Wednesday, October 4, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የቆሻሻው ቁልል የአስተዳደር ውድቀት ማሳያ ነው!

አዲስ አበባ ከተማ በአራቱም ማዕዘናት በቆሻሻ ተውጣለች፡፡ የቀድሞው የረጲ የቆሻሻ መድፊያ ተዘግቶ፣ የሰንዳፋ ዘመናዊ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ማዕከል በአንድ ቢሊዮን ብር ተገንብቶ ሥራ ቢጀምርም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገልግሎቱ ተቋርጧል፡፡ በዚህም ምክንያት አዲስ አበባ በቆሻሻ ተወራለች፡፡ ለበርካታ ቀናት በዋና መንገዶች ላይ ሳይቀር የተከመረው ቆሻሻ ነዋሪዎችን ምን ጉድ መጣ እያሰኘ ነው፡፡ ለዓይንና ለአፍንጫ ከባድ የሆነው የቆሻሻ ቁልል መፍትሔ የሚፈልግለት አካል ከመጥፋቱም በላይ፣ ለተፈጠረው ችግር መፍትሔው ምን እንደሆነ በድፍረት ወጥቶ የሚናገር አልተገኘም፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ አስቸጋሪ ወቅት ቆሻሻው እየተከመረ በነዋሪዎች ጤንነት ላይ አደጋ ጋርጧል፡፡ ይህ የአስተዳደር ውድቀት ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡

አዲስ አበባ የአገሪቱ ዋና ከተማ ብቻ ሳትሆን ልክ እንደ ኒውዮርክ፣ ብራሰልስና ጄኔቫ የታላላቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት መናኸሪያ ናት፡፡ በተጨማሪም የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ናት፡፡ እንግዲህ በዚህ ደረጃ ላይ ያለችው አዲስ አበባ ናት ቆሻሻ መድፊያ አጥታ ጎዳናዎቿና የመኖሪያ መንደሮቿ በቆሻሻ የተዋጡት፡፡ የፌዴራል መንግሥቱም ሆነ የከተማ አስተዳደሩ የሰንዳፋ የቆሻሻ ማስወገጃ ማዕከል አገልግሎት እንዳይሰጥ ሲደረግ፣ በፍጥነት ተንቀሳቅሰው ጊዜያዊ ማስወገጃ ማዘጋጀት እንዴት ያቅታቸዋል? በአሁኑ ጊዜ ‹‹አተት›› ተብሎ በሚጠራው ተላላፊ በሽታ ምክንያት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ እየተወተወተ፣ በሌላ በኩል አዲስ አበባን ቆሻሻ ዳር እስከ ዳር ሲውጣት ምን ይባላል? የነዋሪዎችም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ከተማዋ የሚመጡ ዜጎችና የውጭ ሰዎች ጤንነትና ደኅንነት አያሳስብም ወይ? በስንት መከራ በአንፃራዊነት በመለወጥ ላይ ያለው የአገሪቱ ገጽታስ አያሳስብም? ለመፍትሔ የሚተጋ አካል በግልጽ አለመታየቱ ደግሞ የበለጠ ያሳስባል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ላይ ከአጎራባች ከተሞች ጋር እንዴት ነው የሚሠራው? የደረቅ ቆሻሻ አያያዝንና አወጋገድን የሚመለከተው ሕግ ተግባራዊ ሲደረግና የከተማው ቆሻሻ በአጎራባች ከተማ ይዞታ ላይ በተዘጋጀ ማዕከል ሲደፋ፣ ከአካባቢው መስተዳድርም ሆነ ከሕዝቡ ጋር ያለው የመረጃ ልውውጥ ምን ይመስላል?  በአንድ ቢሊዮን ብር የተገነባ የቆሻሻ ማስወጃ ማዕከል አገልግሎት እንዳይሰጥ የተደረገው ከመነሻው የሰንዳፋ አካባቢ መስተዳድርና የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ስምምነት ስለሌላቸው ነው? ወይስ የተለየ ጉዳይ አለ? አርሶ አደሮች የአዲስ አበባ ከተማ ቆሻሻ በማዕከሉ እንዳይደፋ ከልክለዋል ሲባል ምክንያቱ በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡ መስተካከል ያለበት ችግር ካለም መፍትሔ መፈለግ ይገባል፡፡ መንግሥት በአግባቡ ሥራውን ማከናወን አቅቶት ከሆነም መታወቅ አለበት፡፡

የፌዴራል መንግሥት ከክልሎች ጋር ባለው ግንኙነት በተለይም በሕገ መንግሥቱ በሠፈረው መሠረት በመሬት ጉዳይ ወጥ አቋም ሊኖረው ይገባል፡፡ አዲስ አበባ የፌዴራል መንግሥቱ መቀመጫ እንደመሆንዋ መጠን፣ ለከተማዋ የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶችንና መሰል ጉዳዮችን ለማከናወን ሲያስፈልግ በተለይ ከመሬት ጋር በተገናኘ ከክልሎች ጋር የሚደረገው ግንኙነት የጋራ ጥቅምን ያገናዘበ መሆን አለበት፡፡ በሕግ በዝርዝር ሰፍሮ መታየትም ይኖርበታል፡፡ አዲስ አበባ ከአጎራባች ከተሞች ጋር የሚኖራት ግንኙነት በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተገነባ፣ ዘላቂ የጋራ ጥቅምን የሚያረጋግጥና ፍትሐዊ እንዲሆን መደረግ አለበት፡፡ በመንገድ፣ በኤሌክትሪክ፣ በውኃ፣ በቆሻሻ አወጋገድም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች አዲስ አበባና አጎራባች ከተሞች ጥቅሞቻቸውን ማዕከል ያደረገ ፍትሐዊ ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል ሲባል፣ ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ ስኬት በቁርጠኝነት የሚቆም አመራር ያስፈልጋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይኼ እየታየ አይደለም፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከአጎራባች ከተሞች ጋር ያለው ግንኙነት በሕግ ማዕቀፍ የሚመራና ፍትሐዊ እንዲሆን መሥራት ሲገባ ዝም ማለት ተገቢ አይደለም፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ በቆሻሻ መከመር ብቻ ሳይሆን፣ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በተመለከተ የሚታዩ ችግሮች ብዙ የሚናገሩት አላቸው፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በተለያዩ መድረኮች ድህነትንና ኋላቀርነትን ታሪክ ለማድረግ እንደሚተጋ በተደጋጋሚ ሲናገር ይደመጣል፡፡ በተወሰነ ደረጃ የሚታዩ ለውጦች ቢኖሩም፣ የሚነገረውና መሬት ላይ የሚታየው ችግር አይመጣጠኑም፡፡ ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ በመንግሥት ውስጥ የሚታየው ከፍተኛ የሆነ የማስፈጸም ድክመት ነው፡፡ ከፍተኛ ሀብት ፈሶባቸው የተገነቡ መንገዶች በዘፈቀደ ሲቆፋፈሩና ሲፈራርሱ ይታያሉ፡፡ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች በአግባቡ ስለማይገነቡ መንገዶች በክረምት ወራጅ ውኃ ይጋልብባቸዋል፡፡ በግንባታ ሰበብ በየቦታው በተገነቡ መንገዶች ላይ ሳይቀር ቁፋሮ ይካሄዳል፡፡ የግንባታ ግብዓቶች መንገድ እየዘጉ እንቅስቃሴ ሲያውኩ በስፋት ይታያል፡፡ ለአደጋ የሚዳርጉ ጉድጓዶች መልሶ የሚደፍናቸው ባለመኖሩ ለበርካቶች ሕይወት መጥፋት ሰበብ ይሆናሉ፡፡ ሕዝቡ ሲጮህ ሰሚ የለም፡፡

የከተማው ነዋሪዎች በመኖሪያ ቤት ችግር ሳቢያ በሕገወጥ መንገድ ጎጆ ቀልሰው ሲኖሩ ለዓመታት ዝም ይባልና ድንገት የሚካሄድ የማፍረስ ዘመቻ ሰለባ ይሆናሉ፡፡ በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች የሚደለሉ የክፍለ ከተማና የወረዳ አመራሮች በጎን እየተደራደሩ ብዙ ሺሕ ቤተሰቦችን የሚያስጠልሉ ቤቶች ከተሠሩ በኋላ፣ በአፍራሽ ግብረ ኃይል ድንገተኛ ዕርምጃ ምክንያት ሕፃናትና አቅመ ደካሞች በክረምት ይፈናቀላሉ፡፡ ሙሰኛ ሹማምንት በፈጸሙት ኃጢያት ሳቢያ ብዙኃን ወደ ጎዳና ይጣላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የሚፈናቀሉት ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ዜጎች በመንግሥት ላይ ያላቸው እምነት ይሸረሸራል፡፡ ቅሬታው ይጋጋምና ለነውጥና ለግጭት በር ይከፍታል፡፡ ገና ከመነሻው በአጭሩ መቀጨት የነበረበት ሕገወጥነት በሙሰኛ ሹማምንት ይሁንታ ዓመታት አስቆጥሮ ሕጋዊ ከመሰለ በኋላ፣ ዘግይቶ በሚወሰድ ዕርምጃ በርካቶች ሲፈናቀሉ ችግሩ በቀጥታ የማይመለከታቸው ዜጎች ጭምር ለምሬት ይዳረጋሉ፡፡ በእርግጥ መንግሥት ይወክለናል ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ ይኼ በሕዝብና በመንግሥት መካከል መቆራረጥ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡

ዜጎች በመኖሪያ ቤት፣ በትራንስፖርት፣ በውኃ፣ በኤሌክትሪክና በተለያዩ መንግሥታዊ አገልግሎቶች የሚያጋጥሟቸው ዘገምተኛ የሆኑ አሠራሮች ለመልካም አስተዳደር ዕጦት ዋነኛ ማሳያ ናቸው፡፡ ሁሉም ችግሮች በአንድ ጊዜ ሳይሆን በሒደት እንደሚፈቱ ዕሙን ቢሆንም፣ በተደጋጋሚ ሕዝቡን የሚያሰቃዩ ችግሮችን ተሸክሞ መቀጠል ግን ያበሳጫል፡፡ በመንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ በስፋት የሚታየው የግዴለሽነትና የምንቸገረኝ አሠራር ለሕዝብ ብሶት ዋነኛ አቀጣጣይ እየሆነ ነው፡፡ ብቃት የሌላቸው ሹማምንት የሞሉበት ተቋም መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ችግሮችን ስለሚደራርብ፣ ሕዝብ በአገልግሎት ከመርካት ይልቅ ይማረራል፡፡ በመሬት አስተዳደር፣ በግንባታ ፈቃድ፣ በንግድ ፈቃድ ምዝገባና ዕድሳት፣ በገቢዎችና በተለያዩ አገልግሎቶች መስጫ ተቋማት የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ከአቅም በላይ ናቸው፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሌለበት አሠራር መስፈኑ ለአስተዳደር ውድቀት ማሳያ ነው፡፡ ግብር ከፋዩ ሕዝብ እየተሰቃየ ነው፡፡

አሁን ደግሞ በርካታ ችግሮች ያሉባት ከተማ በቆሻሻ ተወራለች፡፡ በአንድ በኩል ‹‹አተት›› የተባለው ወረርሽኝ ከፍተኛ ሥጋት ነው፡፡ በሌላ በኩል ለወረርሽኙም ሆነ ለሌሎች ተላላፊ በሽታዎች መንስዔ ሊሆን የሚችል የቆሻሻ ቁልል ሌላ ሥጋት ደንቅሯል፡፡ የከተማው አስተዳደር ስለተፈጠረው ችግርም ሆነ የቅርብ ጊዜ መፍትሔ በግልጽ አፍታቶ መናገር አልቻለም፡፡ በምርጫ በተገኘ የሕዝብ ድምፅ ሥልጣን ይዣለሁ የሚለው መንግሥት ለሕዝቡ መረጃ ለመስጠትም ሆነ ስለቀጣዩ ዕርምጃ ምንም ማለት አልፈለገም፡፡ የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ በቆሻሻ ቁልል ውስጥ ሆና የመፍትሔ ያለህ እያለች ነው፡፡ ሰሚ ግን የለም፡፡ ይኼ ደግሞ የአስተዳደር ውድቀት ማሳያ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመገረም እየተመለከቱ አገኟቸው]

ምንድነው እንዲህ ቀልብሽን የሳበው? ስለሰላም ኖቤል ሽልማት ዜና እየተመለከትኩ ነበር። እና...

የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መመሥረትና የአማራ ክልል ጥያቄ

አማራ የኢሕአዴግ አንዱ መሥራችና አጋር ከሆነው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ...

የሽንኩርት ዋጋ ሰማይ የነካበት ምክንያት ምንድነው?

ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት የሸማቾችን ኪስ ካስደነገጡ መሠረታዊ ከሚባሉ...

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ኤግዚቢሽን ማዕከልን እንዲያስተዳድር የተሰጠው ኮንትራት ለምን ተቋረጠ?

በአዲስ አበባ ከተማ ለንግድ ትርዒት ዝግጅት ብቸኛ በመሆን የሚጠቀሰው...

የመከፋት ስሜት!

ከቤላ ወደ ጊዮርጊስ ልንጓዝ ነው፡፡ መውሊድና መስቀልን በተከታታይ ቀናት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግጭቶች በሙሉ ሁሉን አሳታፊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተገቶ የተስፋ ጭላንጭል መታየት ሲጀምር፣ በአማራ ክልል ሌላ ዙር ዕልቂትና ውድመት ሊያደርስ የሚችል ግጭት መነሳቱ ብዙዎችን ያሳስባቸዋል፡፡ በአማራ...

የባለሥልጣናትና የባለሀብቶች ግንኙነት ሥርዓት ይኑረው!

በሕዝብ ድምፅ ሥልጣን የያዘ ፓርቲ የሚመሠርተው መንግሥት ከምንም ነገር በፊት ለሕግና ለሥርዓት መከበር ኃላፊነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንን ኃላፊነት በሚገባ ሊወጣ የሚችለው ሥራውን በግልጽነትና በተጠያቂነት...

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...