Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምሒላሪ ክሊንተን በዴሞክራቲክ ፓርቲ ጉባዔ መጀመሪያ

ሒላሪ ክሊንተን በዴሞክራቲክ ፓርቲ ጉባዔ መጀመሪያ

ቀን:

አሜሪካ እ.ኤ.አ. በ2016 ማብቂያ አካባቢ ለምታካሂደው የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በሪፐብሊካን ፓርቲ በዶናልድ ትራምፕ፣ በዴሞክራቲክ ፓርቲ በሒላሪ ክሊንተን ዙሪያ አነጋጋሪ የሆኑ ጉዳዮች ሲሰነዘሩ ከርመዋል፡፡ ትራምፕ በተለይ በእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ ባላቸው አቋም፣ ክሊንተን ደግሞ በአሜሪካ ግለሰቦች በሚታጠቁት የጦር መሣሪያ ላይ ገደብ ሊጣል ይገባል በሚለው ሐሳባቸው ሲደገፉም ሲተቹም ይሰማል፡፡

በቅርቡ ደግሞ ሒላሪ ክሊንተን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው እያገለገሉ ከአገሪቱ ደንብ ውጪ የግል ኢይሜል ሰርቨር መጠቀማቸው ሌላው መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ትራምፕ በተለይ የእስልምና እምነትንና ሽብርን በአንድ በመፈረጃቸው በኃያላን አገሮች መሪዎች ጭምር ቢተቹም፣ በአገራቸው በሚደረጉ ቅድመ ምርጫ ትንበያዎች ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሊሆኑ ይችላሉ የሚያስብሉ ቁጥሮችን ሲያስመዘግቡ ይታያሉ፡፡ ዲፕሎማቲክ ሴት ናቸው የሚባሉት ሒላሪ ክሊንተንም እንዲሁ በቅድመ ምርጫ ትንበያዎች ትልልቅ ቁጥሮችን ሲያገኙ ይስተዋላል፡፡

ሪፐብሊካኑ ለፕሬዚዳንትነትና ምክትል ፕሬዚዳንትነት የሚያቀርቧቸውን ዕጩዎች ለመምረጥ ጉባዔ ያካሄዱት ከሐምሌ 11 እስከ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ነበር፡፡ 2,472 የሪፐብሊካን ፓርቲ ተወካዮች በተገኙበት በተካሄደው ምርጫም፣ ፓርቲው ዶናልድ ትራምፕ የፓርቲው ዕጩ ፕሬዚዳንት እንዲሁም ማይክ ፔንስ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲወዳደሩ ወስኗል፡፡

የዴሞክራቶች ጉባዔ የተጀመረው ደግሞ ሐምሌ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ሲሆን፣ ሐምሌ 21 ቀን 2008 ዓ.ም. የፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት ዕጩዎችን መርጦ ይጠናቀቃል፡፡

ጉባዔው ባካሄደው የመጀመርያው ቀን ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት ሴናተር በርኒ ሳንደርስ፣ ዴሞክራቶች ሒላሪ ክሊንተንን ወደ ፕሬዚዳንትነቱ ሥልጣን እንዲያመጡ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ሒላሪ ክሊንተን ቀጣይዋ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መሆን አለባቸው፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በጉባዔው ላይ የተገኙት ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማ፣ ዶናልድ ትራምፕን በማጣጣል ጠንካራ ንግግር ማድረጋቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

‹‹ይች አገር ታላቅ አይደለችም፣ ወደ ነበራት ታላቅነት እንመልሳታለን ብሎ ለሚነግራችሁ ጆሮ አትስጡ፤›› ሲሉ ትራምፕ ለቅስቀሳ የሚጠቀሙበትን ‹‹አሜሪካን ዳግም ታላቅ እናደርጋለን፤›› የሚለውን መፈክራቸውን ተችተዋል፡፡ አሜሪካም በአሁኑ ጊዜ በዓለም ኃይል አገር ናት ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ሳንደርስ ክሊንተን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ እንዲተጋ ጉባዔውን ሲጠይቁ በጭብጨባ የተቀበላቸው ሲሆን፣ ደስታቸውን በለቅሶ የገለጹም ነበሩ፡፡ አንዳንዶቹ አፋቸውን በፕላስተር አሽገው ዝምታቸውን አሳይተዋል፡፡

‹‹ትራምፕ አንዱን ካንዱ እያፈራረቀ ሲሰድብ፣ ክሊንተን ልዩነታችን የጥንካሬያችን መገለጫ መሆኑን ተረድታለች፤›› ያሉት ሳንደርስ፣ ‹‹ምርጫው ወሳኝ ነው ብላችሁ ካላመናችሁና ካልተሳተፋችሁ ትራምፕ ወደ ሥልጣኑ ይመጣል፡፡ ይኼም ለእኩል መብት፣ ለአገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ፣ እንዲሁም ለሕዝቡ ነፃነት ምን ማለት እንደሆነ ታዩታላችሁ፤›› ሲሉ የትራምፕ መመረጥ ለአገሪቱ ሥጋት እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

ሃምሳ ሺሕ ያህል ደጋፊዎች ይሳተፉበታል በተባለው በአራቱ ቀን ጉባዔ 5,000 የፓርቲ ተወካዮች የሚገኙ ሲሆን፣ በጉባዔው ማብቂያም የሒላሪ ክሊንተን ዕጩ ፕሬዚዳንትነት ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 15 ሺሕ ጋዜጠኞችም በጉባዔው እየተሳተፉ ነው፡፡

በጉባዔው እያንዳንዱ ፓርቲ የራሱን ዕጩ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሁም የፓርቲውን መዋቅርና ማኒፌስቶ ያቀርባል፡፡ ረቡዕና ሐሙስ በሚኖረው ስብሰባ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ እንዲሁም እ.ኤ.አ. ለ2016 ምርጫ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ይወዳደራሉ ተብለው የሚጠበቁት ቲም ኬይን ንግግር ያደርጋሉ፡፡

ለአራት ዓመታት የቨርጂኒያ ገዥ የነበሩትና እ.ኤ.አ. ከ2012 ወዲህ ደግሞ ኮንግረሱን እያገለገሉ የሚገኙት ኬይን፣ እ.ኤ.አ. በ2008 የአሜሪካ ምርጫም ታዋቂ ነበሩ፡፡ ሆኖም የአገር ውስጥ ባንኮችን ከቁጥጥር ነፃ ማድረግና ነፃ ገበያ ማስፈን የሚለው አቋማቸው ተቀባይነት አሳጥቷቸው ነበር፡፡

 ውርጃን በመቃወም የሚታወቁት ኬይን፣ ለምክትል ፕሬዚዳንትነት ዕጩ ሆነው እንዲቀርቡ በክሊንተን ይሁንታን አግኝተዋል፡፡ ሒላሪ ክሊንተን የ2016ቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ካሸነፉም፣ ምክትል ሆነው የሚመጡት ኬይን የሴኔት መቀመጫ በጊዜያዊ ሰው የሚተካ ሲሆን፣ በቋሚነት የሚመደበውን ለመምረጥ ደግሞ እ.ኤ.አ. በ2017 ልዩ ምርጫ ይካሄዳል፡፡

ሳንደርስና የሒላሪ ክሊንተን ደጋፊዎች ቀጣይዋ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ ቢተጉም፣ የሒላሪ ክሊንተንን ስም የሚያጎድፍ አጀንዳ ዓመት ተሻግሮ በምርጫው ዋዜማ ብቅ ብሏል፡፡

ሒላሪ ክሊንተን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሆኑበት ጊዜ አንስቶ የስቴት ዲፓርትመንቱን የኢሜል ሰርቨር ሳይሆን የራሳቸውን እየተጠቀሙ ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ በአሜሪካ ባለሥልጣናትና የመንግሥት ሠራተኞች የግላቸውን ሳይሆን መንግሥት የሚያቀርበውን ሰርቨር የሚጠቀሙ ቢሆንም፣ በአሜሪካ የሥልጣን ቁንጮ ላይ የሚገኙት ክሊንተን ይህን አላደረጉም፡፡ ጉዳዩ እ.ኤ.አ. በ2015 ተነስቶ የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱም ለምርምራ በሚል ሁሉንም የኢሜይል ልውውጣቸውን አትመው ለኤፍቢአይ እንዲያስረክቡ ተደርገዋል፡፡

የግል ኢሜይላቸውን አስመልክቶ ‹‹ለምቾት የግል ሰርቨር ተጠቅሜያለሁ›› ያሉት ሒላሪ ክሊንተን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሆኑ ጀምሮ 62,320 የኢሜል ልውውጦች እንዳደረጉ፣ ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ መንግሥታዊ የሆኑና ለስቴት ዲፓርትመንቱም የተመለሱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ሒላሪ ክሊንተን በራሳቸው ሰርቨር ኢሜይል መጠቀማቸው ሕገወጥነት ነው ወደሚል መደምደሚያ ባያደርስም፣ አሜሪካውያን በእሳቸው ላይ ያላቸውን እምነት ይሸረሽራል የሚሉ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ነው፡፡

የኢሜይል ልውውጣቸውን አትመው ለኤፍቢአይ ያስረከቡት ሒላሪ ክሊንተን፣ ሰርቨሩንም ለምርመራ እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል፡፡ ሆኖም ይህ ለተቀናቃኞቻቸው የትችት በር ከፍቷል፡፡ ክሊንተን እምነት አጉድለዋል ወደሚል አጀንዳም ተለውጧል፡፡

ክሊንተን የግል ሰርቨር የተጠቀሙት ከጠበቃቸው ጋር መክረው ሲሆን፣ እስካሁን ባሉ መረጃዎችም በኢሜይል ልውውጣቸው ተገኝቷል የተባለ አዲስ ነገር የለም፡፡ ሆኖም ሊበራሎች ክሊንተን ‹‹እጅ ሰጥታለች›› ሲሉ ተሰምተዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...