Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናለዕረፍት የተበተነው ፓርላማ ለአስቸኳይ ስብስባ ተጠራ

ለዕረፍት የተበተነው ፓርላማ ለአስቸኳይ ስብስባ ተጠራ

ቀን:

የ2008 ዓ.ም. የሥራ ዘመኑን አጠናቆ ለዕረፍት ከተበተነ ገና ሦስተኛ ሳምንቱን የያዘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በአስቸኳይ እንዲሰበሰብ በምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ተጠራ፡፡

አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ባስተላለፉት ማስታወቂያ የምክር ቤቱ አባላት ለአስቸኳይ ስብሰባ ማክሰኞ ሐምሌ 19 ቀን 2008 እንዲሰበሰቡ ጥሪ አድርገዋል፡፡ የምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ አንቀጽ 15፣ ‹‹ምክር ቤቱ በዕረፍት ላይ እያለ የምክር ቤቱን ውሳኔ የሚሹ አስቸኳይ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ አስቸኳይ ስብሰባ ሊጠራ ይችላል፤›› ይላል፡፡

የዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ሁለት ደግሞ፣ ‹‹በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 58(4) መሠረት ምክር ቤቱ በዕረፍት ላይ በሚሆንበት ጊዜ አፈ ጉባዔው ወይም ከግማሽ በላይ የሚሆኑ አባላት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ ከጠየቁ፣ አፈ ጉባዔው የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም አስቸኳይ ስብሰባ ይጠራል፤›› ይላል፡፡ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣንና የፓርላማ አባል የሆኑ የሪፖርተር ምንጮች አፈ ጉባዔው አስቸኳይ ስብሰባውን የጠሩት፣ በመንግሥት በኩል ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው ጉልህ ነው የተባሉ ሦስት አዋጆች እንዲፀድቁለት በመጠየቁ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ሦስት አዋጆችም የገቢ ግብር አዋጅ፣ የግብር አስተዳደር ሕግና የጂኦተርማል ሀብት ልማት አዋጆች መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡

በተለይም የገቢ ግብር አዋጁ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የያዘም በመሆኑና ይህም ፋይዳ በተቀጣሪዎች ዘንድም ሆነ በመንግሥት ከተያዘው የሐምሌ ወር ጀምሮ መታየት ያለበት በመሆኑ፣ በአስቸኳይ ስብሰባ እንዲፀድቅ መጠየቁን ምንጮች ተናግረዋል፡፡

እነዚህ አዋጆች ለምክር ቤቱ የቀረቡት ፓርላማው ለዕረፍት ከመበተኑ አስቀድሞ ቢሆንም፣ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ማፅደቅ ባለመቻሉ ለዕረፍት ተበትኗል፡፡ የገቢ ግብር አዋጁ ግብር የማያርፍበት የደመወዝ መጠን አሁን ካለበት 150 ብር ወደ 600 ብር ከፍ እንዲል የሚፈቅድ፣ እንዲሁም 35 በመቶ ግብር የሚያርፍበት አምስት ሺሕና ከዚያ በላይ የሆነ የደመወዝ ገቢ ወደ 10,900 ብር ከፍ እንዲል የሚያደርግ ነው፡፡

ይህ ማሻሻያ በተቀጣሪዎች ወርኃዊ ገቢ ላይ መጠነኛ ጭማሪ የሚያሳይ በመሆኑና ይህም ከሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ መፈጸም ያለበት በመሆኑ፣ አስቸኳይ ስብሰባ መጠራቱን ምንጮቹ ይገልጻሉ፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ አቶ አብዱላዚዝ መሐመድ በቅርቡ እንደገለጹት፣ መንግሥት በገቢ ግብር አዋጁ ውስጥ በተካተተው የቅጥር ገቢ ላይ ብቻ ባደረገው ማሻሻያ ሦስት ቢሊዮን ብር ገቢ በዓመት ያጣል፡፡

ይሁን እንጂ ይኼው የገቢ ግብር አዋጅ የግብር መሠረቱን የሚያሰፋ በመሆኑ፣ ተጨማሪ ገቢ እንደሚሰበስብ መንግሥት በሰፊው ያምናል፡፡ በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተገለጹት አዲስ የገቢ ግብር ዓይነቶች መካከል ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ አየር መንገዶች በኢትዮጵያ ከሚያገኙት የዕቃና የተጓዦች ገቢ ላይ የተጣለ ሦስት በመቶ ግብር፣ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚያካሂዱት ጥበባዊ ወይም የስፖርት ትዕይንት ገቢ 10 በመቶ ግብር፣ እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ዜጐች ኢትዮጵያ ውስጥ በሚያገኙት ገቢ ላይ የተጣሉ የተለያዩ የግብር ዓይነቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ከተጠቀሱት ሕጐች በተጨማሪ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች በተጓደሉ ዳኞች ምትክ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡ ዕጩ ዳኞች እንደሚሾሙ ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡

ሪፖርተር በሌላ በኩል እንደሰማው ከሆነ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አስቸኳይ ስብሰባው በተጠራበት ዕለት በምክር ቤቱ ተገኝተው፣ በተወሰኑ ሚኒስትሮች ላይ ያደረጉትን ሹምሽር እንዲፀድቅላቸው ያስደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህንን ዓይነቱ አስቸኳይ ስብሰባ ፓርላማው በቅርብ ጊዜ የጠራው በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈት ወቅት መሆኑ ይታወሳል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...