Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የንግድ ባንክና ኮንስትራክሽን ባንክ ሠራተኛ ማኅበራት ተዋሃዱ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአርባ ዓመታት በላይ ሲሠራ የቆየውን የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ እንዲጠቀልል መንግሥት ከወሰነ በኋላ የሁለቱ ባንኮች ቅርንጫፎች ተዋህደው፣ ሀብትና ንብረቱንም ንግድ ባንክ ተረክቦ መሥራት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡

በዚህ መካከል የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ መሠረታዊ የሠራተኛ ማኅበር ዕጣ ፈንታ ላይ ከንግድ ባንክ ሠራተኛ ማኅበር ጋር በመነጋገር በመጨረሻም የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ሠራተኛ ማኅበር በንግድ ባንክ ሠራተኛ ማኅበር ሥር እንዲዋሃድ መደረጉ ታውቋል፡፡

የሁለቱ ባንኮች ሠራተኞች ማኅበራት በይፋ መዋሃዳቸውን በማስመልከት ሐምሌ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. በታካሔደ ሥነ ሥርዓት ተገልጿል፡፡ በመሆኑም በንግድ ባንክ መሠረታዊ የሠራተኛ ማኅበር ሥር የተጠቃለለው የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ መሠረታዊ የሠራተኛ ማኅበር ከዚህ ቀደም የነበረው ሕጋዊ ሰውነት ተቋርጧል፡፡

ይህ ቢባልም ግን ኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ በንግድ ባንክ መጠቅለሉ ይፋ ከተደረገ በኋላ የቀድሞው የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ሠራተኞች በሥራ ምደባ፣ በደረጃ እርከንና በመሳሰሉት ላይ ቅሬታቸውን ሲያሰሙ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህንን በሚመለከት የቀደሞው ሠራተኛ ማኅበር ፕሬዚዳንት፣ በአሁኑ ውህደት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አብዱልሃኪም ሙሰማ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ ሲነሱ የነበሩት ችግሮች በባንኮቹ መካከል በነበረው የአሠራር ልዩነት ምክንያት የተፈጠሩ እንደነበሩ ጠቅሰዋል፡፡

በአቶ አብዱልሃኪም ማብራሪያ መሠረት፣ የምደባ ጉዳይ ጎልቶ ሲነሳ የነበረው በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች አመዳደብ ላይ የነበረው የሁለቱ ባንኮች የአሠራር ልዩነት የፈጠረው ነው፡፡ ‹‹ከደረጃ ዝቅ መደረግ አለያም ደግሞ ከሥራ ልምድ ማነስ አኳያ ሳይሆን፣ በእኛ ባንክ ሲሠራበት የነበረውና በንግድ ባንክ ያለው አሠራር መለያየት ያመጣው ነው፡፡ ይህ ሆኖም የደመወዝ ስኬል አልተነካም፡፡ እንደውም ከዚህ በፊት ከነበሩት ይልቅ አዳዲስ ጥቅማጥቅሞችን አግኝተናል፡፡ የነዳጅ ጥቅማጥቅም ጭማሪ ያለው ሲሆን፣ እኛ ያልነበረ የቤት ኪራይ አበል አግኝተናል፤›› ብለዋል፡፡

ሠራተኛው ሳይመደብ ቢቀርና የደመወዝ ደረጃ ላይ ችግር ቢኖር ኑሮ የሠራተኛ ማኅበሩ ጉዳይ ይሆን ነበር ያሉት አቶ አብዱሃኪም፣ ንግድ ባንክ ግን የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ሠራተኞች ባላቸው የሥራ ልምድ ልክ እየተቀበለ ለሁሉም ምድባ መስጠቱ የፈጠረው ችግር እንደሌለ፣ እንዲያውም በተላላኪነት ይሠሩ የነበሩ ወደ ላይ እንዲያድጉ ተደረገው ብር የማሸግ ሥራ ላይ መመደባቸውን አቶ አብደልሃኪም በአወነታዊነት ጠቅሰዋል፡፡

አንድም ጥያቄ ሳይቀነስና የሥራ ዋስትና ጥያቄ ውስጥ ሳይገባ ሁለቱ የሠራተኞች ማኅበራት መዋሃዳቸውን የገለጹት፣ የንግድ ባንክ አሁን የተዋሃደው የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ መሠረታዊ የሠራተኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ሰይፉ ቦጋለ ናቸው፡፡ ሁለቱም ማኅበራት በየራሳቸው ሕጋዊ ሰውነት ቢኖራቸውም፣ በአንድ ተቋም ውስጥ ሁለት የሠራተኛ ማኅበራትን ማንቀሳቀሱ ሠራተኛውንም ተቋሙንም ከመጥቀም ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን በማመን ወደ ውህደት መምጣት ማስፈለጉን ገልጸዋል፡፡

በሁለቱ የሠራተኛ ማኅበራት ውህደት ሳቢያ እስካሁን በአገሪቱ የማኅበራት ውህደት ሒደት ላይ ያልታየ ሥርዓት መታየቱን፣ ሠላማዊ በሆነ አካሄድ ከሁለቱም ማኅበራት ሥራ አስፈጻሚዎች ሽግሽግ ሲደረግ በስምምነት መከናወኑ በጥሩ ምሳሌነቱ ከሁለቱም ወገን ሲነገር ተደምጧል፡፡

የውህደት ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበሩትና ከውህደቱ በፊትም የንግድ ባንክ ሠራተኛ ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ አባይ ደምሴ ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ ሁለቱ ማኅበራት ከመዋሃደቸው ቀድሞ በተካሄደ ውይይት ሦስት አማራጭ ሐሳቦች ቀርበው ነበር፡፡ አንደኛው የሁለቱም ተቋማት የሠራተኛ ማኅበራት ሕጋዊ ሰውነታቸውን ይዘው ይቀጥሉ፣ ሁለቱም ማኅበራት ፈርሰው አዲስ ማኅበር ከሁለቱም ተውጣጥቶ ይመሥረት የሚሉ ሐሳቦችም ቀርበው ነበር፡፡ ይሁንና ይዋሃዱ የሚለው ብልጫ አግኝቶ ማኅበራቱ ለውህደት እንደበቁ ገልጸዋል፡፡

በሁለቱ ማኅበራት መካከል ያለው የሀብት ልዩነት አንዱ የውህደቱ ጥያቄ እንደነበር የጠቀሱት አቶ አባይ፣ በሁለቱ ማኅበራት መካከል ያለው ልዩነት ግን ከፍተኛ ሆኖ በመገኘቱ በሕግ ያላቸው እክል ሰውነት ታሳቢ ተደርጎ እንዲጠቀለሉ ስምምነት መደረጉን ይገልጻሉ፡፡ የንግድ ባንክ ሠራተኞች ማኅበር ሀብት ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን የገለጹት አቶ አባይ፣ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ገና እየተጠራ መሆኑን ሆኖም በቃል አለ ተብሎ የሚገለጸው ግን ከ700 ሺሕ ብር እንደማይበልጥ እየተነገረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የሁለቱም ማኅበራት ሥራ አስፈጻሚዎች አንድ ዓመት የሚቀራቸው በመሆኑ፣ እስከዚያው ድረስ ማለትም እስከ ነሐሴ 2009 ዓ.ም. ድረስ ከሁለቱ ማኅበራት የተውጣጣውና የተሸጋሸገው ሥራ አስፈጻሚ ማኀበር ሥራውን ይቀጥላል፡፡

የንግድ ባንክ ሠራተኞች ብዛት ከ26 ሺሕ በላይ ሲሆን፣ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ሲታከሉበት ከ28 ሺሕ በላይ መድረሳቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች