Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የከተማ ጤና ችግሮች ለጤና ዘርፍ ብቻ መተው የለባቸውም››

ዶ/ር ሚርጊሳ ካባ፣ የከተማ ጤና አማካሪ ቡድን መሪ

ዶ/ር ሚርጊሳ ካባ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጤና ክፍል ባልደረባ ናቸው፡፡ ሶሲዮሎጂ ከዚያም አንትሮፖሎጂ አጥንተዋል፡፡ በጅማ ዩኒቨርሲቲም መምህር ነበሩ፡፡ ሲሠሩ የነበረው በጤና ዘርፍ ስለነበር የጥናት ትኩረታቸውን ጤና ላይ በማድረግ ፒኤችዲያቸውን በማኅበረሰብ ጤና ዘርፍ ሠሩ፡፡ በአጠቃላይ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ከአሥር ዓመት በላይ ሲያገለግሉ በአዲሰ አበባ ዩኒቨርሲቲ መሥራት ከጀመሩ ደግሞ ከሦስት ዓመት በላይ ሆኗል፡፡ ከዚህ ባሻገር ደግሞ በቅርብ የተቋቋመው የከተማ ጤና አማካሪ ቡድን (Urban health think tank) መሪ ሆነው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ በአማካሪ ቡድኑ እንቅስቃሴና በከተማ ጤና ጉዳዮች ዙሪያ ምሕረት አስቻለው ከዶ/ር ሚርጊሳ ካባ ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች፡፡ 

ሪፖርተር፡- የከተማ ጤና አማካሪ ቡድን የማቋቋሙ እንቅስቃሴ እንዴት ተጀመረ?

ዶ/ር ሚርጊሳ፡- መንግሥት ልክ የገጠር ጤና ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደተነሳው የከተማ ጤና ላይም የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ደግፎ ይመስለኛል እ.ኤ.አ. ከ2009 ጀምሮ እንቅስቃሴ ጀምሮ ነበር፡፡ ለዚህ ዩኤስኤአይዲ ድጋፍ ሰጪ፣ ጄኤስአይ በሚባል ተቋም ተግባሪነት ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር ሆነው ይሠራሉ፡፡ ይህ ፕሮግራም ሲጀመር አማካሪ ነበርኩና ፕሮግራሙ ሲገመገም የተረዳነው ነገር በእርግጥ የተሠሩ ጥሩ ሥራዎች ቢኖሩም የከተማ ጤና እንደገጠሩ በኤክስቴንሽን ፕሮግራም ሊሠራ የሚችል አለመሆኑን ነበር፡፡ ይልቁንም በቀጣይ እንደገጠሩ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ሳይሆን ሰፋ ብሎና የከተማ ቅርፅ ይዞ መተግበር አለበት የሚል ነገር ላይ ነበር የደረስነው፡፡  

ሪፖርተር፡- እዚህ ሐሳብ ላይ የተደረሰው እንዴት ነበር?

ዶ/ር ሚርጊሳ፡- የከተማ ጤና የአንድ ተቋም ጉዳይ ባለመሆኑ የተወሳሰበ ነው፡፡ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች እንደገጠሩ ቤት ለቤት ሊዞሩ አይችሉም፣ የከተማ ኗሪ እንደ ገጠሩ የሕክምና አገልግሎት ተደራሽነት ችግርም የለበትም ምክንያቱም የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በየቦታው ይገኛሉና፡፡ ጤናን የሚመመለከት መረጃ እጥረትም በገጠሩ ደረጃ የለም፡፡ አንዱ የሐሳቡ መነሻ ከከተማ ጤና ጋር በተያያዘ የሚሰጠው አገልግሎት ከገጠሩ የተለየና የተሻለ መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው በከተማ ጤና እንደ ግንባታ ዘርፍ፣ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን፣ የትምህርትና ሌሎችም ዘርፎች የሚመለከታቸው መሆኑ ነው፡፡ የከተማ ጤና ጉዳይ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ የገጠሩ ጤናም ቢሆን በተወሰነ መልኩ ዘርፈ ብዙ ነው ስለዚህም የጤናው ዘርፍ ሊሠራ የሚችለው ሥራ በጣም ሰፊ ነው፡፡ በንፅፅር ሲታይ ከተማ ላይ ሌሎች ዘርፎች ከጤና ተቋም ጋር ሆነው ሊሠሩ የሚገባቸው በርካታ ሥራዎች አሉ፡፡ በዚህ ረገድ ጄኤስአይ ከጤና ጥበቃ ጋር በመሆን በሁለተኛ ዙር በተጠቀሰው መልክ መንቀሳቀስ ሲጀምር የአዲስ አበባ የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤትም የእንቅስቃሴው አካል ሆነ፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ የትምህርት ቤቱ ኃላፊነት የሚያተኩረው የከተማ ጤናን በሚመለከት የመረጃ ችግር አለ የለም የሚለውን ማጥናት፣ የከተማ ጤናን የሚመለከት መረጃስ የሚገኘው የት ነው? የከተማ ጤናን በሚመለከት የምርምር ሥራዎችና ፖሊሲ ግንኙነት አላቸው ወይ? በማሉት ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ የመጨረሻውን ለምሳሌነት ብንመለከት ብዙ ጥናቶች የምርምር ሥራዎች ይካሔዳሉ በተለያየ መንገድም ይሠራጫሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሥራዎች ፖሊሲና ፕሮግራም ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩት በጣም ውስን በሆነ ደረጃ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የምርምር ውጤቶችና ፖሊሲዎች አይነጋገሩም ለከተማ ጤናም የተፈጠረ ነገር የለም የሚል ግምት ያስወስዳል፡፡ ስለዚህ በምርምርና በፖሊሲ መካከል ድልድይ የሚፈጠረው እንዴት ነው የሚለው ታሳቢ ተደርጓል?

ሪፖርተር፡- በከተማ ጤና ላይ የተሠሩ ጥናቶች አሉ?

ዶ/ር ሚርጊሳ፡- ከተማ ጤና ላይ ምን ምን ተሠርቷል የሚለውን ስንመለከት ይህ ነው የሚባል የተሠራ ነገር አይገኝም፡፡ በተሠሩ ሥራዎች ላይም ከተሞች በጥቅሉ እንደ ከተማ ባህርዳር፣ አዲስ አበባና ሐዋሳ እየተባሉ ነው የታዩት፡፡ በጥቅል ሳይሆን በከተሞች ውስጥ ያለው ልዩነት መታየት ይኖርበታል፡፡ በከተማ ውስጥ የአገልግሎት አሰጣጥ ልዩነቶች አሉ፡፡ አንዳንድ የከተማ ክፍሎች ላይ ከሞላ ጐደል ከገጠር ጋር የሚመሳሰል ነገር ይታያል፡፡ በከተማ ውስጥ ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎች አሉ በእነዚህ ቦታዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ ለበርካታ የጤና ችግሮች ይበልጥ የተጋለጡ ናቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች አሁን እየተጠኑ ነው፡፡ የከተማ ጤና አገልግሎት ጥራት ምን ይመስላል ጥራትን አዳጋች ያደረጉ ነገሮችስ ምንድን ናቸው? ጥራትስ እንዴት ነው የሚለካው ኅብረተሰቡስ ረክቷል ወይ በሚሉት ነገሮች ላይ ይሔ ነው የሚባል የተሠራ ሥራ የለም፡፡ እዚህ ላይ አሁን ጥናት እየተሠራ ነው፡፡ ትልልቅ የከተማ ችግሮች የሚባሉት የትኞቹ ናቸው የሚያያዙትስ ከምን ጋር ነው የሚሉ ነገሮችም በጥናቱ እየታዩ ነው፡፡ ጥናቶቹ በተማሪዎቻችንና በመምህራን የሚሠሩ ናቸው፡፡ በሌሎች አካላት የከተማ ጤና ላይ የተሠሩ ሥራዎችን መሰብሰብም ሌላው ኃላፊነታችን ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- የመረጃ ማዕከል አቋቁማችኋል?

ዶ/ር ሚርጊሳ፡- የከተማ ጤና ላይ ያሉ መረጃዎችን ሰዎች ማግኘት ቢፈልጉ በሚል የመረጃ ማዕከሉን አቋቁመናል፡፡ ማዕከሉ በዓለም አቀፍ፣ በአፍሪካና በኢትዮጵያ ደረጃ የከተማ ጤና ላይ የተሠሩ ጥናቶችን አደራጅቶ ለተመራማሪዎች፣ ለፖሊሲ አውጪዎች፣ ለጋዜጠኞችና ለሌሎችም ያስቀምጣል፡፡ መረጃዎቹ ኦንላየንም እንዲገኙ መንገድ ፈጥረናል፡፡ ማዕከሉ የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅዶች አሉት ሥልጠናዎችን መስጠት፣ የዲግሪ ፕሮግራም መጀመር ይገኙበታል፡፡

ሪፖርተር፡- አማካሪ ቡድኑ እንዴት ተቋቋመ?

ዶ/ር ሚርጊሳ፡- በአገሪቱ የኅብረተሰብ ጤና ላይ ረዥም ጊዜ የሠሩና አንቱ የተባሉ ባለሙያዎችን በማሰባሰብ አማካሪ ቡድኑ ተቋቋመ፡፡ ዓላማው በፖሊሲና መሬት ላይ ባለው እውነታ መካከል የለውን ቅርበት ማጐልበት ነው፡፡ የቡድኑ ሥራ የሚሆነው ለፖሊሲና ፕሮግራም አውጪዎች ይሔ ጉዳይ እንደዚህ ነው ብሎ ማማከር ነው፡፡ ቡድኑ ከተቋቋመ ወራቶች የተቆጠሩ ሲሆን፣ ሦስተኛውን ዙር ስብሰባ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ነው፡፡ ድጋፍን መጠቀም አለመጠቀም የተጠቃሚው ውሳኔ ሲሆን፣ የቡድኑ ዋና ዓላማ በከተማ ጤና ላይ በመረጃ የተደገፈ ድጋፍ መስጠት ነው፡፡ አማካሪ ቡድኑን ለማቋቋም የተደረጉ እንቅስቃሴዎች ወደ ዘጠኝ ወር ገደማ ወስደዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከጊዜው አንፃር የአማካሪ ቡድኑ መቋቋም አስፈላጊነት ምን ያህል ነው?

ዶ/ር ሚርጊሳ፡- ኢትዮጵያ ወደ ከተሜነት እየሔደች ነው፡፡ እንደሚታየው 18 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ከተሜ ነው፡፡ በ2050 ደግሞ 38 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተማ ውስጥ ይኖራል ተብሎ ይገመታል፡፡ ስለዚህ የከተማ ኗሪ ቁጥር እንዲህ እየጨመረ የሚሔድ ከሆነ የከተማ ጤና ጉዳይም ውስብስብ እየሆነ ይሔዳል ማለት ነው፡፡ እነዚህን ውስብስብ ችግሮች እንደፀባያቸው መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው አማካሪ ቡድኑ ያስፈለገው፡፡ ለምሳሌ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ብንመለከት በአመጋገባችን ከአጠቃላይ የአኗኗር ዘዬአችን ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ እነዚህ በሽታዎች አንዳንዶቹ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ሥራዎች መከላከል የሚቻሉ ናቸው፡፡ ከውጥረትና ከጭንቀት፣ ከመኪና አደጋ ጋርም የተያያዙ አሉ፡፡ እነዚህ ውስብስብ የከተማ ጤና ችግሮች ለጤና ዘርፍ ብቻ መተው የለባቸውም፡፡

ሪፖርተር፡- የትኞቹ ዘርፎች በአማካሪ ቡድኑ ተወክለዋል?

ዶ/ር ሚርጊሳ፡- ጤና ጥበቃ፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የከተማ ልትና ከኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ በአማካሪ ቡድኑ ተወክለዋል፡፡ ከግል ዘርፉ እንዲሁም እንደ ዓለም ጤናና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕፃናት መርጃ ድርጅት፣ ዓለም ባንክ፣ ዩኤስኤአይዲና ጄኤስአይ የመሰሉ ተካትተዋል፡፡ ከግሉ ዘርፍ እንደ ባለሙያ በግላቸው የአማካሪ ቡድኑ አባል የሆኑም አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- አማካሪ ቡድኑ የተነጋገረበትን ነገር፣ ምክረ ሐሳቦችንስ እንዴት ነው የሚያሠራጨው?

ዶ/ር ሚርጊሳ፡- ፖሊሲ ብሪፎች፣ ዜና መዋዕሎች ይዘጋጃሉ፡፡ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር በመተባበር የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀትም ሌላው መንገድ ነው፡፡ አማካሪ ቡድኑ የከተማ ጤና ጉዳይ ከአንድ ዘርፍ በላይ ነው ይላል፡፡ እዚህ ላይ አስምሮ ሌሎች ዘርፎች በጋራ ሆነው የሚሠሩበትን መንገድ መቀየስም ኃላፊነቱ ነው፡፡ የአማካሪ ቡድኑ እንቅስቃሴ በአጠቃላይ የከተማ ጤናን አንድ ዕርምጃ ወደፊት መውሰድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአማካሪ ቡድኑ የአጭር ጊዜ ዕቅድ ምንድን ነው?

ዶ/ር ሚርጊሳ፡- የተለያዩ ዘርፎች የከተማ ጤና ጉዳይ ይመለከተኛል ብለው እንዲመጡና ከጤናው ዘርፍ ጋር እንዲሠሩ ማስቻል፡፡ በከተማ ውስጥ በተለየ መልኩ የተጐዳ ቦታ የተለየ ችግር ያለበት አለ ካልን ይህን በመረጃ አስደግፎ የሚመለከታቸውን አካላት ማሳመንም በቅርብ በተጨባጭ እየተሠሩ ካሉ ሥራዎች መካከል ነው፡፡ በከተማ ጤና የዲግሪ ፕሮግራም መጀመር ደግሞ የረዥም ጊዜ ዕቅዳችን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በከተማ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ይህን ያን ያህል ነው በማለት ቁጥር ሲቀመጥ ይታያል፡፡ የዚህ ዓይነቱ መረጃ እንዴት ይታያል?

ዶ/ር ሚርጊሳ፡- ትክክል ነው በከተማ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ይህን ያህል ነው ተብሎ ይቀመጣል፡፡ ይህ ምን ያህል እውነት ነው የሚለው ግን ጥያቄ ነው፡፡ ምክንያቱም የሚቀመጠው ቁጥር በከተማ ውስጥ የለውን ልዩነት የሚያሳይ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ዴሞግራፊክ ሔልዝ ሰርቬይን ብንወስድ አንድም ቦታ በከተማ ውስጥ ያለውን የአገልግሎት ተደራሽነት ልዩነት አያስቀምጥም፡፡  እንዲሁ ይሔን ያህል ሽፋን አለ ተብሎ ነው የሚቀመጠው፡፡ መንግሥትንም እዚህ ጋር ስህተት አለ ስንል በመረጃ መሆን ስላለበት መረጃውን መያዝ የእኛ አንዱ ሥራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በእስካሁኑ ጉዟችሁ አስቸጋሪ የነበረው ምን ነበር?

ዶ/ር ሚርጊሳ፡- የከተማ ጤና ሲባል ምን የተለየ ነገር አለው የሚል አመለካከት በብዙዎች ዘንድ ነበር፡፡ የከተማ ጤና ይለያል ኢፍትኃዊነም አለ የሚለውን በመረጃ አስደግፎ ብዙዎችን ማሳመን ራሱን የቻለ ሥራ ነበር፡፡ አማካሪ ቡድኑ እንደ ፕሮጀክት ሳይሆን እንደ ፕሮግራም ለረዥም ጊዜ እንዲቀጥል ነው የምንፈልገው፡፡ አሁን የገንዘብ ምንጫችን ዕርዳታ ነው፡፡ ይህም አንደኛው ችግራችን ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል›› አቶ ያዕቆብ ወልደ ሥላሴ፣ የሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ተቋሞችን መደገፍ የግድ እንደሚል ይታመናል፡፡ መንግሥት ሊያደርግ ከሚችለው ድጋፍ አንዱ ደግሞ የውጭ...

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...

‹‹የኤድስ በሽታ ከ10 እስከ 24 ዕድሜ ክልል ባሉ ልጆች በሁለት እጥፍ እየጨመረ ነው›› ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤችአይቪ ኤድስ ዘርፍ...

የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት ከቦታ ቦታ ቢለያይም እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ አዲስ አበባም የችግሩ ሰለባ ከሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዷ ናት፡፡ ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በአዲስ አበባ ጤና...