በአርሲ ዞን ዶዶታ ወረዳ በደረሰው የመሬት መንሸራተት ምክንያት የአካባቢው ነዋሪች ከአንድ ሥፍራ ወደ አንድ ሥፍራ ለመሸጋገር ተቸግረዋል፡፡ የመሬት መንሸራተቱ ወደ ዋናው መንገድ እየሰፋ በመምጣቱም በደረሰው የትራፊክ አደጋ ከአምስት በላይ ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ (ፎቶ በታምራት ጌታቸው)
* * *
ጀግና በሉኝ
ወኔዬ የጠላት መንደር ሲያሸብር
ቁጣዬ ሲያርድ ሲያብረከርክ
ክንዴ ሲያደቅ ሲማርክ
ሞገሴ ከእግሬ ስር ሲያንበረክክ
ትከሻዬን በማእረግ ሞላችሁና
እኔ ጀገንኩኝ ሳልል፣
እናንተው አላችሁኝ ጀግና
ብልሀቴ ችግር ቢያሸንፍ
እውቀቴ ነገር ቢፈታ
ብልጠቴ እየበለጠ
ንቃቴ ቢሆን አለኝታ
ስሜን በማእረግ አጀባችሁና
እኔ ጀገንኩኝ ሳልል፣
እናንተው አላችሁኝ ጀግና
እኔ ግን ዛሬ እንደ አዲስ
ትከሻዬ ማእረግ አማረው
ጀግንነቴ ሙሉ ሆነ
ለስሜም አጀብ አሰኘው
ዘውዱም ከአናቴ ይደፋ
ካባዬም ዛሬ ይደረብ
ትከሻዬም ኒሻን ይክበደው
ማእረግ ይመረጥ ለስሜ አጀብ
ጀግኜ ጀገንኩ አልኳችሁ
በሉ እስኪ ጀግና፣ ጀግና በሉኝ
የድሎች ሁሉ የበላይ
እራሴን አሸነፍኩኝ፡፡
ታዬ አስፋው፣ ‹‹ሐጢሾ›› (2008)
* * *
ልጁን በሰንሰለት አስሮ ያቆየው ፓስተር ታሰረ
ፓስተር ፍራንሲስ ታይዎ ይባላል፡፡ ነዋሪነቱ በናይጄሪያ ሲሆን፣ በልጁ ላይ በፈጸመው ግፍ ሰሞኑን የመገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ ፓስተር ፍራንሲስ የዘጠኝ ዓመት ልጁን ዕቃ ሰርቀሃል በሚል ከወር በላይ በሰንሰለት አስሮ አቆይቶታል፡፡ በአካባቢው የሚገኝ ቤተክርስቲያን አባል የነበሩት አማኞችም ተባባሪ እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ጉዳዩን እየተከታተለ ከሚገኘው የፖሊስ ክፍል በተነገኘው መረጃ መሠረት፣ አባትየው ልጁን በሰንሰለት በማሰር ለመቅጣት የወሰነው ልጁ በተደጋጋሚ እየሰረቀ በማስቸገሩ ምናልባት የሰይጣን መንፈስ አድሮበት ይሆናል በሚል ሥጋት ነው፡፡ ስለልጁ ሁኔታ ለፖሊስ ጥቆማ በማድረግ ነፃ እንዲወጣ ያደረጉ የአካባቢው ነዋሪዎች ናቸው፡፡ ድርጊቱን የፈጸመው ፓስተር ፍራንሲስ በቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡ ጉዳዩንም በናይጄሪያ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የሚሠራው ድርጅት እየተመለከተው ይገኛል፡፡
* * *
የመራጮች ዝርዝር በመቅደድ የተከሰሱት ታዳጊዎች
ታይላንድ ውስጥ ነው፡፡ ሁለት የስምንት ዓመት ታዳጊዎች ትምህርት ቤታቸው አካባቢ መንገድ ላይ እየተጓዙ ትኩረታቸውን አንድ ሮዝ ወረቀት ይስበዋል፡፡ ወረቀቱ መንገድ ላይ የተለጠፈ ሲሆን፣ የአገሪቱን የመራጮች ዝርዝር የያዘ ነበር፡፡ በቀለሙ የተማረኩት ታዳጊዎች ስለይዘቱ ብዙም ሳይጨነቁ ወረቀቱን ቀደው ይወስዱታል፡፡ የአገሪቱ ፖሊስ ልጆች ናቸው ብሎ ክስ ከመመሥረት ወደኋላ አላለም፡፡ የአገሪቱ ሕዝበ ውሳኔ አንድ ወር ሲቀረው የምርጫ ቅስቀሳ ሕግጋትን በመጣስ ቢወነጅላቸውም፣ የታዳጊዎቹ ዕድሜ ከግምት ገብቶ ሳይፈረድባቸው መቅረቱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ የአገሪቱ ፖሊስ ኮማንደር ‹‹ታዳጊዎቹ ወረቀቱን የቀደዱት ሮዝ ቀለሙ ደስ ስላላቸው መሆኑን አምነዋል፤›› ሲልም ገልጿል፡፡ ለዓመታት በፖለቲካዊ ቀውስ ስትናጥ የቆየችው ታይላንድ ለተመሳሳይ ጥፋቶች ከፍተኛ ቅጣት ትጥላለች፡፡
* * *
ማሳጅ ሰጪው ሮቦት ‹‹ኤማ››
ከሰሞኑ ሚረር ያስነበበው ዘገባ የማሳጅ ባለሙያዎችን የሥራ ዕድል ጥያቄ ውስጥ ከቷል፡፡ ታይላንድ ውስጥ የተሠራው ማሳጅ የሚሰጥ ሮቦት ‹‹ኤማ›› የሚል ስም የተሰጠው ሲሆን፣ ዘገባው እንደሚያሳየው ከሰው በተሻለ ማሳጅ ያደርጋል፡፡ ሮቦቱ ስሪዲ (ሦስት አውታር) ቴክኖሎጂ በመጠቀም የሰዎችን የተያያዘ የሰውነት ክፍል በመለየት ማሳጅ ይሰጣል፡፡ ከፍተኛ ብቃት የታየበት የሕክምና ማሳጅ የሚሰጠው ሮቦት የሰውነት ሥሮችን የጤንነት ደረጃ ከመገንዘቡም በላይ የህሙማንን ምላሽ በመከተል ማሳጁን ያከናውናል፡፡ አንድ ሕመምተኛ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳየ ያለውንም ለውጥ ይመዘግባል፡፡ አልበርት ዛንማ በተባለ ባለሙያ የተሠራው ሮቦት ‹‹ኤማ›› ከተሠራ በኋላ አትሌቶችን ጨምሮ ወደ 50 የሚደርሱ ሰዎችን ማሳጅ አድርጓል፡፡ አልበርት እንደተናገረው፣ ሮቦቱ የተሠራው በፍጥነት ሕክምና ለመስጠት ነው፡፡ በፊዚዮቴራፒስት ወይም ፊዚሽያን ትዕዛዝ ማሳጅ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች የሚያክመው ሮቦቱ፣ ግንባር ቀደም ግኝት መሆኑንም ገልጿል፡፡ ብዙ የማሳጅ ባለሙያዎች በሮቦቱ ምክንያት ሥራቸው አደጋ ውስጥ እንደወደቀ ቢያምኑም፣ አልበርት፣ ‹‹አላማችን ባለሙያዎቹን በሮቦት መተካት ሳይሆን ዘርፉን ማሻሻል ነው፡፡ ባለሙያዎቹ በሮቦቱ እርዳታ ብዙ ህሙማን ሊያክሙ ይችላሉ፤›› ብሏል፡፡