መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን በማጥናት ዕርምጃ ለመውሰድ በመዘጋጀት ላይ እያሉ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የተገለጸው ሁለት ኤርትራውያን፣ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸውና የመኖሪያ አድራሻቸው ኤርትራ መሆኑ የተገለጸው ተጠርጣሪዎች፣ ካሳሁን ሸጌ እንዳለው (ቅጽል ስም ቆምጫጬ) እና ብርሃኔ ፀጋዬ አረጋዊ ይባላሉ፡፡
ተከሳሾቹ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፈራረስ ዓላማ አድርጐ ከሚንቀሳቀሰውና በቅርቡ ከግንቦት ሰባት ጋር የተዋሀደው የትግራይ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትሕዴን) አባል በመሆን፣ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ኤርትራ ውስጥ አሁቤት ካምፕ ከሚገኙ ከድርጅቱ አመራሮች ጋር መቀላቀላቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡
ካሳሁን የተባለው ተጠርጣሪ እስከ የካቲት ወር 2007 ዓ.ም. ድረስ ሥልጠና ወስዶ ሌሎችን ማሠልጠኑን፣ በድጋሚ ወደ ማሠልጠኛ ተቋም በመመለስ እስከ ጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም. ድረስ 120 የሚሆኑ የድርጅቱ አባላትን ያሠለጠነ መሆኑንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡
ተከሳሹ ከሌሎች የድርጅቱ አባላት ጋር በመሆን ወደ ኢትዮጵያ በመግባት፣ ስድስት ግለሰቦችን መመልመሉንና ወደ ኤርትራ በመውሰድ ከቡድኑ ጋር መቀላቀሉንም አክሏል፡፡
የሻዕቢያ መንግሥት የስለላ ክፍል ኃላፊና የቡድኑ ግንባር መሪ ጋር በመሆን፣ ከሱዳንና ከኢትዮጵያ ለቡድኑ አባል የሚሆኑ ታማኝነት ያላቸው፣ ብሔርና ቋንቋን መሠረት በማድረግ እንዲመለምሉ አቅጣጫ ተሰጥቷቸው፣ ብዙ ሰዎችን መመልመላቸው በክሱ ተካቷል፡፡
ተከሳሾቹ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ለይተው በማጥናት ዕርምጃ ለመውሰድ ከኤርትራ ግንዳይ ግንባር ተነስተው ሱዳን ከሰላ ሲደርሱ፣ ፍካሬ ኢብራሂም ከሚባል የኤርትራ ደኅንነት አመራር 1,575 የሱዳን ፓውንድ ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ፣ የካቲት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ሁመራ ላይ መያዛቸውን ክሱ ያብራራል፡፡
ብርሃኔ የተባለው ተከሳሽም የትሕዴን ወታደራዊ ማሠልጠኛ አምባ ተክል ማሠልጠኛ ገብቶ ከሌሎች 60 ሠልጣኞች ጋር አብሮ መሠልጠኑን፣ ወደ ኢትዮጵያ በመግባትም ሌሎች ወጣቶችን በመመልመል ወደ ኤርትራ ለሥልጠና መላኩን ክሱ ይገልጻል፡፡ እሱም በሱዳን አድርጐ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ሁመራ ላይ መያዙን ክሱ ይገልጻል፡፡
ተከሳሾቹ በአስተርጓሚ ክሱ ተነቦላቸው በማረሚያ ቤት ሆነው ክሳቸውን እንዲከታተሉ፣ መቃወሚያ ካላቸው እንዲያቀርቡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ለነሐሴ 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡