የዜጎች እኩል ተጠቃሚነት በተግባር እንዲኖር በመላ አገሪቱ ማኅበራዊ ፍትሕ መረጋገጥ አለበት፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ ከአገሩ ሀብት ፍትሐዊ የሆነ ድርሻ፣ ተመጣጣኝ የሆኑ የሥራ ዕድሎችና ተጠቃሚነት ሊኖሩት ይገባል፡፡ ዜጎች በሀብት ክፍፍል፣ በሥራ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በመኖሪያ ቤትና በመሳሰሉት በጥረታቸው መጠን ተጠቃሚ መሆን አለባቸው፡፡ ማኅበራዊ ፍትሕ የሚረጋገጠው ዜጎች መብትና ግዴታቸው በግልጽ ታውቆ ዕውቅና ሲሰጠው ነው፡፡ ከአድልኦና ከመድልኦ ነፃ የሆነ መንግሥት ቅድሚያ የሚሰጠው ለዜጎች እርካታ ነው፡፡ ይህ እርካታ የሚለካው ደግሞ የመንግሥት አሠራር ግልጽና አሳታፊ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ በዜጎች መካከል ልዩነት የሚፈጠረውና ተመጣጣኝ ያልሆነ የኑሮ ዘይቤ የሚስተዋለው፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሌለበት ሥርዓት ሲሰፍን ብቻ ነው፡፡ ይህንን ዓይነቱን የተዛባ አሠራር ማስወገድ የሚቻለው ማኅበራዊ ፍትሕ በማንገሥ ብቻ ነው፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ደግሞ ዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት ትልቅ ሚና አላቸው፡፡
ብዙኃኑ ሠርቶ አደር ሕዝብና የንግዱ ማኅበረሰብ በአግባቡ የሚፈለግበትን ግብርና ቀረጥ እየከፈለ የዜግነት መብትና ግዴታውን ሲወጣ፣ ከግብር ሥርዓቱ ተሸሽገው ለማመን የሚከብድ መጠን ያለው የአገር ሀብት የሚዘርፉ አሉ፡፡ ግብር በመሰወር፣ ቀረጥ ባለመክፈል፣ ኮንትሮባንድ በመነገድና በመሳሰሉት ሕገወጥ ተግባራት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ የአገር ሀብት የሚዘርፉ አልጠግብ ባዮች ባሉበት አገር ውስጥ፣ የተለያዩ ጫናዎችንና የዋጋ ግሽበትን መቋቋም ተስኗቸው የሚደቆሱ ሞልተዋል፡፡ ዕድሜ ልክ ተለፍቶ እንኳን ለማግኘት ለማሰብ የሚያዳግቱ ንብረቶችን በጥቂት ወራት ውስጥ ማከማቸት የሚችሉ ዘመነኞች በሚፈለፈሉበት አገር ውስጥ እንዴት ስለእኩልነት መነጋገር ይቻላል? ምንጩ በማይታወቅ ገንዘብ እጅግ በጣም ዘመናዊና ውድ ተሽከርካዎች፣ ቪላዎች፣ የንግድ ተቋማት፣ ወዘተ የሚያካብቱትን የሚጠይቅ የለም ወይ? በየቦታው እንደ አሸን እየፈሉ ያሉ የአየር በአየር ሚሊየነሮች አገሪቱን በስፋት ማዳረስ ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው? አገራቸውን በቅንነት የሚያገለግሉ ኩሩ ዜጎች ባሉበት አገር ውስጥ፣ ኃፍረተ ቢሶች አገርን እንዲዘርፉ መፍቀድ ያሳፍራል፡፡
በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት በሕጉ መሠረት ለጨረታ መቅረብ የሚገባቸው ፕሮጀክቶች በአቋራጭ በሙስና ሲጠለፉ፣ ግንባታቸው ከሚያወጣው ዋጋ በላይ በእጥፍ ሲጠየቅባቸው፣ በተፈለገው ጊዜ ሳይጠናቀቁ ሲቀሩና የትም ሲባክኑ በስፋት ይታያል፡፡ በጥቅም ሸሪክነትና በመሳሰሉት የተደራጁ ኃይሎች የአገር ሀብት እያወደሙ ያላግባብ ሲበለፅጉ ስለማኅበራዊ ፍትሕ እንዴት መነጋገር ይቻላል? በመንግሥት በጀት የሚገነቡ ሆስፒታሎች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ መንገዶች፣ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ የመስተዳድር ሕንፃዎች፣ ወዘተ ጨረታዎች በሙሰኞች ተጠልፈው ከፍተኛ የአገር ሀብት ይወድማል፡፡ የፕሮጀክቶች አፈጻጸምና የወጣባቸው ወጪ አይገናኝም፡፡ በስንት መከራ ተገንብተው ተጠናቀቁ ሲባል የጥራት ችግር ፈጦ ይወጣል፡፡ የተዘረፈው ሀብትና የሚገኘው ውጤት አይመጣጠንም፡፡ ጥቂት ምርጦች ተቧድነው ሲበለፅጉ ብዙኃኑ ዕዳ ይከፍላሉ፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለበት አሠራር እንዲህ ዓይነቱን አሳፋሪ ድርጊት ነው የሚያፈራው፡፡
በመንግሥት ዕቃ ግዥ፣ ጨረታና የኮንትራት ሥራዎች ላይ ፍትሐዊ አሠራሮች እየተገፉ ሌብነቶች ስለሚበረታቱ ጤናማ የንግድ ውድድር እንዳይኖር እያደረጉ ነው፡፡ ሕጋዊ መንገድ ተከትሎ ተወዳድሮ ከማሸነፍ ይልቅ አማራጭ ማሳደድ የተለመደ ሆኗል፡፡ በዘመኑ ‹ጉዳይ ገዳይ› ተብለው በሚታወቁ ደላሎች አማካይነት ሕገወጥ ተግባራት በመስፋፋታቸው ግዥዎችንና ጨረታዎችን በሕጋዊ መንገድ ተወዳድሮ ማግኘት ፈተና የሆነባቸው ዜጎች ብሶትና ምሬት ጣሪያ ነክቷል፡፡ ሕጋዊው መንገድ እኩል ተጠቃሚነትን የሚደግፍ አሠራር ቢሆንም፣ ሕገወጥነት የበላይነት ይዞ የጥቂቶች መፈንጠዣ ሆኗል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ዓይን አውጣ አሠራር ምክንያት ብዙኃን እየተገፉ፣ ጥቂቶች በአቋራጭ ባገኙት ሲሳይ ይከብራሉ፡፡ አሠራሮች ግልጽነትና ተጠያቂነት ስለሌላቸው በሕጋዊ መንገድ መንቀሳቀስ ሞኝነት፣ ሕገወጡን ጎዳና መያዝ የብልጥነት መለያ ሆነዋል፡፡ ብልጥነቱ ግን አገርን እየገዘገዘ ሕዝብን እያስለቀሰ ነው፡፡ በዜጎች መካከልም ደረጃ እያወጣ ነው፡፡ የኢትዮጵያዊነትን አኩሪ እሴት እየሸረሸረ ነው፡፡
በአንድ አገር ሰላም የሚኖረው ዜጎች ማኅበራዊ ፍትሕ አለ ብለው ሲያምኑ ነው፡፡ ጥቂቶች በማይታመን ፍጥነት የአገሪቱን ሀብት ሲቀራመቱና ብዙኃኑ ከድህነት ወለል በታች ሲሆኑ ስለሰላም መነጋገር አይቻልም፡፡ ብዙኃኑ ሕዝብ የሚፈለግበትን ግብር በአግባቡ ሲከፍል፣ ጥቂቶች በቢሊዮኖች የሚቆጠር ሀብት ሲሰውሩ ማኅበራዊ ፍትሕ ስለሚጠፋ ብጥብጥ ይነሳል፡፡ ጥቂቶች የአገሪቱን መሬት ወረው እየቸበቸቡ ሲከብሩና ቢጤዎቻቸውን ሲያበለፅጉ፣ ብዙኃኑ አንጀታቸው እያረረ አገር ሰላም አይሆንም፡፡ በቂ የሆነ ምግብ፣ ልብስ፣ የትምህርትና የጤና አገልግሎት፣ ለኑሮ ተስማሚ የሆነ መኖሪያ፣ ወዘተ የሌለው ሠርቶ አደር ሕዝብ በብዛት በሚኖርባት አገር ውስጥ፣ ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨምሩ የሚንደላቀቁ ሰዎችን ማየት ያሳፍራል፡፡ ለአገር ህልውናም አደጋ ነው፡፡ የአገር ህልውና የሚያሳስባቸው ወገኖች እንዲህ ዓይነቱን ኢፍትሐዊነት ለማስወገድ መረባረብ አለባቸው፡፡
ማኅበራዊ ፍትሕ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲ መብቶቻቸው የሚከበሩበት፣ በሁሉም መስኮች ጥቅሞቻቸው በአግባቡ የሚስተናበሩበት፣ በጥረታቸው መጠን የሚያገኙበት፣ በሕግ ፊት እኩል የሚሆኑበት፣ ሐሳባቸውን በነፃነት የሚገልጹበት፣ የመንግሥት ጥበቃ የሚያገኙበት፣ በሕጉ መሠረት ብቻ የሚዳኙበት፣ ወዘተ ማዕቀፍ ነው፡፡ ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን ከፍተኛው ኃላፊነት ያለበት በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ነው፡፡ ይኼ ዓይነቱ መንግሥት አሠራሩ ግልጽነትና ተጠያቂነት ስላለበት ለሕዝብ ፈቃድ ታዛዥ ነው፡፡ ኃላፊነቱን በአግባቡ ይወጣል፡፡ በመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በፍትሕ መዛባትና በሙስና በምትናጠው አገራችን መንግሥት ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ አይደለም፡፡ ችግሮቹ መኖራቸውን አምኖ ዕርምጃ ለመውሰድ እየሠራሁ ነኝ ከማለት ውጪ፣ ጠብሰቅ ያለና የሚያረካ ዕርምጃ ሲወስድ አይታይም፡፡ ይልቁንም በእነዚህ ችግሮች የተማረረ ሕዝብ በየቦታው ምሬቱን እየገለጸ ነው፡፡ የፈለገውን ያህል ለማድበስበስ ቢሞከርም የሕዝብ ብሶት እየገነፈለ እየወጣ በተለያዩ ሥፍራዎች ለግጭቶች መነሳት ምክንያት እየሆነ ነው፡፡
በመላ አገሪቱ የሚገኙ ዜጎች ግዴታቸውን እየተወጡ መብታቸውን ሲጠይቁ ዝም ማለት አይቻልም፡፡ በተለይ የመብት ጥያቄዎች እየተገፉ የማያስፈልጉ ግጭቶች ከሚቀሰቀሱ ይልቅ፣ የሕዝብን የልብ ትርታ እያዳመጡ ምላሽ መስጠት የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ነው፡፡ በተለይ ከመጠን በላይ የሆነ የአገር ሀብት እየተዘረፈ ጥቂቶች ያላግባብ የሚበለፅጉበትን ሕገወጥ እንቅስቃሴ ማስቆም የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ኃላፊነት ብቻም ሳይሆን የህልውናውም ጉዳይ ሊሆን ይገባል፡፡ ሕዝብ ጥያቄ ሲያነሳ በቅጡ አዳምጦ ምላሽ መስጠት ሲገባ፣ ያልሆነ አተካሮ እየፈጠሩ ግጭት አንዲባባስ ማድረግ ሊያበቃ ይገባል፡፡ የሕዝብ ጥያቄዎችን በማፈንና የተጣመመ ትርጉም በመስጠት የጥጋበኞችን አጀንዳ ማራመድ አገርን ይጎዳል፡፡ በተለይ በዝርፊያ በሚገኝ ጥቅም ልባቸው የተደፈነ ወገኖች ማኅበራዊ ፍትሕ እንዳይኖርና ተጠያቂነት እንዳይነሳባቸው የሕዝብን ድምፅ ከማፈን ወደኋላ አይሉም፡፡ ሕግ መከበር አለበት፡፡ መንግሥት በሕግ የሚገደድበትን አሠራሩን ለሕዝብ ግልጽ ያድርግ፡፡ መሸፋፈኑ ይበቃል፡፡
በተለይ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ብቃት የሌላቸው፣ ከዝርፊያ በስተቀር ምንም የማይታያቸው፣ የአገርና የሕዝብ ጉዳይ የማያሳስባቸው፣ ከጠባብ ቡድናዊ ፍላጎት የዘለለ ዓላማ የሌላቸውና በደመነፍስ የሚኖሩ በቃችሁ ሊባሉ ይገባል፡፡ አለበለዚያ የዜጎች ተጠቃሚነት በሌለበት ማኅበራዊ ፍትሕ ሊኖር አይችልም!