Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበአዲስ አበባ ለሚገነቡ ፕሮጀክቶች የፈረንሣይ መንግሥት 75 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ሰጠ

በአዲስ አበባ ለሚገነቡ ፕሮጀክቶች የፈረንሣይ መንግሥት 75 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ሰጠ

ቀን:

የፈረንሣይ የልማት ድርጅት ለኤሌክትሪክ ኃይል ሥርጭት መቆጣጠሪያ ማዕከል (ናሽናል ሎድ ዲስፓች ሴንተር) ማስፋፊያ ፕሮጀክትና ለአዲስ አበባ የፈጣን አውቶብስ መንገድ ግንባታ 75 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ሰጠ፡፡ ሐሙስ ሐምሌ 21 ቀን 2008 ዓ.ም. የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትሩ አቶ አብዱላዚዝ መሐመድና በኢትዮጵያ የፈረንሣይ የልማት ኤጀንሲ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ሚስ አን ቻብሊን የብድር ስምምነቱን ተፈራርመዋል፡፡

የፈረንሣይ ልማት ድርጅት የሰጠው ብድር በአዲስ አበባ ለሚገነቡ ሁለት የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች እንደሚውል አቶ አብዱላዚዝ በወቅቱ ተናግረዋል፡፡ የመጀመርያውና የብድሩን ትልቅ ድርሻ የሚወስደው (40 ሚሊዮን ዩሮ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በአገር አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክ ቁጥጥርና ሥርጭት የሚያደርግበት ጣቢያ ግንባታ ነው፡፡

በእርግጥ ከአሥር ዓመት በፊት የመቆጣጠሪያ ማዕከል ግንባታ ተካሂዶ ነበር፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በመገንባት ላይ ያሉና ተገንብተው ኃይል በማመንጨት ላይ የሚገኙ ጣቢያዎች እየበዙ በመምጣታቸው፣ ማዕከሉ አቅሙን ማሳደግ አስፈላጊ እንደሆነ ታምኖበታል፡፡ አቶ አብዱላዚዝ እንደገለጹት፣ ግንባታው ሲጠናቀቅ የኤሌክትሪክ ኃይል በብቃት እንዲገባ በማድረግ የኃይል መቆራረጥንና አደጋን በመከላከል በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ያደርጋል፡፡ 

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የብሔራዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ሥርጭት መቆጣጠሪያ ማዕከሉ በአገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ማዕከል ቁጥጥር ለማድረግ፣ ለብልሽት የተዳረጉ አውታሮች በፍጥነት ጥገና እንዲያገኙ ለማድረግና ከሌሎች ሥራዎች ጋር ተዳምሮ የኃይል መቆራረጥ እንደሚያስቀር በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ አቶ አብዱላዚዝ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በቀድሞው የኃይል ሥርጭት መቆጣጠሪያ ማዕከል ግንባታ የፈረንሣይ ኩባንያ ተሳታፊ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህ ማዕከል የሚገኘው በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ገርጂ አካባቢ ነው፡፡

የብድሩ ቀሪ 35 ሚሊዮን ዩሮ ለአዲስ አበባ የቀላል አውቶብሶች የፍጥነት መንገድ ግንባታ ይውላል ተብሏል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማውን ትራንስፖርት አገልግሎት ወደ ብዙኃን ትራንስፖርት ለማሸጋገር ማቀዱን ገልጿል፡፡

በዚህ መሠረት በመጀመሪያው ዙር ከፍተኛ ሕዝብ በሚበዛበት ከዊንጌት በመሳለሚያ ጀሞ ድረስ ለፈጣን አውቶብስ ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ መንገድ ለመገንባት ታቅዷል፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት 85 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚያስፈልግ የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ያብባል አዲስ በቅርቡ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስረድተዋል፡፡ በዚህም መሠረት የፈረንሣይ የልማት ኤጀንሲ ለዚህ ፕሮጀክት 35 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ሰጥቷል፡፡

አሥራ ስድስት ኪሎ ሜትር ርዝመት ይኖረዋል ተበሎ የሚጠበቀው የአዲስ አበባ ፈጣን አውቶብስ መንገድ በከተማው ብቸኛው ነው፡፡ ከዚህ ፕሮጀክት በመቀጠል በሰባት ኮሪደሮች የፈጣን አውቶብስ መንገድ ግንባታ እንደሚካሄድ አቶ ያብባል ተናግረዋል፡፡

‹‹የከተማው የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ ወደ ብዙኃን ትራንስፖርት መሸጋገር ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ የመሠረተ ልማት ግንባታና የአውቶብስ አቅርቦት ላይ እየሠራን እንገኛለን፤›› በማለት አቶ ያብባል ገልጸዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...