‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱን ባህል አትኩሮ የሚያጣጥምና የሚወድ ነው፡፡ ቴአትር ቤቱ ይሞላል፡፡ ግን ከቴአትር አንፃር (ከድርሰቱ) ያየነው እንደሆነ ብዙ የሚተቹ ነገሮች አሉ፡፡ እንደ ቴአትር አዋቂ ተመልካች ቴአትሮቹን ብናያቸው ብዙ ግድፈቶች እናገኛለን፡፡ ተመልካቹ ለዚያ ሁሉ ደንታ የለውም፡፡ የራሱን ሕይወት ማየት ይወዳልና ይመጣል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ጥበቡ ሳይሆን ተመልካቹ ነው የሚፈታተነን፡፡ ደግሞ የኛን አገር ቴአትር እንዳያድግ የገደለው ቴአትር ቤቶች በመንግሥት እጅ መሆናቸው ነው፡፡ ቴአትር ቤቶች አንድ ዓይነት ሥራ ነው የሚሠሩት፡፡››
የቴአትርና ፊልም አዘጋጅ፣ ጸሐፌ ተውኔትና የውዝዋዜ አሠልጣኝ የነበረውና ባለፈው ዓርብ ሥርዓተ ቀብሩ የተፈጸመው አባተ መኩሪያ (1932- 2008)፣ በአንድ ወቅት ስለ አገሪቱ ቴአትር ሒደትና ገጽታን በገመገመበት ጊዜ የተናገረው። ‹‹ተንቀሳቃሹ ቴአትር ቤት››፣ ‹‹ሦስት ዓይና›› የሚል ቅጽሎች ያተረፈው ጠቢቡ አባተ
በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ውስጥ ስማቸው በዐቢይነት ከሚነሱትና አኩሪ ጠቢባን አንዱ ነበር፡፡ በተለይ በተውኔት አዘጋጅነት ስመ ጥር ለመሆኑ ዘመን ተሻጋሪ ተውኔቶችን ወጥ እና ትርጉሞች በማዘጋጀቱ ይጠቀሳል፡፡ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚን ከመሠረቱትም አንዱ ነበር።