Tuesday, January 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹ግጭት በተነሳ ቁጥር ምክር ቤቱ ክልሎች ውስጥ ቸኩሎ ጣልቃ ሊገባ አይችልም›› ...

‹‹ግጭት በተነሳ ቁጥር ምክር ቤቱ ክልሎች ውስጥ ቸኩሎ ጣልቃ ሊገባ አይችልም›› አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ

ቀን:

‹‹የዘንድሮ ምክር ቤት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከነበሩበት የተሻለ ነው›› አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ፣ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር

ዘንድሮ በተጠናቀቀው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ የሥራ ዘመን በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ግጭቶችና የሞት አደጋዎችን ቢከሰቱም ምክር ቤቱ አፋጣኝ ምላሽ እየሰጠ አለመሆኑን ለሚቀርቡ ትችቶች፣ አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ምክር ቤቱ በሚመለከተው ጉዳይ ላይ የዘገየበት ነገር የለም፣ ቸኩሎም በክልሎች አንድ ጉዳይ በተከሰተ ቁጥር ጣልቃ ሊገባ አይችልም ሲሉ ትችቶችን አስተባበሉ፡፡

ሐሙስ ሐምሌ 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በምክር ቤቱ የመከላከያ አዳራሽ ከምክር ቤቱ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ ጋር በመሆን በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ በተጠናቀቀው የፓርላማ የመጀመሪያ የሥራ ዘመን ምክር ቤቱ ከምንጊዜውም በላይ የተሻለ የክትትል ሥራ መከናወኑን፣ ከሕዝብ ለተነሱ ጥያቄዎች በአግባቡ መልስ የተሰጠበት እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ምክር ቤቱ ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት በተመለከተ ከተደረገው ገለጻ በኋላ፣ ከጋዜጠኞች ለሁለቱ ባለሥልጣናት ጥያቄዎች ተነስተውላቸው ነበር፡፡ ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል ዘንድሮ በኦሮሚያ፣ በአማራና በጋምቤላ ክልሎች የተለያዩ ግጭቶች ተከስተው በመቶዎች የሚቆጠሩ መሞታቸውን፣ ፓርላማው በግጭቶቹ ምክንያት አስቸኳይ ስብሰባ አለመጥራቱ፣ ብሔራዊ የሐዘን ቀን አዋጅ በፍጥነት አላወጀም የሚሉ ትችቶችን አስመልክቶ ከሪፖርተር ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡

ለማሳያም ያህል በኦሮሚያ ተቀስቅሶ የነበረው ተቃውሞና ግጭትን በተመለከተ ከሦስት ወራት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በምክር ቤቱ ቀርበው ማብራሪያ እስኪሰጡ ድረስ፣ በፓርላማው ለምን እንዳልተነሳ ተያይዞ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ለዚህም ምላሽ የሰጡት አፈ ጉባዔ አባዱላ በፌዴራላዊ ሥርዓቱ መሠረት ክልሎች በራሳቸው አስተዳደር የሚያከናውኑበት ሥርዓት እያለ፣ ምክር ቤቱ ዘሎ ሊገባ እንደማይችል ገልጸዋል፡፡

‹‹ምክር ቤቱ በአንዳንድ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ይዘገያል ይባላል፡፡ መታወቅ ያለበት አገሪቱ ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ አገር ናት፡፡ የፌዴራል ሥርዓት ነው የምንከተለው፡፡ በዚህ ሥርዓት እያንዳንዱ የራሱ የሆነ ክልላዊ አስተዳደር አለው፣ የራሱ ምክር ቤትና የራሱ አስፈጻሚ ያለው ነው፡፡ በእያንዳንዱ ክልል በተከሰቱ ጉዳዮች የምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ይጠራል ማለት አይደለም፡፡ እነዚህን ማየት፣ ማጥራት አለብን፡፡ ክልሎች የሚሠሩትን የራሳቸውን ሥራ ማክበር ይገባናል፡፡ ከዚያ ካለፈ መጣራት የሚገባቸው ነገሮች በኮሚቴ እንዲጣሩ ይደረጋል፡፡ ነገር ግን አንድ ጉዳይ በተከሰተ ቁጥር በክልሎች እንግባ ብንል ሕጉም አይፈቅድልንም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹እንደ ጋምቤላ ያለውን ደግሞ ጉዳዩን ቀድመን ሳናጣራ ልንወስን የምንችለው ነገር የለም፡፡ ክስተቱ በተፈጠረበት ወቅት የተለያዩ ሚዲያዎች የተለያዩ ዜናዎችን ይዘው በሚወጡበት ሁኔታ ተቻኩሎ መሰብሰብ የሚያስፈልግ አልነበረም፡፡ የተሟላ መረጃ ሳይኖር በሩጫ የሚፈጸም ነገር የለም፡፡ ቢደረግም ጉዳት ይኖረዋል፡፡ በእኔ እምነት ምክር ቤቱ በሚመለከተው ጉዳይ ላይ የዘገየበትና የተጓተተበት ነገር የለም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡፡

በተጨማሪም፣ ‹‹ምክር ቤቱ ዓላማው የሞት ሪፖርት ማቅረብ ወይም ማድመጥ አይደለም፤›› ያሉት አፈ ጉባዔው፣ ምክር ቤቱ ግጭት ሲከሰት ወዲያው ከመጠየቅ ይልቅ ዘግይቶ የሞት ሪፖርት እስኪቀርብለት ይጠብቃል የሚለውን ትችት አጣጥለውታል፡፡

ለወደፊቱ የተለያዩ ክስተቶች ሊያጋጥሙ የሚችሉበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል የገለጹት አፈ ጉባዔው፣ ‹‹ምክር ቤቱ በሚያገባውም በማያገባውም ጉዳይ የሚያደርገው ነገር ይኖራል ተብሎ መገመት የማይቻል ነው፤›› ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ‹‹በአገራችን ምንም ችግር እንዲኖር አንፈልግም፡፡ ሰላም እንዲኖር እንፈልጋለን፡፡ የአንድ ነገር ችግር በሞት ቁጥር አይለካም፡፡ በዓለም ላይ እንደምናየው በሁለት ደቂቃ የቦምብ ፍንዳታ እስከ 200 ሰው ያልቃል፡፡ ስለዚህ አደጋው 200 ሰው ስለሞተ ወይም ስላልሞተ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ብቻ ሊቆስል ይችላል፡፡ ዋናው ጉዳይ የተቃጣው አደጋ ምን ዓይነት ነው የሚለው ነው እንጂ፣ የአደጋው መጠን በሞተ ሰው ብቻ የሚለካ አይደለም፡፡ ጉዳዩን ከሕገ መንግሥቱ አኳያ መመልከትና ከፌዴራላዊ አደረጃጀታችን አንፃር መመልከት ነው ተገቢው ጉዳይ፤›› ብለዋል፡፡

አፈ ጉባዔውም ሆኑ የመንግሥት ዋና ተጠሪው ምክር ቤቱ ከመራጩ ሕዝብ የሚነሱ ወቅታዊና አገራዊ ጉዳዮችን ተመልክቶ መልስ በመስጠት ረገድም ሆነ ሥራ አስፈጻሚውን አካል ተከታትሎ በመቆጣጠር፣ እንዲሁም ተገቢውን ክትትል በማድረግ የተከናወነው አፈጻጸም ከመቼውም ጊዜ የተሻሻለ እንደበር ገልጸዋል፡፡

የአሁኑ ምክር ቤት ሙሉ ለሙሉ በገዢው ፓርቲ አባላት የተያዘ መሆኑ እየታወቀ፣ በፊት ከነበሩት የፓርላማ ዘመናት እንዴት የተሻለ ሥራ ሠርቷል ተብሎ ሊመዘን እንደሚችል ለተጠየቁት ጥያቄ አቶ አስመላሽ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ይህ ጥያቄ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ የሕዝብ ጥያቄ በዚያ ደረጃ ብቻ መታየት የለበትም፡፡ በገዢው ፓርቲ አባላት መካከል በፖሊሲ ጉዳይ ምክር ቤት ውስጥ ክርክር ሊኖር አይችልም፡፡ በስትራቴጂም ሆነ በፕሮግራም ክርክር ማድረግ አይጠበቅባቸውም፤›› ሲሉ አቶ አስመላሽ አብራርተዋል፡፡

ነገር ግን በፖሊሲ ወይም በፕሮግራም ደረጃ ክርክር አይደረግም ማለት በአፈጻጸም ወይም በዕቅድ አተገባበር ዙሪያ ክርክር ሊኖር አይችልም ማለት እንዳልሆነ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ‹‹በሥራ አስፈጻሚው ያልታዩ ችግሮችን ጎልጉሎ ማውጣትና መተቸት የፓርቲ ዲሲፕሊን አይከለክልም፡፡ ይህ ደግሞ በተግባር ታይቷል፡፡ አንድ የምክር ቤት አባል ትችት ስላቀረበ ወይም በሥራ አስፈጻሚው የቀረቡ ሪፖርቶችን ላለመቀበል አቋም በመያዙ የተጠየቀም ሆነ የተገመገመ የለም፤›› ብለዋል አቶ አስመላሽ፡፡

ለአብነትም በዓመቱ ውስጥ 64 ሕጎች ቀርበው መፅደቃቸውን፣ ከእነዚህም ውስጥ ሦስትና አራት በሚሆኑ ሕጎች አባላት ተቃውሞና ድምፀ ተአቅቦ ማድረጋቸውን አቶ አስመላሽ አስረድተዋል፡፡

‹‹እኔ በምስክርነት መናገር የምችለው 1/3ኛ የምክር ቤት ወንበሮች በተቃዋሚዎች ተይዘው ከነበሩበት ወቅት ይልቅ፣ የዘንድሮው ምክር ቤት የተሻለ ነው፤››    በማለት ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...