የአመራር ብቃት ማሳያ ከሆኑ ተጠቃሽ ነጥቦች መካከል ዋነኞቹ የትምህርትና የልምድ ዝግጅት፣ የሥነ ልቦና ጥንካሬ፣ ድፍረት፣ ሀቀኝነት፣ ተነሳሽነት፣ ሠርቶ የማሠራት ችሎታና ኃላፊነትን በአግባቡ የመወጣት አርዓያነት ናቸው፡፡ አመራር ማለት ማዘዝና ማሠራት ሳይሆን በምሳሌነት የሚጠቀስ ውጤታማ ተግባር በስኬት እንዲከናወን ግንባር ቀደም መሆን ማለት ነው፡፡ በመንግሥታዊ ተቋማት ውስጥም ሆነ በግል ድርጅቶች ስኬትን ማስመዝገብ የሚችሉ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ብቃት ያለው አመራር የሚሰጡ ብቻ ናቸው፡፡ በአነስተኛ ደረጃ ያለ ተቋምን ከመምራት ጀምሮ አገርን እስከ መምራት ድረስ ባለው መዋቅር ከፍተኛ የሆነ የአመራር ብቃት ያላቸው ሰዎች ስኬት በስኬት ሲሆኑ፣ ይህ ክህሎት የጎደላቸው ግን ሁሌም የውድቀት ተምሳሌቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ዓይነቶቹ በተለይ በብዙ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ ሠርተው ማሠራት ስለማይችሉ ተቋማትን እያሽመደመዱ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ከፍተኛ ሀብት የፈሰሰባቸው ትልልቅ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ይካሄዳሉ፡፡ ከእነዚህ በርካታ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ውስጥ ምን ያህሉ ናቸው በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ የሚጠናቀቁት? ምን ያህሉስ ናቸው ጥራታቸውና ደረጃቸው በሚፈለገው መጠን የሚገኘው? የአገሪቱን የፋይናንስና የግዥ ሕጎች ተከትለው የሚከናወኑ ፕሮጀክቶችስ ምን ያህል ናቸው? ብዙ ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ በመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች ልዩ ክትትልና ቁጥጥር የሚደረግባቸው ፕሮጀክቶች በጥንቃቄ በጊዜያቸው ተገንብተው ለሚፈለጉበት ዓላማ ሲውሉ፣ እምብዛም ትኩረት የማይሰጣቸውና ክትትል የማይደረግባቸው ደግሞ ከመጓተታቸውም በላይ የአገር አንጡራ ሀብት ሲያባክኑ ይታያሉ፡፡ ኃላፊነት በማይሰማቸው ሹማምንትና አልጠግብ ባይ በሆኑ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ወድቀው የሙስና መጫወቻ ይሆናሉ፡፡ በተለይ ብቃት የሌላቸው አመራሮች የሚመሩዋቸው ከሆኑ ደግሞ ተስፋ ያስቆርጣሉ፡፡
ከፍተኛ ክትትልና ቁጥጥር ከሚደረግባቸው ውጪ በጠንካራና በሀቀኛ አመራሮች የሚመሩ ፕሮጀክቶችን ወይም ተቋማትን ብንመለከት፣ በግልጽ የሚታይ ውጤታማነትና ስኬት ያስመዘግባሉ፡፡ ስማቸውም በአርዓያነት ይነሳል፡፡ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ምንም እንኳ ልዩ ክትትልና ድጋፍ የሚደረግለት ፕሮጀክት ቢሆንም፣ በጠንካራ አመራር እጅ ስለሚገኝ ቀንና ሌሊት እየተሠራ ከፍተኛ ውጤት እያሳየ ነው፡፡ በቅርቡ በሐዋሳ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ ተገንብቶ የተጠናቀቀው የኢንዱስትሪ ፓርክ ሌላው የብቁ አመራር ማሳያ አብነት ነው፡፡ ብዙ ባይወራላቸውም ሌሎች ተመሳሳይ ስኬቶች አሉ፡፡ ሁለ ነገራቸውን ለአገራቸው ዕድገትና ልማት የሰጡ ዜጎች በሚሰጡዋቸው ተምሳሌታዊ አመራሮች በጉልህ የተመዘገቡ ስኬቶች አሉ፡፡ በተቃራኒው ግን የተለያዩ ምክንያቶችን እየደረደሩ የረባ ሥራ ሳያከናውኑ በአገርና በሕዝብ ላይ የሚቀልዱ ሞልተዋል፡፡ ቢኖሩም የማይጠቅሙ ባይኖሩም የማያጎድሉ ለምን እንደሚሾሙ ያስተዛዝባል፡፡
በየትኛውም አገር መንግሥት የሕዝብን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች እንዲያስተዳድር በሕዝብ የሚሾም አካል ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ መንግሥት የሕዝብ ኃላፊነት ስላለበት አሠራሩ ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት ነው፡፡ በመሆኑም የአገርን ፀጥታ ማስከበር፣ የሕዝቡን ማኅበራዊ ዋስትና ማረጋገጥ፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በብቃት መምራት፣ ለአካባቢ ጥበቃ ልዩ ትኩረት ማድረግ፣ ሕግ ማስከበር፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማስጠበቅ፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ማድረግ፣ ብልሹ አሠራሮችን ማስወገድ፣ ወዘተ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ እነዚህን ጠቃሚ ተግባራት ለማከናወን ደግሞ አመራሩ ብቃት ያለው፣ ለአገሩ የሚያስብ፣ ከወገንተኝነት የፀዳ፣ ዴሞክራትና ደፋር ሊሆን ይገባዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ በቁርጠኞች የተሞላ መንግሥት የሕዝብን ፍላጎት ከማርካት በተጨማሪ፣ ዘለቄታዊ ሰላምና ብልፅግና ለማምጣት እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ብቁ ይሆናል፡፡
በአገራችን በተጨባጭ የሚታየው ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው፡፡ በበርካታ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ ከላይ እስከ ታች ባሉ መዋቅሮች ውስጥ ያሉ አመራሮች ብዙዎቹ ችግር አለባቸው፡፡ የመጀመሪያው በትምህርትና በልምድ ያላቸው ዝግጅት የሚያስመካ አይደለም፡፡ ያላቸው ተነሳሽነት ደካማ ነው፡፡ መፈክር ከማስተጋባት የዘለለ ድፍረት የላቸውም፡፡ ይልቁንም ብዙዎቹ በአድርባይነትና በአስመሳይነት የተተበተቡ በመሆናቸው፣ ትዕዛዝ እንደ ወረደ ከመቀበል ውጪ የመሞገት ብቃት የላቸውም፡፡ ተጠራጣሪና ፈሪ በመሆናቸው በዙሪያቸው ያሉ ጠቃሚ ባለሙያዎችን ለመጠቀም ይሠጋሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በየቦታው በመልካም አስተዳደር ዕጦት የሚጮሁ ዜጎች ድምፅ በጉልህ ይሰማል፡፡ አንድን ጉዳይ በቶሎ ፈጽሞ ዜጎችን ከማገልገል ይልቅ፣ የተለያዩ ጉዳዮችን የያዙ ዶሴዎችን መከመር የተለመደ ሆኗል፡፡ እንኳን በአርዓያነት ሠርቶ ለማሠራት ከበታቾቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት የተበላሸ ነው፡፡ ተቋማቱን የቅራኔና የእልህ መወጫ መድረክ እያደረጓቸው ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ብልሹ አሠራሮች በዝተዋል፡፡ የተሰጣቸውን በጀት በአግባቡ የማይጠቀሙ፣ በሕጉ መሠረት ሒሳብ የማያወራርዱና ሕገወጥ ግዥዎችን የሚፈጽሙ አገሪቱን በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ብሮችን እያሳጧት ነው፡፡ በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር ያወጣው ሪፖርት፣ በአስተዳደሩ የተለያዩ ቢሮዎች በ11 ወራት ውስጥ 17 ሚሊዮን ብር በሕገወጥ መንገድ ወጪ ተደርጓል ይላል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሕገወጥ አሠራሮች በየቦታው መስፋፋት የቻሉት በአመራሮች ብቃት ማጣት፣ ግድ የለሽነትና ተጠያቂነት መጥፋት ነው፡፡
ከእንዲህ ዓይነቱ አሳዛኝ ተግባር በተጨማሪ በሕዝቡ ላይ የሚፈጸሙ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች አሉ፡፡ ገዥው ፓርቲም ሆነ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት እነዚህ ችግሮች መኖራቸውን አምነው ለማስተካከል ቃል ቢገቡም አልተቻለም፡፡ ሕዝቡ በመልካም አስተዳደር ችግር፣ በፍትሕ መዛባትና በሙስና ምክንያት ከመጠን በላይ መጎዳቱ በጥናቶች እየተረጋገጠ፣ ችግሮቹ ፈንድተው ለግጭቶች መቀስቀስ ምክንያት መሆናቸው በግልጽ እየታየ፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የመፍትሔ ሐሳቦች እየተጠቆሙ፣ ወዘተ ዝምታ ሰፍኗል፡፡ በጊዜያዊ ዘመቻ መንግሥታዊ ተቋማትን ከችግሮች ለማፅዳት በዝቅተኛና በመካከለኛ አመራሮች ላይ ዕርምጃ መወሰዱ ቢሰማም አጥጋቢ አይደለም፡፡ ከአንዱ ቦታ በብልሹ አሠራር የተነሳ ሹም ሌላ ቦታ ይሾማል ወይም አማካሪ የሚባል አስገራሚ ማዕረግ እንደ ካባ ይደረብለታል፡፡ አገሪቱ የወላድ መሀን ትመስል ለአገራቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ በትምህርት፣ በልምድ፣ በአመራር ችሎታና በመሳሰሉት የዳበሩ ዜጎች ይገፋሉ፡፡ የፖለቲካ ወገንተኝነት ትልቁ መለኪያ ሆኖ ሠርተው ማሠራት የሚችሉ ችሎታ በሌላቸው ይጋረዳሉ፡፡ በአንዳንድ ቦታዎችማ የቤተ ዘመድ ጉባዔ ይመስል የተደራጁ ዘመዳሞች ተቋማትን ይቆጣጠራሉ፡፡ የጥቅም ግጭት ሊያስነሱ በሚችሉ ቦታዎች ሳይቀር ዘመዳሞች ተሰባስበው ተቋማትን ያሽመደምዳሉ፡፡ አገሪቱ ግን ሰው አላጣችም፡፡
አገርን በአግባቡ ማስተዳደር የሚቻለው ብቃት ያላቸው ዜጎች ለሚመጥኑት ኃላፊነት ሲሰየሙ ነው፡፡ ለአገራቸው ቀናዒ የሆኑና ሁለገብ ችሎታ ያላቸውን ዜጎች በተፈላጊው የኃላፊነት ቦታ መሾም ጥቅሙ ለአገር ነው፡፡ የአመራር ክህሎት ያላቸው እኩልነትን ያሰፍናሉ፡፡ ተጠያቂነት እንዲኖር ያመቻቻሉ፡፡ ሙስናን በፅናት ይታገላሉ፡፡ የሚተኩዋቸውን በብቃት ያዘጋጃሉ፡፡ ለሚያከናውኑት እያንዳንዱ ተግባር ኃላፊነት ስለሚወስዱ ደፋሮች ናቸው፡፡ ለአድርባይነትና ለአስመሳይነት ፊት አይሰጡም፡፡ ለሕዝብ እርካታ ስለሚጨነቁ የሚቆጥቡት አይኖራቸውም፡፡ ከዘመኑ ቴክኖሎጂና አስተሳሰብ ጋር እኩል ስለሚራመዱ ለወጣቱ ትውልድ ልዩ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ የሚመሩዋቸው ተቋማት በሲስተም ሥራቸውን እንዲያከናውኑና ዘለቄታ እንዲኖራቸው መሠረት ይጥላሉ፡፡ ብልሹ አሠራሮች ፈጽሞ እንዲወገዱ ያደርጋሉ፡፡ ሠራተኞች መብቶቻቸው እንዲከበሩ፣ ጠያቂና ሞጋች፣ እንዲሁም ምክንያታዊ እንዲሆኑ ያግዛሉ፡፡ የአገር ሀብት እንዳይባክን ይልቁንም ውጤታማ በሆነ መንገድ ሥራ ላይ ውሎ ስኬት እንዲያስመዘግብ ይረዳሉ፡፡ እነዚህን በሻማ ብርሃን ሳይቀር ፈልጎ አገርን ማሳደግ ይሻላል? ወይስ ብቃት አልባዎችን ሰብስቦ መደናገር? መፍትሔው ግን የመጀመሪያው ነው፡፡ በአገር መደራደር ስለማያስፈልግ፡፡ ለዚህም ነው ሠርተው ማሠራት የማይችሉ ገለል ይደረጉ የሚባለው!