Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኩባንያዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት በድርድር ጭምር እንዲሳተፉ ተወሰነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ቦርድ በራሳቸው አቅም ወይም ከመንግሥት ጋር በሚደረግ ሽርክና በኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች በጨረታ ብቻ እንዲስተናገዱ ያወጣውን ትዕዛዝ በማሻሻል፣ ኩባንያዎቹ በድርድር ጭምር እንዲስተናገዱ መመርያ መስጠቱን ምንጮች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ቦርድ ቀደም ሲል በግልና በሽርክና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችን ለመገንባት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመው በመደራደር ላይ የነበሩ ኩባንያዎች፣ ድርድሩ ተቋርጦ በጨረታ ብቻ እንዲስተናገዱ ወስኖ ነበር፡፡

ነገር ግን በዚህ ውሳኔ ቅር የተሰኙ አገር በቀልና የውጭ ኩባንያዎች፣ አቤቱታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ቦርድ ሰብሳቢ ለኮሙዩኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል አቅርበዋል፡፡

ቦርዱ መንግሥት ለግሉ ዘርፍ እንዲሰጡ ያቀዳቸውን ፕሮጀክቶች በተለይ በርከት ያሉ ኩባንያዎች የሚፈልጓቸውን በጨረታ፣ አነስተኛ ወይም አንድ ኩባንያ ብቻ የሚፈልጋቸውን ፕሮጀክቶች ደግሞ በድርድር ለማስተናገድ ማቀዱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከ14 በላይ ኩባንያዎች በኃይል ዘርፍ ለመሰማራት ጥያቄ አቅርበው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ሲደራደሩ ቆይተዋል፡፡ ሁነኛ ኃይል አመንጪ ኩባንያዎችን ለማግኘት ጨረታ ተመራጭ መንገድ ነው በሚል ምክንያት የድርድር ሒደቶች እንዲቋረጡና ከዚህ በኋላ በጨረታ ብቻ መረጣ እንዲካሄድ ተወስኖ ነበር፡፡

ነገር ግን ኩባንያዎቹ ቅሬታቸውን ካቀረቡ በኋላ መንግሥት ውሳኔውን በድጋሚ መርምሮ ማሻሻያ ማድረጉ ተመልክቷል፡፡ በተለይ በጂኦተርማል ኃይል ማመንጫ ዘርፍ በግልና ከመንግሥት ጋር በሚደረግ ሽርክና በኃይል ግንባታ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አንዳንድ አሠራሮች እንዲስተካከሉ ጥያቄ ማቅረባቸውም ታውቋል፡፡

በተለይ የእንግሊዝ፣ የአሜሪካ፣ የእስራኤልና የጃፓን ኩባንያዎች በተለያዩ ጊዜያት በተናጠል አሠራሩ እንዲስተካከል ያቀረቡት ጥያቄ በመንግሥት በመታመኑ፣ የጂኦተርማል ሀብት ልማት አዋጅ ሐምሌ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. እንዲሻሻል ተደርጎ በድጋሚ ፀድቋል፡፡

በአዋጁ መሠረት በጂኦተርማል ኃይል ዘርፍ መሰማራት ለሚፈልጉ ኩባንያዎች ፈቃድ የሚሰጠው የኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለሥልጣን ነው፡፡

መንግሥት በአገሪቱ ያለውን ከፍተኛ የኃይል ማመንጫ ልማት በራሱ አቅምና ከውጭ በሚገኙ ብድር ብቻ ማካሄድ እንደማይችል፣ ይልቁኑም በግልና ከመንግሥት ጋር በሚደረግ ሽርክና ልማቱን ማካሄድ ተመራጭ መሆኑን የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልጉ የሕግ ማዕቀፎች የተዘጋጁ ሲሆን፣ በርካታ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን ከማሳየት በተጨማሪ ዝርዝር ዕቅዳቸውንም እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በጻፈው ደብዳቤም ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት በራስ ኃይልና በሽርክና ለመሰማራት ፍላጎት ያሳዩ ኩባንያዎች እንዲስተናገዱ ማሳሰቢያ መስጠቱ ታውቋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች