Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ኧረ ግራ አታጋቡን!

እነሆ መንገድ። ከስድስት ኪሎ ወደ ፈረንሣይ ልንጓዝ ነው። ከወትሮው ሞቅ ያለ ግርግርና ድንብርብር ታክሲ ተራውን አተራምሶታል። “ምንድነው ነገሩ?” ይሉኛል ጭጋግ የሸፈነው መነጽራቸውን አፍንጫቸው ላይ እያንሸራሸሩ። “ምን አውቄ ብለው ነው?” ሳይጠየቅ አንዱ መለሰላቸው። ሳይጠየቁ የሚመልሱ የበዙት የተጠየቁት ከነጎዱበት የምቾትና የማጭበርበር አገር አንመለስ ስላሉ ይሆናል። “ድሮስ እኔ አንተን መቼ ጠየቁኩህ?” ብለው አዟውንቷ መነጽራቸውን ሲያወልቁ ሌላ ሦስተኛ ሰው ተደርቦ፣ “የቺካጎን የኤሌክትሪክ ባቡር መብረቅ ስለመታው ሰው ባቡር መሳፈር ፈርቶ ታክሲ ስለመረጠ ነው፤” አላቸው። “እሰይ እሱም አንድ ነገር ነው፤” አሉ አዛውንቷ። “ምኑ?” ሲላቸው  ተደራቢው፣ “መምረጥ መቻሉ ነዋ፤” ብለው ሳቃቸው ቀደመ። “እንዴ! እንዴ! እሱማ ምን ጥርጥር አለው? የሃምሳ ቤቶችን ከፐ ዘር በስተቀር አበላልጦ የመምረጥ መብቱ የተጠበቀ ነው፤” ብሎ አንድ ጎልማሳ እዩኝ እዩኝ ይል ጀመር።

ወያላው “ኧረ ዝናብ አታስመቱኝ ገባ ገባ በሉ። እህል መሰልኳችሁ እንዴ? አልበቅልም እኮ፤” እያለ ይለፈልፍብናል። “የፐ  ምን ማለቱ ነው?” አዟውንቷ አሁንም ወደኔ እያዩ ሲጠይቁ አንድ የረጠበ ፂሙን እየላገ ተረጋግቶ የቆመ ወጣት፣ “ፖለቲካ ነው። ምንም አይሠራልዎትም። በጡረታ ዕድሜዎ ቀንቶ ነው፤” ብሎ ያን ጎልማሳ አሳጣው። “ጉድ እኮ ነው፤” እያሉ አዛውንቷ ፊት ሄደው ገቡና መሀል መቀመጫ ላይ ሥፍራ ያዙ። ሄጄ አጠገባቸው ተቀመጥኩ። ከእኛ ጀርባ ጎልማሳውና ፂማሙ ወጣት ተቀመጡ። መጨረሻ ወንበር ፀጉሯንና ጭኗን በብጣቂ ስስ ፌስታልና ጨርቅ ነገር የሸፈነች ሎጋ ዘመናይ ቀጥሎ ባለሱቅ ነኝ የሚል፣ ከዚያ ደግሞ ዝምተኛ ‘ዳዲ ኬፕ’ የጨሰ ጎልማሳና አንድ ልጅ እግር ተሳፋሪዎች አሉ። ከፊት ሌሎች። እንደ ፊትና ኋላ አቀማመጣችን ሐሳባችንም ፊትና ኋላ ሆኗል ዘንድሮ!

ጉዟችን ተጀምሯል። የክፍል ኃላፊ መምህሩ ደርሶ ከች እንዳለበት ረብሸኛ ክፍል ግማሹ የታክሲያችን ተሳፋሪ በብብቱ የያዛትን መጽሐፍ እያወጣ ማንበብ ጀመረ። ‹‹ምን ጉድ ፈላ?›› አሉ አዟውንቷ ግር ብሏቸው። ከፊታችን የተሰየመች ቀጭን ወዟ የደረቀ ወጣት፣ ‹‹ንባብ ለሕይወት በሚል መፈክር ተነቃቅተን ማንበብ ጀምረናል። በወሬ ብቻ አገር አይቆምም ተባብለን አንድ ፊደልና ብዕር እስኪቀር ለማንበብ ቆርጠን ተነስተናል፤›› አለቻቸው። አዟውንቷ ብቻቸው በፈገግታ ውስጥ ቆይተው፣ ‹‹ወረት አይሁን እንጂ ሸጋ ነው፤›› ብለው ዝም ቢሉ ከጀርባችን የተሰየመው ጎልማሳ እጅ ሳያወጣ፣ ‹‹ጸሐፊ ሲኖር እኮ ነው የሚነበበው፤›› ብሎ የማይወጣው ነገር ውስጥ ገባ። ‹‹እሺ ሐያሲው? ንገረን እስኪ ማንን እናንብብ?›› ብሎ ጢማሙ ፀብ ፀብ ሲለው ጎልማሳው ዘወር ብሎ፣ ‹‹መጀመርያ ራስህን አንብብ፤›› አለው።

‹‹ራሴን ለማንበብ መሰለኝ ሌሎች የጻፉትን የማነበው?›› ስትል የፊተኛዋ፣ ‹‹ለዛ አይደል መናበብ ያቃተን?  ሁሉም ጣት ቀሳሪ፣ ሁሉ ችግሩን በቁስ አካላዊ አተያይ ብቻ ተመልካች፣ እኔስ ማነኝ ቤቴስ ምንድነው? የሚል ብዕር የሌለው ተነቦ ነው ተነጋግሮ መግባባት፣ መናበብና መደማመጥ የሚመጣው?›› ብሎ ጨለምተኛው ጎልማሳ ነገሩን ሲያሳክረው፣ ‹‹ፀጥታ! እናንብብበት። እስከ ዛሬ የሰማናችሁ ይበቃል!›› አለ መጨረሻ ወንበር የተቀመጠው ልጅ እግር። ‹ፍየል ከመድረሷ ቅጠል መበጠሷ› ተረተበት። ‹‹እኔ ግን የምለው እዚህ አገር የሚጀመር ነገር ሁሉ በዘመቻና በመፈክር ካልሆነ አይሰምርም ማለት ነው?›› ስትል ያች ዘመናይ፣ ‹‹ቀድሞ ነገር በመፈክርና በዘመቻ ተጀምሮ ሲሰምር ያየሽው ነገር አለ?›› አላት ነገር ነገር ያለው ጎልማሳ። ‹አቦ እናንብብበት› ሲል የአንባቢው ግሩፕ ይጮሃል። የወትሮው ጫጫታ ምሁራዊ ሙግት በመሰለ ውኃ የማይቋጥር ጫጫታ ይደምቃል። ይኼም የጉዟችን አካል ነው!

ጋቢና ከተሰየሙት ሁለት ሴቶች አንደኛዋ በስልክ ከጓደኛዋ ጋር እያወራች ነው። ‹‹ባክሽ ሰሞኑን ታይት ነኝ፤›› ስትል አዟውንቷ ሰሙ። ‹‹እንዴት ነው ነገሩ እነዚህ ልጆች ልብሱ አላረካ ቢላቸው እነሱ ራሳቸው ልብሱን መሆን ጀመሩ ደግሞ። ይኼ ታይት የሚባል ቅጥ የለሽ ነገር እኮ በጠበጠን እናንተ፤›› እያሉ ያማትቡ ጀመር። ‹‹መቼም ይህቺን ይህቺን ሰበብ አድርገን ግንብ እገነባለሁ የሚል ኢትዮጵያዊ ዶናልድ ትራምፕ በቀጣዩ ምርጫ እንዲወዳደር እየጠበቅን ባልሆነ፤›› ሲል አንዱ፣ ‹‹እስከሚቀጥለው ምርጫ በሰላም መድረሳችንን በምን አወቅክ?›› ሲል ሰምተን ሌላው ማን ይሆን ብለን ወደኋላ ስንዞር፣ ‹‹ምርጫ? ምንድነው ምርጫ?›› ብሎ ከፊት ሌላ ተሳፋሪ ፊቱን ሳያስመታ የልቡን ተናገረ። ‹‹ተው! ተው›› እናንተ ልጆች ኋላ፤ ቀዳዳ ጆንያ ሲያፈስ አይታይም ተው ኋላ! አስታዋሽ በሌለው ራስ ወዳድ አገር፣ አገር አገር ባይ ነው የሚደነጋገር . . . ተው ኋላ! ብያለሁ፤›› እያሉ አዟውንቷ መቆጣት ጀመሩ።

‹‹አይዞዎት እማማ። እኛ ለኮሜንት እንጂ ለብሎክ አንወዳደርም ሞኞች አይደለንም፤›› እያለ ፂማሙ ወጣት ሲያፅናናቸው፣ ‹‹ግን አንተ ኢትዮጵያዊ ትራምፕ የተባለው ሰው የሚገነባው ግንብ ማንንና ማንን ለመለያየት ነው?›› ብሎ ባለዳዲ ኬፕ ጠየቀ። ‹‹አልተለያየንም እንዴ እስካሁን?›› ብላ ጋቢና ያለች ተሳፋሪ ስታሸሙር፣ ‹‹በታይት ለባሽና በስኪኒ ለባሽ መሀል መስመር ለማስመር ነዋ፤›› አለ ጎልማሳው። ‹‹አንድ መስሎኝ ሁለቱም . . .›› ስትል ባለሚኒዋ ሲያቀብጣት፣ ‹‹ታዲያ ሌላማ ምን ያልተለየ ነገር አለ ቆንጂት? የቀረን አንድነት የልብስና የፋሽን ነው፤›› ብሎ ነገር በልቶ ነገር አስበላን። ያደለው ዋንጫ ይበላል እኛ እህል ሳንበላ ነገር እንበላለን!

ወያላችን ሒሳብ ተቀብሎ መልስ ማደል ጀምሯል። ‹‹ቻይና የፕላስቲክ ሚሳይል ማክሸፊያ ሠራች የሚባለው እውነት ነው?›› ብሎ አንዱ ጨዋታ አስቀየረን። ‹‹ወይ ቻይና! ስንቱን አከሸፈው ስንቱን ተቆጣጥረው?  ስንቱን አምታታው ይዘልቀዋል ግን?›› አለ ከሾፈሩ ጀርባ የተሰየመው ወጣት። አዛውንቷ፣ ‹‹ከእኛ ጋር ጦርነት አስበው ይሆን?›› ሲሉ ታክሲያችን በምፀት ሳቅ ተናጠች። ‹‹እኛ? ማነን እኛ? ስንት ነን እኛ?›› ሲል ጎልማሳው አሁንም ያቺን ጎሉን ፍለጋ፣ ‹‹እኛን ሳይዋጉ አሸንፈውን ምን ብለው ይዘጋጁልናል እማማ። ይኼው ወረውናል፤›› አለች ቆንጂት። ‹‹ኧረ እባካችሁ ወሬ እያጣመሙ መንዛት አይበጅም ተው። መቼ ወረሩን? ኑ አግዙን አልናቸው መጡ። ይኼ ሁሉ መንገድ፣ ቀለበት አልቦ አምባር፣ ወዘተ. ቻይና ባትመጣ ይሠራል?›› ስትል ንባብ ሕይወቴ እያለች የምትንዘረዘረው ወጣት፣ እሱንማ ከአንቺ በፊት ቴሌቪዥኑ ደጋግሞ ደጋግሞ አውርቶ ጠገብነው። ይልቅ አሁን ጥያቄው ሂዱ ቢባሉ ይሄዳሉ ወይ ነው?›› ሲል ጎልማሳው ፂማሙ ቀበል አድርጎ፣ ‹‹ዓለም ወደ አንድ መንደር እየጠበበች ባለችበት በዚህ ጊዜ፣ ሕዝብ ከሕዝብ እየተፈላለገ ለጥምረት፣ ለንግድ፣ ለባህል፣ ለትውፊትና ለተሞክሮ በቋመጠበት በዚህ ጊዜ እኛስ ብንሆን ለምን ሂዱ እንላለን?›› ብሎ አፈጠጠበት። ‹‹በቃ። ኢትዮጵያ ልዩ ባህልና ታሪክ ያላት አገር ናት። ምንም ቢሆን ምን ፈረንጅ ሁሌም ጠላታችን ነው። አባቶቻችን አሻፈረኝ ብለው ያባረሩትን ዘር እኛ ገና ለገና ችግር ፈርተን መንበርከክ አለብን?›› ሲል መላው የታክሲያችን ተሳፋሪ ተደናግጦ እየዞረ አየው። አሁን ይኼ አስተሳሰብ ልዩነትን የማቻቻል አቅሙ ምን ድረስ ነው? መርሁና እኛ ስላልተመጣጠንን አይመስላችሁም በዚህም በዚያም መንገድ አደናቃፊ የበዛው?!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። መጨረሻ ደርሰን ለመቆም ጥቂት ሲቀረን መንገዱ በጎርፍ ስለተጥለቀለቀ አማራጭ መፈለግ ግዴታ ሆነብን። ሁለት የትራፊክ ፖሊሶች ፊትና ኋላ ቆመው ተሽከርካሪዎችን ያስተናብራሉ። ልክ ተራችን ሲደርስ ከፊት ለፊታችን ያለው የትራፊክ ፖሊስ ሾፌራችንን፣ ‹‹ወደኋላ ዞረህ ተመለስና በሚቀጥለው መታጠፊያ ግባ፤›› አለው። የኋላኛው የታክሲያችንን መሪ መሸብለል ሲያይ እየሮጠ መጥቶ፣ ‹‹የለም ወደፊት ቀጥል እንዳትዞር፤›› ብሎ ጮኸ። ሾፌራችን በትህትና መጀመርያ የተቀበለውን ትዕዛዝ እየፈጸመ እንደሆነ አስረዳ። የትራፊክ ፖለሱ ተናደደ። ‹‹እኔን ስማኝ እሱን ተወው፤›› አለው ጮክ ብሎ። ይኼኔ ያ ከፊት ለፊታችን የቆመው እየሮጠ መጥቶ፣ ‹‹ትዞራለህ አትዞርም?›› ብሎ ከኪሱ 13 ቁጥር መፍቻ አወጣ። ሾፌሩ ሳንዱች ሆነ።

ትራፊክ ፖሊሶች አጠገብ ላጠገብ ሆነው አይነጋገሩም። ብቻ አንዱ ያዘዘውን ትዕዛዝ ሌላው እዚያው አጠገቡ ቆሞ ለመሻር አሰፍስፎ ቆመው ይገለማመጣሉ። ይኼው ነው። ያ የትኩስ ድንች ቀልድ ነገር አሁን ነው የመጣው። ‹‹የበላይ ለበታቹ ይወረውራል፣ የበታቹ ለበታቹ እያለ ወርዶ መጨረሻ ሕዝብ ይደቆሳል፤›› ብሎ ጎልማሳው ሲጀምር ሁሉም በምሬት ያግዘው ጀመር። አዛውንቷ መስኮታቸውን ከፍተው፣ ‹‹ምናለበት የሰው ክብር ቢኖራችሁ? የእኛን ጊዜ እየገደላችሁ እናንተ እኔ እበልጤ እኔ እበልጥ ዕቃ ዕቃ ትጫወታላችሁ?›› ሲሉት አንደኛውን ትራፊክ፣ ‹‹እርስዎ የሚያገባዎት ነገር የለም። ከእኔ ጋር መነጋገር አይችሉም፤›› አላቸው። ከአንቱታው ሌላ የንቀቱ ቁልቁለት መጨረሻ አልነበረውም። ‹‹ምን ዓይነት ጊዜ ላይ ደረስን?›› ስትል ቆንጂት ከሷም ብሶ፣ ‹‹የዕድገት፣ የብልፅግናና የሰላም ጊዜ ላይ ነዋ፤›› አላት ባለዳዲ ኬፑ። ‹‹እኮ ወደኋላ ወይስ ወደፊት? ኧረ እባካችሁ ንገሩን?›› ሲል አንዱ ከመሀል ወንበር፣ ‹‹ወዳጄ ወደ ጎንም አትርሳ፡፡ ቁም ነገሩ እንቅስቃሴው እንጂ አቅጣጫው አይደለም፡፡ ገባህ?›› ሲለው እንኳን ጠያቂው እኛም አልገባንም ነበር፡፡ እንዲህ ጥልቅ እያሉ ግራ የሚጋቡ አልበዙም? ኧረ ግራ አታጋቡን!  መልካም ጉዞ!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት