Sunday, January 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮ ቴሌኮም በጐረቤት አገሮች ለመሰማራት መንግሥትን የፖሊሲ ድጋፍ ጠየቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

አሥር ኩባንያዎች በቀጣዩ ማስፋፊያ ለመሳተፍ ፉክክር ላይ ናቸው

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአፍሪካ ግዙፍ የገበያ መሠረት የያዘው ኢትዮ ቴሌኮም በአፍሪካ አገሮች ለመስፋፋት መንግሥት እንዲፈቅድለት ጥያቄ ማቅረቡን፣ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለሪፖርተር ገለጹ፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ አንዱዓለም አድማሴ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ‹‹ከድንበራችን ወጥተን መሥራት እንፈልጋለን፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በአቅራቢያችን ካሉ አገሮች ጋር መሥራት የምንችል በመሆኑ ፍቀዱልንና እንሥራ፤›› በማለት ጥያቄ ማቅረባቸውን የገለጹት አቶ አንዱዓለም፣ ይህንን ፍላጐት ከሚያበረታቱ የኢትዮ ቴሌኮም ቦርድ አባላት መካከል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የኮሙዩኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ይገኙበታል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የቴሌኮም ዘርፍን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ማድረግና ኢትዮ ቴሌኮምን ወደ ግል ማዘዋወር አለበት የሚል ዓለም አቀፍ ግፊት ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ ኢትዮ ቴሌኮም ወደ ሌሎች የጐረቤት አገሮች ለመስፋፋት ጥያቄ ማቅረቡ ተቃርኖን ያሳያል፡፡

አቶ አንዱዓለም ራሳቸውም ኢትዮ ቴሌኮም ሊሸጥ ይቅርና ለሌላ የውጭ የቴሌኮም ኩባንያም ፈቃድ መሰጠትም የለበትም የሚል አቋም የሚያራምዱ ናቸው፡፡

‹‹ይህንን ለማድረግ ገና ነን፡፡ እን ፈረንሣይ እስካሁን 30 በመቶ ድርሻ በፍራንስ ቴሌኮም ላይ አላቸው፡፡ አሜሪካም ብትሆን ሁሉን ነገር አልፋ ኢኮኖሚዋን ሊበራላይዝ ስታደርግ የቴሌኮም ዘርፍን ለአሜሪካ ኩባንያዎች እንጂ ለሌላ አልሰጠችም፤›› ብለዋል፡፡

በመሆኑም ገና የኢኮኖሚ ጥያቄዋ ያልተፈታ አገር ትልቅ ገቢ የሚያስገኝላትን ቴሌኮም መያዝ ይጠበቅባታል ብለዋል፡፡

‹‹ለምሳሌ አገር አቀፍ የባቡር ፕሮጀክቱ ላይ 20 ቢሊዮን ብር አካባቢ ድጋፍ ያደረገው ኢትዮ ቴሌኮም ነው፡፡ በአሁኑ ዓመት ብቻ 28 ቢሊዮን ብር ያስገባ ተቋም ነው፤›› የሚሉት አቶ አንዱዓለም፣ መንግሥት ዘርፉን ይዞ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት 47 ሚሊዮን የሞባይል ደንበኞች ያሉት ኢትዮ ቴሌኮም በዓለም አቀፉ የቴሌኮም ኅብረት የዚህ ዓመት ሪፖርት መሠረት ከአፍሪካ በግዙፍነቱ ሁለተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ ግዙፍ የኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ተንቀሳቅሶ ውጤት ያስመዘገበ አገር ወደ ጐረቤት አገሮች ቢገባ ‹‹ይሳካለታል›› የሚል እምነት አቶ አንዱዓለም አላቸው፡፡

‹‹ቻድ ሊሆን ይችላል፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን ብቻ ፈቃድ ይሰጠን ብዙም ሳንፈራገጥ ይሳካልናል፤›› ብለዋል፡፡

በተያያዘ ዜና ኢትዮ ቴሌኮም ሰሞኑን ባወጣው የማስፋፊያ ጨረታ አሥር ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ፉክክር ውስጥ እንደሚገኙ ከዋና ሥራ አስፈጻሚው ለመረዳት ተችሏል፡፡

ኖኪያ፣ ኤረክሰን፣ ሁዋዌና ዜድቲኢ ዋናዎቹ ተፎካካሪዎች መሆናቸውን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ያቀረቡትን ገንዘብም ሆነ ሌሎች ዝርዝሮችን መናገር ጨረታውን ያስተጓጉለዋል በማለት ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

በዋናነት ግን ገንዘብ ማምጣት የኩባንያዎቹ ግዴታ መሆኑንና የመንግሥት ዋስትናም እንደማይሰጣቸው ይህም በመሥፈርትነት መካተቱን ገልጸዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች