Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊያገገመ መሬት

ያገገመ መሬት

ቀን:

ከአዲስ አበባ 628 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ነው፡፡ ክልሉ የአምናውን ድርቅ መጥፎ አሻራ ለማጥፋት እየሠራ መሆኑን ይገልጻል፡፡ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ኅብረተሰብ በአብዛኛው አርብቶ አደር ነው፡፡ የማኅበረሰቡ 20 በመቶ በከተማ 80 በመቶ ደግሞ በገጠር ይኖራል፡፡ አርብቶ አደሩ የእንስሳት ግጦሽና ውኃ ፍለጋ ረዥም ርቀት ይጓዛሉ፡፡

በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር አማካይነት በልማቱ ወደኋላ ለቀሩ ክልሎች የተለየ ድጋፍ ከሚሰጣቸው ክልሎችም አንዱ ነው፡፡ በክልሉና በፌዴራል መንግሥት የተወሰኑትን አርብቶ አደሮች በመንደር በማሰባሰብ በከፊል አርሶ አደር እንዲሆኑና ኑሯቸውን በተረጋጋ መንገድ እንዲመሩ ለማድረግ ተሠርቷል፡፡ በዚህ መልክ ሙሉ በሙሉ ወደ ግብርናው የገቡ ቢኖሩም ድርቁ አካባቢው ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ ከባድ በመሆኑ የታሰበውን ያህል ምርት ማግኘት እንዳልቻሉ ይናገራሉ፡፡

በክልሉ ቱሉ ጉሌት ወረዳ ጀሬሌ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ኢብራሒም መሐመድ ባለፈው ዓመት ስንዴ፣ በቆሎና ማሽላ ዘርተው የነበረ ቢሆንም ከሁሉም መሰበሰብ የቻሉት 40 ኩንታል የማይሞላ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ አቶ ኢብራሒም ጥሩ ዝናብ ባለበት ወቅት በዓመት ሁለት ጊዜ እንደሚዘሩና እንደሚሰበሰቡ በመግለጽ ጥሩ የዝናብ ሥርጭት በታየበት በዘንድሮው ክረምት አምና ያጡትን ለማካካስ ጭምር የዘሩትን ስንዴ እያሳጨዱ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በምትኩ ክረምቱ ጠንክሮ ሳይገባ፣ ማሽላ ስንዴና በቆሎ ለመዝራት በጠቅላላው 50 ሰዓት ለማረስ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ይገልጻሉ፡፡

ወይዘሮ ሮውዳ ሐሰን የአምስት ልጆች እናት ነች፡፡ በጂሪሌ ቀበሌ ነዋሪ ስትሆን ከአርብቶ አደርነት ወደ አርሶ አደርነት ከመጣች ጥቂት ዓመታት አስቆጥራለች፡፡ የአምናው ድርቅ በእርሻ ሥራዋ ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ ስትገልጽ ‹‹ለዘንድሮ የሚሆን ዘር እንኳን አላስቀረልኝም›› ትላለች፡፡ 25 ሄክታር ላይ የዘራችው ስንዴ ሊለማላት አልቻለም፡፡ እዛው ማሳው ላይ ነው የቀረባት፡፡ ዘንድሮ ግን ምርጥ ዘር ተሰጥቷት ሁለት ትራክተሮችን በማስገባት  በ25 ሄክታር መሬቷ ላይ እያረሰች መሆኑን ትገልጻለች፡፡

በድርቅ በከፍተኛ ሁኔታ ከተጎዱ ክልሎች የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ውስጥ የሚገኘው ሲቲ ዞን አንዱ ነው፡፡ የክልሉ መንግሥት ድርቁ ያደረሰውን ጉዳት ለመቋቋምና ምናልባት ተመሳሳይ ነገር ቢከሰት በሚል የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሠራ እንደሆነ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱላሂ ዋሂ ሙሐመድ ይገልጻሉ፡፡ በደረሰው ድርቅ ዞኑ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ይናገራሉ፡፡ በዚህ ዞን 2000 ሄክታር በማዘጋጀት ሁለት ሺሕ አባወራ ከፊል አርብቶ አደሮችን ወደ አርሶ አደር ለማምጣት እየተሠራ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ የአምናው ድርቅ ሁሉን ነገር ያሳጣቸውን 400 የሚሆኑ አርብቶ አደሮችን እንዲሰባሰቡ በማድረግ ከሞት የተረፉ እንስሶቻቸውን ይዘው ከፊል አርሶ አደር እንዲሁኑ አስችሏል፡፡ ይህ ሁለት ሺሕ ሄክታር በመስኖ የሚለማ ነው፡፡ ከፍተኛ የአካባቢ ጥበቃም ይደረግለታል፡፡ ንፁህ የመጠጥ ውኃ ማቅረብ የሚያስችል ፕሮጀክትም እየተተገበረ ነው፡፡ ከብቶቻቸው ላለቁባቸውም ከክልሉ በተፈቀደ በጀት ለእያንዳንዱ አርብቶ አደር አምስት ሴትና አንድ ወንድ ፍየል ተሰጥቷል፡፡

ከድሬዳዋ ዘጠና ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሲቲ ዞን ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ውስጥ ከሚገኙ 11 ዞኖች ውስጥ አንዷ ነች፡፡ በዞኑ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እየሆኑ መሆኑን ቦታው ላይ ተገኝቶ መመልከት ይቻላል፡፡ አንዳንድ ችግሮችም ይስተዋላሉ፡፡ ለምሳሌ የመስኖ ውኃ ከጥልቅ ጉድጓድ የሚወጣ ሲሆን፣ ይህም ግን በተወሰነ መልኩ ችግር ሆኗል፡፡ በዞኑ የመንደር ማሰባሰብ 100 ሺሕ አባወራዎችን የሚይዝ መኖሪያ መንደር በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡

በዚህ መንደር ከተሰባሰቡት ከፊል አርሶ አደሮች በንግድ ሥራ የተሰማራው አቶ ሙሐመድ ሐሰን አንዱ ነው፡፡ አርብቶ አደር ነበር፡፡ 90 ፍየሎች 11 ከብቶች ነበሩት፡፡ ከአምናው ድርቅ የተረፉለት 13 ፍየል እና 1 ከብት ብቻ እንደሆነ በሐዘን ይገልጻል፡፡ በአሁኑ ወቅት የክልሉ መንግሥት ባዘጋጀው የሰፈራ ፕሮግራም መኖሪያ አግኝቷል፡፡ ከድርቁ የተረፉት እንስሳቶቹ ማገገሚያ ገብተዋል፡፡ አንድ ሄክታር የእርሻ መሬት ተሰጥቶታል፡፡ እሱን ለማልማትም እየተዘጋጀ መሆኑን ነው፡፡ ከመኖሪያ ቤቱ ግማሹን ከፍሎ ሱቅ በመክፈት ንግዱንም ለመጀመር ደፋ ቀና እያለ ነው፡፡ ሱዑዳ ሐሰንም ሌላኛዋ ሰፋሪ ነች፡፡ አርብቶ አደር ነበረች፡፡ የነበሯትን እንስሶች ሙሉ በሙሉ በማጣቷ ወደዚህ ሰፈራ ጣቢያ ልትመጣ ችላለች፡፡ ለመቋቋሚያ ይሆናት ዘንድ አምስት ሴት ፍየሎች እና አንድ ወንድ ፍየል ተሰጥቷታል፡፡ አሁንም መሻሻል ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ይሰማታል፡፡

በሌላ በኩል በድጋፍ መልክ የሚሰጡ 40 ሺሕ ፍየሎችን ለመግዛት በዝግጅት ላይ መሆኑ በክልሉ መንግሥት ተገልጿል፡፡ በአካባቢው ስንዘዋወር በበቆሎ ማሳዎች ላይ በቆሎ በማሽን ሲፈለፈል ተመልክተናል፡፡ በአንድ የበቆሎ መፈልፈያ ማሽን ላይ ከአምስት እስከ አሥር የሚሆኑ ሠራተኞች ይገኛሉ፡፡

በአጠቃላይ በክልሉ የውኃ ሥራዎች ምን እንደሚመስል የገለጹልን አቶ ሐሰን አደን ሐሰን የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ናቸው፡፡ ‹‹በክሉሉ የውኃ ጉዳይ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ በአብዛኛው አርብቶ አደር እንደመሆኑ መጠን እንደየአካባቢው የሚለያዩ የጥልቅ ጉድጓድ፣ የከርሰ ምድር፣ ውኃ እንደዚሁም የክረምትንም በማጠራቀም ሥራዎች እየተሠሩ ነው›› ይላሉ፡፡ በዘንድሮው ዓመትም 760 የሚሆኑ በብርካኖ (ውኃ ማቆር) ደረጃ እያንዳንዳቸው ለ500 አባወራ መጠጥና ለከብቶቻቸው ተሠርቶ መጠናቀቁን ይናገራሉ፡፡ ወጪያቸውም ለእያንዳንዱ 550 ሺሕ ብር መሆኑ ተገልጿል፡፡

ሌላው አንድ ሚሊዮን ሜትር ኩብ የሚይዝ በአፈርዳም (ውኃ ማቆር) ሲስተም እየተሠራ ያለና የክልሉን የውኃ አቅርቦት በመጠኑም ቢሆን ከፍ የሚያደረገው ሥራ ነው፡፡ በክልሉ የዚህ ዓይነት በጠቅላላ 104 የሚገነቡ ሲሆን አንዱ 3.4 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞለት እየተሠራ እንደሆነ ከአቶ ሐሰን መረዳት ተችሏል፡፡ ሌላው በሲቲ ዞን በመንደር ማሰባሰብ ላሉት የመስኖ እርሻ አገልግሎት እንዲሰጥ ጉድጓድ ተቆፍሮ ለሁለት ሺሕ ሄክታር ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

የበሬድ ወረዳ ከቀብሪህ በያህ ዞን 25 ክሎ ሜትር ወደ ውስጥ ገባ ብሎ ይገኛል፡፡ የወረዳው ሊቀመንበር አቶ አብዱራዛቅ አብዱ በወረዳው 250 ሄክታር ከእንስሳትና ከሰው ንክኪ ነፃ የሆነ መሬት ለማዘጋጀት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለጊዜው የደረሰው ግን 150 ሄክታር ብቻ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ቀሪውን በሚቀጥሉት ወራት በማዘጋጀት ለቀጣዩ ዓመት ዝግጁ እንደሚሆን በመግለጽ፤ በክልሉ በኤሊኒኖ ተፅዕኖ በእንስሳት ላይ የደረሰውን ጉዳት ግን ለመቀነስ መቻሉን ያስረዳሉ፡፡ ለወደፊቱም በክልሉ እንደዚህ ዓይነት 100 የሚሆኑ ነፃ መሬቶችን ለማዘጋጀት እንደታሰበም ጠቀመዋል፡፡ ክልሉ ከአምናው ድርቅ እያገገመ  ቢሆንም አሁን ደግሞ በናሊና በከፍተኛ ዝናብ የሚመጣ ጎርፍ እንደሌላው የአገሪቱ ክፍል እዚህም እርሻዎች ላይ ጉዳት አድርሶ እንደነበር መሆኑን ለማየት ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንትና የክልሉ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሱሁአድ አህመድ ፋራህ በክልሉ ስለደረሰው ጉዳትና አሁን በአጠቃላይ ድርቅን ለመቋቋም ምን እየተሠራ እንደሆነ ከሪፖርተር ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ‹‹የአምናው ድርቅ ትልቅ ጉዳት አድርሶብን ነው ያለፈው እንደዚሁም ትልቅ ትምህርት ሰጥቶናል፡፡ የተጎዱትን ከማቋቋም ጀምሮ ችግሩን በዘለቄታዊ ለመፍታት የጀመራቸውን የውኃውን፣ የመንደር ማሰባሰቡን፣ እንደዚሁም የተፈጥሮ ሀብቱን መንከባከብ አጠናክረን እየሠራን ነው›› በማለት ዋናው ለዘለቄታው መፍትሔ የሚሆነው በየጊዜው ውኃና ግጦሽ ፍለጋ የሚንከራተተውን አብዛኛው አርብቶ አደር በመንደር በማሰባሰብና ከፊል አርሶ አደር እንዲሆን ማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ሌላው በክልሉ ያሉ የውኃ ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ መዘግየታቸውን ምክንያቱ ደግሞ በአብዛኛው የኤሌክትሪክ ኃይል ችግር በመሆኑ ይህንን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር በማድረግ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል 3.6 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ሲኖረው የሕዝቡ ቁጥር ደግሞ 6.2 ሚሊዮን ይደርሳል፡፡ አኗኗሩም 80 በመቶ በገጠር 20 በመቶ በከተማ ነው፡፡ አብዛኛው አርብቶ አደር ነው፡፡ ክልሉ በ11 ዞንና በ91 ወረዳዎች እንዲሁም 1224 ቀበሌዎች የተከፋፈለ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...