Tuesday, January 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹መንግሥት ኢትዮ ቴሌኮምን መሸጥም ሆነ ሌላ ኩባንያ እንዲገባ መፍቀድ የለበትም››

አቶ አንዱዓለም አድማሴ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ

አቶ አንዱዓለም አድማሴ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ አቶ አንዱዓለም በዕድሜ ወጣቱ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ማኔጅመንቱን ከፍራንስ ቴሌኮም ከጥቂት ዓመታት በፊት ተረክበዋል፡፡ አቶ አንዱዓለም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአካውንቲንግ፣ በመቀጠል በቢዝነስ ማኔጅመንት፣ በኋላ ኢዱኬሽናል ሊደርሽፕና ማኔጅመንት ተምረዋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜያቸውን በማስተማር ያሳለፉ ሲሆን እ.ኤ.አ. ከ2010 ጀምሮ ነው ኢትዮ ቴሌኮምን በዋና የውስጥ ኦዲተርነት የተቀላቀሉት፡፡ ከዚያም ወደ ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ያደጉት፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ከየት ወዴት እየሄደ እንደሆነ ለማየት ዮሐንስ አንበርብር ከአቶ አንዱዓለም ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን በአዋጅ ፈርሶ ነው ኢትዮ ቴሌኮም ከስድስት ዓመታት በፊት የተመሠረተው፡፡ እርስዎ የኢትዮ ቴሌኮም የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሥራ አስፈጻሚ እንደ መሆንዎና ከኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን ወደ ኢትዮ ቴሌኮም በተደረገው የለውጥ ሒደት ውስጥ እንደመሳተፍዎ፣ በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለውን ለውጥ እንዴት ይገመግሙታል?

አቶ አንዱዓለም፡- የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽንና ኢትዮ ቴሌኮምን ማወዳደር አይቻልም፣ አሁን ባለበት ሁኔታ፡፡ የቀድሞው ኮርፖሬሽን በምን ደረጃ ላይ ነበር? ኢትዮ ቴሌኮም ምን ይመስላል? ብለህ በተለያየ መንገድ ልታስቀምጠው ትችላለህ፡፡ በቴክኖሎጂ፣ በውስጥ አደረጃጀት፣ በገቢ፣ በደንበኛ ብዛት አሁን በታጠቀው ቴክኖሎጂ እንዲሁም በሠራተኞች አቅም ማለትም ከአመራር፣ ከቴክኒክ ዕውቀትና  ከኮሜርሺያል ዕውቀት ጋር ብትመዝነው በፍፁም ሊወዳደሩበት የሚችሉበት ሚዛን አይደለም አሁን ያለው፡፡ የቀድሞው ኮርፖሬሽን በራሱ ጊዜ በወቅቱ የሠራቸው በጣም ጥሩ ነገሮች አሉ፡፡ ልትኮንነው የምትችለው ነገር አይደለም፡፡ ይህ ተቋም ከ126 ዓመት በላይ ነው ያስቆጠረው፡፡ በዓለማችን የቴሌኮም ቴክኖሎጂ ከገባ ከ17 ዓመት በኋላ ነው ቴክኖሎጂው ወደ ኢትዮጵያ የመጣው፡፡ ረዥም ጊዜ የቆየ ታሪካዊ ሒደቶች በውስጡ ያለፉበት ተቋም ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በፈረንሣይ ዜጋ ነበር ሲመራ የነበረው፡፡ በኋላም ስዊድኖች፣ ከዚያም ኢትዮጵያውያን ተረክበውት ያቆዩት፡፡ እ.ኤ.አ. በ2010 በተቋሙ ላይ በተደረገው ለውጥም በድጋሚ ፈረንሣዮች በሥራ አስፈጻሚነት የመሩት ተቋም ነው፡፡ የዕድሜውን ያህል ግን አልተሠራም፡፡ አሥር ዓመት ወደኋላ ብትመለስ የደንበኛው ብዛት ስንት ነበር? በጣም ውስን ነበር፡፡ ቴክኖሎጂ የገባው በቅርብ ጊዜ ነው፡፡ ፈረንሳዮቹ በድጋሚ በመጡበት እ.ኤ.አ. በ2010 አካባቢ እንኳን የደንበኛው ብዛት ከነበረበት ስድስትና ሰባት ሚሊዮን በአንድ ጊዜ 47 ማሊዮን ነው የመጣው፡፡ መንግሥት ለአገሪቱ ለውጥ ትኩረት ያደረገባቸው መስኮች ግብርና፣ ትምህርትና ጤና ናቸው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ግን የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ላይ ኢንቨስት ማድረግ አለብኝ ብሎ ተነሳ፡፡ እዚህ ዘርፍ ላይ ትኩረት ካደረግኩኝ አገሪቱ ላይ ለውጥ አመጣለሁ ብሎ አመነ፡፡ ለዚህ ደግሞ የግድ ቴሌኮምን ማዘመን የግድ ነው፡፡ ምክንያቱም ቴሌኮም ለሁሉም ዘርፍ ስኬት አስቻይ (Enabler) ነው፡፡

ለምሳሌ ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ብትመለከት ኢትዮ ቴሌኮም ብቻ በአገሪቱ ጠቅላላ አገራዊ ምርት (GDP) ላይ 3.5 በመቶ አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት ነው የሚለው፡፡ የብሮድባንድ ልማትን በአሥር በመቶ ማሳደግ ቢቻል በአገሪቱ ጂዲፒ 1.3 በመቶ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ ይህንን መሠረት በማድረግ ኩባንያውን እንዴት አድርጎ መለወጥ እንዳለበት ነው ያቀደው፡፡ ሁለት መንገድ ነው የነበረው፡፡ አንዱ ‹ሪቮሊዩሽን› ተብሎ የሚጠራው ሙሉ በሙሉ አፍርሶ አዲስ መገንባት፣ ሁለተኛው ደግሞ ኢቮሊውሽን የምንለው ቀስ በቀስ ለውጥ ማምጣት ነበር፡፡ አገሪቱ ካለችበት ፈጣን ዕድገት አንፃር ሁለተኛውን አማራጭ መከተል አይቻልም፡፡ ስለዚህ እናፍርሰውና አዲስ እንገንባ በሚል ነው የተወሰነው፡፡ ነገር ግን እናፍርሰው ሲባልስ ይህንን ማድረግ የሚያስችል የአደረጃጀት ዕውቀት፣ አቅም፣ ባለሙያ አለን ወይ የሚለው ጥያቄ መጣ፡፡ በወቅቱ ይህ አቅም አልነበረም፡፡ በመሆኑም በዘርፉ ዓለም አቀፍ ዕውቅናና ተሞክሮ ያላቸውን ኩባንያዎች እናስገባ ተብሎ ተወሰነ፡፡ በዚህ መሠረት ፍራንስ ቴሌኮም ጨረታ አሸንፎ ኩባንያውን የማደራጀትና የማስተዳደር ኃላፊነት ተረከበ፡፡ ፍራንስ ቴሌክም ይህንን ኃላፊነት ሲረከብ የተቋሙ አደረጃጀትና የውስጥ አሠራር የመሳሰሉት በሙሉ ኋላቀር ነበሩ፡፡ በማኑዋል ነው ይሠራ የነበረው፡፡ አሁን በቅርቡ ነው ከነበረበት ማኑዋል አሠራር ሰብስበን የተቋሙን ሒሳብ አውቶሜትድ አድርገን ሒሳብ የዘጋነው፡፡ ፍራንስ ቴሌኮም ለሁለት ዓመት በቆየበት ጊዜ ውስጥ ዋና ሥራ አስፈጻሚና የምክትል ማዕረጎችን ጨምሮ ያዘ፡፡ አራት ማዕረጎችን ግን መንግሥት መልቀቅ የለብኝም ብሎ ነበር የወሰነው፡፡ አንዱ ሒደት ነው፡፡ እኔም የመጀመሪያ ቦታዬ ይህ ማዕረግ ነበር፡፡ ዋና የውስጥ ኦዲተር ሆኜ ነው ከፈረንሣዮቹ ጋር የመጣሁት፡፡ ሁለተኛው ፋይናንስ፣ ሦስተኛው የደኅንነት ዘርፍ፣ አራተኛው የሕግ ዘርፍ ነው፡፡ እነዚህ ማዕረጎች በኢትዮጵያውያን ከመያዛቸው ውጪ በሙሉ እስከ ባለሙያ ድረስ በፈረንሣዮቹ ነበር የተያዘው፡፡ የሥራ ሒደቶችን ነው በመጀመሪያ የቀረፁት፡፡ ከ500 በላይ አሠራሮችና የሥራ ሒደቶችን ነበር የቀረፁት፡፡ በመቀጠል የውስጥ ሥርዓቶችን ወደ ማዘመን ነው የተሻገሩት፡፡ ወደ ‹ኢንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላኒንግ› (ERP) ነው የመጡት፡፡ የወረቀት ሥራን ዜሮ ወደ ማድረግ ነው የቀየሩት፡፡ ከግዢ እስከ የአበል ክፍያ፣ የሠራተኛ የዕረፍት ፈቃድ አውቶሜትድ ነው ያደረጉት፡፡ በመቀጠል የሠሩትና ትልቅ ለውጥ የምንለው የዕውቀት ሽግግር ነው፡፡ ከማኔጅመንት አወቃቀር ጀምሮ እስከ ስትራቴጂካዊ ቡድን ፈጥረው ነው የመጡት፡፡ ሲወጡ ከ14 ሺሕ በላይ ሰነዶችን አስረክበው ነው፡፡ ይህ ትልቅ ሀብት ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮ ቴሌኮምና የቀድሞውን ኮርፖሬሽን ማወዳደር አይቻልም፡፡ የዛሬ ገቢና ወጪን ማወቅ እንችላለን፡፡ በየወሩ ሒሳብ መዝጋት እንችላለን፡፡ የዕውቀት ክፍተቱን ሳይቀር ለመዝጋት እኔን ማነው የሚተካኝ ብለው አስበውና መልምለው ለመንግሥት አስወስነው ነው የሄዱት፡፡

በጣም ውጤታማ ሥራ እንደሠሩ ተቋሙ በተፈለገው ደረጃ ላይ እንዳለ ብናውቅም፣ ስለዚህ ውጤታማ ሥራ ማውራት የማንችልበት ምክንያት በወቅቱ ኔትወርኩ በእጅጉ ተጨናንቆ ስልክ መደዋወል የማያስችል መሆኑ ነበር፡፡ አዲስ አበባ ታንቃለች፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችና ፋብሪካዎች ታንቀዋል፡፡ ኅብረተሰቡ ብዙ ሞባይል ይዟል፡፡ እኛ ሲም ካርድ መሸጥ አላቆምንም፣ ከፍተኛ ችግር ነበር፡፡ ኔትወርኩ መሸከም የሚችለው 20 ሚሊዮን ደንበኛ ሆኖ ሳለ በወቅቱ 23 ሚሊዮን ደንበኛ ነበር፡፡ መሆን የበረበት ያለህ የኔትወርክ አቅም 80 በመቶ ብቻ መጠቀም ነው፡፡ እኛ ግን ከ80 በመቶ ብቻ ሳይሆን ከመቶ በመቶ አልፎ ማንም መደወል የማይችልበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ስለውስጥ አደረጃጀት ስኬትህ ብታወራ አንድ ግለሰብ ጋ ያለ ስልክ እስካልሠራ ድረስ ትርጉም የለውም፡፡ በመሆኑም በፍጥነት ወደ ማስፋፊያ ሥራ ነው የገባነው፡፡ ይህንን ሥራ ለመሥራት መንግሥት ከቀድሞው ተሞክሮ በመነሳት ሥራው ከአንድ በላይ በመሆኑ ኩባንያዎች እንዲይዙት ተደርጎ ጨረታው ወጣ፡፡ ቀደም ሲል አንድ ኩባንያ ነበር ዜድቲኢ (ZTE) የሚባል፡፡ በዚህኛው ጨረታ ግን ፕሮጀክቱ በ13 ማስፋፊያ ቦታዎች እንዲከፈልና በእያንዳንዱ ላይ ኩባንያዎች እንዲወዳደሩ ነው የተደረገው፡፡ ፉክክር የሚያመጣ በመሆኑ ለእኛ ትልቅ ጥቅም የነበረው አካሄድ ነበር፡፡ የራሱ ውጣ ውረድ ቢኖረውም በፕሮጀክቱ ሦስት ኩባንያዎች ተሳትፈው አሁን 80 ሚሊዮን ደንበኛ መሸከም የሚችል ኔትወርክ ተፈጥሯል፣ በሞባይል ዘርፍ ማለቴ ነው፡፡ አሁን አጠቃላይ የደንበኞቻችን ብዛት በሁሉም አገልግሎቶች ወደ 48 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ከዚህ ውስጥ ባለገመድ ስልክ 1.1 ሚሊዮን ሲሆን ቀሪው ሞባይል ነው፡፡ ይህንን ከቀድሞው ኮርፖሬሽን ጋር ማወዳደር ያስቸግራል፡፡ በገቢ ደረጃም ብትመለከተው ልዩነቱ እጅግ ሰፊ ነው፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ ወደ 28 ቢሊዮን ብር ነው ገቢ የሰበሰብነው፡፡ ቀደሞ የነበረው 2G እና 3G ቴክኖሎጂ ነበር አሁን 3.5G ወይም “HSPT” የሚባለው ቴክናሎጂ ነው በመላ አገሪቱ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ ይህም ማለት በ3G እና በ4G መካከል የሚገኝ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ አዲስ አበባ ላይ ደግሞ “LT” ቴክኖሎጂ ነው የዘረጋነው፡፡ MVAS የሚባል ቴክኖሎጂ ባለቤትም ሆነናል፡፡ እሴት የሚጨምሩ አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችልና ከ69 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን የማስተናገድ አቅም ያለው ነው፡፡ የጠቀስኩት 69 ሚሊዮን ደንበኛ ማለት ከአምስት ሚሊዮን በላይ ደንበኛ ያለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እንደ አንድ ደንበኛ ተቆጥሮ ነው፡፡ ስለዚህ ትልቅ አቅም ነው አሁን ያለን፡፡ ድሮ ሞኖፖሊ ናችሁ በማለት እዚያና እዚህ የሚያላጉን ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ወደ መሸለም ነው የገቡት፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም አሁን በገነባው አቅም ምክንያት ወደ አሥር ሽልማቶች በዚህ ዓመት አግኝቷል፣ በተለያዩ መለኪያዎች፡፡ አሁን ማነቆ አይደለንም፡፡ ከፍላጎትና ከዕድገቱ ጋርም ትከሻ ለትከሻ ሳይሆን ቀድመን ነው የምንጓዘው፡፡ ብዙ የሚቀረን ሥራ አለ፡፡ ጥራትን ከማረጋገጥና ከመሳሰሉት ጋር በተያያዘ፡፡ ዓለም አቀፉ የቴሌኮም ኅብረት ያለፈው ሩብ ዓመት ሪፖርትን ለምሳሌ አይተኸው ከሆነ ኢትዮ ቴሌኮምን በግዝፈቱ ከአፍሪካ ሁለተኛ አድርጎታል፡፡ ናይጄሪያ ላይ ያለው “MTN” ነው የሚቀድመው፡፡ በዓለም ላይ ካሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎች ደግሞ በግዝፈቱ ኢትዮ ቴሌክም 38ኛ እንደሆነ ነው ሪፖርቱ የሚገልጸው፡፡

ሪፖርተር፡- የደንበኛ ብዛት ብቻውን ጠቃሚ ትርጉም አለው ማለት ያስችላል? ምክንያቱም አንድ ግለሰብ ሁለትና ከዚያ በላይ ሲም ካርዶች ሊኖሩት ይችላል፡፡ በተግባር ግን ሊጠቀም የሚችለው አንድ ሲም ካርድ ነው፡፡ ሲም ካርዶችን የመቀያየር ዕድሉን ከግምት በማስገባት ማለቴ ነው፡፡ የጥራት ችግርስ ሊታይ አይገባውም?

አቶ አንዱዓለም፡- ዓለም አቀፉ የቴሌኮም ኅብረት (ITU) የደንበኞች ብዛት ሲል ምን ማለቱ ነው? ትክክለኛ በኔትወርኩ የሚደውሉ ሰዎች ስንት ናቸው የሚሉትን በግልጽ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ የደንበኞች ብዛትን ለመለካት አምስት ደረጃዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ኢትዮ ቴሌክም 47 ሚሊዮን የሞባይል ደንበኛ አለው ሲል 47 ሚሊዮኑም ኔትወርኩን በመጠቀም ንቁ ተሳታፊ አይደሉም፡፡ ይህ ጠቅላላ ኔትወርኩ የተሸከመው የደንበኞች ብዛት ነው፡፡ የመጀመሪያው የደንበኞች ዓይነት “Active users” የምንላቸው በየጊዜው የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ ሁለተኛው “Inactive users” የምንላቸው ናቸው፡፡ ይህ ደንበኛ ሲም ካርድ ገዝቷል ግን ኪሱ ውስጥ ወይም የሆነ ቦታ ነው ያለው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ “two way blocked” የምንለው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ደንበኛው ለተወሰኑ ወራት ውጭ አገር ሄዶ ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም በተለያዩ ምክንያቶች አየር ሰዓት የማይሞላ ጥሪም የማይቀበል ይሆንና መደወልም ጥሪ መቀበልንም እንዳያስተናግድ ይደረጋል፡፡ ሌላኛው ደግሞ ለበርካታ ዓመታት ሲም ካርዱን ባለመጠቀሙ ምናልባትም አገር ቀይሮ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ውሉ እንዲቋረጥ ይደረጋል፡፡ በመቀጠልም ቁጥሩ ለሌላ ሊሰጥ ይችላል፡፡ እነዚህ ተደምረው ነው የደንበኞች ብዛት ወይም “Customer Base” የሚባለው፡፡ ምክንያቱም ካርድ ሲሞላ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ፡፡ ውሉ ያልተቋረጠ እስከሆነ ድረስ ማለቴ ነው፡፡ አገሮች የየራሳቸው መሥፈርት አላቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደንበኛው ሲም ካርዱን ለአንድ ዓመት ካልተጠቀመበት ወይም ለስድስት ወራት ካልተጠቀመበት ለሌላ አሳልፈው ይሸጣሉ፡፡ ጥያቄው እኛ ይህንን ማድረግ እንችላለን ወይ ነው፡፡ በቴክኖሎጂ አቅም ማለቴ አይደለም፡፡ ይህንን ማድረግ እንችላለን ግን ምን ዓይነት ማኅበረሰብ ነው ያለን? የተማረው ኅብረተሰብ እንኳን ይህንን ብናደርግ ምን ያህል ይረዳናል የሚሉትን በማገናዘብና ኅብረተሰባችንን ለመደገፍ ስንል አልመረጥነውም፡፡ ይሁን እንጂ ምን ያህሉ የሲም ካርድ ባለቤት ከመሆን ባለፈ ተጠቃሚ ነው የሚለውን እናውቃለን፡፡ ለምሳሌ ልዩ ተጠቃሚዎች የምንላቸው አሉ፡፡ ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ የሚደውሉ፡፡ ለምሳሌ በአጠቃላይ ተጠቃሚ የምንላቸው ከ47 ሚሊዮን ደንበኞች ውስጥ ከ20 እስከ 30 ሚሊዮን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይህ ቁጥር በየወሩ የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ 35 ሚሊዮን ሊሆንም ይችላል፡፡ የሚገቡ የሚወጡ አሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የሪፖርት አቀራረብ ሥርዓት አለ ለማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ ሲነገር ግን የሁሉንም ድምር የሚቀመጠው፡፡ ለያይቶ ማስቀመጡ አገልግሎቱን ለሚሰጠው ደንበኛ የቢዝነስ ሞዴል ነው ዋነኛ ጠቀሜታው፡፡

ጥራትን በተመለከተ ዘወትር የምታረጋግጠው አይደለም፡፡ ሽልማቶች ሲሰጡህ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሰዋል ለማለት አይደለም፡፡ ጥረትህን ነው የሚያሳየው፡፡ ከየት ተነስተህ የት ደርሰሃል የሚለውን ነው በእኛ ረገድ የተመለከቱት፡፡ በአንድ ጊዜ ከስድስት ሚሊዮን ደንበኛ ወደ 47 ሚሊዮን ደንበኛ አምስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ደርሰናል፡፡ ይህ ኩባንያ ይህንን ያህል ኢንቨስትመንት አካሂዶ ይህንን ለውጥ አመጣ፡፡ ሌሎቹ 500 ሺሕ ዶላር አውጥተው እንደ ጉድ ነው የሚቆጠረው፡፡ ዘጠና ዘጠኝ በመቶ የደረሰውማ ምን ያስፈልገዋል? ያደረግነውን ጥረት፣ ተስፋ ሰጪና ዘላቂነት ያለው መሆኑን ተመልክተው ቀደም ሲል የሰጡንን አስተያየት ተቀብለን በማሻሻል፣ አንዳንዶቹ በአመራር፣ እንዲሁም ምርጥ አገልግሎት ሰጪ በሚሉ መሥፈርቶች ነው የተሸለምነው፡፡ ይህ በሽልማት ብቻ የተገነዘብነው አይደለም፡፡ ፍራንስ ቴሌኮም ከወጣ በኋላ የኢትዮ ቴሌኮምን ጤናማነት እንዲያጠና ለአሜሪካው ማካንዚ ኩባንያ ሰጥተነው ነበር፡፡ በዚህ ኩባንያ ግምገማ መሠረት ኢትዮ ቴሌኮም በሁለተኛ ደረጃ ላይ ነው የተገኘው፡፡ በአንዳንዶቹ መሥፈርቶች አሉ ከሚባለት ዓለም አቀፍ አገልግሎት ሰጪዎች በላይ ነው ያገኘነው ደረጃ፡፡ በመሆኑም በዚህ ኩባንያ ግምገማ መሠረት ኢትዮ ቴሌኮም ጤናማ ነው፡፡ ነገር ግን ወደ 13 እንከን ያለባቸው (Broken Practice) አሠራሮችን ጠቁመውናል፡፡ ይህንን ካስተካከላችሁ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ትደርሳላችሁ ብለውናል፡፡ ይህንን የግምገማ ውጤታቸውን ይፋ አድርገውታል፡፡ ጥራትን በተመለከተ ማንኛውም አገልግሎት ሰጪ እክሎች ይገጥሙታል፡፡ ምክንያቱም ጥራት የብዙ ድምሮች ውጤት በመሆኑ፡፡ እኛ አገልግሎት የምንሰጥበት አካባቢ በተለይም ዋነኛዋ አዲስ አበባ የተረጋጋ አመቺ ከባቢያዊ ሁኔታ ውስጥ አይደለችም፡፡ በየጊዜው ግንባታዎች ይከናወናሉ፡፡ ትናንት ያልነበረ ፎቅ ዛሬ ላይ የማሠራጫ መሣሪያዎችህን ይጋርዳል፡፡ ፋይበሮች ይቆራረጣሉ፡፡ ቴክኖሎጂው አለን ቢሆንም ግን የጥራት ጉዳይን ማሻሻል የሚገባን ሥራ ነው፡፡ ጥራትን ማረጋገጥ ደግሞ የማይቋረጥ ክትትልን የሚጠይቅ ነው፡፡ እኛም ወደዚህ ደረጃ ለመምጣት እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ዓመት ኢትዮ ቴሌኮም ካገኛቸው ሽልማቶች አንዳንዶች በጥርጣሬ ሲመለከቱና ጥርጣሬያቸውን ሲገልጹ የሰሙ ይመስለኛል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ሽልማቶቹን ገዝቶ ነው የሚል ሐሜት ሳይሰሙ የሚቀር አይመስለኝም፡፡ ምን ተሰማዎት?

አቶ አንዱዓለም፡- በተለያዩ ምክንያቶች ሰዎች የራሳቸውን ዕይታ ሊያስቀምጡ ይችላሉ፡፡ ከእውነታው ግን መራቅ አይቻልም፡፡ እውነቱ ሁልጊዜ ከጀርባ አለ፡፡ ሽልማቶች በሚሰጡበት ጊዜ ራሳቸውን የቻሉ መሥፈርቶችና የመለያ ሒደቶች ስለሚኖሩ ያንን ዓይነት ዕይታ ያላቸው ሰዎች በእያንዳንዱ ሸላሚ ተቋም ድረ ገጽ ገብተው ማየት ይችላሉ፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም የሕዝብ ኩባንያ ነው፡፡ በሕዝብ ኩባንያ ላይ አላስፈላጊ ገጽታ መፍጠር አያስፈልግም፡፡ እኔ እውነቱን ስለማይ ለሚባለው ነገር ስሜት አይኖረኝም፡፡

ሪፖርተር፡- የቴሌኮም ማስፋፊያዎች በውጭ ኩባንያዎች ለዚያውም ራሳቸው ገንዘብ በሚያመጡ ኩባንያዎች ነው እየተሠሩ ያሉት፡፡ በቅርብ ጊዜም የ1.6 ቢሊዮን ዶላር ማስፋፊያ ሲከናወን የኩባንያዎች ሽኩቻ እንደነበር ይታወሳል፡፡ እንዲህ ዓይነት ፕሮጀክቶችን የማስተዳደር አቅም ኢትዮ ቴሌኮም ገንብቷል? የኩባንያዎች ጥምዘዛን መቋቋም የሚችል አቅም አለው?

አቶ አንዱዓለም፡- እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ብቻ ሳይሆን በአገር አቀፍ ደረጃም ፕሮጀክቶችን የመምራት ልምድ እየዳበረ ነው ያለው፡፡ ምክንያቱም ከግዙፍ ፕሮጀክቶች ጀርባ እነማን እንዳሉ ማወቅ የፕሮጀክቱ ባለቤት ድርሻ ነው፡፡ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ጀርባ የሚመጡት በብዙ አገሮች ተሳትፈው ልምድ የቀመሩ፣ በቀላሉ ብዙ ነገሮችን በእነሱ ጥቅም ዙሪያ ማድረግ የሚፈልጉና እንዴት መወጣት እንዳለባቸው የሚያውቁ ናቸው፡፡ እነዚህን በልጦ መገኘት ያንተ ድርሻ ነው፡፡ በእኩል ደረጃም አይደለም ከእነሱ በልጦ መገኘት ነው፡፡ እንደ ኢትዮ ቴሌኮም በቅርቡ ሙሉ በሙሉ በሚጠናቀቀው ፕሮጀክት ትልቅ የፕሮጀክት አስተዳደር ልምድም ወስደንበታል፡፡ በትክክልም መርቶታል ብዬ ነው የማምነው፡፡ ምክንያቱም ፕሮጀክቱን ከመጀመራችን አስቀድመን ከቀደመው የ1.5 ቢሊዮን ዶላር NGN ፕሮጀክት ትምህርት ለመውሰድ ሞክረናል፡፡ በመጀመሪያ የተሠራው ይህ ነው፡፡ በመቀጠል ምንድነው ማስተካከል ያለብን? እንዴት ነው ጥቅማችንን ማስከበር ያለብን? የሚለውን ገምግመን ነው የተነሳነው፡፡ በመንግሥት ስትራቴጂ መሠረትም ብዙ ኩባንያዎች መሳተፍ የሚችሉበት ጨረታ ነው ያወጣነው፡፡ ስለዚህ ኩባንያው ለራሱ ሲል ነው የሚኖረው ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም ሦስት ኩባንያዎች በአማካሪነት ቀጥረናል፡፡ ኩባንያዎቹ የጨረታ ዶክመንት ከማዘጋጀት ጀምሮ ተሳትፈዋል፡፡ በመሆኑም ለተጫራች ኩባንያዎቹ ፈታኝ ሁኔታ ነው የፈጠርንባቸው፡፡ ስለዚህ የሌሎችንም እውቀት ተጠቅመናል፡፡ ይህንን እውቀት የእኛ ባለሙያዎች እንዲቀስሙም አድርገናል፡፡ ያለፉትን ሁለት ዓመት ተኩል በእያንዳንዷ ማክሰኞ ዕለት የኢትዮ ቴሌኮም ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኮሚቴ ይሰበሰባል፡፡ በእያንዳንዱ ረቡዕ ዕለት ደግሞ በፕሮጀክቶቹ ላይ የሚሳተፉ ኩባንያዎችን እንጠራለን፡፡ የግምገማችንን ሪፖርት ለዶ/ር ደብረ ጽዮን እንልካለን፡፡ እሳቸው ካነበቡ በኋላ ሐሙስ ማታ እንሰባሰባለን፡፡ ውሳኔ የሚያስፈልገው ነገር ካለ ወደ ቦርድ ይሄዳል፡፡ በዚህ መልኩ ዕለት በዕለት ነው የምንከታተላቸው፡፡ ሁዋዌ ኩባንያ ቀድሞ ስለጨረሰ ክትትላችንን አሁን አቁመናል፡፡ በሌሎቹ ላይ ዜድቲኢና ኤሪክሰን ላይ አሁንም ቀሪ ሥራዎች ስላሉ ክትትል ይደረጋል፡፡ ኩባንያዎቹ እርስ በርሳቸው ስለሚፎካከሩና ጥሩ ግንኙነት ስለሌላቸው እኛን ከበድ ያለ ሥራ ውስጥ ከተውናል፡፡ ነገር ግን የእኛ ዓላማ ጥቅማችንን ማስከበር ስለሆነ በጥሩ ሁኔታ የሠራንበትና የተጠቀምንበት እንዲሁም ትልቅ ልምድ ያገኘንበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በመጀመሪያ ላይ ዜድቲኢና ሁዋዌ ለተባሉት ኩባንያዎች ነበር ፕሮጀክቱ በእኩል የተካፈለው፡፡ በኋላ ላይ ውዝግብ ነበር፡፡ ዜድቲኢ ከተሰጠው ፕሮጀክት እንደወጣ ተገልጾ ነበር፡፡ ምንድን ነበር የውዝግቡ መነሻ? አጠቃላይ ሁኔታውን ቢያብራሩልን?

አቶ አንዱዓለም፡- በጨረታው መሥፈርት መሠረት ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች ገንዘብ ይዘው የመምጣት ግዴታ ነበረባቸው፡፡ የሚያመጡት ገንዘብ ደግሞ በጣም ዝቅተኛ ወለድ የሚከፈልበት እንዲሆን ነው በመሥፈርትነት ያስቀመጥነው፡፡ ይህንን ማሟላት ካልቻሉ ጨረታ ውስጥ መግባት አይችሉም፡፡ የክፍያ ዘመንም ሌላው መሥፈርት ነው፡፡ የተራዘመ የክፍያ ጊዜ እስከ 13 ዓመት አድርገን ነው የመጣነው፡፡ የእፎይታ ጊዜን ሳይጨምር ማለቴ ነው፡፡ የተደራደርንበት ገንዘብ “Per line cost” (በአንድ መስመር ምን ያህል ያስከፍለናል) በሚል ነው፡፡ በመሆኑም ከዚህ ቀደም ከነበረበት ደረጃ በጣም ወርደው ነው ሁለቱም ኩባንያዎች የመጡት፡፡ ምክንያቱም ሁለቱ ኩባንያዎች ከፍተኛ ፉክክር ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ እኛ እንዲያውም ሰግተን ነበር፡፡ ምክንያቱም ወደ አላስፈላጊ የዋጋ ጦርነት ውስጥ ገብተው ሥራውን መሥራት የማይቻልበት ሁኔታ እንዳይገጥማቸው አሳስቦን ነበር፡፡ ግን ዋናው ጉዳያችን የአገራችንን ጥቅም ማስከበር ነበረብን፡፡ አንድ የሚገርም ነገር ባነሳ ለምሳሌ አሮጌውን ኔትወርክ ነቅለው በአዲስ እንዲተኩ ያደረግነው በነፃ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም የነቀሉትን ዕቃ እንወስዳለን አሉ፡፡ አይደረግም አልን፡፡ አሮጌውን ነቅለውና አዲስ ተክለው፣ የተነቀለውን አሽገው ወደኛ መጋዘን እንዲያቀርቡ ያደረግነው ያለ ሰባራ ሳንቲም ክፍያ ነው፡፡ ከዚያ የምንከፍላቸው አዲስ ለሚገነቡት ነው፡፡ ቀድሞ የነበረው ኔትወርክ 20 ሚሊዮን ደንበኛ መሸከም የሚችል ነበር፡፡ የ20 ሚሊዮን ደንበኛ ማሠራጫዎችን ነቅለው በነፃ ነው የተኩት፡፡ ሌላው ጦርነታቸው አዲስ አበባ ላይ ያለውን ፕሮጀክት ለመውሰድ ነበር፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ከተማ ነች፡፡ እዚህች ከተማ ላይ ማንነታቸውን አስመሰከሩ ማለት የሌላኛውን አፍሪካ አገር በሙሉ ተቆጣጠሩ ማለት ነው፡፡ ይህ ኔትወርክ የማን ነው ተብሎ ሲጠየቅ ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበት ነው፡፡ በነፃ ሥሩ ብትላቸው የሚሠሩት ነው፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ የተቀረፀው ማስፋፊያ “4G LT” ነው፡፡ ይህ ደግሞ ዓለም የደረሰበት አዲስ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የአዲስ አበባን ፕሮጀክት ለሁለት ከፍላችሁ ስጡን አሉን፡፡ ይህ ለእኛ የሚቻል አልነበረም፡፡ ምክንያቱም የኔትወርክ ግጭት ያመጣል፡፡ ስለዚህ አልተቀበልናቸውም፡፡ ስለዚህ የአጠቃላይ ፕሮጀክቱን ሃምሳ ሃምሳ በመቶ አካፈልናቸው፡፡ ሁዋዌ ሰሜንና ሰሜን ምሥራቅ አዲስ አባን ጨምሮ ነው፡፡ ዜድቲኢ ደግሞ ደቡብና ደቡብ ምዕራብን ወሰደ፡፡ በዚህ ጊዜ ኩርፊያ ተጀመረ፡፡ ለምን አዲስ አበባ ተወሰደብኝ በሚል፡፡ በመቀጠልም ዜድቲኢ በኮንትራቱ የተስማማንበትን ትቶ አሮጌውን ኔትወርክ በነፃ አልነቅልም አለ፡፡ የቻይና ኩባንያዎቹ በነበራቸው ፉክክር የተነሳ በአንድ መስመር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚሰጠው ዋጋ ወርደው ነው የገቡት፡፡ በጣም የሚገርመው ግን አውሮፓዊው ኩባንያ ኤሪክሰን ከእነሱም ወርዶ መግባቱ ነው፡፡ ዜድቲኢ አሮጌውን ኔትወርክ አልነቅልም የሚልበት ምክንያት ቀድሞ የገነባሁት እኔ ነኝ የራሴን ኔትወርክ አልነቅልም ነው፡፡ ምክንያቱም 200 ሚሊዮን ዶላር ያከስረኛል፤ ስለዚህ እዚያው ላይ ላስተካክል አለ፡፡ እኛ ደግሞ ጊዜውን ጨርሷል ነቅለህ አዲስ ትከል፣ አለበለዚያ ውጣ አልነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሁለት ኩባንያዎችን መረጥን፡፡ ኖኪያንና ኤሪክሰንን መረጥን፡፡ ቀሪውን ሁለት ማስፋፊያ ደግሞ በራሳችን ልንሠራ ወሰንን፡፡ ኖኪያ የመዋቅር ለውጥ ላይ ስለነበረ የእኛን ጥያቄ መቀበል አልቻለም፡፡ ኤሪክሰን ወዲያው መጣ፡፡ ገንዘብ ይዞ መምጣት እንዳለበት ተነገረው ይዞ መጣ፡፡ ስለዚህ አራት የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን እንችላለን አሉ ተሰጣቸው፡፡ ይህንን ልክ ስናደርግ ዜድቲኢ ተመልሶ መጣና ለመደራደር ፈለገ፡፡ እኛ ደግሞ ከኤሪክሰን ጋር ብዙ ነገሮችን ጨርሰን ውል ልንፈራረም ጫፍ ደርሰናል፡፡ ስለዚህ የቀሩትን ሁለት የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ውሰድ አልነው ወሰደ፡፡ ምክንያቱም ማንም ሳያምነን በፊት ገንዘብ ይዞ መጥቶ የቀድሞውን ኔትወርክ የሠራው ዜድቲኢ ነው፡፡ ባለውለታችን ነው፡፡ በዚህ መልኩ ሦስቱም ኩባንያዎች መሳተፍ ጀመሩ፡፡ ነገር ግን ኤሪክሰን ትንሽ መንገራገጭ ጀመረ፡፡ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ችግር ገጠመው፡፡ ለማደራጀት ጊዜ ወሰደባቸው፡፡ ሌሎችም ችግሮች ነበረባቸው፡፡ በዚህ የተነሳ ከዜድቲኢና ከሁዋዌ ፈጣኑ ማነው? በተሻለ ማን ነው የሠራው? የሚለውን ግምገማ ኤሪክሰን ከያዛቸው ፕሮጀክቶች አንዱን ነጥቀን ለሁዋዌ ሰጠነው፡፡ ኤሪክሰን አሁንም አልጨረሱም ሁዋዌ ግን ጨርሶ ወጥቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ሰሞኑን አዲስ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ጨረታ አውጥታችኋል? ምንድነው ግብ ያደረገው? ምን ያህል ኩባንያዎችስ ፍላጎት አሳዩ?

አቶ አንዱዓለም፡- አንዱ ታሳቢ የምናደርገው የመንግሥትን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በኋላ አንገት ለአንገት ተናንቀን መሄድ የለብንም፡፡ እኛ ቀድመን ካልሄድን ሌላው ዘርፎ ማነቃነቅ አይቻልም፡፡ አንድ የኢንዱስትሪ መንደር አንድ የመንደር ያህል መጠን ይዞ እየመጣ ባለበት ወቅት እኛ መተኛት አንችልም፡፡ ስለዚህ እየሠራን ያለነው ሦስተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ነው፡፡ ሌሎች ዘርፎች በሦስተኛ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የሚያቅዱትን ወይም የሚተገብሩትን ቀድሞ ማስተናገድ የሚችል ኔትወርክ መዘርጋት አለብን፡፡ ከዚህ ተነስተን ነው በቅርቡ ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን እንዲገልጹ ግልጽ ማስታወቂያ ያወጣነው፡፡ ፍላጎት የማሳወቂያው ጊዜ አሁን ተጠናቋል፡፡ በአብዛኛው በዚህ ማስታወቂያ የምንፈልገው ይዘው የሚመጡትን ገንዘብ ነው፡፡ ፋይናንስ ይዘው መምጣት ግዴታቸው ብቻ ሳይሆን የመንግሥት የዋስትና ጥያቄ ማንሳት የለባቸውም፡፡ ይህ የማንደራደርበት ጉዳይ ነው፡፡ ራሱ ኢትዮ ቴሌክምን አምነው መምጣት አለባቸው፡፡ ምክንያቱም የሚከፍለው ኢትዮ ቴለኮም ነው፡፡ ሌላ ነገር እንኳን ቢከሰት ወደ መንግሥት መሄድ የለበትም፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ጋ ብቻ ነው መጠናቀቅ ያለበት፡፡ አሁን በማስፋፊያነት ያቀረብናቸው ዘጠኝ ምድቦችን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የዳታ ማዕከል ማስፋፊያ፣ ክላውድ ሴንተር ማስፋፊያዎችም በዚህ ጨረታ ተካተዋል፡፡ እነዚህ ዳታ ሴንተር ወይም ክላውድ ሴንተር የምንላቸው የተለያዩ ተቋማት ዳታ ሴንተሮችን የምናስጠልልባቸው ናቸው የሚሆኑት፡፡ ለምሳሌ ንግድ ባንክ የራሱ ዳታ ሴንተር አለው፡፡ ነገር ግን አደጋ ቢደርስ ዳታውን መልሶ ማግኘት የሚችልበት ሁኔታን ለማመቻቸት እኛ ጋ ግዙፍ የሆነ ዳታ ሴንተር ተቋቁሞ ወደዚህ መጫን አለበት፡፡ እኔ አሁን ለምሳሌ ሌላ ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጥ የተማላ ሁለተኛ ቢሮ አለኝ፡፡ እዚህ ጋ አደጋ ቢከሰት የት ሆኜ መመሪያ መስጠት እችላለሁ? ሁሉንም ዓይነት አገልግሎት የሚሰጥ የተሟላ ሌላ ቢሮ አለኝ፡፡ ተመሳሳይ ሁኔታ ለሌሎች መፍጠር የምንችልበት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ነው፡፡ በተጨማሪም መብራት ኃይል ላይ ጥገኛ ሆነን መቀጠል ስለማንችል ይህንን ችግር የምንቀርፍበት ፕሮጀክት ነው የቀረፅነው፡፡

በዓለም ላይ በቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ላይ ተዋናይ የሆኑ ኩባንያዎች ይታወቃሉ፡፡ የኔትወርክ መሣሪያ አምራችና ሠሪዎች አራቱ ኤሪክሰን፣ ሁዋዌ፣ ዜድቲኢ፣ ኖኪያና አልካቴል (አሁን ላይ አንድ ሆነዋል) ሁሉም መጥተዋል፡፡ ነገር ግን ሌሎችም እንዲመጡ ገንዘብ የማምጣት መሥፈርቱን እስከ 50 ሚሊዮን ዶላር አውርደንላቸዋል፡፡ ይህንን ያደረግነው የበለጠ ተሳታፊ እንዲኖር ለማድረግ ነው፡፡ አንድ ቢሊዮን ዶላር ማምጣትን እንደ መስፈርት ብናስቀምጥ ሊመጡ የሚችሉት ይታወቃሉ፡፡ ይህንን በማድረጋችን አሥር ኩባንያዎች ናቸው የመጡት፡፡ በአጠቃላይ ቀጣዩ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ፍላጎትን መሠረት ያደረገ ነው የሚሆነው፡፡ ለምሳሌ የአዲስ አበባ ኔትወርክ ከተጨናነቀ የተወሰነ ማስፋፊያ ይጨመራል፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወደ 103 ሚሊዮን ደንበኛ ለማድረስ አቅደናል፡፡ አሁን የደረስንበት አቅም 80 ሚሊዮን ነው፡፡ 23 ሚሊዮን ብንጨምር እንደርሳለን፡፡ በተጨማሪም ከኢንፎርሜሽን ሲስተም ጋር የተያያዙ፣ ከፓወር ሶሉሹን የተያያዙ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ሁሉን አምጥተህ ስትሰጣቸው እነርሱ ራሳቸው ከሌላ ገዝተው ይተክሉልኃል፡፡ እኛ በቀጥታ ከአምራቾቹ ጋር መገናኘት እንዲያስችለን አድርገን ነው ጨረታውን ያወጣነው፡፡ ለዚህ ነው እስከ 50 ሚሊዮን ዶላር የፋይናንስ አቅርቦቱን ያወረድነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት ፖሊሲ ቻርጅ ኤንድ ኮንትሮል ሲስተም የተባለ ቴክኖሎጂና የቴክኖሎጂም መገልገያ መሣሪያዎች ምዝገባ ለማካሄድ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ባለቤት ብትሆኑም፣ ማኅበረሰቡ ቫይበርና ፌስቡክን ሊዘጋ ነው የሚል ሥጋት ገብቶታል፡፡ ሥጋቱ ተገቢ ነው?

አቶ አንዱዓለም፡- ተገቢ አይደለም ሥጋቱ፡፡ ውዥንብሩን ለመቅረፍ እኛም ሞክረናል፡፡ ከዚህ ቀደም የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ ሲፀድቅ ስካይፒን (Skype) መንግሥት ሊዘጋ ነው በሚል ጩኸት ነበር፡፡ ነገር ግን መንግሥት ወጥቶ የገለጸው ማንም ሰው ለግል ጥቅሙ እስካዋለው ድረስ ችግር እንደሌለውና መጠቀም እንደሚችል ነው፡፡ ነገር ግን ቴሌ ሴንተር ስካይፒ ማስደወል አትችልም ነው ያለው፡፡ ምክንያቱም ይህ ሥራ የኢትዮ ቴሌኮም ነው፡፡ ለእኛ ፖሊሲ ቻርጅ ኤንድ ኮንትሮል ሲስተም የቢዝነስ ሞዴል ነው፡፡ ለምሳሌ ልጅህ አላስፈላጊ ድረ ገጽ ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ ይህንን ለመከላከል (Parental Control) በወላጆች ጥያቄ አገልግሎት ለመስጠት ነው፡፡ ሌላው ይህ ሲስተም ተግባራዊ ሲደረግ ለኢትዮ ቴሌኮም የትኛው የማሠራጫ ታወር ብዙ መጨናነቅ ገጥሞታል የሚለውን መለየት ያስችለናል፡፡ ለምሳሌ መርካቶ ቀን ላይ ኔትወርኩ በጣም ነው የሚጨናነቀው፡፡ ከ12  ሰዓት በኋላ ደግሞ ባዶ ነው፡፡ ሲኤምሲ አካባቢ ቀን ባዶ ነው፡፡ ኔትወርኩ ማታ ላይ ሲጨናነቅ ታየዋለህ፡፡ ይህ የሰዎችን እንቅስቃሴ ነው የሚያሳይህ፡፡ ይህ ሲስተም ተግባራዊ ሲሆን ግን መርካቶ አካባቢ ሲጨናነቅ ከመርካቶ ወጣ ባለ አካባቢ በሚገኝ ነፃ ኔትወርክ ከዚህ ሰዓት እስከዚህ ሰዓት ብትጠቀሙ ዋጋው ይቀንሳል ብለህ መልዕክት በመላክ፣ የተጨናነቀውን ኔትወርክ ለማስተንፈስ የሚረዳ ነው፡፡ ያንን የሚወስነው ዋና ሥራ አስፈጻሚው ነው፡፡ ጥቅም ላይ ያልዋለ ነፃ ኔትወርክ ሲያይ እዚህ አካባቢ ያላችሁ ከዚህ ሰዓት ጀምሮ ዋጋው ይህን ያህል ነው ብሎ መልዕክት ይልካል፡፡ በዚህ የተነሳ የሰውን እንቅስቃሴ መቀየር የሚያስችል ሲስተም ነው፡፡ የመገልገያ መሣሪያዎች ምዝገባን በተመለከተ የቴክኖሎጂው ባለቤት ሆንን እንጂ ሥራው የመንግሥት ነው፡፡ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጎ የሕዝብን ጥቅም ሳይነካ ተግባራዊ የሚደረግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በርካታ ኢትዮጵያውያን ውጭ ካሉ ዘመዶቻቸው ጋር በመጠቀም ስልክ ይደዋወላሉ፡፡ ይህ የኢትዮ ቴሌኮምን ገቢ በመጉዳቱ ኩባንያው ቫይበርን ለመዝጋት አቅዷል ይባላል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ከቫይበር አፕሊኬሽን አምራች ጋር ትርፍ ለመጋራት የሚቻልበትን ድርድር እንደሚያደርግ ይገልጻል፡፡ በዚህ ረገድ የትኛውን መንገድ እየተከተላችሁ ነው?

አቶ አንዱዓለም፡- ዓለም የሚሄድበትን አካሄድን ነው የምንከተለው፡፡ አንደ አገር ማድረግ የሚባን ተመሳሳይ አፕሊኬሽን በአገር አቀፍ ደረጃ በመፍጠር፣ ገቢውንም ሆነ ተጠቃሚነቱን ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት ነው፡፡ ለምሳሌ ወደ ቻይና ብንሄድ ዊቻት፣ ባይዱ የሚባሉትን አፕሊኬሽኖች አልምተው ወደ ራሳቸው አገር አምጥተውታል፡፡ ኮሪያም ብትሄድ ተመሳሳይ ነው፡፡ እኛም የራሳችንን አፕሊኬሽን በማበልፀግ መሥራት ነው ያለብን፡፡ ይህንን ማድረግ የሚችሉ ብቁ የሆኑ ባለሙያዎችን አገር ውስጥም ሆነ ውጭ አገር እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ወደዚህ ከሄድን ሕዝባችንም እነዚህ አፕሊኬሽኖችን መጠቀም ይጀምራል፡፡ ያኔ ቫይበር ጭንቀታችን ሊሆን አይችልም፡፡ አሁንም ቫይበር የሚያስጨንቀን አይደለም፡፡ ምክንያቱም የእኛን ኢንተርኔት መጠቀሙ አይቀርም፡፡ አሁን ከዓለም አቀፍ ደረጃ የቴሌኮም ገቢ ከስልክ ጥሪ ወደ ኢንተርኔት እየተሻገረ በመሆኑ እኛም እዚህ ላይ መሥራት አለብን፡፡ ኅብረተሰቡንም በአጠቃቀም ረገድ ማስገንዘብ ይኖርብናል፡፡ የኢንተርኔት አጠቃቀም አስገራሚ በሆነ መልኩ በየዓመቱ 40 በመቶ እያደገ ነው ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ፡፡ የመገልገያ መሣሪያዎች መመዝገቢያ ቴክኖሎጂውን በተመለከተ እኛን የበለጠ የሚጠቅመን ገበያችንን ለማወቅ ነው፡፡ አሁን ዝም ብለን ነው 4G ተጠቀሙ 3G ተጠቀሙ እያልን መልዕክት የምንልከው፡፡ ይህንን ቴክኖሎጂ ብንጠቀም ግን ስንት 4G መጠቀም የሚያስችል ስልክ ተጠቃሚው ዘንድ አለ? ምን ያህሉ 3G ይጠቀማል? የሚለውን በተጨማሪም ምን ያህሉ ስልክ ሳምሰንግ ነው? ምን ያህሉ ቴክኖ ነው? የሚለውን ጨምሮ ለማወቅ ያስችለናል፡፡ አዲስ ነገርም አይደለም፡፡ ሁሉም አገልግሎት ሰጪዎች የሚጠቀሙበት ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ያው እኛ አገር አዲስ ነገር ሲመጣ የሚስተዋሉ ዕይታዎች ናቸው፡፡ ሌላው መንግሥትን የሚመለከት ነው፡፡ እንደ ስርቆትና ታክስን የተመለከቱ ነገሮችን ለመከላከል፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ ሲውል በእርግጠኝነት ስርቆትን ያስቀረዋል ወይም በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሰዋል፡፡ ባትሪ ለመስረቅ ካልሆነ ጥቅም አይኖረውም ስልኩ፡፡ የሆነ ሆኖ መንግሥት የኅብረተሰቡን ጥቅም በማይነካ መልኩ ተግባራዊ የሚያደርገው ጉዳይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ጥሪዎችን በመጥለፍ በአገር ውስጥ ቁጥር የሚያወጡ የኢትዮ ቴሌኮምን ሥራ በሕገወጥ መንግድ የሚሠሩ በርካታ ጥቃቅን ኦፕሬተሮች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉና አልፎ አልፎ ብቻ እንደሚያዙ ይነገራል፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም ሠራተኞችም የዚህ ተባባሪ ናቸው የሚል ወቀሳ አለ፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ አንዱዓለም፡- ይህ በጣም የተፈተንበት ችግር ነው፡፡ አሁን ትኩረት እየደረግን ያለነው እዚህ ችግር ላይ ነው፡፡ ከቦርዱም፣ ከሚከታተለን ሚኒስቴርም ሆነ ከሌሎች አካላት ድግፍ አግኝተን እየሠራንበት ያለ ጉዳይ ነው፡፡ እንደ ኩባንያ እያደማን ያለ ችግር ነው፡፡ ሁሉም የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የሚገጥማቸው ችግር ነው፡፡ የሚለየን ነገር መጠኑ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ስታንዳርዱ መሠረት በዚህ ስርቆት መታጣት ያለበት ገቢ (Revenue Leakage) ሁለት በመቶ ድረስ ነው፡፡ በመጭበርበር ሊሆን ይችላል፣ ቢል የማይደረግ ሊሆን ይችላል፣ በሌሎች ምክንያትም ሊሆን ይችላል፡፡ ከሁለት በመቶ በላይ መሄድ የለበትም ነው፡፡ ከዚህ በታች የሚያወርዱም አሉ፡፡ አንተ ያነሳኸው ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣ ጥሪን ወደ ኢትዮ ቴሌኮም እንዳይገባ አድርገው (By Pass) የሚያጭበረብሩትን ነው፡፡ ምንድነው የሚያደርጉት አሜሪካ ካሉ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ጋ ሄደው ይደራደራሉ፡፡ ጥሪ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ባስገቧቸው መሣሪያዎች የኢትዮ ቴሌኮም ኔትወርክ ዘሎ ወደ እነርሱ እንዲገባ ያደርጉና ጥሪው በኢትዮጵያ ቁጥር ለተደወለለት ሰው እንዲደርስ ያደርጋሉ፡፡ ስለዚህ እኛ በብር እናገኛለን እነርሱ በዶላር ያገኛሉ፡፡ ከውጭ ጥሪ የምናገኘው በዓመት የገቢያችንን ወደ 25 በመቶ ነበር፡፡ አሁን ግን እየወረደ ነው የመጣው፡፡ አሁንም ቢሆን የምናስገባው የውጭ ምንዛሪ ቀላል አይደለም፣ ነገር ግን እያጣን ነው፡፡ እስከነጭራሹ የሚደራደሩ ሁሉ አሉ፡፡ አሜሪካ ካለ ቴሌኮም ኦፕሬተር ጋ ሄደው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለ ቴሌኮም ኦፕሬተር በጥሪ ዋጋ ይደራደራሉ፡፡ እኛ ከምንሰጠው በታች የሚሰጡ በመሆኑ ኩባንያዎቹ እነሱን ይመርጣሉ፡፡ ይህንን ማድረግ አሜሪካ ውስጥ ወንጀል አይደለም፡፡ በዚህ ምክንያት አሜሪካ ውስጥ ያሉ ኩባንያዎች ቅናሽ ፍለጋ ከእኛ ጋር ስምምነት አይፈጽሙም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ጥሪዎች በኢትዮጵያ ቁጥር ሲወጡና ቁጥሮቹን ወዲያው እንዳወቅን ሲም ካርዱን እንዘጋዋለን፡፡ ነገር ግን ከመዝጋታችን በፊት ሁለት ሰዓት እንኳን ቢያስደውሉ ትልቅ ገንዘብ ነው ለእነሱ፡፡ ገንዘቡ ራሱ ወደ ኢትዮጵያ አይመጣም፡፡ እዚያው የባንክ አካውንት አላቸው፡፡ የአሜሪካው ኩባንያ እዚያው አካውንት ገንዘቡን ያስገባላቸዋል፡፡ እኔ አንዳንዴ ለምንድነው ጥሪ ወደእኛ የማትልኩት ብዬ ደብዳቤ እጽፋለሁ፡፡ አይ ከእናንተ ያነሰ ታሪፍ አግኝቻለሁ ይሉኛል፡፡ የት እኔ እኮ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛ ኦፕሬተር ነኝ ብዬ ብመልስም፣ አይ እኛ አግኝተናል ይሉኛል፡፡ ወንጀሉ በጣም አደገኛ ነው፡፡ ሲም ካርድ አስመስሎ መሥራት ድረስ የሚሄዱ አሉ፡፡ ሲም ካርዶቻችንን ኤክስፖርት ሲያደርጉ እኮ ተይዘዋል፡፡ እነዚህን ሲሞች ያባዟቸዋል፡፡ አንዷን ሲም አንድ ሺሕ ጊዜ ያባዟትና ይጠቀማሉ፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በሚጠቀሙት ሲም ካርድ አማካይነት ያሉበትን ቦታ ማወቅ ይችላል፡፡ አንዳንዶቹ ግን ይህንንም ማጭበርበር ይችላሉ፡፡ አዲስ አበባ ቁጭ ብለው እኛን ባህር ዳር ሊያሳዩን ይችላሉ፡፡ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ነገር ግን በሌባና ፖሊስ መንገድ መፍታት አንፈልግም፡፡

ሪፖርተር፡- ከግላዊ መብት ጋር በተያያዘ ኢትዮ ቴሌኮም ይወቀሳል፡፡ ሌሊት ላይ አጭር መልዕክት ያለ ግለሰቡ ፍላጎት በመላክ፡፡ የእከሌ ስልክ አሁን ክፍት ነው ደውልለት ዓይነት መልዕክት በመላክ የሰዎችን ግላዊ መብት (Privacy) ይጋፋል፡፡ ይህንን በተመለከተ ያቀዳችሁት ነገር አለ?

አቶ አንዱዓለም፡- ትክክል ነው፡፡ ደንበኞቻችን መከበር አለባቸው፡፡ የማይፈልጉት አጭር መልዕክት ሊደርሳቸው አይገባም፡፡ መላክ የለብንም፡፡ በተጨማሪም ሰዓት ማክበር ይኖርብናል፡፡ አሁን ከ11 ሰዓት በኋላ አንልክም፡፡ በተቃራኒው ደግሞ እሴት ጨምረው የሚሠሩ አጋር ድርጅቶች አሉን፡፡ እነሱ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በማምጣት መልዕክት ይልካሉ፡፡ እነሱም በሕጉ መሠረት የደንበኞችን ግላዊ መብት ሳይጥሱ እንዲሠሩ እያደረግን ነው፡፡ የብሮድካስት ኤጀንሲ ራሱ በዚህ ረገድ ሕግ አለው፡፡ እኛ አጭር መልዕክት መላክ የምንችለው የኢትዮ ቴሌኮምን ምርትና አገልግሎት ለማስተዋወቅ ነው፡፡ ሁለተኛ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ትላልቅ ጉዳዮችን በተመለከተ መልዕክት እንድንልክ ሕጉ ይፈቅድልናል፡፡ ደንበኛውን ሳናስፈቅድ ማለት ነው፡፡ ከእነዚህ ውጪ መልዕክት ለመላክ የደንበኛው ፈቃድ መጠየቅ አለበት፡፡ ከብሮድካስት ኤጀንሲ ጋር በመነጋገር ቢያንስ አንድ ጊዜ ፈቃደኛ ነህ ወይ የሚል መልዕክት ተልኮ ፈቃደኝነቱን ላልሰጠ ደንበኛ መልዕክት እንዳይልክ ተግባብተን በዚሁ አግባብ እየሠራን ነው፡፡ ይህንን የማያከብሩ እሴት የሚጨምሩ አጋር ድርጅቶችን ፈቃድ እስከ መሰረዝ እንሄዳለን፡፡ ተበዳዮችም በሕግ መጠየቅ ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ሌላው ከዚሁ የፕራይቬሲ ጉዳይ ሳንወጣ ኢትዮ ቴሌኮም እንደ መንግሥት ተቋምነቱ የመንግሥትን ፍላጎት በማክበር የደኅንነት ሥራ ወይም አገራዊ ሥጋቶች ሲገጥሙ ማኅበራዊ ድረ ገጾችን የመዝጋት ሥራ ይኖርበታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ቢዝነስ ተቋም መንቀሳቀስ አለበት፡፡ ይህንን ሚዛን እንዴት ነው መጠበቅ የሚቻለው? የደንበኞችን እምነትስ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል?

አቶ አንዱዓለም፡- የኢትዮ ቴሌኮም ሥልጣን በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም እንደዚህ ዓይነት ሥራ ውስጥ አይገባም፡፡ ኅብረተሰቡም ይህንን ሊያውቅ ይገባል፡፡ አንድ የግል ቴሌኮም ኦፕሬተር ሥራው አገልግሎት ሰጥቶ ደንበኞቹን ማርካት ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮምም ከዛ የዘለለ ሥራ የለውም፣ ሥልጣንም የለውም፡፡ ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ሥልጣን የተሰጠው አካል አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ነገር ግን ደንበኞች የሚገኙት የኢትዮ ቴሌኮምን መሠረተ ልማት ስለተጠቀሙ ነው?

አቶ አንዱዓለም፡- ይህ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ የእኛ መሠረተ ልማት የመንግሥት ነው፡፡ የመንግሥት ተቋማት ሊጋሩት ይችላሉ፡፡ አዲስ አበባ ፖሊስ ለምሳሌ የእኛን ታወሮች ተጋርተዋል፡፡ ሌላ ታወር መትከል ስለሌለባቸው፡፡ ሌላ መሬትም መውሰድ የለባቸውም ለዚህ ሲባል፡፡ ከዚያ ውጪ ግን ኢትዮ ቴሌኮም ኦፕሬተር ብቻ መሆኑን በእርግጠኝነት ልነግርህ እችላለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮ ቴሌኮም አሁን ግዙፍ እየሆነ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ሌሎች ኦፕሬተሮች ወደ ኢትዮጵያ ቢገቡ ማወዳደር ይችላል? ኢትዮ ቴሌኮም የግል እንዲሆን መንግሥት በቅርቡ ሊፈቅድ ይችላል? ይህ ቢሆን እርስዎ የሚመርጡት ምንድነው?

አቶ አንዱዓለም፡- ከመጨረሻው ልነሳልህ፡፡ ሦስት የተለያዩ አማራጮችን ልታይ ትችላለህ፡፡ አንደኛው ሙሉ በሙሉ ወደ ግል መዞር አለበት የሚሉ አሉ፡፡ አይ የለም ኢትዮ ቴሌኮም ይቆይ ሌሎች መግባት እንዲችሉ ይፈቀድ የሚሉ አሉ፡፡ ሌላኛው አይ ኢትዮ ቴሌኮም ብቻ በሞኖፖሊው መቀጠል ነው ያለበት ብለው የሚከራከሩ አሉ፡፡ የእኔ ግልጽ አቋም ሦስተኛው ነው፡፡ ወደ ግል ይዞታ መዞር የለበትም፡፡ ሌሎች እንዲገቡም መፈቀድ የለበትም፡፡ ምክንያቱም በጣም ገና ነው፡፡ የሁሉንም የዓለማችን ቴሌኮም ኦፕሬተሮች ታሪክ ብትመለከት መጀመሪያ የመንግሥት ነበሩ፡፡ ምክንያቱም ሁሉንም ሌሎች ዘርፎች የሚያሠራ ነው፣ ገንዘብ ነው፣ ጉልበት ነው፣ መረጃ ነው፣ ‹‹ኢኪውቲ›› የምታመጣበት ነው፡፡ እነ ፖላንድ ገና አሥር ዓመት አልሞላቸውም ወደ ግል ሲያዞሩ፡፡ እኛ እኮ ገና አሁን ነው ቀና ማለት የጀመርነው፡፡ ፈረንሣይ እኮ እስካሁን 30 በመቶ በመንግሥት እጅ ነው፡፡ ወደ አሜሪካ ብትሄድም ለራሳቸው ኩባንያዎች እኮ ነው የሰጡት፡፡ በስትራቴጂ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ዝም ብለህ ተነስተህ የምትበትነው አይደለም፡፡ የሚሰበሰበው ገንዘብ ወዴት ነው የሚሄደው ወደ ልማቱ ነው፡፡ እኛ የምሥራቅ አፍሪካ ማዕከል ነው መሆን የምንፈልገው፡፡ ሌሎች እንዲገቡ ቢፈቀድ ሱዳን ላይ የሚፈጠረው ነው የሚሆነው፡፡ ሱዳን ውስጥ ያሉ ኩባንያዎች ገንዘብ ይሰበስባሉ፣ ይዘው ይወጣሉ፡፡ ገንዘብ ይዘው የሚወጡት የሱዳንን አይደለም ወደ ብላክ ማርኬት ሄደው ወደ ዶላር ይቀይሩታል፡፡ ስለዚህ ወደ ተጭበረበረ የውሸት ኤክስፖርት ይገባሉ፡፡ ጣጣው ብዙ ነው፡፡ እኛ እኮ የሰበሰብነውን ገንዘብ መልሰን ለልማት ነው የምናውለው፡፡ እስካሁን 20 ቢሊዮን ብር ለባቡር ፕሮጀክቶች አውጥተን ደግፈናል፡፡ ገና ግብር በአግባቡ መሰብሰብ ባልቻልንበት ግብር ለመክፈል ፈቃደኛ ያልሆነ ነጋዴ ይዘህ ይህንን ማድረግ አዋጭ አይደለም፡፡ የበለፀጉት አገሮች ይህንን ሁሉ አልፈው ሙሉ ትኩረታቸውን ደኅንነትና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ ስላተኮሩ ነው ስለፕራይቬታይዜሽን የሚሰብኩት፡፡ እኛ እኮ ገና ከኢኮኖሚ ጥያቄ አልወጣንም፡፡ ስለዚህ መንግሥት አሁን የያዘውን አቋም ይዞ መቀጠል ነው ያለበት፡፡ እኛ እኮ አሁን ከ28 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ እያመጣን ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን እንደ ቢዝነስ ተቋም መሥራት ነው ያለብን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ለልማት ፕሮጀክቶች የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ተፈቀደ

የገንዘብ ሚኒስቴር በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በሎጀስቲክስ፣ በኮንስትራክሽን፣ የባለኮከብ ሆቴሎች...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

የውጭ ኢንቨስትመንት ባንኮች በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ እንዲሠማሩ የሚፈቅድ መመርያ እየተዘጋጀ ነው

በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን፣...

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...