መንግሥት አገርን በማልማት የዜጎችንም የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የሚያደርገው ጥረት ከሚያስደስታቸው ሰዎች አንዱ ነኝ፡፡ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችና ትልልቅ የማምረቻ ተቋማት ምሥረታ በሚካሄድበት በዚህ ወቅት የአስመሳይነትን ጭንብል የለበሱ እኩያን ግን በመንግሥታዊ ተቋማት ኃላፊነታቸው ስም ሥልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም፣ ፍትሕን በማዛባት፣ ዜጎችን በማማረር የግል ጥቅማቸውን የሚያካብቱ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በመልካም አስተዳደር እጦት የተንገሸገሸውን ማኅበረሰብም ሆነ መንግሥት ራሱን ለመታደግ በማሰብ ከላይ እስከታች ባሉት የመንግሥት መዋቅሮችና ተቋማት ውስጥ የሰፈነውን ኪራይ ሰብሳቢነትና አድሎአዊ አሠራር ለመበጣጠስ ቆርጦ የመነሳቱን ደውል ስሰማ ተደስቻለሁ፡፡
ስለሆነም እንደ ዜጋም የመንግሥትን ጥቅም እየጎዱ ያሉትንና ተባባሪዎቻቸውን በምኖርበት ወረዳ በግሌ የደረሰብኝን በደልና የታዘብኩትንም በማስረጃ አስደግፌ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5/6 ወይም በተለምዶ ጣሊያን ሰፈር ደጃዝማች/ነሲቡ በሚባለው ሰፊር ውስጥ በግል ይዞታዬ በቤት ቁጥር 1651 መኖሪያ ቤት ነዋሪ ነኝ፡፡ አቤቱታዬን ማቅረቤ ለአቤቱታዬ ትኩረት በመስጠትና ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ተገቢውን ፍትሕ እንዳገኝ በማመን ነው፡፡
መንስዔው ሕጉና ፖሊሲው ጋር ራስን አዋህዶ ልማታዊ መንግሥታችን የሚያራምደውን መልካም አስተዳደር ለማስፈንና ተገቢውን የሕግ ማስከበርና መብቶችን በየደረጃቸው ሕግን ተከትሎ ለመሄድ ቅንነቱና ሐቀኝነቱ የሌላቸው በየደረጃው በመንግሥት ኃላፊነት ተሰጥቷቸው በሕዝብ አገልግሎት ሰጪነት የተመደቡ ኃላፊዎች፣ ሕገወጥ የመሬት ወራሪዎችን፣ የመንግሥትና የሕዝብ የሆነውን ባዶ መሬት በመውሰድ ጉዳት አድርሰዋል፡፡
መንግሥት ሰነድ አልባና ጨረቃ ቤቶችን ሕጋዊ ለማድረግ ጥናቱን ጨርሶ ሐሳቡን በሚያንሸራሽርበት ወቅት፣ ይህንኑ ተገን አድርገው በተወረሰ መኖሪያ ቤት ቁጥር 1643 ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኘው ባዶ ቦታ ላይ በተከራይነትም ሆነ በአካባቢው በነዋሪነታቸው የማይታወቁ ሰዎች ቀድሞም እንደነበሩ በማስመሰል በመንግሥትና በሕዝብ ሀብት ላይ ሕገወጥ ግንባታ እንዲካሄድ ከወራሪዎች ጋር በማበር የመሬት ሽሚያ ከመፈጸም ባሻገር ሕገወጥ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ከመፀዳጃ ቤት ጋር በግድግዳ በማስደገፍ ጭምር እንዲገነባ አድርገዋል፡፡ ሌሎችም የሚከራዩ ቤቶች በወራሪዎች ተሰርተውና በካርታ እንዲካተቱ ተደርገው ሰነድ በ2 ገጽ ከተዘጋጀ በኋላ አንዱ በመንግሥት በተወረሰ ቤት ቁጥር 1643 ከሀ/ለ/አ/ የተባለ ስያሜ ተሰጥቶ በሌላ ገጹ ሰነድ አልባ ተብሎ በወረዳና በክፍለ ከተማ መዝገቦች ውስጥ ይገኛል፡፡ በውስጥ ታዋቂ ቁጥር 307 በመሰናዶ የይዞታ ማረጋገጫ ክፍል እየተጻፈ አንድ ጊዜ ኪራይ ቀመስ የመንግሥት ቤት እየተባለ በሌላ ገጹ ደግሞ የግል ይዞታ ተደርጐ የቤቱ ሕጋዊነት እንዲረጋገጥና ካርታ እንዲያገኝ ተደርጐ ሕጋዊ የድጋፍ ደብዳቤ ተጽፎለታል፡፡ ከዚህም አልፎ በቤት ቁጥር 1651 ለሚታወቀው ቤት ካርታ፣ የ1652 ቤት ቁጥር ደግሞ በወራሾች ስም በሰነድ አልባነት ከመረጋገጡ በፊት የመንግሥትን ጥቅም ባልጠበቀ መልኩ ሕግ ተጥሶ ለሦስተኛ ወገን በሽያጭ እንዲተላለፍ ተደርጓል፡፡ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ከወረዳው ጀምሮ ‹‹ሕግ ይከበር፣ መብት ይጠበቅ›› በማለት ቅሬታዬን ከወረዳ በደረጃው እስከ መሬት ማኔጅመንት የግንባታና ቁጥጥር ከዚህ ባሻገርም የክፍለ ከተማ ቅሬታ ሰሚ ቀርቤ ሕጉ በትክክለኛው መንገድ እንዲከበር፣ መብት እንዲጠበቅ፣ ሰነድና ካርታም ከመሬት የአየር ካርታ ጋር ተገናዝቦ ስህተት እንዲታረም ጠይቄያለሁ፡፡ ሕገወጡ ግንባታና መጸዳጃው በቤቴና በጤናዬ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት እንዲወገድልኝ አመልከቻለሁ፡፡
በዚህ አኳኋን ትግሌና አቤቱታዬ ቀጥሎ ከወረዳ እስከ ክፍለ ከተማ ግንባታና ፈቃድ ቁጥጥር ክፍል ድረስ ጉዳዩ ደርሶ በጽሑፍ ማስረጃ ሰንድዶት የነበረው አካሄድ፣ ዋናው ሥራ አስፈጻሚ ለፍትሐዊነት ባላቸው አመለካከት ጭምር ቦታው ድረስ ተገኝተው፣ ከእሳቸውም ጋር ከየክፍሉ የተውጣጣ ኮሚቴ ታክሎበት በተደረገው ማጣራት ችግሩ እውነትም ስለመኖሩ ተረጋግጧል፡፡ ሕገወጥ ግንባታ በቤቴ ላይ ያውም ከመጸዳጃው ጭምር መገንባቱና ይኸው ሕገወጥ ግንባታ ከሰነድ ጋር ተገናዝቦ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ባሉበት ተረጋግጦ፣ የግንባታ ተቆጣጣሪው ስህተት ታርሞ በአስቸኳይ ለግል ተበዳይ መልስ እንዲሰጣቸው በማለት ያዘዙበት አስረጂ ጽሑፍ በእጄ ይገኛል፡፡
ከዚህ ባሻገር ግንባታና ቁጥጥሩ በተረጋገጠው መሠረት ሕገወጡ ግንባታ እንዲወገድ ለወረዳ የተጻፈው ደብዳቤ ላይ ቃለ ጉባዔ ጭምር ተያይዞ በአስረጂነት የቀረበበት ሰነድ እጄ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ቀደም ሲል ከነበረው የመሬት አስተዳደር ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ባለው ምክንያት ሥራ አስኪያጁ የወረዳው ግንባታና ቁጥጥር ኃላፊዎች ከቦታቸው የተነሱ ቢሆንም፣ በተተኪ ከመጡት ሥራ አስፈጻሚ፣ የወረዳ ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ብሎም ከደንብ አስከባሪነት እስከ ምክትል ሥራ አስፈጻሚነት በዛው ወረዳ የተዋረድ ሥልጣን ያገኙ ሰዎች በማናለብኝነት፣ የሕግ የበላይነትን ወደ ጎን በመተው ውሳኔው ተፈጻሚ ሳይደረግ እንዲቆይ አድርገዋል፡፡
ወደ አዲስ አበባ አስተዳደር ቅሬታ ሰሚና ከንቲባ የሕግ አማካሪ ወደ ነበሩት ሰው ቢሮ አምርቼ ቅሬታዬን አቅርቤ ነበር፡፡ በአዲስ አበባ አስተዳደር ሥር በሚገኘው የግንባታና ቁጥጥር ባለሥልጣን በኩል ጉዳዩ ታይቶ፣ በሙያተኞች ተረጋግጦ እንዲገለጽላቸው ቢመራም የባለሥልጣኑ ጽሕፈት ቤት ግን ሙያተኛ ሳያጥረው፣ ራሱ አረጋግጦ ውሳኔ መስጠት ሲችል ከረጅም ጊዜ በኋላ እንደገና ወደ ወረዳ ግንባታና ቁጥጥር ባለሥልጣን ቢሮ በመምራት ተጣርቶ አስተያየት እንዲሰጥበት ወደ ኋላ መልሶታል፡፡
ባለጉዳይ ለማንገላታት የተደረገው አካሄድ፣ ሥልጣንና ኃላፊነቱን በአግባቡ የመንግሥትና የሕዝብ አደራን ለመወጣት እንደማይጠቀምበት የሚሳብቅበት ነው፡፡ ግንባታና ቁጥጥር ባለሥልጣንም አቤቱታዬን ለማምከን የቆረጠ መስሏል፡፡ በተገቢው መልኩ የከንቲባው የሕግ አማካሪ ጽሕፈት ቤት መልስ መስጠት እየተገባው፣ ከዚያም በመቀጠል ወደ ከንቲባው ደርሶ ውሳኔ እንዲያገኝ ማድረግ ሲገባ፣ እነሆ ያልተፈጸመው ተፈጽሟል በማለት በማህተም የተረጋገጠ የጽሑፍ ማስረጃ የተሰጠበት ሰነድም በእጄ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ይህ ሕገወጥ የቤት ግንባታ ከነመፀዳጃ ቤቱ በቤቴ ግድግዳ ላይ ተሠርቶ ባለበት እንዳለ አንድ የጽሕፈት ቤትና ኃላፊነት በጎደለው መልኩ፣ እውነታው ቁልጭ ብሎ እየታየና ግንባታው ፈጥጦ እንደቆመ ባለበት ጊዜ፣ ያልተደረገውን ተፈጽሟል ማለት ተገቢ አይሆንም፡፡
ይህ ሳያንስ የሚደርስብኝ ዛቻና ማስፈራሪያ ቢቀጥልም፣ መንግሥት ከአስጨበጠን ግንዛቤ በመነሳት አቤቱታዬን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ርስዎ ሳቀርብ፣ ክቡርነትዎ መበደሌን የሚመሰክሩ ሰነድና ተጨባጭ ማስረጃዎች እንዳሉኝ ለማመሳከርና ለመመርመር፣ ቦታው ላይም ማንኛውም መርማሪ መጥቶ ቅሬታዬንና አቱታዬን ያቀረብኩበትን ምክንያት ገለልተኛ በሆነ አካል እንዲያጣራ ቢደረግ ምንኛ ፍትሕ እንደማገኝ በማመን ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ሲነሳ ሲጣል ቆይቶ እነሆ እስካሁን ድረስ ተፈጻሚ ባለመሆኑ ለዕለት ኖሮ ማሟያንና የሥራ ጊዜን እየተሻማ ሥራ እያስፈታ መሆኑ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮም ለአካባቢው በተያዘው ዕቅድና ፕላን መሠረት ይዞታዬን ለማልማት እንዳልችልም እንቅፋት ሆኖብኛል፡፡
አቤቱታዬን በየደረጃ ላሉ ኃላፊዎች በማቅረቤ በመሬት ወራሪዎችና በአስተዳደሩ የበቀል ዕርምጃና ማስፈራሪያ እየደረሰብኝ እንደምገኝ ስገልጽ፣ አሁንም ለክቡርነትዎ ባቀረብኩት አቤቱታ ለበለጠ የበቀል ዕርምጃ በመሬት ወራሪዎችም ሆነ በአስተዳደሩ መጋለጤን በማሳሰብ ነው፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የመንግሥትን የሕግ ከለላ እየጠየኩ፣ ተገቢና ትክክለኛ ውሳኔ አግኝቼ፣ አቤቱታዬን ካቀረብኩበት ጊዜ ጀምሮ የራሴን ቦታ በራሴ ለማልማት ያቀረብኩት ጥያቄም ትኩረት ተሰጥቶት፣ በአስተዳደሩ በፈጠረው ችግርም ውሳኔ አግኝቶ ይዞታዬን የማልማት ፈቃድ ይሰጠኝ ዘንድ የድረሱልኝ ጥሪዬን በትህትና አቀርባለሁ፡፡
(ኢብራሒም መሐመድ፣ ከአዲስ አበባ)
*******************
ይዞታዬን የማልማት መብቴ ይከበርልኝ
ነዋሪነቴ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ አራዳ ክፍለ ከተማ፣ በወረዳ 1/02/03 አሜሪካን ግቢ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በቤት ቁጥር 161/1/2 ውስጥ ነው፡፡ ይህ ቤት የግል ይዞታዬና ከወላጆቼ የወረስኩት፣ አፅመ ርዕስት የሆነ የግል መኖሪያ ቤት ሲሆን፣ ይህንንም ሕጉን ተከትዬ ከወላጆቼ ሕልፈት በኋላ በውርስ ያገኘሁት ነው፡፡ ሕጉ በሚጠይቀው መልኩ ሁሉንም አሟልቼ ከሌሎች ባለይዞታዎች ጋር ተካቶልኝ ብቆይም የድርሻዬን የማልማት ጥያቄ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ሳቀርብ ቆይቼ እስካሁን ግን ምላሽ አላገኘሁም፡፡ በአስተዳደሩ በየጊዜው የኃላፊዎች መለዋወጥ መከሰቱና በጊዜው ውሳኔ ሊሰጠኝ ባለመቻሉ ምክንያት የግል ይዞታዬን ለማልማት አልቻልኩም፡፡ ገንዘብ ባንክ እንዲያስገባ በታዘዝኩት መሠረት ይህንኑ አከናውኛለሁ፡፡ እስካሁንም ገንዘቡ በባንክ እንደሚገኝ እየገለጽኩ፣ አሁንም ግን ጉዳዬ ያልተቋጨና ውሳኔ ሳላገኝ እንዲሁ እገኛለሁ፡፡ ተገቢውና የተሟላ ማስረጃ ያለኝ መሆኑን እየገለጽኩ፣ አቤቱታዬን ተመልክቶ፣ ሕጉና መርኁን ተከትሎ ለአካባቢው በተያዘው የልማት ዕቅድ መሠረት የግል ይዞታዬን ለማሟላት ይፈቀድልኝ ዘንድ የሚመለከተውን አካል በትህትና እጠይቃለሁ፡፡
(ሐጂ አደም መሐመድ ኑር፣ ከአዲስ አበባ)