Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበሕገወጥ መሬት ወረራ ተሳትፈዋል የተባሉ በሊዝ አዋጁ የተቀመጠው ቅጣት ሊጣልባቸው ነው

በሕገወጥ መሬት ወረራ ተሳትፈዋል የተባሉ በሊዝ አዋጁ የተቀመጠው ቅጣት ሊጣልባቸው ነው

ቀን:

ከግንቦት 1997 ዓ.ም. ጀምሮ የሚመለከተው የመንግሥት ተቋም ሳይፈቅድ መሬት በመውረር ግንባታ አካሂደዋል የተባሉ በሕግ ተጠያቂ እንደሚደረጉ፣ ግንባታቸውም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚፈርስ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

በቅርቡ በተለይ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ወረገኑና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ቀርሳ ኮንቱማ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕገወጥ ግንባታዎችን ለማፍረስ ባደረገው ዘመቻ፣ ችግር ፈጥረዋል ተብለው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦች ላይ ሕጉ ተፈጻሚ እንደሚደረግ ተመልክቷል፡፡

የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 በአንቀጽ 35 ንዑስ አንቀጽ 1(ለ) ላይ እንደተደነገገው፣ አዋጁን ለማስፈጸም የወጡ ደንቦችን ወይም መመርያዎችን በመተላለፍ የከተማ ቦታ አጥሮ የያዘ፣ ግንባታ ያካሄደና ወይም አዋሳኝ ቦታ ከይዞታው ጋር የቀላቀለ ከሰባት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡ በገንዘብም ከ40 ሺሕ እስከ 200 ሺሕ ብር ድረስ ቅጣት እንደሚጣል በሊዝ አዋጁ ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን አዋጁ ከወጣ አራት ዓመታት ቢቆጠርም፣ ቅጣቱ ተፈጻሚ ሳይሆን ቆይቷል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ሕገወጥ በተባሉ አካላት ላይ ሕጉ ተፈጻሚ እንደሚደረግ ተመልክቷል፡፡

የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታምራት አስናቀ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ደንብ በማስከበር ሒደት እንቅፋት ከመሆን በተጨማሪ ሁከት የፈጠሩ 38 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ይገኛሉ፡፡ በእነዚህ ላይ ምርመራ በማድረግ ጥፋተኛ ሆነው በተገኙት ላይ ሕጉን ተፈጻሚ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም አቶ ታምራት ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ወረገኑ አካባቢ በ50 ሔክታር መሬት ላይ መንግሥት ሳይፈቅድ ግንባታ አከናውነዋል በተባሉ አካላት ላይ በቅርቡ ዕርምጃ መወሰዱ ይታወቃል፡፡ አቶ ታምራት እንዳሉት፣ አብዛኞቹ ሕገወጥ ግንባታዎች በሚቀጥለው ዓመት ከኅዳር ወር ጀምሮ እንደሚፈርሱ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትንና ደላሎችን ጭምር ለይተናል፤›› በማለት መንግሥት ጉዳዩን አምርሮ እንደያዘው አቶ ታምራት ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው መጠነ ሰፊ ዘመቻ የተካሄደበትና የሰው ሕይወት ጭምር የጠፋበት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ቀርሳ ኮንቱማ አካባቢ ነው፡፡ ሰኔ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. የወረዳ አንድ ሥራ አስፈጻሚና ሁለት የአዲስ አበባ የፖሊስ መኮንኖች ሕይወት ካለፈ በኋላ የከተማው አስተዳደር ሕገወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተዋል ያላቸውን በቁጥጥር ሥር በማዋል በርካታ ግንባታዎችን አፍርሷል፡፡

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍፁም ካህሳይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሕግ በማስከበር ሒደት እንቅፋት የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ እየተካሄደ ባለው ማጣራት ተጠያቂ የሚሆኑት እየተለዩ ነው ብለዋል፡፡

‹‹ሙሉ በሙሉ ሕገወጥ ግንባታዎችን አፍርሰናል፡፡ ግንባታዎቹ ከፈረሱ በኋላ 293 ሔክታር መሬት ወደ መሬት ባንክ ገቢ ሆኗል፤›› በማለት አቶ ፍጹም ገልጸው፣ ‹‹ይህ መሬት ለተለያዩ የኢንዱስትሪ ግንባታዎች ይውላል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በዘመቻ ከተገኘው 293 ሔክታር መሬት ውስጥ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት በ70 ሚሊዮን ዩሮ ለሚገነባው ዘመናዊ ቄራ 20 ሔክታር መሬት መሰጠቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ1988 እስከ 1997 ዓ.ም. የተገነቡ ሕገወጥ ይዞታዎችን ሕጋዊ ለማድረግ የሚያስችል መመርያ አውጥቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከንቲባ ድሪባ ኩማ የከተማውን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፣ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ዋዜማና በኋላ በተለይ ከ1996 ዓ.ም. እስከ 1998 ዓ.ም. ድረስ ሕገወጥ የመሬት ወረራ ተካሂዶ 5,700 አባላት ያሏቸው ማኅበራት ሕገወጥ ግንባታ አካሂደዋል ብለዋል፡፡ እነዚህ ሕገወጥ ግንባታዎች የከተማውን ፕላን ሳያቃውሱ ሕጋዊ እንዲሆኑ መወሰኑን ተናግረዋል፡፡

ይህ ውሳኔ የተላለፈው በርካታ ሰዎች የተሳተፉበትና ግንባታውም ሰፊ በመሆኑና እንዲሁም በፍርድ ቤት ተይዞ ለዓመታት ሲንከባለል የቆየ ጉዳይ ስለነበረ ነው ብለው፣ ከዚህ በተጨማሪም ጉዳዩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እያስነሳ ስለነበር ከተማው ታሪካዊ ውሳኔ በማሳለፉ ጉዳዩን ቋጭቶታል ሲሉም አክለዋል፡፡  

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማው 20 ሺሕ ሕገወጥ ግንባታዎች መኖራቸውን ቢገልጽም፣ የአስተዳደሩ ምንጮች ግን ግንባታዎቹ ከ100 ሺሕ በላይ እንደሚሆኑ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በተለይ አስተዳደሩ በወቅቶች እየከፋፈለ ሕገወጦችን ሕጋዊ ማድረግና ገሚሱን ደግሞ ሕገወጥ በማለት በዘመቻ እየፈረሰ መሆኑ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ የአድሎአዊነት ጥያቄ እያስነሳ ነው፡፡ ምክንያቱም በተመሳሳይ መንገድ የሊዝ አዋጅ ከሚፈቅደው ውጪ ተገቢው የመንግሥት አካል ሳይፈቅድ የተያዘ ሁለት ቦታዎች ቢኖሩ አንዱን ሕጋዊ፣ ሌላውን ደግሞ ሕገወጥ በማለት መፈረጅ ሕጋዊ መሠረት እንደሌለው የሚከራከሩ በርካታ ናቸው፡፡

ነገር ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕገወጦችን ሕጋዊ የሚያደርግበት ምክንያት ተንሰራፍቶ የቆየውን ሕገወጥነት መቋጫ ለማበጀት እንጂ ሕገወጥነት ለማበረታታት እንዳልሆነ፣ ከዚህ በኋላ ግን ሕገወጥ ወረራ በፍፁም ተቀባይነት የሌለው ድርጊት መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶ በመግለጽ ላይ ይገኛል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...