በኢትዮጵያ በኩል ለሚገነባው መስመር 110 ሚሊዮን ዶላር ብድር ተለቋል
በኢትዮጵያ በኩል እስከ ኬንያ ድንበር ከ400 ኪሎ ሜትር በላይ የሚረዝምና ኢትዮጵያን ከኬንያ ጋር በኃይል የሚያገናኝ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ሊጀመር ዝግጅቶች መጠናቀቃቸው ተሰማ፡፡ በሁለቱም አቅጣጫ 2,000 ሜጋ ዋት ማስተላለፍ የሚችሉና 500 ኪሎ ቮልት የሚሸከሙ የኤሌክትሪክ መስመሮች እንደሚዘረጉ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የሪፖርተር ምንጮች እንዳረጋገጡት፣ ከኢትዮጵያ በኩል በወላይታ ሶዶ ከተማ አድርጎ ኮንሶን አቋርጦ ወደ ኬንያ ድንበር እስኪደርስ ድረስ በጠቅላላው 434 ኪሎ ሜትር የሚረዝሙ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን ለመገንባት የተዋዋለው፣ ቻይና ኤሌክትሪክ ፓወር፣ ኢኪውፕመንት ኤንድ ቴክኖሎጂ (ሲኢቲ) የተባለውና የስቴት ግሪድ ኮርፖሬሽን እህት ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያው በተያዘው ወር የሲቪል ሥራ ግንባታ መጀመሩን ምንጮች ገልጸው፣ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ገንብቶ እንዲያስረክብ የሚጠበቀውን ፕሮጀክት ከዚያ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ መዘጋጀቱን ይናገራሉ፡፡
በሁለት ምዕራፎች ከሚተከሉት የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች አንደኛው ከወላይታ ሶዶ እስከ ኮንሶ ድረስ 200 ኪሎ ሜትር የሚዘረጉ ሲሆን፣ ከኮንሶ እስከ ኬንያ ድንበር ማለትም ሱስዋ ተብሎ እስከሚጠራው አካበቢ ድረስ 234 ኪሎ ሜትር የሚዘረጉ መስመሮችን ግንባታ ለማካሄድ ዝግጅት ተደርጓል፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ በሰጠው ከ110 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብድር ግንባታው የሚካሄደው የኃይል ማስተላለፊያ ፕሮጀክት ከኢትዮጵያ ኬንያ፣ እንዲሁም ከኬንያ ኢትዮጵያ በሁለቱም አቅጣጫ 2,000 ሜጋ ዋት ኃይል ማስተላለፍ የሚችሉ ከፍተኛ የኃይል ተሸካሚ መስመሮች የሚዘረጉበት ነው፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት በሁለቱ መንግሥታት ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ በሁለት ዙር 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለኬንያ ለማቅረብ የሚያስችላትን ግንባታ ማካሄድ ልትጀምር ተዘጋጅታለች ሲሉ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ከአራት ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ስቴት ግሪድ ኮርፖሬሽን ከ1.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት፣ ኃይል የሚያስተላልፉ መስመሮችንና ሁለት ትልልቅ ሰብስቴሽኖችን ለመገንባት መዋዋሉ ይታወሳል፡፡ በዚህም መሠረት ኩባንያው እያንዳንዳቸው 500 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኃይል ተሸካሚ መስመሮችን በሆለታና በዴዴሳ ከገነባቸው ሁለት ትልልቅ ሰብስቴሽኖች ጋር ለማገናኘት የሚያስችሉ ግንባታዎች አጠናቆ፣ የጣልያኑ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ የሚያካሂደውን የህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን እየተጠባበቀ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡
ይኸው ስቴት ግሪድ ኩባንያ የአዲስ አበባን የቀላል ባቡር መስመር የኃይል አቅርቦት ሥርዓት ከመዘርጋቱም በተጨማሪ፣ በአሁኑ ወቅት በስምንት ዋና ዋና የአገሪቱ ከተሞች የኃይል ማሠራጫ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ የሚገኝ ግዙፍ የቻይና ኩባንያ ነው፡፡