Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልለኢትዮጵያ የጥበብ ሥራዎች ‹‹ልዩ ዝክር›› የተደረገበት የሞሮኮው ፊልም ፌስቲቫል

ለኢትዮጵያ የጥበብ ሥራዎች ‹‹ልዩ ዝክር›› የተደረገበት የሞሮኮው ፊልም ፌስቲቫል

ቀን:

በዮናስ ዓብይ ከሁሪብጋ (ሞሮኮ)

በሞሮኮ የንግድ ከተማ ከሆነችው ካዛብላንካ በደቡባዊ ምሥራቅ በምትገኘው የሁሪብጋ ከተማ በተዘጋጀው 19ኛው የአፍሪካ ፊልም ፌስቲቫል ለኢትዮጵያ የሥነ ጥበብና ፊልም ነክ ሥራዎች ልዩ ዝክር ተደርጓል፡፡ በያሬድ ዘለቀ ተዘጋጅቶ ከወራት በፊት ለዕይታ የቀረበው ‹‹ላምብ›› የተሰኘው ፊልም በፌስቲቫሉ ልዩ ክብር የሚሰጠውን ሽልማት አሸናፊ ሆኗል፡፡

ከሐምሌ 8 እስከ ሐምሌ 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ለስምንት ቀናት የተዘጋጀው 19ኛ የአፍሪካ ፊልም ፌስቲቫል በሁሪብጋ (The 19th African Film Festival in Khouribga) ከ20 በላይ የአፍሪካ አገሮች የሥነ ጥበብ፣ ሥነ ጽሑፍና የፊልም ሥራዎች ቀርበዋል፡፡ ዓውደ ርዕይ፣ የፓናል ውይይቶችና ልምድ ልውውጦችም ተካሔደው ነበር፡፡ የኢትዮጵያዊውን ላምብ ጨምሮ የ15 አገሮች ፊልሞች ለዕይታና ለውድድር ቀርበው፣ ፌስቲቫሉ በደማቅ ዝግጅት ቅዳሜ ሐምሌ 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ተጠናቋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ፌስቲቫሉ የአፍሪካ አገሮች የሥነ ጽሑፍ፣ የጥበብ ሥራዎቻቸውንና ባህላቸውን በጋራ ለማሳደግና በመቀራረብ የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት የጋራ መድረክ መፍጠር የሚል ዓላማ እንዳነገበ አዘጋጆቹ ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ ዓላማ የዘንድሮው ፌስቲቫል በዋናነት ለኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍና የጥበብ ዝግጅቶች የተለየ ቦታ መስጠታቸውን አዘጋጆቹ የገለጹ ሲሆን፣ ታዋቂዋ የፎቶግራፍ ባለሙያ፣ የሥራ ፈጠራና ዘርፈ ብዙ ሙያ ባለቤት የሆነችው አይዳ ሙሉነህ፣ ሥራዎቿን በዝግጅቱ ላይ አቅርባ አድናቆት አግኝታለች፡፡ በተጨማሪም በዓውደ ርዕዩ የኤፍሬም ሰለሞን ረቂቅ የሥዕል ሥራና ባለፉት ዓመታት የቀረቡ የኢትዮጵያውያን የሥዕል ሥራዎች ለዕይታ ቀርበው ነበር፡፡

በተለይም እ.ኤ.አ. በ2009 ያሳተመችውና ዓለም አቀፍ ዝና ያስገኘላትን ኢትዮጵያ ትናንትና ነገ (Ethiopia past – forward) የሚለው የፎቶ ስብስቧ በፓናል ውይይቱ ላይ ቀርቧል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያን ያለፉትንና የቅርብ ጊዜያት ታሪክና ባህል በዝግጅቱ ላይ ማቅረብ ችላለች፡፡

የፎቶ ስብስቦቹ ለቀለም አመራረጥና ለአነሳስ ጥበብ የምትሰጣቸውን ልዩ ትኩረት፣ በአጠቃላይ ሥራዋን አብራርታለች፡፡

‹‹ፎቶ አንድ የጥበብ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን፣ የማኅበረሰብን፣ የአገርንና የአካባቢን እንዲሁም ባህልንና እምነትን በምስል ለመግለጽና በማስረጃነት የማቆያ መሣሪያ›› አድርጋ እንደምትመለከተው አይዳ አስረድታለች፡፡

ነገር ግን ማንኛውንም ፎቶ የእውነታ፣ የትክክለኝነት ማረጋገጫ ብቻ ሳይሆን እውነታን በማዛባት በተቃራኒው እንደሚቀርብም ገልጻለች፡፡

ከፎቶግራፍ ሥራዎቿ በተጨማሪ የግል ታሪኳን፣ ልምዷንና እንዲሁም ስኬቷን በፓናል ውይይቱ ላይ ተናግራለች፡፡

ትውልዷ በኢትዮጵያ ይሁን እንጂ አብዛኛውን የሕይወት ዘመኗን በውጭ ያሳለፈችው አይዳ በየመን፣ እንግሊዝ፣ በቆጵሮስ፣ በካናዳና በአሜሪካ ተዘዋውራ ኖራለች፡፡ በዋሺንግተን ፖስት በፎቶግራፈርነት የሠራችው አይዳ፣ በ2000 ዓ.ም. ወደ ትውልድ አገሯ በመመለስ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ትንቀሳቀሳለች፡፡ ደስታ የተባለ ድርጅትም ከፍታ የተለያዩ ወጣቶችን በፎቶና ፊልም ጥበብ በማሠልጠን ላይ ትገኛለች፡፡ በፊልም ፌስቲቫሉ ዝግጅት ላይም ለአገሯና ለአህጉሪቱ ባደረገችው የጥበብ ሥራዎችና ተፅዕኖ ፈጣሪነቷ የክብር ሽልማት ተበርክቶላታል፡፡

በዚሁ የሞሮኮው ዝግጅት ላይ ለውድድር ከቀረቡት የ15 አገሮች የፊልም ሥራዎች አንዱ የሆነው የያሬድ ዘለቀ ፊልም (ላምብ) የዓመቱ ምርጥ ፊልም በሚለው ዘርፍ አሸናፊ ባይሆንም፣ በዓመታዊው ዝግጅት ላይ ከፍተኛ ክብር እንደሚሰጠው የተነገረለትን ‘ኦስማን ሶሞበኔ’ ኦዋርድ አሸናፊ ሆኗል፡፡

ሽልማቱን በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የላምብ ፊልም ዋና ተዋናዩ የ14 ዓመቱ ታዳጊ ረድኤት አማረ (በትወና ስሙ ኤፍሬም) እና ሌላዋ ተዋናይ ራሄል ተሾመ ተቀብለዋል፡፡

የዚሁ ፊልም ተዋናይ የሆነችው ወጣት ቅድስት ስዩም (ፅዮንን ሆና የተወነችው) ምርጥ የሴት ተዋናይ ተብላ በሁለተኛ ደረጃ ተመርጣለች፡፡

‹‹ለመጀመሪያ ጊዜ ተዋናይ ሆኜ በሠራሁበት በላምብ ፊልም መሸለሜ ያልጠበኩት ነበር›› በማለት ቅድስት ለሪፖርተር ገልጻለች፡፡ ‹‹ገና ወጣት ነኝ፡፡ ይህ ሽልማት ደግሞ ቀድሞ ከነበረኝ ተስፋ በላይ ሌላ ተስፋ ሰጥቶኛል›› ስትልም ታክላለች፡፡ በቅርቡ ወደ ስዊዘርላንድ ተጉዛ የሁለተኛ ፊልሟን ቀረጻ ሠርታ መመለሷን የምትገልጸው ቅድስት፣ በሞሮኮው ዝግጅት ላምብ ያገኘው ሽልማት የበለጠ ጠንክራ እንድትሠራ እንደሚያደርጋት ትገልጻለች፡፡

በሁብሪጋው የተካሔደውን ዝግጅት አስመልክቶ እንዴት እንዳገኙ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ተሳታፊዎች፣ ዝግጅቱ ጥሩ ልምድ የተቀሰመበት መድረክ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

‹‹ሞሮኳውያን አዘጋጆች በጥበብ ግንኙነት መፍጠራቸው ትልቅና መልካም አጋጣሚ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ከእነሱ ሰፊ ነገር መማር እንችላለን፡፡ በተለይ በቱሪዝምና በባህል ብዙ ርቀት ተጉዘዋል፡፡ ባህላዊውንም ሆነ ዘመናዊውን ይዘው በዚህ ዝግጅት ላይ መቅረባቸው ብዙ ነገሮችን እንድንማር አስችሎናል›› በማለት አይዳ ለሪፖርተር ገልጻለች፡፡

‹‹ዝግጅቱ ለእኛ መልካም አጋጣሚዎች የፈጠረና እራሳችን ከዓለም አቀፍ ጥበብና የጥበብ ባለሙያዎች ጋር እንድንተሳሰር እያደረግን ነው›› ያለችው ደግሞ ራሄል ወይም በላምብ ላይ የአዜብን ገፀ ባህሪ ወክላ የተወነችው አርቲስት ነች፡፡ እንዲሁም በዝግጅቱ ላይ የክብር እንግዳ የነበሩትና ለኢትዮጵያ ጥበብ የተበረከተውን የክብር ሽልማት የተቀበሉት በራባት የኢትዮጵያ አምባሳደር የሺ ታምራት ‹‹ዝግጅቱ የኢትዮጵያን ባህልና፣ ታሪክን ገጽታ በትክክል ለማንፀባረቅ የተመቻቸ መድረክ ነበር›› በማለት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አዘጋጆቹም በዘንድሮው ፌስቲቫል ለኢትዮጵያ ትኩረት የተሰጠበትን ምክንያት ሲያስረዱ፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጥልቅ ባህል፣ የብዙ ዓመታት ታሪክና የተለያዩ እምነቶች የሚገኙባት አገር በመሆኗ የጥበብ ሥራዎቿን ለመዘከር ታስቦ ነው ብለዋል፡፡

የጥበብ ሥራን ለማሳደግ የኢትዮጵያ የጥበብ ባለሙያዎችን ከሞሮኮ አቻዎቸው ጋር በጋራ እንዲሠሩና ልምዶቻቸውን እንዲለዋወጡ ማድረግ አንዱ ዓላማቸው እንደሆነ አዘጋጆቹ ገልጸዋል፡፡

ዝግጅቱን በዋና ስፖንሰርነት ድጋፍ ያደረገው በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቁ የማዳበሪያና ፎስፌት አምራችና አቅራቢ በሆነው የኦሲፒ ግሩፕ ሥር ያለው የኦሲፒ ፋውንዴሽን ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...