Sunday, September 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽንና አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ለመሥራት ተፈራረሙ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ራሱን ችሎ ከተቋቋመ አምስት ዓመታትን ያስቆጠረው የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲና ተክለብርሃን አምባዬና ቤተሰቡ ኮርፖሬት ግሩፕ፣ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ሐምሌ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ተፈራረሙ፡፡

ሁለቱ ተቋማት ያሉባቸውን ክፍተቶች በመነጋገርና አንደኛው የአንደኛውን በመሸፈን ለመሥራት የተፈራረሙት፣ ለተወሰኑ ጊዜያት ብቻ ሳይሆን ለረዥም ጊዜና አገሪቱ ብቁ ዜጎችን የማፍራት አቅሟ የተሟላ እስከሚሆን ድረስ የሚቀጥል መሆኑን የተቋማቱ ተወካዮች ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሀብታሙ ኃይሉ እንደተናገሩት፣ ዩኒቨርሲቲው ስምንት ፕሮግራሞች አሉት፡፡ ስድስቱ የምህንድስና ሲሆኑ ሁለቱ የሶሻል ናቸው፡፡ በመሆኑም ተማሪዎችን በንድፈ ሐሳብ ደረጃ የሚያውቁትን በተግባር ለመሥራት ፋብሪካ ወይም ኢንዱስትሪ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡ የጀመሩትን የቴክኖሎጂ ትምህርት ወደ ተግባር ወይም ወደ መሬት ለማውረድ ላለፉት ሦስት ዓመታት ብዙ ኢንዱስትሪዎችንና ፋብሪካዎችን ለማነጋገር መቻላቸውን ገልጸው፣ አሁን ግን ኢንዱስትሪዎቹና ፋብሪካዎቹ ወደነሱ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

ተማሪዎቻቸውን ለልምምድ (ኢንተርንሺፕ) በመላክ ብቻ ተገድቦ የነበረውን እንቅስቃሴ የሚገታ፣ በጋራ ተነጋግሮና ተስማምቶ ለመሥራት ተክለብርሃን አምባዬና ቤተሰቡ ኮርፖሬት ግሩፕ ወደ ዩኒቨርሲቲው መምጣቱ እንዳስደሰታቸው ዶ/ር ሀብታሙ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ከተፈራረሙበት ቀን ጀምሮ ሁለቱ ተቋማት የዕውቀት ሽግግር ከማድረግም በተጨማሪ፣ ዩኒቨርሲቲው በገነባው የልቀት ማዕከል ውስጥ የሚደረጉ ምርምሮችን ለመጠቀም እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡ በልቀት ማዕከላቸው የሪአክተር ቴክኖሎጂ (ኑክሌየር) ሥልጠናም መስጠት መጀመራቸውንም አክለዋል፡፡

ከኮርፖሬት ግሩፑ ጋር ትስስር የሚያደርጉት ክፍተቶቻቸውን ለመሙላትና ሙሉ ለመሆን እንደሆነ የተናገሩት ዶ/ር ሀብታሙ፣ መንግሥት ካስቀመጠው የቀጣና ትስስር ፎረም ይልቅ ከኮርፖሬት ግሩፑ (ከግል ተቋማት) ጋር ያደረጉት የተናጠል ትስስር መልካምና ውጤታማ መሆኑን አስረድተው፣ እስከ ዘለቄታው በመተራረም የተሳካ ሥራ እንደሚሠሩ ምኞታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተክለብርሃን አምባዬና ቤተሰቡ ኮርፖሬት ግሩፕ የዕቅድና ቢዝነስ ልማት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሲሳይ ተክሉ በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ ኮርፖሬት ግሩፑ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ያደረገው የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡

በኮንስትራክሽን፣ በማኑፋክቸሪንግና በኢንዱስትሪ መስኮች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ የሚገኘው ኮርፖሬት ግሩፑ፣ ከኤድናሞል ኢንተርቴይንመንት በስተቀር ሁሉም ከተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ጋር ትስስር ያላቸው መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ተቋሙ ከ23 ዓመታት በፊት በ23,000 ብር ካፒታል የተቋቋመው በዩኒቨርሲቲ ሲያስተምሩ ተገፍተው በወጡት ኢንጂነር ተክለብርሃን አምባዬ መሆኑን ጠቁመው፣ አሁን የድርጅቱ ካፒታል ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱንና በሁሉም ድርጅቶች ከ6,000 በላይ ሠራተኞች እንዳሉት ተናግረዋል፡፡

በኧርነስት ኤንድ ያንግ አማካሪ ድርጅት የአሥር ዓመታት ስትራቴጂካዊ ፕላን አስጠንቶ፣ በብቃትና በጥራት እየሠራ የሚገኝ ድርጅት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ከዩኒቨርሲቲው ጋር ያደረጉት የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ ወደፊት ወደ ልዩ ግንኙነት ተቀይሮና እንደ አንድ ተቋም በመተያየት ኮርፖሬት ግሩፑ ያሉበትን ክፍተቶች የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ ተማሪዎቹ ያለባቸውን ክፍተቶች ኮርፖሬት ግሩፑ በመሙላት፣ የአገርን ዕድገት በአገር ዜጎችና ተቋማት ማቀላጠፍ እንደሚቻል ያላቸውን ተስፋ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች