Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልክረምትን በየፈርጁ

ክረምትን በየፈርጁ

ቀን:

ጠዋት የሥራ መግቢያ ሰዓት ስለተቃረበ የእግረኞችና የተሽከርካሪዎችም ቁጥር ጨምሯል፡፡ አራት ኪሎ ያለው አስፋልት ግራና ቀኝ የቆሙት ታዳጊዎች ሎሚ ቀለም መለዮ ለብሰው እግረኞችና ተሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር ይሞክራሉ፡፡ እግረኞች በእግረኛ ማቋረጫ መንገድ እንዲያቋርጡ ይናገራሉ፡፡ መኪኖች ለእግረኞቹ ቅድሚያ እንዲሰጡ በእጃቸው ምልክት ያሳያሉ፡፡ የትራፊክ ፍሰቱን ፈር ለማስያዝ በአራት ኪሎ ጎዳና ከቆሙት በጎ ፍቃደኛ ትራፊኮች የ16 ዓመቷ እታፈራሁ አዳሙ አንዷ ነች፡፡

ታዳጊዋ የምትኖረው አራት ኪሎ አካባቢ ሲሆን፣ በአፄ ናኦድ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ ከሳምንት በፊት ከጓደኞቿ ጋር መንገድ ላይ ሳለች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መስጠት ለሚፈልጉ ታዳጊዎች የወጣ ማስታወቂያ ታያለች፡፡ የመኪና አደጋ የብዙዎችን ሕይወት እየቀጠፈ በመሆኑ ባለን አቅም አንድ ነገር ማድረግ አለብን ብለው በጎ ፍቃደኛ ትራፊክ ለመሆን ከጓደኞቿ ጋር ተመዘገቡ፡፡ ሥልጠና ከወሰዱ በኋላም ወደ ሥራ ገቡ፡፡

እታፈራሁና ጓደኞቿ ጠዋት ከ1 ሰዓት እስከ 4 ሰዓት ከሰዓት ከ10 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት ይሠራሉ፡፡ እግረኞችና አሽከርካሪዎች የትራፊክ ደንብ እንዲከተሉ ለማድረግ ሲሞክሩ ሕግጋቱን የሚያከብሩ እንዳሉ ሁሉ ከታዳጊዎቹ ጋር እሰጣ ገባ የሚይዙም አይጠፉም፡፡ ‹‹የትራፊክ ሥራ በመሥራቴ አንድ ሕይወት እንኳን ባተርፍ ቀላል አይደለም፤›› የምትለው ታዳጊዋ፣ ለወደፊት ትራፊክ መሆን እንደምትፈልግ ትናገራለች፡፡ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱን የምትሰጠው መደበኛ ትምህርቷን እንስከምትጀምር ቢሆንም በክረምት የእረፍት ጊዜዋ ማኅበረሰቡን በማገልገሏ ደስተኛ ናት፡፡

እንደሷው በበጎ ፈቃደኝነት የክረምት ትራፊክ የሆኑ 3,000 ወጣቶች በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የወጣቶች ተሳትፎ ንቅናቄ አስተባባሪ አቶ የኋላእሸት ሰይድ እንደሚናገረው፣ ወጣቶቹ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ባለባቸው 25 አደባባዮችና 30 የመንገደኛ ማቋረጫዎች ተሰማርተዋል፡፡

ክረምትን በተለያየ መንገድ የሚያሳልፉ ታዳጊዎችና ወጣቶች ያሉ ሲሆን፣ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት መሰማራት ለሚፈልጉ ቢሮው አማራጮች አቅርቧል፡፡ ከትራፊክነት በተጨማሪ የወቅቱ አሳሳቢ የጤና ችግር ስለሆነው አተት ማስተማር፣ ችግኝ መትከል፣ ደም መለገስ፣ የማኅበረሰብ ፖሊስ መሆንና ማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት ተካተዋል፡፡ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ ከተጀመረ 14 ዓመታት ተቆጥሯል፡፡ በየዓመቱም በሺዎች የሚቆጠሩ ታዳጊዎች አገልግሎቱን ይሰጣሉ፡፡

አቶ የኋላእሸት እንደሚለው፣ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ወጣቶች በማኅበረሰቡ ዘንድ አንገብጋቢ የሆኑ እንደ ትራፊክ አደጋና የአተት በሽታ ለመከላከል አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ያስችላል፡፡ ‹‹በክረምት ማኅበረሰቡን ከማገልገላቸው ጎን ለጎን ኃላፊነትም ይማሩበታል፡፡ ደም ልገሳና ችግኝ ተከላ የመሳሰሉ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶችን ከክረምት ባለፈ በበጋም እንዲገፉበት እናደርጋለን፤›› ይላል፡፡

ሰኔ ደርሶ ትምህርት ቤቶች ሲዘጉ ሦስት ወር ክረምቱን በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከሚሰጡ ውጭ ማጠናከሪያ ትምህርት የሚማሩ፣ ተሰጥኦዋቸውን ለማዳበር የሚሞክሩ፣ ከከተማ ከተማ የሚዘዋወሩና በሌላም መልኩ የሚያሳልፉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ክረምትን ሥራ ላይ በመሰማራት ገንዘብ ለማግኘትና ልምድ ለመቅሰም የሚጠቀሙበትም ጥቂት አይደሉም፡፡ በሊስትሮነት፣ በታክሲ ረዳትነት፣ ጋራዥ ቤት በመካኒክነት የሚሠሩ እንዲሁም በተለያዩ ድርጅቶች ኢንተርን በመሆን የሚያገለግሉ ወጣቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የእነዚህ ወጣቶች ክረምት በቀጣዩ ዓመት የሚማሩበትን ደብተርና ሌሎችም መገልገያ ቁሳቁሶች ለማሟላት በሚደረግ ሩጫ የተሞላ ሲሆን ይስተዋላል፡፡

በክረምት በዕለት ከዕለት ሕይወትና በሥራ ጠቀሜታ ያላቸው ነገሮችን መማር የሚመርጡ ደግሞ የመንጃ ፍቃድ፣ የኮምፒውተር፣ የማርሻል አርት (ራስን መከላከል) እና ቋንቋ ትምህርት ይወስዳሉ፡፡ አንዳንዶች በክረምት እረፍት ከማድረግ የዘለለ ፍላጎት አይኖራቸውም፡፡ የክረምት ክንውኖች በአንድ ሰው ፍላጎት፣ ተሰጥኦ፣ የገንዘብ አቅምና የሚፈለገው ነገር ባለው አቅርቦት መጠን ሊወሰኑ ይችላሉ፡፡

 ለ14 ዓመቷ ቅድስት ሲሳይ ክረምት ተሰጥኦዋን የምታዳብርበት ነው፡፡ በአቢሲኒያ የሥነ ጥበብና ሞዴሊንግ ትምህርት ቤት ቴአትር ትማራለች፡፡ ቅድስት ጸሐፌ ተውኔትና ተዋናይት መሆን ትፈልጋለች፡፡ ከመደበኛ ትምህርት ውጪ ያለውን ጊዜዋን የምትሰጠውም ለዚሁ ነው፡፡ ኮከበ ጽባህ የምትማረው ቅድስት አብዛኛውን ክረምት የምታሳልፈው ቴአትር በመጻፍ ነው፡፡ የአማርኛ መምህራኖቿ እንዲገመግሙላትም ትሰጣለች፡፡ ዘንድሮ ደግሞ በቴአትር ባለሙያዎች ለመታገዝ ወደ ትምህርት ቤት አምርታለች፡፡ ‹‹ለወደፊት ደራሲና ተዋናይት ለመሆን ከአሁኑ መዘጋጀት አለብኝ፡፡ ትምህርቱ የቴአትር ጽሑፍ፣ ዝግጅትና ትወናን ያካተተ ስለሆነ ይጠቅመኛል፤›› ትላለች፡፡

ተሰጥኦዋን ለማዳበር በምትወስደው ትምህርት ቤተሰቦቿ እንደሚያበረታቷትና በትምህርት ቤቱ ከሷ ጋር ተመሳሳይ ዝንባሌ ካላቸው ታዳጊዎች ጋር መገናኘቷ እንዳስደሰታት ትናገራለች፡፡ ባነጋገርናት ወቅት እሷና የክፍል ጓደኞቿ አጭር ኮሚዲ ተውኔት ጽፈውና አዘጋጅተው በክፍል ውስጥ ለማሳየት እየተሰናዱ ነበር፡፡ ከመምህራኖቻቸው በሚሰጣቸው ገንቢ ሂስ ብዙ እንደምትማርም ተስፋ ታደርጋለች፡፡

በትምህርት ቤቱ ሥዕል፣ ሙዚቃ፣ ባህላዊና ዘመናዊ ውዝዋዜ፣ ሞዴሊንግ፣ ባህላዊና ዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት የሚማሩ ታዳጊዎች ቁጥር ክረምት ላይ እንደሚጨምር የትምህርት ቤቱ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ገነት ከበደ ትናገራለች፡፡ ለክረምት ትምህርት ቤቱ ስለሚጠብ ሌላ ቦታ ይከራያሉ፡፡ ሥልጠና የሚሰጠውም ከአምስት ዓመት ጀምሮ ላሉ ነው፡፡ ትምህርት ቤቱን በጎበኘንበት ወቅት የየዘርፉ ተማሪዎች በየዕድሜያቸው ተከፋፍለው እንደሚማሩ አስተውለናል፡፡ የሥዕል ተማሪዎች ቁጥር የሚያመዝን ሲሆን፣ ንድፈ ሐሳብና ተግባራዊውን ትምህርት ይወስዳሉ፡፡ የፒያኖና ጊታር  የውዝዋዜ ተማሪዎችም የክረምቱ ብርድ ሳይበግራቸው በየክፍላቸው ትምህርቱን ተያይዘውታል፡፡

ወ/ሮ ገነት እንደምትለው፣ ከተማሪዎቹ ወላጆች መካከል የልጆቻቸውን ዝንባሌና ችሎታ ተገንዝበው እንዲያዳብሩ እንዲሁም ልጆቻቸው መዋያ ከሚያጡ ብለው የሚያስተምሩም አሉ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ክረምት የሚሰጡ የሙያ ትምህርቶች በተለያየ ሙያ መሰማራት ለሚፈልጉ ታዳጊዎች አጋዥ መሆናቸው እየታወቀ ቢመጣም፣ አሁንም የብዙ ቤተሰቦች አመለካከት እንዳልተስተካከለ ትናገራለች፡፡

‹‹አንዳንድ ቤተሰቦች ልጆቻውን ለማስተማር መስዕዋትነት ይከፍላሉ፡፡ ልጆቹም ተሰጥኦዋቸውን አውቀው ለማዳበር ይሞክራሉ፡፡ ከቀለም ትምህርት በተጨማሪ በሙያ ትምህርቶች መግፋት እንደሚቻል እየታወቀ መምጣቱ የተማሪዎችን ቁጥር ጨምሮታል፤›› ትላለች፡፡ ትምህርት ቤቱ በየክረምቱ መጨረሻ ተማሪዎች የሠሯቸውን የሚያሳዩበት ዐውደ ርዕይ በማዘጋጀት ያበረታታቸዋል፡፡

በሌላ በኩል ክረምት የሙያ ትምህርት መማር የሚፈልጉ ብዙዎች ቢሆኑም ገንዘብና በአቅራቢያ ትምህርት ቤት ማጣት እንቅፋት ይሆናሉ፡፡ ይህ ችግር ቢቀረፍ የሙያ ትምህርት ፍላጎት ያላቸው ሁሉ ማግኘት እንደሚችሉ ትገልጻለች፡፡

በክረምት ትምህርት ቤቶች ሳያስፈልጓቸው በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የሚሳተፉ ወጣቶችን በየሠፈሩ ማየትም የተለመደ ነው፡፡ የታዳጊዎች ብይ፣ ቃጤ፣ ቴዘርቦልና ገመድ ዝላይ የሚደራውም በክረምት ነው፡፡ በየሠፈሩ ባገኙት ሜዳና አስፋልት ላይም ኳስ የሚጫወቱ ወጣቶች ብዙ ናቸው፡፡ ወጣቶችን አሰባስበው የሚያሠለጥኑ ቀድሞ በክለቦች የነበሩ ታዋቂ ኳስ ተጨዋቾችም ይገኙበታል፡፡ ስፖርታዊ ክንውኖችን በሰመር ካምፕ ለዓመታት ካካሄዱ መካከል የኮች ካርሎስ ሰመር ካምፕ ይጠቀሳል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ግንባር ቀደም ከሆኑ ሰመር ካምፖች አንዱ ሲሆን፣ የተመሠረተው በካርሎስ ቶርንተን ነው፡፡ ካምፑ ዘንድሮ 11ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ቀድሞ በኤንኤፍኤል ኳስ ይጫወት የነበረው ካርሎስ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ የመሠረተው ካምፕ፣ ዘንድሮ 150 ወጣቶች በቅርጫት ኳስ ይሠለጥኑበታል፡፡

ካርሎስ ‹‹ሰመር ካምፑን የጀመርኩት አሜሪካ ውጥስ የነበረኝን ተሞክሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ማስተላለፍ ስለምፈልግ ነው፤›› ሲል ይገልጻል፡፡ በካምፑ ክረምት ላይ ሥልጠና ከወሰዱ ወጣቶች ፕሮፌሽናል የቅርጫት ኳስ ተጨዋቾች የሆኑ እንዳሉም ይናገራል፡፡ እሱ እንደሚለው፣ በክረምት ባላቸው ትርፍ ጊዜ ተመሳሳይ ካምፖችን የሚቀላቀሉ ወጣቶች ቁጥር ጨምሯል፡፡ ጽንሰ ሐሳቡም እየተለመደ መጥቷል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ልዩ ልዩ ክንውኖች የሚካሄዱባቸው ቦታዎችም እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ የሱ ሰመር ካምፖች ሲኤምሲ፣ ወሎ ሠፈርና ሻላ ፓርክ ይገኛሉ፡፡

ሰሚት አካባቢ የሚኖረው የ13 ዓመቱ አክሊሉ መርሻ ክረምትን የሚያሳልፈው ስኬት በማድረግ፣ ፑል በመጫወት፣ ሞተርና ሳይክል በመንዳት ነው፡፡ በአካባቢያቸው ለሳይክል መንጃ የሚሆን ቦታ መዘጋጀቱ ክረምትን በጥሩ ሁኔታ እንዲያሳልፍ አስችሎታል፡፡ በአካባቢያቸው ለእግር ኳስ መጫወቻ የሚሆን ሜዳ ቢኖርም የክረምቱ ጭቃ አላላውስ ስላላቸው አይጠቀሙበትም፡፡ አክሊሉ ክረምትን እየተዝናና ማሳለፍ እንደሚፈልግ ይናገራል፡፡

ከሱ የተለየ ሐሳብ ያላት ሊያ አብርሃም የመጀመርያ ዓመት የአካውንቲንግ ተማሪ ስትሆን፣ ክረምትን በአንድ መሥሪያ ቤት ኢንተርን ሆና እያሳለፈች ነው፡፡ በመሥሪያ ቤቱ ኦዲት ስለማድረግ እየተማረች እንደምትገኝና ለሚቀጥለው ዓመት ትምህርቷና ለወደፊት ሥራዋ እንደምትጠቀምበት ትናገራለች፡፡ ባለፉት ዓመታት ክረምት ላይ ማጠናከሪያ ትምህርት ትወስድ ነበር፡፡

‹‹ኢንተርን የሆንኩት ለሁለት ሳምንት ቢሆንም ብዙ ነገር እየተማርኩ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት ማጠናከሪያ ትምህርት ስማርም በሚቀጥለው ዓመት እጠቀምበት ነበር፤›› ትላለች ሊያ፡፡ ማጠናከርያ ትምህርት እንድትወስድ የሚገፏፏት ቤተሰቦቿ እንደሆኑም ትናገራለች፡፡

ወ/ሮ መንበረ መስፍን የአምስት ልጆች እናት ናቸው፡፡ ልጆቻቸው ክረምትን በሚፈልጉት መንገድ እንዲያሳልፉ ቢፈቅዱም አንዳንዴ ጣልቃ ይገባሉ፡፡ ‹‹ብሔራዊ ፈተና በሚፈተኑበት ዓመት ክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት እንዲማሩ አድርጌያለሁ፡፡ ከዛ ውጪ ባሉት ዓመታት መዝናኛም ይሁን ትምህርት ሰጪ ነገር አድርገዋል፤›› ይላሉ፡፡ ከልጆቻቸው መካከል ሁለቱ ክረምት ላይ መርካቶ በሚገኝ የቤተሰብ ሱቅ እንዲሠሩ አድርገውም ነበር፡፡ ይኽም ኃላፊነት እንደሚያስተምራቸው ያምናሉ፡፡

ከልጆቻቸው መካከል በክረምት ከከተማ ውጪ ያሉ ዘመዶች ጋር መቆየት የሚፈልጉም ከራርመው ይመጣሉ፡፡ ቀደም ባሉ ጊዜያት ክረምት ላይ በበጎ ፍቃደኝነት ገጠር ሄዶ የማስተማር ነገር እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን ‹‹የፊደል ሠራዊት›› በደርግ ደግሞ ‹‹መሠረተ ትምህርት›› የተባለው የመማር ማስተማር እንቅስቃሴ ተጠቃሽ ነው፡፡ ክረምት ማገባደጃ፣ ላይ ‹‹ቡሔ ካለፈ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት›› እየተባለ የሚጠበቀው የቡሔ በዓል የብዙዎች የክረምት ትውስታ መሆኑንም ወይዘሮዋ ይናገራሉ፡፡

አቶ ኖላዊ ተስፋሁን ክረምት ልጆች ተሰጥኦዋቸውን የሚያዳብር ትምህርት የሚወስዱበት ወቅት ቢሆን መልካም ነው ይላል፡፡ ፎቶ አንሺ ሲሆን፣ ሁለት ልጆቹ በማያ ትምህርት ቤት ውስጥ የፎቶግራፍ ትምህርት እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ ‹‹በትምህርት ቤቱ የተለያዩ ኮርሶች እንደ አማራጭ ሲቀርቡ ልጆቼ የመረጡት ፎቶ ነበር ‹እኔን በማየት የሙያው ፍቅር አድሮባቸው ሊሆን ይችላል፤›› ይላል፡፡ ልጆቹ የተማሩትን ዘወትር ይከታተላል፡፡ በቀሪ ሕይወታቸው እንደሚጠቀሙበትም ያምናል፡፡

ተመሳሳይ ትምህርት ቤቶች መበራከታቸው ለታዳጊዎች ጥሩ መሆኑን ይናገራል፡፡ ኮርሶቹ ለቀለም ትምህርት አጋዥ እንደሆኑና ከዕድሜ እኩዮቻቸው ጋር ልምድ እንዲለዋወጡ ዕድል እንደሚከፍቱም ያክላል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...