በምርጫ መቶ በመቶ አሸንፌያለሁ ባለበት ማግሥት፣ በከፍተኛ የሕዝብ ተቃውሞና ሌሎች ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ገብቷል። ይህ ሁኔታ ደግሞ ቢያንስ ችግሮቹ የሚገለጹበትን መልክ በማንሳት በግልጽ ችግር አለብኝ እንዲል አስገድዶታል። ከላይ ከተጠቀሰው ፖለቲካዊ ሁኔታ ተነስቼ አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ ሦስት ቢሆኖች (Scenarios) ያሉ ይመስለኛል። እንደሚለከተው ቀርበዋል፡፡

አንደኛ ቢሆን፡- አገሪቱ ከውስጥ የሕዝብ ጥያቄ በሚፈጠረው ብጥብጥና ምናልባት የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትና የኃይል ጫና ተጨምሮበት መንግሥት መቆጣጠር ከሚችለው በላይ ሁኖ የመንግሥት መፈራረስና ሁከት ሊመጣ ይችላል። ይህ አማራጭ የመከሰት ዕድሉ አነስተኛ እንኳን ቢሆን እንደ አንድ ሊሆን የሚችል ጉዳይ ታይቶ እንዳይከሰት መሥራት ያስፈልጋል። የመሆን ዕድሉ ግን ዜሮ አይደለም። ባለፈው በኦሮሚያ ተፈጥሮ የነበረው የሕዝብ አመፅ በመንግሥት መዋቅር ላይ በተለይ በክልሉ መንግሥታዊ መዋቅር ላይ ፈጥሮት የነበረ ጫና በጣም ከፍተኛ ነው። በፌዴራል መንግስት የፀጥታ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ነው አመፁ የቆመው። አመፁ በስፋትም በጊዜም ቢቀጥል ኖሮ በተጨማሪም ሌሎች ተጓዳኝ የሕዝብ አመፆች ቢነሱ ኖሮ፣ በማዕከላዊ መንግሥት ላይ ሊፈጠር ይችል የነበረውን ችግር መገመት አይከብድም።

ሁለተኛ ቢሆን፡- ረዘም ላለ ጊዜ አሁን ባለው ቀውስ ውስጥ መቆየት ነው። ይህ ከሁሉም አማራጮች የመሆን ዕድሉ የላቀ ነው። አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ገዥ ፓርቲ በጠቅላላም ሆነ በተወሰነ ክፍሉ መጠነኛ ለውጦችን በውስጡ በማድረግ በግልጽ ያመነበትን የመልካም አስተዳደር ዕጦትና ሙስና ቴክኒካዊ፣ አስተዳደራዊ ትርጉም በመስጠት በዚህ ዓይነት ማዕቀፍ ውስጥ በመሆን ለመፍታት በመሞከር፣ የተወሰነ ጊዜ የጣላቸውን የሥራ ኃላፊዎችን በማስወገድ ከቀውሱ ለመውጣት ጊዜ ለመግዛት በመፈለግ የሚፈጠር ሁኔታ ሊመጣ ይችላል። አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ገዥ ፓርቲ በተፈጥሮ ሊያደላበት የሚችል የመጀመርያ ምርጫው የሚሆን በመሆኑ የመከሰት ዕድሉ የሰፋ አማራጭ ነው። ይህ አማራጭም ችግሩን ለተወሰነ ጊዜ ሊያዘገየው እንደሆነ እንጂ አይፈታውም።

ለተወሰነ ጊዜ በማዘግየት ችግሩ ይበልጥ ሥር እየሰደደ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለውም ዕድል እየጠበበ እንዲሄድ ያደርጋል። በዚህ ጊዜም በአገሪቱ ያለው ቀውስ እየተባባሰ ከመሄዱም በላይ፣ በመጨረሻም በጣም አውዳሚ በሆነ መንገድ ችግሩን ለመፍታት ለሚፈልጉ ኃይሎች የተመቻቸ ሁኔታ ይፍጥርላቸዋል። ስለሆነም ፈጥኖ የሚታየው የመፍትሔ አቅጣጫ የመሆን ዕድሉም የሰፋ አማራጭ ሆኖ ሳለ አገሪቱን አሁን በሚያስከፍለው ዋጋ፣ ይህ ኋላ በሚያስከትለው ነውጥ እጅግ የከፋው ነው፡፡ ይህ ሁኔታ እስካሁን ድረስ የተመዘገቡትን ድሎች ጠራርጎ ያጠፋል፡፡ አገሪቱን ወደኋላ ይመልሳል ብቻ ሳይሆን፣ ቀጥሎ የሚመጣውም ምን ዓይነት ሥርዓት እንደሆነ መተንበይና መገመት አይቻልም፡፡ እነዚህ ሁለት አማራጮች በጊዜ ሊለያዩ ካልሆነ በስተቀር በጣም ተመሳሳይ ናቸው። በራሳቸው መንገድ የሚከሰቱም ስለሆኑ እንዳይከሰቱ ምን እናድርግ በሚለው ሐሳብ ላይ ካልሆነ በእነሱ ላይ ብዙ መናገር አይቻልም።

ሦስተኛ ቢሆን ሰላማዊ፡- ሥርዓት ያለውና በንቃት የሚመራ ለውጥ መጀመር ነው። ይህ ማለት አሁን በአገራችን ፖለቲካዊ ቀውስ እንዳለ በማመን ይህንን ቀውስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ተከትለን በሰፊ የፖለቲካዊ ኃይሎችና የምልዓተ ሕዝቡ ተሳትፎ ለመፍታት የሚያስችል ፖለቲካዊ ሒደት መጀመር ነው። ይህ አማራጭ ከላይ የተገለጹትን ሌሎች ቢሆኖች እንዳይከሰቱ ለማድረግ ያስችላል። በመሆኑም በአገራችን የወደፊት ዕድል ያገባናል የምንል ዜጎች በሙሉ ተንቀሳቅሰን ዕውን እንዲሆን ማድረግ አለብን የሚል እምነት አለኝ። የዚህ ፖለቲካዊ ሒደት ዓላማና እንዴት ሊፈጸም ይችላል የሚለው ሐሳብ መጨረሻ ላይ እመለስበታለሁ።

የትግራይ ሕዝብ

በአገራችን ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ስላለው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጉዳይ ስናነሳ የትግራይን ሕዝብ ለብቻ ነጥሎ ማንሳት ለምን አስፈለገ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ተገቢ ጥያቄ ነው። እዚህ ላይ ማንሳት የምፈልገው ጉዳይ የትግራይ ሕዝብ በታሪኩ ራሱን ኢትዮጵያ ለምትባለው አገር መመሥረትና በታሪኳ ውስጥ በተለያዩ ውድቀቶችም ሆነ ድሎች ዋና ተዋናይ አድርጎ ነው የሚያስበው። ከዚህ ውጪ በሌላ መንገድ አያስብም። አሁንም ችግሮችን ስናነሳና መፍትሔ ስንፈልግ በዚህ በታሪክ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው አስተሳስብ ውስጥ ሁነን ነው። የትግራይ ሕዝብ ለብቻው የሚያስበው መፍትሔ አልነበረም፣ የለም። አሁን ባለው ከላይ የተገለጸው የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ተነስተን መፍትሔ ስናፈላልግ የትግራይ ሕዝብ ምን ማድረግ ይጠበቅበታል? አሁን ባለው የፖለቲካ ሁኔታ ራሱን እንዴት ያስቀምጣል? ለሚለው ጥያቄ መፍትሔ ሲፈለግ ለትግራይ ሕዝብ ብቻ የተለየ ከዚያ አንፃር ብቻ የተቃኘ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራስያዊ ሥርዓት ለማስፈን፣ ከዚህ ሥርዓትም እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝቦች እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን በማሰብ ነው።

የትግራይ ሕዝብ ይህ አሁን ያለውን የፖለቲካ ሥርዓት ለማምጣት ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በመሆን ታግሎ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሎ ያመጣው ነው። በመሆኑም እስካሁን ድረስም ሆነ ለወደፊትም ሥርዓቱን ለሕዝብ ጥቅም እንዲውል ከማድረግ አንፃር ያለው ድርሻ ከፍተኛ ነው። በተለይ ደግሞ እንደ ሕዝብ በዘለቄታው ጥቅሙ የሚከበርለት በሕገ መንግሥት ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲገነባ ስለሆነ። አሁን በትግራይ ወጣቶችና ጉዳዩ ያሳስበናል ብለው የሚያምኑ የትግራይ ተወላጆች ቀደም ብሎ በተነሳው ጥያቄ ላይ ግልጽ የሆነ ሐሳብ የለም፡፡ በመሀል አገር ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች በትግራይ ተወላጆች ላይ ጥላቻ ይንፀባረቃል። የትግራይ ሕዝብ በሥርዓቱ እላፊ ተጠቃሚ እንደሆነ ተደርጎ ይወራል፣ ይታያል። ተጨባጭ ሁኔታው ደግሞ ከዚህ የተለየ ነው። በእርግጥ ሁኔታውን ሕዝብን በማጣላት እንጠቀማለን ብለው የሚመኙ ፀረ ዴሞክራሲ ኃይሎች ያራግቡታል። እነዚህን ኃይሎች ካሰቡትና ከተመኙት ውጪ ማሳመን አይቻልም። ግን ደግሞ በተጨባጭ የሕዝቦች መራራቅ አለ። ይህ ለምን መጣ? እንዴት እንፍታው? ብሎ ማሰብና መወያየት ተገቢ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም የትግራይ ተወላጅ በመሆኔና ከዚህ ሕዝብ ጋር በተለያዩ ሁኔታዎች ሁኜ ስለታገልኩና ስላታገልኩ ሁኔታውን በተሻለ አውቀዋለሁ፡፡ ስለዚህ የሚታየኝን ሐሳብ የማቅረብና ቢያንስ ይህ አሳሳቢ ጉዳይ የኅብረተሰቡ አጀንዳ ሆኖ እንድንወያይበት፣ ሐሳብ እንድንለዋወጥበት ማድረግ ይገባል ብየ ስላመንኩበት ነው።  አሁን ባለችው ኢትዮጵያ የትግራይ ሕዝብ የሚኖረው ድርሻና የሚጫወተው ሚና ምን መሆን አለበት? የትግራይ ሕዝብ የሥልጣን ዘመኑን በፀጥታ ኃይሎች ድጋፍ የሚያራዝም፣ በየጊዜው ከሕዝብ እየተነጠለና በሕዝብ እየተጠላ የሚሄድ የፖለቲካ ሥርዓት ጠባቂና ተከላካይ ነው መሆን ያለበት? ወይስ ሌላ ምርጫ አለው? የትግራይ ሕዝብ አሁን ባለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ የሚወስደው የፖለቲካ አቋም ምን ይሁን? ብሎ መጠየቅ ይገባል። ለሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦችስ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን የሚጥስ ፖለቲካዊ ሥርዓት ጠባቂ ተደርጎ የተለየ ጥቅም የሚያገኝ ጠላት ተደርጎ ነው መታየት ያለበት? ወይስ በዴሞክራሲና በእኩልነት ላይ ለተመሠረተ የሕዝቦች አንድነት፣ ለሕዝቦች መብት መከበር፣ ለትክክለኛ ፍትሕና ለፍትሐዊ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በፊታውራሪነት የሚታገል ሕዝብ ተደርጎ ነው መታየት ያለበት? ብለን እየጠየቅን መልሱን መፈለግ ይኖርብናል።

ወደ ዝርዝር ጉዳይ ከመግባቴ በፊት በሕወሓት መሪነት የተካሄደው የትጥቅ ትግልና ይህ ትግል ያስመዘገበው ድል ዴሞክራሲያዊ፣ አብዮታዊና ትክክለኛ ነበር የሚል እምነት አለኝ። ደርግን የመሰለ ፀረ ዴሞክራሲ አፋኝ መንግሥትን ታግሎ መጣል ዴሞክራሲያዊም አብዮታዊም ነበር። ለጭቁን ሕዝቦች መብት መረጋገጥ የተደረገ ትግል ዴሞክራሲያዊ ካልሆነ ዴሞክራሲያዊነት ምን ሊሆን ነው? ስለሆነም በሕወሓት መሪነት በተደረገው ትግል በተለያዩ ደረጃዎች በተራ ተዋጊነትም በከፍተኛ አዛዥነትም ቦታ ላይ ሆኜ መሳተፌን እኮራበታለሁ። እነዚያን ጀግኖች እየመሩ የእነሱን ጥረት እያስተባበሩ ለድል መብቃት በታሪክ መታደል ነው እላለሁ፡፡ ይህ ማለት በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደገለጽኩት ሕወሓት የአማልክት ስብስብ ነበር፣ ስህተት አልነበረውም፣ ችግሮች አልነበሩም ማለቴ አይደለም። በድምር ሲታይ የደርግን ሥርዓት ለማሸነፍና ለመጣል በተደረገው ትግል ውስጥ ዴሞክራሲያዊና አብዩታዊ ባህሪው ከሁሉም በየጊዜው ሲያጋጥሙ ከነበሩ ችግሮች ያመዘነና የበለጠ ነበር። ስለሆነም ነው በአሸናፊነት የዘለቀው የሚል እምነት አለኝ።

የትግራይ ሕዝብ የደርግን ጨቋኝ ሥርዓት ለመጣል ከፍተኛ ዋጋ ይክፈል እንጂ፣ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች እላፊ ጥቅም ለማግኘት አልተመኘም፣ በተጨባጭም አላገኘም። በፌዴራል መንግሥት በርከት ያሉና ወሳኝ የሚባሉ የሚኒስቴር ቦታዎችን መያዝና በዚህ ሳቢያ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ባላቸው ቅርበት የተወሰነ ጥቅም የሚያገኙ የትግራይ ተወላጆች ካሉ፣ የትግራይ ሕዝብ የእላፊ ጥቅም ማግኘት ማስረጃዎች ተደርገው መወሰድ አይችሉም። ይባስ ብሎ በራሱ ጥረት ብዙ ችግሮችን ተቋቁሞ በኢኮኖሚው ረገድ ደህና የተራመደውም፣ በእነዚህ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ተጠግተው ጥቅም ከሚያገኙት ጋር እየተደመረ እንዲታይና  የሌሎች ሕዝቦችን አሉታዊ ስሜት ማነሳሻም እየሆነ ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ የአገሪቱ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት ሥራውን ሠርቶና ሀብት አፍርቶ ለመኖር የሚፈልገውም የትግራይ ተወላጅ ቀላል ያልሆነ ሥጋት ውስጥ ከቶታል፡፡ ይህ መሆን የሌለበት ጉዳይ ነው።

የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች ሕዝቦች የተለየ እላፊ ጥቅም አልፈለገም ሲባል፣ ለሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚሰጠው መብትና ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ሠርቶ መበልፀግ ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች በሚገባ ተከብረውለት መኖር ደግሞ ማንም ሊከለክለውና ሊነጥቀው አይገባም፡፡ በእኩልነትና በመፈቃቀድ ሕዝቦች መብቶቻቸው ተጠብቀውላቸው ተከባብረው የሚኖሩባት አገር እንድትሆን ነው ያ ሁሉ ዋጋ የተከፈለው። ይህንን ደግሞ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በመሆን ሊጠብቀው ይገባል፡፡  ድርሻውን የሚነጥቀው ኃይል እንዲኖር አይፈቅድም። ከላይ የተቀመጡትን ሐሳቦች መነሻ በማድረግ በእኔ አመለካከትና እምነት የትግራይ ሕዝብ የሰብዓዊና የፖለቲካዊ መብቶች በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ የሕዝቦች አንድነት በፍትሕ ላይ ለተመሠረተ የሕዝብ መብት ጥበቃ፣ ይህንን መሠረት አድርጎ የሚመጣ ኢኮኖሚያዊ ብልፅግናና ማኅበራዊ ልማት ለማምጣትና እነዚህ መብቶች ስፋትና ጥልቀት ኖሯቸው ተግባር ላይ እንዲውሉ የሚታገል መሆን አለበት እላለሁ። እነዚህ በሕገ መንግሥቱ የሠፈሩ መብቶች ሳይሸራረፉና ሳይገደቡ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆኑ፣ ጊዜው ሲፈቅድ ደግሞ ስፋትም ጥልቀትም እንዲኖራቸው በመታገልና ተግባር ላይ እንዲውሉ በማድረግ ነው እንደ ሕዝብ ጥቅሙ የሚከበረው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን በተወሰነ ታሪካዊ አጋጣሚ ሥልጣን ላይ የወጡ ከሱ የፈለቁ መሪዎችን የሥልጣን ዕድሜ ለማራዘም ሲባል፣ መንግሥታዊ መብቶችን የሚገድቡ ሕጎችና መመርያዎችን መደገፍ የለበትም እላለሁ፡፡

የትግራይ ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ ተጠብቀውለት ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በጋራ፣ በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ በተመሠረተ ፅኑ አንድነት እንዲኖር ዋናው ዋስትናው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትና የራሱ የትግራይ ሕዝብ ጥንካሬ ናቸው። ሕገ መንግሥቱን የትግራይ ሕዝብ ሊጠብቀውና ተግባር ላይ እንዲውል የሚፈለገውን ያህል የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የአፋር፣ የሶማሌ፣ በአጠቃላይ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሳይሸራረፍና ሳይገደብ ተግባር ላይ እንዲውል ይፈልጋሉ። ዋናው ዋስትናችን ደግሞ ይህ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የትግራይ ሕዝብ በፌዴራል መንግሥት የሚኖረንን ድርሻ በተገቢው መንገድ እየተወጣን፣ ከዚህ ጋር ጎን ለጎን በትግራይ ውስጥ የአገሪቱ ሕግና አቅማችን የፈቀደልንን ያህል የትግራይ ክልል በሕዝቡ ጥረትና ብቁ አመራር በመስጠት፣ የኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሰፈነበትን እንዲሆን ማድረግ ይጠበቅብናል። ይህ ሌላው ተጨማሪ ዋስትናችን ነው።

የመከላከያ ሠራዊት ሚና

እ.ኤ.አ. ከግንቦት 17 እስከ 21 ቀን 1993 ኢሕአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ ከሁለት ዓመት በኋላ አዲስ አበባ ላይ አንድ ትልቅ ሲምፖዚየም ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ይህ ሲምፖዚየም የመወያያ አጀንዳው በሚቀረፀው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ላይ ሰፊ ውይይት ማካሄድ ነበር፡፡ ሲምፖዚየሙ “Symposium on the Making of the New Ethiopian Constitution” ተብሎ ነበር የተሰየመው። በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ከፍተኛ ዝና የተጎናፀፉ ምሁራን ከተለያዩ አገሮች መጥተው በዚህ የአራት ቀናት ሲምፖዚየም በጣም ጥልቀት ያላቸው ሐሳቦችን በተለያዩ መስኮች አቅርበዋል። በዚህ ሲምፖዚየም እኔም በኢትዮጵያ የሚመሠረተውን ሠራዊት በተመለከተ ሐሳብ እንዳቀርብ ተጋብዤ ነበር። በስምፖዚየሙ ተገኝቼ ሐሳቡን አቅርቤያለሁ። ይህ ጽሑፍ ሲቀርብ እንደ የግል አስተያየት ሆኖ ቢቀርብም በወቅቱ ከመለስ ጋር በስፋት ተወያይተንበታል፡፡ ይህ ማለት በጽሑፍ የቀረቡት ሐሳቦች አሠራሩን ተከትለን የድርጅት አመራር ውሳኔ አልተሰጠበትም እንጂ፣ የድርጅቱ የኢሕአዴግን በሠራዊት ግንባታ ላይ የነበረውን መሠረታዊ አስተሳሰብ ያንፀባርቅ ነበር ማለት እችላለሁ፡፡ በኋላም በዚህ በቀረበው ጽሑፍ ውስጥ ያሉትን ዋና ዋና ጉዳዮች እንደ መመርያ ልንጠቀምባቸው ሞክረናል።

በሲምፖዚየሙ በቀረበው ጽሑፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ሐሳቦች ተሰንዝሯል። ያኔ አሁን ‹‹Security Sector Reform›› (SSR) እየተባለ የሚጠራውና እጅግ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘው አስተሳሰብ ገና ሳይታወቅና ስምም ሳይወጣለት፣ በመሠረቱ ይህ አስተሳሰብ የሚመራባቸው አንኳር አንኳር ሐሳቦችን ለሠራዊት ግንባታ ሒደት ልንመራባቸው እንደሚገባ አስቀምጠን ነበር። ሁሉንም እነዚህ አስተሳሰቦች እዚህ መድገም አስፈላጊ አይደለም። በዚያ ጽሑፍ እንደ ማጠቃለያ ሆኖ የተቀመጠን አንድ ዓረፍተ ነገር ግን እዚህ መጥቀስ አሁን ሠራዊታችን እንደዚያ ነው ያለው ወይ? ብሎ ለመጠየቅ ተገቢ ስለመስለኝ እጠቅሰዋለሁ። ‹‹We must create a citizen’s army. We must create a military which is loyal to and a servant of the people and which cannot be miss-directed to serve the interest of an elite or of those who might abuse their power. We must create an army which belongs to the people.›› ያኔ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰባችን ገና ሳይበከል እያለ ነው ያስቀመጥነው፡፡ አሁንስ ምን ዓይነት ሁኔታ ነው ያለው?  

እኛን መሰለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ሽግግር በሚደረግበት ኢኮኖሚው ኋላቀር የሆነና ብዝኃነት በበዛበት አገር የሚገነባ የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ግንባታ አጋዥ እንዲሆን ከተፈለገ ከማንኛውም የፓርቲ፣ የጎሳ፣ የሃይማኖትና የፖለቲካዊ ወገንተኛነት በፀዳ መልኩ ሥራው መሠራት ይኖርበታል። ይህ መርህ ከተጣሰና ሠራዊቱን እንደ ተቋም በሚመሩት መሪዎች ወገንተኛ በሆነ ፖሊቲካ ውስጥ የሚገባ ከሆነ፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያሰናክላል ብቻ ሳይሆን ለአገር ውድቀትና ብተና ምክንያት ይሆናል። የአገር መከላኪያ ሠራዊት በአገሪቱ በሚደረጉ ፖሊቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ጣልቃ እየገባ ተፅዕኖውን የሚያሳርፍ ከሆነ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖ ከባድ ይሆናል። ለዚህ ነው የሠራዊት አጠቃላይ አቅም በሲቪል መዋቅሩ ካሉት ሌሎች አካላት የበለጠ እንዳይሆን ጥንቃቄ መደረግ ያለበት። የሠራዊት ቁጥር አስፈላጊ ከሆነ በላይ እንዳይበዛ፣ በጀቱ ከአገሪቱ አቅም ጋር ተመጣጣኝ እንዲሆን፣ የገንዘብ አወጣጡና ደረጃው ቁጥጥር እንዲደረግበት፣ በሕዝብ በተመረጡ በሲቪል ባለሥልጣናት ሙሉ ቁጥጥር ውስጥ እንዲገባ፣ ወዘተ የሚደረገው።

እዚህ አንድ ማንሳት የምፈልገው ጉዳይ አገርን በኢንዱስትሪ ዕድገት ለማፋጠን የሚደረገው እንቅስቃሴ በዋናነት በጄኔራሎች የሚመራበት መንገድ አይገባኝም፡፡ በተለምዶ ሜቴክ እየተባለ የሚጠራው አደረጃጀት በአገሪቱ ያሉትን የኃይል ማመንጫ፣ የስኳር ፋብሪካ፣ የባቡር ሐዲድ ሥራዎች፣ እንዲሠራ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ እነዚህ ሥራዎች አገር ውስጥ ቢሠሩ ጥሩ ነው፡፡ ግን ለምን በጄኔራሎቹ ቁጥጥር ሥር ይሆናሉ? በአገር መከላከያ ውስጥ የሚገኝ ቴክኒካዊ ብቃት ካለ ታንክን፣ አውሮፕላን፣ ተሽከርካሪዎችን፣ የመገናኛ መሣሪያዎችን፣ ወዘተ. ይጠግን ብቃት ካለውም ይፈብርክ፡፡ ከዚህ በላይ ብቃታቸው ተፈላጊ የሆኑ የሠራዊት አባላት ካሉም በሲቪል መዋቅሩ ውስጥ ገብተው ሥራውን ይሥሩ፡፡ ምንም እንኳን በሕግ ራሱን የቻለ አወቃቀር ያለው ቢሆንም፣ አሁን ከአገር መከላከያ ጋር ያለው ቁርኝት ግን አላስፈላጊ ነው እላለሁ፡፡ ይህ ግዙፍ በጀት ያለው አደረጃጀት በሕግ አውጭው አካል ተጠያቂ እንዳይሆን የአገር የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ እየተባለ የሚሸፋፈን ነገር እንዲኖር ስለዚህም ተጠያቂነት የሌለው ብክነት እንዲፈጠር ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሥራ በመስጠትና በመከልከል በአገሪቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ መቅረት ይችል የነበረ አላስፈላጊ ተፅዕኖ ፈጣሪ ይሆናል፡፡ ይህ በድምር ደግሞ የአገር መከላከያው ተቋም በአገሪቱ ፖለቲካዊ ሕይወት ውስጥ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ይጨምራል፡፡ እንደ መርህ ግን ወደ ተደላደለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሚደረግ ሽግግር የአገር መከላከያ ኃይል በጠቅላላው በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን አላስፈላጊ ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም መቀነስ ነው መሆን ያለበት፡፡ አሁን በአገራችን ያለው ሁኔታ ይህንን መርህ የተከተለ አይደለም፡፡    

አንድ አገር ሉዓላዊነቱን ጠብቆ ሕዝብ በመረጠው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትና የአኗኗር ዘይቤ ያለምንም የውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ እንዲመራ በማስቻል የአገር መከላከያ ሠራዊት እጅግ ከፍተኛ ድርሻ ያለውን ያህል፣ ከዚህ በላይ መስመር አልፎ በአገሪቱ ውስጣዊ ፖሊቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ጣልቃ እየገባ ተፅዕኖ የሚያሳድርና ለመምራት የሚከጅል ከሆነ ደግሞ፣ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል። በሕገ መንግሥት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ ያለ አገር ይህንን ከሠራዊት ሊመጣ የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ መቃወምና መቆጣጠር ይገባዋል። ይህ ካልሆነ በሥርዓቱና በአጠቃላይ የአገሪቱ ቀጣይ ህልውና ላይ ከፍተኛ አደጋ ሊደቅን ይችላል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይ አንዳንድ ዘረኛ የሆኑ አስተሳሰቦች ጎላ ብለው ሲነገሩና በአገራችን የሕዝቦች መነሳሳት ሲበራከት የትግራይ ተወላጆች፣ የፀጥታ ኃይሉ በአጠቃላይ፣ የመከላከያ ኃይሉን ደግሞ በተለይ እንደ መከታ የማየት አዝማሚያ ይደመጣል። በነሱ አነጋገር መከላክያ ተጠናክሮ የሕዝብ መነሳሳቱን እንዲቆጣጠርና አገሩን ‹‹እንዲያረጋጋ›› ፍላጎታቸውን ይገልጻሉ። ይህ የተለየና የተሻለ አማራጭና የመፍትሔ ሐሳብ ከማጣትና በችግሩ ከመጨነቅ የሚመጣ ይመስልኛል፡፡ ግን ደግሞ ችግሩን ያባብስ እንደሆነ እንጂ አይፈታውም፡፡ በመከላክያ ኃይል ጣልቃ ገብነት የሚጠበቅ የትግራይ ሕዝብ መብት ሆነ ጥቅም የለም። ቀደም ብሎ የነበሩ ገዥ መደቦች የፈጸሙትን ስህተት ለመፈጸም ከቃጣን ደግሞ አንችለውም። እነሱን እንኳን ከትግራይ ሕዝብ የበዛ ሕዝብ፣ የበለጠ ሀብት፣ የተሻለ ተሞክሮ፣ የተሻለ የተማረ የሰው ኃይል ይዘው አልቻሉትም፡፡ ምክንያቱም አስተሳሰቡ አድኃሪ ስለሆነና ሕዝብ ለመጨቆን የሚቃጣ ስለሆነ አይቆምም።

ከላይ የሚታዩት የሠራዊት አዛዞች የትግራይ ተወላጆች በርከት ብለው ቢታዩም ሠራዊቱ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ስብጥር ነው። በዚህ አካል ውስጥ ወገንተኛ የሆነ ፖለቲካዊ አቋም ከተያዘ ራሱን ተቋሙን ከውስጥ ለማፍረስ እንደወሰነ መታወቅ አለበት። በተቋሙ ውስጥ ያሉት አባላት የሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ልጆች ስለሆኑ በየብሔር ብሔረሰቦቻቸው ተከፋፍለው ተቋሙ ይፈረካከሳል። ይህ ደግሞ ሰበቡ እጅግ ከፍተኛ ነው። የአገር መከላክያ ሠራዊት የአንድን አገር ሉዓላዊነት ጠብቆ አንድ አገር እንዲሠራ ከሚያስችሉት ተቋማት ዋናው ምሰሶ ነው። በእዚህ ተቋም ውስጥ የሚመጣ መፈረካከስ አገሪቱን በሙሉ ይዞ ነው የሚፈረካከሰው። ስለዚህ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይጠይቃል። ዋነኛው የጥንቃቄ ዕርምጃ ደግሞ እንደ ተቋም ወደ ወገንተኛ ፖለቲካ (የብሔር፣ የፓርቲና የሃይማኖት፣ ወዘተ.) አለመግባት ነው። ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮውን ብቻ መፈጸም ነው። ስለዚህ የመከላከያ ኃይል በማጠናከር ፖለቲካዊ ጫዋታ ውስጥ እንዲገባ ማሰብ በእሳት እንደመጫወት መሆኑ መታወቅ አለበት።

ከዚህ በተጨማሪ ግን እንዲያው ድንገት ይህ ጉዳይ ተሳክቶ ሠራዊቱ አገሪቱን ለጥቂት ጊዜ ቢያረጋጋ፣ ውለታ ፈጽሜያለሁ የሚለው ሠራዊት ወይ ራሱ ንጉሥ ይሆናል (ደርግ እንዳደረገው) ወይም አንጋሽ ይሆንና የአገሪቱን ፖለቲካ ወታደሮቹ በሚፈልጉት መንገድ ያምሱታል። የፈለጉትን ይሰቅላሉ፣ ያልፈለጉትን ያወርዳሉ፤ በዚህ ሒደት አገር ሰላም፣ መረጋጋት፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚባል ነገር ታጣለች። ወታደሮቹ እንደፈለጉ ይፈነጩባታል። ይህ ደግሞ አሥርት ዓመታት ወደ ኋላ መመለስ ነው። ይህን የሚመኝ ንፁህ ህሊና ያለው ዜጋ ያለ አይመስለኝም። በአጠቃላይ በፀጥታ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት የሚፈታ የፖለቲካ ችግር በኢትዮጵያ ውስጥ የለም። የፀጥታ ኃይሎች በተለይ የአገር መከላክያ ሠራዊት ጥሩ ውጤት የሚያመጣው የትክክለኛ ፖለቲካ ተቀጥያ፣ የትክክለኛ ፖለቲካ ማስፈጸሚያ ሆኖ ሲያገለግል ነው። በአጭሩ ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጠለትን ተልዕኮ ሲፈጽም ብቻና ብቻ ነው። ይህ ደግሞ በብዙ በዚህ ጉዳይ ከፍተኛ ምርምር ያደረጉ ሊቃውንት ተነግሮ ያደረ ጉዳይ ነው።

የመፍትሔ ሐሳቦች

ከላይ እንደተገለጸው አገራችን በከፍተኛ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ነው ያለችው፡፡ ይህ ቀውስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መሠረት በማድረግ፣ በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚያስችል ፖለቲካዊ ሒደት በቅርብ ጊዜ ካልተጀመረ አገራችን እንደ አንድ ህልውናውና ሉዓላዊነቱን የጠበቀ አገር ለመቀጠል አዳጋች በሚሆንበት ሁኔታ ላይ እንደርሳለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ የዚህ አሁን አገራችን የምትገኝበት ፖለቲካዊ ሁኔታ ዋናው ምክንያት ደግሞ በትንሹ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች መተግበር አለመቻል ነው፡፡ መፍትሔውም ሰፊ ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ በመፍጠር መጀመር አለበት፡፡ በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና የተሰጣቸውን ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተግባር ላይ በማዋል የሚጀመር ፖለቲካዊ ሒደት ዋና ዓላማው ዴሞክራሲያዊ ምኅዳሩን በማስፋት ሕዝብ በመንግሥት ላይ ሊኖረው የሚገባውን የመቆጣጠር አቅም መጨመር፣ ተዓማኒነት ያለው አስተዳደር መመሥረትና፣ ከዚያም በኋላ ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ጥልቀትና ስፋት እየጨመረና እየጎላ የሚሄድበትን መደላድል ማመቻቸት ይሆናል፡፡

አሁን አገራችን ካለችበት ቀውስ ለመውጣት በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡትን ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶችን ያለምንም መሸራረፍ ተግባር ላይ በማዋል ሁሉም ፖለቲካዊ ኃይሎች ያለምንም ተፅዕኖ በሰላማዊ ፖለቲካዊ ውድድር የሚሳተፉበትን ሁኔታ በማመቻቸት መጀመር አለበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኅብረተሰቡ በሲቪክ ማኅበራት ሆነ በተናጠል በየግሉ በሚያደርገው ሰፊ ተሳትፎ፣ አሁን አገራችን ያለችበትን ፖለቲካዊ ቀውስ በሚገባ እንዲገነዘብ በማድረግ ፖለቲካዊ ተሳትፎውን ከፍ ማድረግ ይገባል፡፡ በሒደትም ሕዝብ በመንግሥት አሠራር ላይ ያለውን ተፅዕኖ የሚያሳድግበት፣ በሰፊ የሕዝብ ተሳትፎ በሚመሠረት ፖለቲካዊ ሥርዓትም ይበልጥ መተማመን የሚፈጠርበት፣ ቅሬታዎቹንና የሚያያቸውን ጉድለቶች ሳይሸማቀቅ የሚወያይበት፣ ከዚህ እየተነሳም መፍትሔ የሚያቀርብበት ፖለቲካዊ ሁኔታ መፍጠር አለበት፡፡ ከዚህ ጋር ጎን ለጎን ኅብረተሰቡ ፖለቲካዊ አስተሳሰቡን ከሚስማማውና የአገራችንን ፖለቲካዊ ችግሮች መፍታት ይችላል ብሎ ከሚያምንበት ፖለቲካዊ ፓርቲ ሥር በእምነት የሚደራጅበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት፡፡ ይህ ሒደት በጊዜ እየተጠናከረ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ አግባብ ችግሮችን በመፍታት ቀውሱን ማስወገድ የሚቻልበት ሁኔታ እየጎላ መምጣቱን የሚያይበት፣ በመሆኑም በኅብረተሰቡና በፖለቲካዊ ኃይሎች መካከል መተማመን እየጠነከረ የሚሄድበት ሁኔታ መፍጠር ይገባል፡፡

በመጨረሻም ጊዜውንና ሕግን ጠብቆ በሚደረግ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ምልዓተ ሕዝቡን ያሳተፈና ተዓማኒነት ያላቸው ዓለም ዓቀፋዊ የምርጫ ታዛቢዎች የተሳተፉበት ምርጫ በማካሄድ ኅብረተሰቡ የሚፈልገውን የፖለቲካ ፓርቲ እንዲመርጥ ማስቻል ይገባል፡፡ የፖለቲካዊ ኃይሎችም በዚህ ሒደት የሚገኝን የምርጫ ውጤት በፀጋ የሚቀበሉበት፣ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግም የሚስማሙበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡

ይህንን ሰፊ እንቅስቃሴ የሚጠይቅ በመጨረሻም በሚቀጥለው የምርጫ ዘመን የሚቋጭ ፖለቲካዊ ሒደት ለማስፈጸም በአገራችን ካሉት የተለያዩ ፖለቲካዊ ፓርቲዎች ተስማምተው የሚያቋቋሙት ይህንን ሒደት የሚመራ መዋቅር መፈጠር አለበት፡፡ ይህ ከፖለቲካ ፖርቲዎች ጋር በመስማማት የሚፈጠር ዓላማው ከላይ የተገለጹትን ሁኔታዎች ማሳካት የሆነ አካል፣ ከመንግሥት የዕለት ተዕለት ሥራ ተለይቶ ዋናው ሥራው አሁን ያለውን ቀውስ በመፍታት ከላይ የተገለጸውን ምርጫ ማካሄድ ይሆናል፡፡ በዚህ ወቅት መንግሥታዊ መዋቅሩ የመንግሥት የዕለት ተዕለት ሥራ ሳይስተጓጎል ሲደረግ እንደነበረው ሥራውን ይቀጥላል፡፡ ይህ ሒደት የታለመለትን ግብ እንዲመታና በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ በፍጥነት እስከ መጪው ምርጫ ድረስ ከፍተኛ የፖለቲካ ሥራ መሠራት አለበት ብዬ አምናለሁ።

እነዚህ ከላይ የተቀመጡትን ዓላማዎችና የመፍትሐረ ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ከመናገርና ከመጻፍ የዘለለ በርካታ ተጨባጭ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው ግልጽ ይመስለኛል፡፡ ይህንን ሰፊ ሥራ በተለያዩ ሙያዎች (Disciplines) ዕውቀት ያላቸው ሰዎች መጀመሪያ ሐሳቡን በአግባቡ አደራጅተው ቢያስቀምጡትና ከዚህ የተነሳ ዝርዝር ዕቅድ መጥቶለት ቢተገበር የበለጠ ውጤት ይኖረዋል፡፡ ይህ የሚታሰበው እንቅስቃሴ ገዥው ፓርቲና እሱ የሚመራው መንግሥትም ችግሮቹን በግልጽ እየተናገረና  የመፍትሔ ፍላጎት ያለው መሆኑን እየገለጸ ስለሆነ፣ በውስጡ ያሉትን ችግሮች (ችግሮቹን ለመፍታት የሚደረገውን እንቅስቃሴ የማይቀበሉ ኃይሎች እንደሚኖሩ ግልጽ ስለሆነ) ፈትቶ የችግሩ መፍትሔ አካል ይሆናል ከሚል ይነሳል፡፡

የመፍትሔ ሐሳቦች አጠቃላይ ባህሪ ገዥው ፓርቲና ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች በጋር በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን መብቶች በሙሉ ሳይሸራረፉ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር ይሆናል፡፡ የተጠቀሰውን ሁኔታ ለመፍጠር ምን መደረግ አለበት? የሚለው ሐሳብ የፖለቲካ ኃይሎች ራሳቸው በሚያደርጉት ምክክርና ድርድር ዝርዝር አካሄዱ የሚወሰን ቢሆን ይመረጣል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አንዳንድ መታየት ያለባቸውን ጉዳዮች ለመጠቆም ግን እንደገና መታየት ያለባቸው ሕጎች ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ የምርጫ ሕግጋት፣ የሰላማዊ ሠልፍ፣ የሚዲያ የፓርቲ ምዝገባ፣ ወዘተ. በጠቅላላ ሕዝቡን አደራጅቶ፣ በነፃ ሐሳቡን ገልጾ፣ የፈለገውን የፖለቲካ ፓርቲ ተቀላቅሎ በፍላጎቱ እንዲመርጥ፣ ፓርቲዎቹም ሐሳባቸውን ተገቢው መንገድ በመንግሥት ሚዲያም ጭምር ያለ ተፅዕኖ እንዲገልፁ፣ ከሕግ አንፃር ሁኔታዎችን ማመቻቸትና ተግባር ላይ እንዲውሉ ማድረግ፣ መልሶ መደራጀት ያለባቸው አካላት ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ የምርጫ ኮሚሽን፣ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የመንግሥት ሚዲያ ቦርድ፣ ወዘተ፡፡ የጠቅላላ እንቅስቃሴው ውጤት የሚለካው በኅብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ የመተማመን (Confidence Building) መንፈስ በመፍጠር ኅብረተሰቡ በፖለቲካዊ ሒደት ትልቅ ተስፋ እንዲያሳድር በማድረግና በመጨረሻም ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተካሂዶ ውጤቱ ተዓማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ በማስቻል ነው፡፡

በዚህ ሒደት የፀጥታ ኃይሎች እንደ ሌሎቹ የመንግሥት የሥራ አስፈጻሚ አካላት በማንኛውም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ከመግባት ሙሉ በሙሉ መቆጠብ ይኖርባቸዋል፡፡ ዋናው ሥራቸው የአገር ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የፖለቲካ ኃይሎች በጋራ መድረካቸው የተሰማሙበትን ማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማንኛውም የታጠቀ ኃይል (የመንግሥት ሆነ የፖለቲካ ኃይሎች የሚያሰማሩት) የሕዝቡን ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ለመገደብ ወይም የእንቅስቃሴውን ውጤት በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ተፅዕኖ ለመፍጠር የሚደረግ እንቅስቃሴ መቆጣጠር አለባቸው፡፡  

ማጠቃለያ

በእኔ አመለካከት አገራችን ለመፍታት አስቸጋሪ ወደሆነ ፖለቲካዊ ቀውስ ልትገባ ትችላለች። ከዚህም አልፎ እንደ አንድ ሉዓላዊነቷን ያስጠበቀች አገር ለመቀጠል የማትችልበት ደረጃ ልትደርስ ትችላለች ብዬ አስባለሁ። ይህንን ለማስቀረት የሚያስችል የመሰለኝን ሐሳብ አቅርቤያለሁ፡፡ የእኔ ሐሳብ ብቻ ነው ትክክል የሚል አቋም የለኝም። ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ ስለሆነ በሠለጠነ መንገድ የመንደር ስድቡንና አሉባልታውን አስቀርተን በጉዳዩ ላይ እንነጋገርበት የሚል ሐሳብ አለኝ። ችግር መኖሩን መንግሥት በግልጽ ያመነበት ስለሆነ ችግሩን መደበቅ አይቻልም። የችግሩ መንስዔዎች ምንድን ናቸው? እንዴትስ ይፈታሉ? በሚለው ሐሳብ ላይ ደግሞ የተለየ አስተሳሰብ ካለ (የመንግሥት፣ የገዥው ፓርቲም ሆነ የሌላ የፖለቲካ ኃይል) እንስማው። በአጠቃላይ አሁን አገራችን በምትገኝበት ሁኔታ ላይ ያለፍርኃት ሙሉ ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ተጠቅመን እንወያይበት።

በእኔ አመለካከት ይህ አሁን የሚታየው ፖለቲካዊ ችግር ከፖለቲካዊ ሥርዓቱ አወቃቀርና ከኢኮኖሚ ሁኔታው የሚነሳ ስለሆነ ሥርዓታዊ (Systemic) ነው የሚል እምነት አለኝ። ስለሆነም ነው ኢሕአዴግ ችግሩን እያየና እያወቀው እየተነጋገረበት እያለም ለመፍታት ያስቸገረው ብዬ አምናለሁ። ለወደፊትም በገዥው ፓርቲ መዋቅርና ገዥው ፓርቲ በቀየሰውና በሚመራው የሕዝብ እንቅስቃሴ ብቻ አይፈታም የምለው። ከገዥው ፓርቲ፣ ገዥው ፓርቲ ካዋቀረው መዋቅርና እሱ ከሚመራው የሕዝብ እንቅስቃሴ በተጓዳኝና እኩል፣ እንደሱ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርገው የሚያደርጉት ሰፊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ተጨምሮበት ነው ችግሩን መፍታት የሚቻለው የሚል እምነት አለኝ። የዚህ ሁሉ መቋጫው ደግሞ ነፃ፣ ፍትሐዊና በገለልተኛ ዓለም አቀፍና አገራዊ ታዛቢዎች የተመሰከረለት ምርጫ በማካሄድ ሕዝብ የመረጠው መንግሥት ሲመሠረት ነው ጉዳዩ ቀስ በቀስ እየተፈታ የሚሄድ ብዬ አምናለሁ። ሕዝብ መንግሥትን በተለይ የሥራ አስፈጻሚውን መቆጣጠር ሲችል ነው አሁን እየታዩ ያሉ ችግሮች የመፍትሔ መንገድ የሚበጀላቸው ብዬ አምናለሁ።

ዴሞክራሲና ነፃ የሕዝብ ምርጫ በአንድ ወቅት ሥልጣን ላይ ያለን ፓርቲ ፍላጎትና ምኞት ማሳኪያ መሣሪያዎች አይደሉም። ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እፈልጋለሁ ብሎ ያመነ ፓርቲ ከዚህ ጋር አብሮ ሕገወጥ በሆነ የጉልበት መንገድ እኔን ብቻ እንጂ ሌላውን ፓርቲ እንዳትመርጥ ማለት የለበትም። ሕገ መንግሥታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሒደት ነው፡፡ ውጤት ደግሞ በሕዝብ ፍላጎት የሚወሰን ነው። በአንድ ወቅት በሥልጣን ላይ ያለ ፓርቲ የዴሞክራሲያዊ ሒደት ውጤት ማሸንፍም መሸነፍም መሆኑ አውቆ፣ አምኖ ተቀብሎ መሄድና በዚህ መንገድ መሥራት አለበት። አንድ ፓርቲ ‹‹ዘለዓለም›› በሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚመኝ ከሆነ አስተማማኙ መንገድ ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አይደለም።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የኢሕአዴግ ነባር ታጋይና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም የነበሩ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው   [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን...

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣...

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች...

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...