Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትየኢትዮጵያን የአልማዝ ኢዮቤልዩ ተሳትፎ ያጀበው የተፋለሰውና ፈሩን የሳተው የሪዮ ኦሊምፒክ መጽሔት

የኢትዮጵያን የአልማዝ ኢዮቤልዩ ተሳትፎ ያጀበው የተፋለሰውና ፈሩን የሳተው የሪዮ ኦሊምፒክ መጽሔት

ቀን:

የመላውን ዓለም ኅብረተሰብ ካላዳንች ልዩነት የሚያስተሳስረው ታላቁ የኦሊምፒክ ጨዋታ ከአራት ዓመት ቆይታ፣ ከአንድ ኦሊምፒያድ በኋላ ዳግም በሪዮ ሊከሰት አምስት ቀኖች ብቻ ቀርተውታል፡፡ የደቡብ አሜሪካዋ ብራዚል መዲና ሪዮ ደጂኔሮ 31ኛውን ኦሊምፒያድ ለማስተናገድ እንግዶቿን እየተቀበለች ነው፡፡ ሐምሌ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. በልዩ ሥነ ሥርዓት በሚከፈተው ‹‹የ2016 የሪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች›› ከሚካፈሉት አገሮች መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያም ዝግጅቷን አጠናቅቃ ጉዟዋን ጀምራለች፡፡ 38 አትሌቶችን እንደምታሳትፍ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ይፋ አድርጓል፡፡

ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች መካፈል ከጀመረች ዘንድሮ 60ኛ ዓመት በመሆኑ የሪዮ ኦሊምፒክ ተሳትፎዋ ከአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓሏ ጋር አስተሳስራ የምታከብረው ለመጀመርያ ጊዜ በ16ኛው ኦሊምፒያድ ሜልቦርን (አውስትራሊያ) ሲካሄድ ከተካፈለችባቸው አትሌቲክስና ብስክሌት በተጨማሪ ውኃ ዋናን ጨምራ መገኘቷ ነው፡፡ በተለይ ከሜልቦርን እስከ ባርሴሎና ከተካሄዱትና በተለይ ኢትዮጵያ በተካፈለችባቸው ሰባት ኦሊምፒያዶች በተወዳደረችበትና ከአትላንታ ጀምሮ እስከ ለንደን በተካሄዱት አምስት ኦሊምፒያዶች አንድም ተወዳዳሪ ባላለፈችበት ብስክሌት ውድድር ዘንድሮ በሪዮ ብቸኛውን ብስክሌተኛ ፅጋቡ ገብረማርያን አሳትፋለች፡፡

በ31ኛው ኦሊምፒያድ የሚሳተፈውን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ልዑካን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ባሰናበቱበትም ሆነ፣ ከዚያ ቀደም ብሎ ስለኦሊምፒክ ተሳትፎ ጋዜጣዊ መግለጫ በተሰጠበት ወቅት የተሠራጨው ኦሊምፒያዲያዊ መጽሔት (በየአራት ዓመቱ የሚዘጋጅ መጽሔት) የኢትዮጵያን የ60 ዓመት ተሳትፎ አልማዝ ኢዮቤልዩ እንዲያዘክር ታስቦ መዘጋጀቱ ተወስቷል፡፡

- Advertisement -

ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ኦሊምፒክ በመጣ ቁጥር፣ ኢትዮጵያም ስትሳተፍ በአገሪቱ ስላለው ኦሊምፒካዊ እንቅስቃሴ፣ ስለተወዳዳሪዎችና ተያያዥ ጉዳዮች እየዘገበ ሲያወጣ፣ በኦሊምፒክ መንደሮችም ለሚመለከታቸው ሲያሠራጭ ኖሯል፡፡ ባለፉት ኦሊምፒያዶች/ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከታተሙት መጽሔቶች ለዘንድሮው የሪዮ ኦሊምፒክ የኢትዮጵያን ተሳትፎ እንዲያጅብ ተዘጋጅቶ የታተመው ልዩ መጽሔት፣ ወደ አገሪቱ የዘለቀው የዘመኑ የኅትመት ቴክኖሎጂ ትሩፋት ተቋዳሽ በመሆኑ ማራኪና ሳቢ በሆነ መልክ ለመታየት ችሏል፡፡ ከቀደሙት ልቋል፡፡ ይዘት ላይ ሲመጣ ግን ጥያቄ አስነስቷል፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? አሰኝቷል፡፡

በጎጆ ክሬኤቲቭ ሚዲያ የተዘጋጀው ‹‹ኦሊምፒክ – ሪዮ 2016›› የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሪዮ ኦሊምፒክ መጽሔት 91 ገጾች አሉት፡፡ በመጽሔቱ ሽፋን የመጽሔቱ ርዕስ ሆኖ የቀረበው የኦሊምፒክ ቀለበቶች የተሳሰሩበት ምስል ሲሆን፣ ርዕሱ ግን በገጽ ሁለት የመጀመርያው ዐምድ ከዝግጅት ክፍሉ ዝርዝር ራስጌ ላይ ነው የሰፈረው፡፡

መጽሔቱ በቀዳሚነት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት፣ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትርና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት መልዕክቶችን አስተናግዷል፡፡

በተከታታይም በቀረቡት መጣጥፎች ‹‹50 የግማሽ ምዕት ዓመት ተሳትፎ››፣ ኦሊምፒክና ኢትዮጵያ፣ ከሜልቦርን ጀምሮ ያለውን ታሪካዊ ጉዞ ሲመዘገብ፣ ‹‹ቆይታ›› በሚል ዐምድ ሥር ከቀረቡ ዘጠኝ ቃለ ምልልሶች ሁለቱ ለስፖርት ሚኒስተር ዴኤታውና ለብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ከመቅረባቸው ሌላ ሰባቱ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ቦርድ አባላትና ዳይሬክተር የተስተናገዱባቸው ናቸው፡፡

የቀድሞው ብስክሌተኛ ገረመው ደምቦባ ከፅጋቡ ገብረማርያም ጋር ስለተሳሰሩበት፣ ስለወርቃማዎቹ ኦሊምፒያኖች፣ ስለኮከቦቹ አባት ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ እንዲሁም ወቅታዊ የኦሊምፒክ ተግዳሮት ስለሆነው ዶፒንግ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡

‹‹የሪዮ ተስፋዎች›› በሪዮ ኦሊምፒክ የሚሳተፉ አትሌቶች ስምና የሚወዳደሩበት ዓይነት የያዙ ፎቶዎች በመጨረሻው ገጽ ተቀምጠዋል፡፡ በእንግሊዝኛ የተጻፉ ሦስት መጣጥፎችም ይገኙበታል፡፡

‹‹ኦሊምፒክ ሪዮ 2016›› ሲመዘን

የመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ፣ ማኔጂንግ ኤዲተርና ፎቶግራፈር አቶ ሻውል ታደሰ ‹‹የዋና አዘጋጁ መልዕክት›› በሚል ባሰፈሩት ጽሑፍ እንዲህ ብለዋል፡፡ ‹‹መጽሔቱ ከአገራችን የኦሊምፒክ የተሳትፎ ጅማሬ ሜልቦርን ጀምሮ እስከ 2016ቱ ሪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት ድረስ የሚዳሰስ ሆኖ ተዘጋጅቷል፡፡ . . . የተሻለ መረጃ ምንጭና የኦሊምፒክ ታሪካችን ማጣቀሻ በሚሆን መልኩ እንዲሰናዳ የቻልነውን ሁሉ አድርገናል፡፡ ይህ . . . መጽሔት በፕሮፌሽናል ስታንዳርድ እንዲዘጋጅ ጥረት አድርገናል፤›› ዋና አዘጋጁ እንዳመለከቱት መጽሔቱ ሆኖ ተገኝቷል? ዋና ዋና ነጥቦችን በማንሳት እንፈትሽው፡-

‹‹ኦሊምፒክ እና ኢትዮጵያ››

መጽሔቱ ስለ ኢትዮጵያና ኦሊምፒክ ጥምረት ከማውሳቱ በፊት የኦሊምፒክን ጥንተ ታሪክ፣ ዘመናዊ ኦሊምፒክ ከመጀመሩ እ.ኤ.አ. 1896 በፊት ስለነበሩት ጥንታዊ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች (በይፋ ከሚታወቀው ከክርስቶስ ልደት በፊት 776 ዓመታት ጀምሮ) ጥልቅ ነገሮችን እንደቀደሙት የኦሊምፒክ መጽሔቶች ከማምጣት ይልቅ ‹‹ቅድመ መነሻ›› ብሎ ያመጣው፣ በግሪክ በነበሩት ጦርነቶች ምርኮኛ የሆኑና ሞታቸውን የሚጠባበቁ በጥንቱ ኦሊምፒክ ጨዋታ ባገኙት ድል ምክንያት ነፃ መሆናቸውን የኦሊምፒክ መነሻ እንደሆነ አድርጎ ነው፡፡ ከ2,800 ዓመታት በፊት በየአራት ዓመቱ በኦገስት ወር ለአምስት ቀናት ስለተካሄዱት ጨዋታዎችና ባህላዊ መሰናዶዎች (እስከተቋረጠበት 394 ዓ.ም. ድረስ) እንደ መንደርደሪያ ቢቀርብ በርግጥ የታሪክ ማጣቀሻ ይሆን ነበር፡፡

‹‹የመጀመርያው ኦሊምፒያድ በ1896 እ.ኤ.አ. ላይ በግሪክ ከተማ አቴንስ ሲካሄድ፤ ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በቅኝ አገዛዝ ለመቆጣጠር ጦርነት አውጆ በዓድዋ መራሩን ሽንፈት የቀመሰበት ወቅት እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያወሳሉ፡፡›› በርግጥ በ1995 ዓ.ም. የታተመው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መጽሔት ይኼንን ያወሳ ሲሆን፣ የዘንድሮውም መጽሔት የጠለፈው ከርሱ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

እውነታው ግን እንዲህ አይደለም፡፡ የመጀመርያው ኦሊምፒያድ እየተካሄደ አይደለም ወራሪው የኢጣሊያ ሠራዊት ኢትዮጵያን የወረረው፡፡ ዘመናዊው ኦሊምፒክ ከመካሄዱ አንድ ወር አስቀድሞ እንጂ፡፡ ማርች 1 ቀን 1896 (የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም.) የዓድዋ ጦርነት ተካሄደ፡፡ ኤፕሪል 6 ቀን 1888 ዓ.ም. (መጋቢት 27 ቀን 1888 ዓ.ም.) የመጀመርያው ኦሊምፒያድ ተከፈተ፡፡ የመጽሔቱ ሌላው ስህተት በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ኢትዮጵያን የወረረው ‹‹ፋሺስት ጣሊያን›› ብሎ መጥቀሱ ነው፡፡ ፋሺዝምና ፓርቲው ጣሊያን ውስጥ የተፈጠሩት በ1920ዎቹ ሆኖ ኢትዮጵያን በቤኔቶ ሞሶሎኒ አማካይነት የወረረ ጊዜ (1928-1933) የተንፀባረቀ ነው፡፡

አፍሪካውያን በኦሊምፒክ እንዲሳተፉ የባሮን ፒየር ደ ኩበርቲን ፍላጎትና ርዕይ እንደነበረ አይሳትም፡፡ ከዘመናዊ ኦሊምፒክ ምሥረታ 10 ዓመት በኋላ እ.ኤ.አ. በ1906 በግሪክ በተዘጋጀው የፓን ሔሌኒክ ኦሊምፒክ ግብፃውያን ስፖርተኞች ሲሳተፉ የደቡብ አፍሪካ ሯጮችም በ1908 ኦሊምፒክ ተገኝተው ነበር፡፡ አፍሪካ የኦሊምፒክን መንፈስ እንድትረዳው የሚያስችል አህጉራዊ ውድድር የአፍሪካ ጨዋታዎች እንዲካሄድ መፈለጋቸውም አልቀረም፡፡ የመጀመርያው ኦሊምፒክ ጨዋታ በተካሄደ በ27ኛው ዓመት በኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ጉባኤ ላይ ይህንኑ አንፀባርቀዋል፡፡ በቅድሚያ ግብፅ እንድታዘጋጅ ሐሳብ ቢያቀርቡም ውድቅ ተደርጎባቸዋል፡፡ ዳግመኛው የፈረንሣይ ግዛት በነበረችው አልጀሪያም ለማከናወን ቢያስቡም አውሮፓውያኑ ወይ ፍንክች ብለዋል፡፡ አፍሪካ በአብዛኛው በቅኝ ገዢዎቹ አውሮፓውያን ሥር ስለነበረች ኦሊምፒክ መሰል ጨዋታዎች እንዲካሄድ ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ የሪዮ ኦሊምፒክ መጽሔት ግን ያቀረበው ያልተነገረ ያልተፈጸመ ታሪክ ነው፡፡ ‹‹. . . ግብፅ ኦሊምፒክን ለማስተናገድ ዝግጅቷን ብታሳውቅም አውሮፓውያን በመቃወማቸው ሳይሳካ ቀረ፡፡ . . . አልጀሪያም በተመሳሳይ ውድድር እንድታስተናግድ ሐሳብ አቅርበው በድጋሚ ሳይሆንላቸው ቀረ፡፡›› የመላው አፍሪካ ጨዋታዎችን ከኦሊምፒክ ጨዋታዎች ጋር ማዛነቅ እንዴት ነው ነገሩ?

እ.ኤ.አ. በ1924 በፓሪስ በተካሄደው 8ኛው ኦሊምፒያድ በወቅቱ የኢትዮጵያ አልጋወራሽና ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ የነበሩት ንጉሥ ተፈሪ መኰንን አገር ቤት ከተመለሱ በኋላ በቀጣዩ ኦሊምፒክ አገሪቱን ለማሳተፍ ማሰባቸው አልቀረም፡፡ በዚሁ መሠረት በአምስተርዳሙ የ1928 ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ኢትዮጵያ ብትጠይቅም ተቀባይነት አላገኘችም፡፡ መጽሔቱ ይኽንን ሒደት የዘገበው ቢሆንም ከአምስተርዳም ኦሊምፒክ በኋላ የሆነውን እንዲህ አዛብቶታል፡፡

‹‹ከ13 ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ስፖርት ኮንፌዴሬሽን ቢመሠረትም . . .  ለ8 ዓመታት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አላደረገም ነበር፤›› እዚህ ላይ የባሕረ ሐሳብ (ካሌንደር) ጥያቄ ይነሣል፡፡ እ.ኤ.አ. 1928 ላይ 13 ሲደመር ውጤቱ 1941 ይሆናል፡፡ ይህም ወደ ኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ ሲለወጥ 1933 ዓ.ም. ነበር፡፡ ወቅቱ ፋሺስት ኢጣሊያ ድል የተመታበት ነበር፡፡ ኮንፌዴሬሽኑ በዚያን ጊዜ አልተመሠረተም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስፖርት ኮንፌዴሬሽን (ኢሕስኮ) በአዋጅ የተቋቋመው ጥቅምት 1941 ዓ.ም. (ኦክቶበር 1948) ነበር፡፡

በሜልቦርን ኦሊምፒክ አበበ ቢቂላ ተወዳዳሪ ነበር?

ኢትዮጵያ ከስድሳ ዓመት በፊት በኅዳር 1949 ዓ.ም. (ኖቬምበር 1956) ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለመሳተፍ ሜልቦርን ተገኘች፡፡ በአትሌቲክስና በብስክሌትም ተወዳደረች፡፡ በአትሌቲክስ ንጉሤ ሮባ፣ በየነ አያኖ፣ ኃይሉ አበበ፣ ለገሠ በየነ፣ ማሞ ወልዴ፣ በቀለ ኃይሌ፣ ገብሬ ብርቄ፣ ባሻዬ ፈለቀ፤ በብስክሌት ገረመው ደምቦባ፣ ተሰማ አሞሳ፣ መንግሥቱ ንጉሤ፣ አበበ ማሞ፣ መስፍን ተስፋዬ፣ ፀሐዬ ባሕታ ይዛ ተገኘች ቢሉ እውነታ ይሆን ነበር፡፡

‹‹ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም›› እንዲሉ የዘንድሮው መጽሔት አዲስ ተረታዊ ‹‹ታሪክ›› አስነብቦናል፡፡ አበበ ቢቂላ የሜልቦርን ኦሊምፒክ የ100 ሜትር ተወዳዳሪ እንደነበረ ነግሮናል፡፡ እስቲ እናንብበው፡፡

‹‹በማራቶን ኢትዮጵያን በመወከል እንዲወዳደሩ የተመረጡና አስገራሚ ታሪክ ያላቸው ሁለት ኦሊምፒያኖችም የታሪክ መዛግብት ያስታውሳቸዋል፡፡ እነዚህ ሁለት ማራቶኒስቶች የአዲስ አበባው ጋሻውና ከማይጨው የተገኘው ብርሃኑ ነበሩ፡፡ ሁለቱ አትሌቶች በንጉሣዊ ሥርዓቱ ለኦሊምፒክ እንዲዘጋጁ በተሰጠ መመርያ፣ ለአገራቸው የሜዳሊያ ክብር ካስገኙ ብሔራዊ ጀግኖች ተብለው ትልቅ የክብር ሽልማት እንደሚያገኙ ቃል ተገብቶላቸው ነበር፡፡ ስለሆነም ሁለቱ ኦሊምፒያኖች ለኦሊምፒኩ ዝግጅት ሲያደርጉ በታላቅ ወኔ ነበር፡፡ ጋሻው ከደብረዘይት ናዝሬት በተጨማሪ በሰበታ የገጠር መንገዶች አያሌ ኪሎ ሜትሮችን ሲሸመጥጥ ይታይ ነበር፡፡ ብርሃኑ በበኩሉ በማይጨው መስኮች ሰፊ ርቀት እየሸፈነ ሲለው ደግሞ የአምባላጌ ተራራን ሽቅብ እየጋለበ ዝግጅቱን ያጧጡፍ ነበር፡፡ ጋሻውና ብርሃኑ ከሜልቦርን ኦሊምፒክ ተሳትፏቸው በተያያዘ ሁለት ጓደኞቻቸውን ተዋውቁ፡፡ እነሱም አበበ ቢቂላና ማሞ ወልዴ ነበሩ፡፡ አበበና ማሞ በማራቶን መወዳደር ቢኖርባቸውም በሜልቦርን ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክለው ለመሰለፍ የበቁት በ100 ሜትር ውድድር ነበር፡፡ በማራቶን የተወዳደሩት ጋሻውና ብርሃኑ 17ኛና 19ኛ ደረጃ አግኝተው በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ የመጀመርያ ተሳትፎ አመርቂ የሚባል ውጤት አገኙ፡፡››

የጋሻውና የብርሃኑ ታሪክ ከየት ነው የተገኘው? ማነውስ የጻፈው፣ ሁለቱ ‹‹አትሌቶች›› አባት የላቸውም? ለምን አልተጠቀሰም?

ለኦሊምፒኩ ልምምድ ደብረዘይትን፣ ናዝሬንና ሰበታን ያካለለው የጋሻው ሩጫና የማይጨው መስኮችንና የአምባላጌ ተራራን ሽቅብ ሲጋልብ ስለነበረው ብርሃኑ የሩጫ ገድል ከየት ተገኘ? ቢሉ ከድርሳነ ባልቴት ካልሆነ ከምን ይገኛል? የአበበ ቢቂላን ታሪክ በልቦለድ መልክ አዛብቶና አዛንቆ ከጻፈው ፖል ራምባሊ ተወስዶ ይሆን?

በአጭሩ አበበ ቢቂላና ሜልቦርን አይተዋወቁም፡፡ አበበ የኦሊምፒክ የሩጫ ሕይወቱ የተጀመረው በሮም እንጂ በሜልቦርን አልነበረም፡፡ ማሞ ወልዴ በሜልቦርን የተወዳደረው በ800፣ በ1,500 ሜትርና በ4 X 400 ሜትር ዱላ ቅብብል እንጂ በ100 ሜትር አልነበረም፡፡ የ100 ሜትር ተወዳደሪያችን ንጉሤ ሮባ ሲሆን፣ በማራቶን የሮጡት ባሻዬ ፈለቀና ገብሬ ብርቄ ነበሩ፡፡ ባሻዬ ፈለቀ 29ኛ፣ ገብሬ ብርቄ 32ኛ ሆነው ማጠናቀቃቸውን የ1956 ሜልቦርን ኦሊምፒክ ሰነድ አስረግጦ ይነግራል፡፡

በሜልቦርን 17ኛ የወጣው ኒውዚላንዳዊው አልበርት ሪቻርድስ፣ 19ኛ የወጣው አውስትራሊያዊው ጆን ሩሰል ሆነው ሳለ ‹‹ጋሻውና ብርሃኑ 17ኛና 19ኛ ደረጃ አገኙ›› በማለት በድፍረት እንዴት ተቀመጠ? በድርሳነ ባልቴት ካልሆነ፡፡

የሜልቦርን ኦሊምፒክ ማራቶንን ያሸነፈው አፍሪካዊው የአልጄሪያ ልጅ በቅኝ ገዢዋ ፈረንሣይ ስም የተወዳደረው አሊየን ሚሙን ኦካቻ ነው፡፡ መጽሔቱ የአበበ ቢቂላን የሮምና የቶኪዮ ኦሊምፒኮች ወርቃማ ድል ለማድመቅ የተጠቀመባቸው ሐረጎች ስህተትን ከመሸመት አልዳነም፡፡

የሮሙን የጳጉሜን 5 ቀን 1952 ዓ.ም. (ሴብቴምበር 10 ቀን 1960) የአበበን ድል ያጀበው ‹‹አፍሪካ ዓለምን በአትሌቲክስ ማሸነፍ የጀመረችው በዚህ ታሪካዊና ፈር ቀዳጅ የኢትዮጵያ ኦሊምፒያን ድል ነበር›› በሚል ዐረፍተ ነገር ነው፡፡ አበበ ቢቂላ የመጀመርያው ጥቁር አፍሪካዊ የኦሊምፒክ ባለወርቅ እንጂ የመጀመርያው አፍሪካዊ የኦሊምፒክ ወርቅ ተሸላሚ አይደለም፡፡

ደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ ምክንያት ከቶኪዮ 1964 ኦሊምፒክ ጀምሮ ከመታገዷ በፊት፣ በ1908 ለንደን ኦሊምፒክ በ100 ሜትር ወርቅ፣ በ1912 ስቶክሆልም በማራቶን ወርቅና ብር፣ ከ1920 አንትዌርፕ እስከ 1952 ሔልሲንኪ በአትሌቲክስና በቦክስ ወርቆችን ሰብስባለች፡፡ ግብፅም በ1912 አምስተርዳም ኦሊምፒክ በግሪኮ ሮማን ነፃ ትግልና በክብደት ማንሳት ሁለት ወርቆች ማግኘታቸውን ልብ ይሏል፡፡

አበበ በቶኪዮ ኦሊምፒክ በማራቶን ዳግማዊ ድሉን አጣጥሟል፡፡ ይህን ድሉን ለማድመቅ መጽሔቱ ‹‹እስከዛሬም ድረስ በሁለት ተከታታይ የኦሊምፒክ ውድድር በማራቶን ያሸነፈ አትሌት አልተፈጠረም›› በማለት በድፍረት ደምድሞታል፡፡ እስከ 1980 ሞስኮ ኦሊምፒክ እስከተካሄደበት ድረስ ቢሆን ወይም ዘንድሮ 1972 ዓ.ም. ቢሆን ባለመጽሔቶቹ እውነታነት ይኖራቸዋል፡፡ የዛሬ 36 ዓመት ምሥራቅ ጀርመናዊው ዋልዴማር ስፒንንክስ ሞስኮ ላይ በማራቶን ሲያሸንፍ የአበበን ታሪክ ተጋርቷል፡፡ በ1968 ዓ.ም. (1976) ሞንትሪያል ላይም አሸንፏልና፡፡

ሌላው የታሪክ ዝበት በሜክሲኮ ኦሊምፒክ ማራቶን አሸናፊው ማሞ ወልዴ ዕድሜ የተጠቀሰበት አገባብ ነው፡፡ እንዲህም አለ መጽሔቱ ‹‹በ1968 እ.ኤ.አ. በሜክሲኮ ከተማ ማሞ ወልዴ የአበበን ዱካ በመከተል በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ሲያሸንፍ በ43 ዓመቱ መሆኑ አነጋጋሪ ነበር፡፡›› ማንን ነው ያነጋገረው?  ከምንስ ተገኘ? በ1925 ዓ.ም. የተወለደው ማሞ የሜክሲኮን ድል ያጣጣመው በ36 ዓመቱ ነበር፡፡

ከስምንት ዓመት በፊት በቤጂንግ ኦሊምፒክ ‹‹በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር ውድድሮች ቀነኒሳ በቀለና ጥሩነሽ ዲባባ ሁለት ሁለት ወርቅ ሜዳሊያዎችን በመውሰድ በኦሊምፒክ ታሪክ በምሩፅ ይፍጠር የተሠራውን ክብረወሰን በመስተካከል ኢትዮጵያዊ ብቸኛ የዓለም አትሌቶች ሆኑ፤›› በማለት በዚች ፕላኔት ከኢትዮጵያውኑ ውጭ ድርብ ድል በሁለት ርቀቶች ያስመዘገበ እንደሌለ መገለጹ ያስገምታል፡፡ የኦሊምፒክ ዜና መዋዕሎችን ማየቱ ይቆይና ቢያንስ ከአራት ዓመት በፊት በለንደን ኦሊምፒክ እንግሊዛዊው የሶማሊያ ተወላጅ ሞ ፋራህ በ10ሺ እና በ5ሺ ማሸነፉ የኛን አትሌቶች አስከትሎ መግባቱ እንዴት ይዘነጋል?

በ1912ቱ የስቶክሆልም ኦሊምፒክ በሁለቱ ርቀቶች ያሸነፈው ፊንላዳዊው ጆሃን ሐንስ፣ በ1952ቱ ሔልሲንኪ ቼኮዝሎቫኪያዊው ኢሜል ዛቶፔክ፣ በ1956ቱ ሜልቦርን ላይ ቮሎዲሚር ኩትስ (ሶቪየት/ዩክሬን)፣ በ1972ቱ ሙኒክና 1976ቱ ሞንትሪያል ላይ ፊንላንዳዊ ላሲቨረን ያሸነፉት የት ሄዶ ነው?  እነ ቀነኒሳን ‹‹ብቸኛ የዓለም አትሌቶች ሆኑ›› የተባለው፡፡ መጽሔቱ ቃፊር የለውም እንዴ?

‹‹አይዘነጌዎቹ››

መጽሔቱ ‹‹ሜልርቦርን ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ አሀዱ›› [ጽሑፉ እንደተጻፈው ነው የተጻፈው] በሚል ርዕስ አይዘነጌዎቹ ብሎ በሜልቦርን የተሳተፉትን ዘርዝሯል፡፡ መጽሔቱ እርስ በርሱ እንደሚጋጭ አንዱ ማሳያ እነዚያ በቀዳሚ ገጾች የተወሱት የተረቶቹ ‹‹ጋሻውና ብርሃኑ›› እዚህ የሉም፡፡ መጽሔቱ በሙጫ ፀያፍ እያጣበቀውም ቢሆን ታሪኩን ቀጥሏል፡፡ ‹‹. . . ለአገራቸው የመጀመርያ በሆነው የኦሊምፒክ ተሳትፎ መድረክ በስታዲየሙ የተገኙት የኢትዮጵያ ልጆች እነዚህ ነበሩ፤›› ብሎ እ.ኤ.አ. በ1956 ከስድሳ ዓመት በፊት ኢትዮጵያን የወከሉ አትሌቶች እንዲህ ዘርዝሯል፡፡ ‹‹በብስክሌት ገረመው ደምቦባ፣ መስፍን ተስፋዬ፣ ፀሐዬ ባህታና መንግሥቱ ንጉሤ፤ በአትሌቲክስ፣ ማሞ ወልዴ፣ ገብሬ ብርቃይ፣ ባሻይ ፈለቀ፣ ኮንጃው በየነ፣ አየነው ባገኝ፣ በየነ ለገሰ፣ ቤኬ ኃይሌ፣ ሮባ ንጉሤና አበበ ኃይሉ››

ከነዚህ መካከል በሕይወት ያሉትና የሌሉትም ቤተ ዘመዶቻቸው ስማቸው ባግባቡ አለመጻፉን ሲያዩ ምን ይሰማቸው ይሆን? የተዘበራረቀውን የፋና ወጊ አትሌቶቻችንን ስም እስቲ እንየው፡፡ ‹‹ገብሬ ብርቃይ› የተባለው ገብሬ ብርቄ፣ ‹‹ኮንጃው በየነ›› በየነ አያኖ፣ ‹‹ሮባ ንጉሤ›› ንጉሤ ሮባ፣ ‹‹አበበ ኃይሉ›› ኃይሉ አበበ ተብሎ መጻፍ ነበረበት፡፡

የብስክሌት ሽግግር ከገረመው ደምቦባ ወደ ፅጋቡ ገብረማርያም??

  ‹‹በመሃል አራዳ ተጠራ ስማቸው

ካሳ በብስክሌት በኳስ ይድነቃቸው››

በ1920ዎቹ መገባደጃ በአዲስ አበባ ተወዳጅ ከነበሩት ስፖርቶች ሁለቱ እግር ኳስና ብስክሌት ነበሩ፡፡ ብዙ ብስክሌት ጋላቢዎች ይድነቃቸውን ጨምሮ ነበሩ፡፡ ከነዚያ መካከል ገናና የነበረው ካሳ ፈዲል ነበር፡፡ በእግር ኳሱም የመጀመርያው የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ተጨዋቾች አንዱ የነበሩት ይድነቃቸው ተሰማም ኮከብ ነበሩና ሁለቱን ኮከቦች በመንቶ ግጥም አራዳዎች ያወሷቸው ነበር፡፡

ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መካፈል ስትጀምር ከዘመኑ ኮከቦች ልቆ ይገኝ የነበረው ገረመው ደንቦባ ነበር፡፡ በሜልቦርን ኦሊምፒክ ከርሱ ጋር የተሰለፉት ከላይ ከተዘረዘሩት በተጨማሪ መጽሔቱ የረሳው ተሰማ አሞሳን ነበር፡፡

በሜልቦርን የተጀመረው የብስክሌት ተሳትፏችን ከሮም እስከ ባርሴሎና በርካታዎችን በማወዳደር ዘልቋል፡፡ በሮም እነአድማሱ መገራ፣ በቶኪዮ እነ ፍሥሐጽዮን ገብረየሱስ፣ በሜክሲኮ እነየማነ ንጉሤ፣ በሙኒክ እነተከስተ ወልዱ (ጄጋንቲ)፣ በሞንትሪያል (ሳይካፈሉ ቢመለሱም) እነዳዊት አድማሱ (የሮሙ ተወዳዳሪ የአድማሱ መግራ ልጅ)፣ በሞስኮ እነ ኃይለሚካኤል ከድር፣ በአሁን ጊዜ አሠልጣኝ የሆኑት እነ ዓይናለም ይርጉና ደጀኔ አበበ፣ በባርሴሎና እነ ኃይሉ ፋና በተወዳዳሪነታቸው ይታወሳሉ፡፡ ከባርሴሎና በኋላ በተከናወኑት አምስት ኦሊምፒያዶች በብስክሌት አንድም ተወዳዳሪ ሚኒማ አሟልቶ ባለመገኘቱ ለማካፈል አልተቻለም፡፡ ዘንድሮ ግን ፕሮፌሽናል ብስክሌተኛው ፅጋቡ ገብረማርያም በሪዮ ኦሊምፒክ ጎዳናዎች ኢትዮጵያን ወክሎ ይጋልባል፡፡

የኢትዮጵያ ብስክሌት የኦሊምፒክ ታሪክ ጉዞ ይህ ሆኖ ሳለ መጽሔቱ ‹‹የብስክሌት ሽግግር ከገረመው ደምቦባ ወደ ፅጋቡ ገብረማርያም›› በሚል ርዕስ ሁለቱን ብስክሌተኞች አስተሳስሯል፡፡ ስለሌሎቹ ለምን አልተነሳም? ከሜልቦርን ኦሊምፒክ በኋላ ኢትዮጵያ ለ60 ዓመታት አልተካፈለችም ማለት ነው? ይህን እንድንል ያስገደደን የሪዮ ኦሊምፒክ ልዑካን በብሔራዊ ቤተመንግሥት አሸኛኘት ሲደረግላቸው የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን ያደረጉት ንግግር ነው፡፡ ሚኒስትሩ እንዲህ አሉ፡- ‹‹የሪዮ ተሳትፏችን ከቀደምቶቹ የሚለየው፣ ለየት የሚያደርገው ከሜልቦርን በኋላ ተሳትፏችን ተቋርጦ የነበረው የዕርምጃና የብስክሌት ውድድር ዳግም የምንሳተፍ መሆኑ ነው፡፡››

የኢትዮጵያ ብስክሌትና ኦሊምፒክ የተፋቱት ከ24 ዓመት በፊት ከባርሴሎና በኋላ እንጂ ከ60 ዓመት በፊት አለመሆኑን ለሚኒስትሩ መረጃ የሚያቀብል አልተገኘም ይሆን? የዕርምጃ ውድድር ቢሆን ኢትዮጵያ በሜልቦርን ኦሊምፒክ አልተወዳደረችበትም፡፡ ከሙኒክ ኦሊምፒክ ወዲህ የአፍሪካ ሻምፒዮኑ ሁንዴ ጦሬ ፋና ወጊ ሆኖ በሞስኮም ከተከስተ ምትኩና ዋሚ ቢራቱ ጋር ተሰልፏል፡፡ በባርሴሎና ኦሊምፒክም ሸምሱ ሀሰን ተከትሎታል፡፡ እንደብስክሌት ሁሉ ዕርምጃውም ከባርሴሎና በኋላ ሳትሳተፍ እስከ ሪዮ ዘልቋል፡፡ ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ የምትሳተፈው በሴቶች ዕርምጃ ውድድር በአስከሌ ቲክስ አማካይነት ነው እንጂ የወንዶቹ አሁንም እንደራቀ ነው፡፡

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትሩን ያሳታቸው መልዕክታቸው የሰፈረበት የዘንድሮው ሪዮ ኦሊምፒክ መጽሔት ‹‹የብስክሌት ሽግግር ከገረመው ደምቦባ ወደ ፅጋቡ ገብረማርያም›› ብሎ ያሰፈረው መጣጥፍ ይሆንን? ‹‹ያመኑት ፈረስ…›› ሆነ እንጂ፡፡

‹‹ወርቃማዎቹ ኦሊምፒያኖች››

መጽሔቱ በተለይ ከሮም እስከ ለንደን በተከናወኑትና ኢትዮጵያ በተሳተፈችባቸው 12 ኦሊምፒያዶች 21 ወርቁን ያስገኙ አትሌቶች ከአበበ ቢቂላ እስከ ቲኪ ገላና ፎቶግራፋቸውን ካጭር መግለጫ ጋር አውጥቷል፡፡ በሚገባቸው ልክ አጥሮም ቢሆን በምልዐት ለመግለጽ ግን አልታደለም፡፡

አበበ ቢቂላ

አበበ ቢቂላ በሮምና በቶኪዮ ማራቶኑን የፈጸመበት ጊዜ እቅጩን አልተቀመጠም፡፡ በሮም 2፡15፡16.2 ተብሎ መመዝገብ ሲገባው ‹‹2፡16፡2›› መባሉ፣ በቶኪዮ 2፡12፡11፡2 ተብሎ መመዝገብ ሲገባው ‹‹2፡12፡11›› መባሉ አዛብቶታል፡፡ በሜክሲኮ ኦሊምፒክ ለሦስተኛ ድሉ ተወዳድሮ አቋርጦ መውጣቱም አልተገለጸም፡፡ ሌላው ስህተት በሁለቱ ኦሊምፒያዶች ሁለት ወርቅ ያገኘውን አበበ ‹‹ብቸኛው ኦሊምፒያን ነው›› ማለት የሞንትሪያልና የሞስኮ ኦሊምፒኮች አሸናፊ ምሥራቅ ጀርመናዊን አለማስታወስ ነው፡፡

ማሞ ወልዴ

ከኢትዮጵያውያን አትሌቶች በአጭር፣ በመካከለኛና ረዥም ርቀቶች እንዲሁም ማራቶን የተወዳደረ ከማሞ ወልዴ በቀር ማንም የለም፡፡ በሜልቦርን በ800 ሜትር፣ በ1,500 ሜትርና በ4×400 ሜትር ዱላ ቅብብል፣ በቶኪዮ በ10 ሺ ሜትር፣ በሜክሲኮ በ10 ሺ ሜትርና በማራቶን ተወዳድሯል፡፡ በኦሊምፒክ ተወዳዳሪነት ከአበበ ቢቂላ ይቀድማል፡፡ በቶኪዮ አራተኛ፣ በሜክሲኮ የብር ሜዳሊያ፣ በማራቶን ወርቅ አጥልቋል፡፡

መጽሔቱ ይህንን ታላቅ አትሌት ነው ‹‹ከአበበ ቢቂላ በኋላ የኢትዮጵያ ብቸኛ ተስፋ አንተ ብቻ ነህ ተብሎ በሜክሲኮ ኦሊምፒክ የተሳተፈው፤›› በማለት በመሰለኝና በደሳለኝ የገለጸው፡፡ ይህ አገላለጽ አበበ በሜክሲኮ እንዳልተሳተፈ አድርጐ የሚያሰማ ነው፡፡ አበበ ከማሞ ወልዴና መርዓዊ ገብሩ ጋር አብሮ 17 ኪሎ ሜትር ከሮጠ በኋላ አቋርጦ ነው የወጣው፡፡ ማሞ ወልዴ በአራተኛው የኦሊምፒክ ተሳትፎ ሙኒክ ላይ በ41 ዓመቱ የነሐስ ሜዳሊያ በማግኘት አንጋፋው የማራቶን ባለድል ሆኗል፡፡ ይህንን ገጸ ታሪክ ‹‹ታሪካዊው›› መጽሔት ከቁብ አልቆጠረውም፡፡

ቀነኒሳ በቀለ

መጽሔቱ ‹‹ቀነኒሳ በ10 ሺ ሜትር ሦስት ጊዜ፣ በ5 ሺ ሜትር አንድ ጊዜ በአጠቃላይ 4 የኦሊምፒክ የወርቅ፣ እንዲሁም በ5 ሺ ሜትር 1 የብር ሜዳሊያ ያስመዘገበ ነው፤›› ይለናል፡፡ ቀነኒሳ በአቴንስና በቤጂንግ ካገኛቸው የ10 ሺ ሜትር ሁለት ወርቆች ውጪ ሦስተኛውን ወርቅ መቼ ነው ያገኘው? ለመጨረሻ ጊዜ ከአራት ዓመት በፊት ለንደን ሮጦ ያገኘው አራተኛነትን ነበር፡፡

በወርቃማዎቹ ኦሊምፒያኖች መግለጫው ያንዳንዶቹ አትሌቶች ያለም ሻምፒዮና ውጤት ሲገለጽ፣ የሌሎች አለመግለጹ የወጥነት ችግር ተንፀባርቆበታል፡፡ ስለኦሊምፒክ ድል እየተወሳ ከሌሎቹ ተለይቶ የማሞ ወልዴ የሜክሲኮ ድሉን የሚያንፀባርቀውን ፎቶ ትቶ በሌላ ውድድር ያሸነፈበትን ፎቶ በዋናነት መለጠፍ ምነው? ያሰኛል፡፡

መጽሔቱ የአርትዖት ችግር የተደቀነበት በሰዋስውና በአገባብ ብቻ አይደለም፡፡ የኦሊምፒክ ጽንሰ ሐሳብና ስያሜዎች አኃዞች (terms) አጠቃቀም ካለመረዳት የመነጩም አሉበት፡፡ ኦሊምፒክ ከማለት ይልቅ ‹‹ኦሊምፒያድ›› (እየተቀላቀለም ቀርቧል)፣ የ2016 ሪዮ ኦሊምፒክ ወይም 13ኛው ኦሊምፒያድ መባል ሲገባው ‹‹13ኛው ኦሊምፒክ›› መባሉ ስህተት ነው፡፡ ኦሊምፒያድ የኦሊምፒክ ባሕረ ሐሳብ ቀመር ነው፡፡ ከቁጥር ጋር የሚያያዝ በየአራት ዓመቱ የሚመጣውን ጨዋታ አመልካች ነው፡፡

በአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆነ በአንዳንዶች መልዕክት ላይ የኢትዮጵያን የሜልቦርን ኦሊምፒክ ተሳትፎ ዘመንን በኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ (ካሌንደር) ሲጽፉ ‹‹የ1948 ዓ.ም. ኦሊምፒክ ተሳትፎዋ…›› እያሉ የገለጹት ስህተት ነው፡፡ እ.ኤ.አ. 1956 ወደ ኢትዮጵያ ሲቀየር ከመስከረም እስከ ታኅሣሥ 22 ከሆነ ሰባት፣ ከታኅሣሥ 23 በኋላ ከሆነ ስምንት ዓመት ይቀነሳል፡፡ በቀደሙት የኦሊምፒክ መጽሔቶችም ሆነ በሪዮው በተመሳሳይ ስምንት ዓመት በመቀነስ 1948 ዓ.ም. መደረጉ ስህተት ነው፡፡ የሜልቦርን ኦሊምፒክ የተካሄደው የመጽሔቱ አዘጋጆች ልብ አላሉትም እንጂ ‹‹ሜልቦርን የኢትዮጵያ አሀዱ›› ብለው በጻፉት መጣጥፍ አጠገብ በለጠፉት ሎጎ ላይ ጨዋታው የተካሄደው ‹‹20 Nov – 8 Dec 1956›› እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ ይህም ወደ ኢትዮጵያ ሲቀየር ኅዳር 1949 ዓ.ም. ይሆናል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ በ12 አገራት [ከተሞች መባል ነበረበት] በተካሄዱ 12 ኦሊምፒያዶች በ5 የተለያዩ ስፖርቶች ተሳትፋለች፤›› ይላል፡፡ ከአትሌቲክስ፣ ብስክሌት፣ ቦክስና ዋና፣ ሌላ አምስተኛው ስፖርት ማን ነው? ኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪኳ 60 ዓመት ሆኖ ‹‹የግማሽ ምዕተ ዓመት (50 ዓመት) ተሳትፎ›› ብሎ ማስቀመጥ ለምን አስፈለገ? ለዕይታ በሚስበው ባለቀለም መጽሔቱ ውስጥ የተካተቱት ፎቶዎች ያለመግለጫ (ካፕሽን) መውጣታቸው ፎቶዎቹን ዲዳ አድርጓቸዋል፡፡

መጽሔቱ ከፕሬዚዳንቱና ከሚኒስትሩ፣ ከኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንትና ከኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባሏ መልዕክት በስተቀር በሌሎቹ ቃለ ምልልሶች ምትክ (እነርሱ በዓመታዊ መጽሔት ለብቻ መውጣት ይችሉ ነበር) የኢትዮጵያን ኦሊምፒክ ታሪክ ፕሬዚዳንቶችና አንቀጽ ከነጓዙ፣ በ12 ኦሊምፒያዶች የተካፈሉ አትሌቶችና ያገኟቸው ውጤቶች፣ የክረምት ኦሊምፒክ ተሳትፎ ወዘተ በዚህ ኦሊምፒያዲያዊ መጽሔት ያልወጣ ምን ላይ ሊወጣ ነው?

ከአቶ ይድነቃቸው ተሰማ በኋላ ብቸኛዋ ኢትዮጵያዊት የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማይን ቃለ ምልልስ ከማድረግ ይልቅ መልዕክታቸውን ማቅረብና ማስቀመጥ የሚገባው ከፕሮቶኮል አንፃር ከብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ቀጥሎ መሆን ይገባው ነበር፡፡

የመጽሔቱ ዋና አዘጋጁ አቶ ሻውል ታደሰ በመግቢያ መልዕክታቸው እንደጻፉትና በፊርማቸው እንዳረጋገጡት መጽሔቱ ‹‹የተሻለ የመረጃ ምንጭና የኦሊምፒክ ታሪካችን ማጣቀሻ በሚሆን መልኩ በፕሮፌሽናል ስታንዳርድ እንዲዘጋጅ አድርገናል፤›› ያሉት ምኞት እንጂ ከተግባር አልዋለም፡፡ ይልቁንም መጽሔቱ የኢትዮጵያን የአልማዝ ኢዮቤልዩ የኦሊምፒክ ተሳትፎን ያጀበው በሙጫ ጸያፍ በተጣበቀ ፈሩን በሳተና በተፋለሰ መልኩ ነው፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...