Tuesday, February 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

መንግሥት በአግባቡ ሥራውን የሚያከናውነው ራሱን ሲያፀዳ ብቻ ነው

በልዑል ዘሩ

ሪፖርተር ጋዜጣ ቅጽ 21 ቁጥር 1686 ሰኔ 19 ቀን 2008 ዕትም እጄ ገብቶ ነበር፡፡ ጋዜጣው እንደተለመደው ሁሉ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግን ‹‹የቤት ሥራዎችህን በአግባቡ ከውን!›› ሲል አጥብቆ ያሳሰበበትን ርዕሰ አንቀጽ ይዟል፡፡ በመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ ከሕዝብ ጋር ስለመታረቅ፣ መንግሥታዊ የአፈጻጸም ብቃት፣ ድርቅና የጎርፍ አደጋ፣ እንዲሁም የኢትዮ ኤርትራ ግጭት ላይ ያተኮሩት ምክረ ሐሳቦች ልባም ከተገኘ ብዙ የሚያሠሩ ጭብጦችን ይዘዋል፡፡

እኔም በግል እምነቴ ከእነዚህ ነጥቦች ጋር የተሳሰሩና የተለዩም ቢሆኑ የመንግሥት የቤት ሥራዎች ናቸው የምላቸውን ነው ለመተንተን የወደድኩት፡፡ እነዚህን ወቅታዊ ፈታኝ ሁኔታዎች መንግሥት አያውቃቸውም የሚል መነሻ ባይኖርም፣ ተግባር ገብቶ በግልጽነትና በድፍረት መከወን ላይ ያለውን እግር መጎተት ግን ያቁም፣ ያስተካክል በሚል ሥሌት ነው የምሞግተው፡፡

የመልካም አስተዳደር ጉዳይ

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዓመቱ መጨረሻ ስብሰባ ላይ ሲናገሩ፣ ‹‹መልካም አስተዳደር በአንድ ጀንበር የሚረጋገጥ አይደለም፡፡ ዘንድሮ ግን ጉዳዩን አጀንዳ አድርገን ትግል በመጀመራችን ቢያንስ ሙስና፣ ብልሹ አሠራርና ደካማ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዳይባባስ አድርገናል፡፡ ለቀጣይ ንቅናቄም መነሻ አሠራር መዘርጋት ጀምረናል፤›› ብለዋል፡፡

የዘንድሮ የመልካም አስተዳደር ‹‹ትግል›› በአዲስ አበባ፣ በአማራ፣ በድሬዳዋ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይና በደቡብ ክልሎች ብቻ ከአምስት ሺሕ በላይ መካከለኛና ዝቅተኛ የመንግሥት መካከለኛና ዝቅተኛ ሹመኞችን ከኃላፊነትም አስነስቷል፡፡ ከእነዚህ መካከል ወደ ወህኒ የተወረወሩም አሉ፡፡ ግን ድምር ውጤቱ ምን አስገኘ? ትግሉስ ምን ደረጃ ላይ ቆሟል መባል ይኖርበታል፡፡

አንዳንድ ተገልጋይ ዜጎችና ባለሀብቶች እንደሚናገሩት አሁንም በአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ሌብነቱና መደራደሩ አለ፡፡ (በተለይ መሬት፣ ገቢ፣ ንግድና ብቃት ማረጋገጥ…) የመሳሰሉት ዘርፎች ላይ ‹‹የሽያጭ ማጣሪያ›› የሚመስል መቀባበል እንደ ደራ ነው፡፡ በእርግጥ ለዚህ ችግር አለመቀረፍ ጉቦ አቀባዩ የኅብረተሰብ ክፍል ዋነኛ ተጠያቂ መሆኑ ባይቀርም፣ የሕዝብ ሀብት ቅርጥፍ አድርገው በልተው በሞቀ ሁኔታ የሚኖሩ ባለሥልጣናት ሁኔታ ሌላውንም እንዳደፋፈረው ይገመታል፡፡

ከመንግሥት ሥልጣናት ጋር ዝምድና፣ ሽርክናና ቅርርብ ምክንያት የሚገኙ የጨረታ ሥራዎች፣ የመሬት፣ የቤት፣ የብድር አቅርቦትና መሰል ‹‹ምቹ ሁኔታዎች›› ሁሉ የፍትሐዊነት ተጠየቅን ያስነሳሉ፡፡ ለእነዚህ ከሕዝብ ዓይንና ጆሮ ያልተሸሸጉ ድርጊቶች ‹‹ለምን!?›› የሚል ሞጋችና ታጋይ ከጠፋ ውርደትን የሚያስከትሉ ናቸው፡፡

የመልካም አስተዳደር ትግል መጀመርን በማሳበብ የውሳኔ ሰጪነት ፍርኃት ስለመንገሡም ይነገራል፡፡ ጥቃቅኑ ውሳኔ ሁሉ በኮሚቴና በስብሰባ ከመፈጸም አንስቶ ቀን ከሌት በግምገማ ተጠምዶ መዋል መደበኛ ሥራው ላይ የሚያሳድረው ጫና ቀላል አይሆንም፡፡ ከዚሁ ባልተናነሰ የማሻሻያ ዕርምጃው ግለትና ጥንካሬም ቢሆን ከቦታ ቦታ (ከክልል ክልል) የተለያየ ነው፡፡ በእያንዳንዱ የሥራ ኃላፊና ፈጻሚ ውስጥ ያለው የባለቤትነት ስሜትም ቢሆን የነጠፈና የተቀዛቀዘ ሆኖ ይታያል፡፡

እዚህ ላይ በጥብቅ መፈተሽ ያለበት የሲቪል ሰርቪሱ የመፈጸምና የማስፈጸም አቅምና ጥንካሬ ጉዳይ ነው (ይህ ነጥብ በሪፖርተር ርዕሰ አንቀጽም ላይ ተነስቷል)፡፡ ከፌዴራል እስከ ወረዳና ቀበሌ ባሉት የመንግሥት መዋቅሮች ጠንካራና ተወዳዳሪ ሙያተኛና የሥራ ኃላፊዎች ሊኖሩ ይገባል፡፡ የአገር ፍቅር ስሜት (ከመንደርተኝነትና ቡድንተኝነት የፀዳ) እና ሥነ ምግባርም ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው፡፡

እነዚህ እውነታዎች መጓደላቸውን በርካታ ማሳያዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡ የዋና ኦዲተር ሪፖርት የዘረዘራቸው ተቋማትና የሕዝብ ሀብት፣ በስኳር ኮርፖሬሽን፣ በውኃና መስኖ፣ በቤቶች ልማት፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የቆጠራና የምርመራ ውጤቶች ላይ የታየውን ገመና ታዝበናል፡፡ እንደ አገር ‹‹ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ›› በሚመስሉ ሪፖርቶች እየተጀቦኑ በጥቂት ታታሪ መሪዎች ጥረት ብቻ አገርን ለመቀየር ማሰብ የሚሆን ጉዳይ አይደለም፡፡ መጨናገፉም አይቀርም፡፡

ከእነዚህና ከሌሎች በርካታ እውነታዎች አንፃር መልካም አስተዳደርን ይበልጥ ለማጎልበት ገና ብዙ ሥራ ያስፈልጋል፡፡ የሰው ለውጥ ብቻ ሳይሆን የሥርዓት ማሻሻያ፣ የፖሊሲ ክለሳ ካስፈለገም መታየት አለበት፡፡ የአሿሿምና የምደባው ጉዳይም ከጠባቡ ክብ (Circle) ወጥቶ በአገራዊ ስሜት ወቅቱና መድረኩ የሚጠይቃቸውን ሰብዕናዎች እንዲያስብ ካልተደረገ፣ እየተቧደነ የመዝረፍንም ሆነ ሕዝብ የማስመረሩን በረራ የሚገታ ፍሬን መያዝ የሚቻል አይሆንም፡፡

ሕዝብ ይደመጥ፣ ይሳተፍ

ኤሕአዴግ (አሁን ያለው መንግሥት) ይመሰገንባቸው ከነበሩ ነገሮች አንዱ ሕዝብ የማማከርና የማሳተፍ ጥረት የማያደርግ መሆኑ ነበር፡፡ ይህ በተለይ ከትጥቅ ትግሉ አንስቶ እስከ ምርጫ 97 ድረስ ‹‹የተሻለ›› ነበር የሚሉ ሰዎችን አዳምጣለሁ፡፡ ከዚያ ወዲህ ግን መንግሥት ወደ ሕዝብ የሚወርደውና የሚያማክረው ለምርጫ ሰሞን ብቻ ነው ይባላል፡፡ ይህን ለማረጋገጥም አስገዳጅና የተፅዕኖ ውሳኔዎችን ‹‹በመጫን›› ጭምር ሕዝብ ላይ የሚያሳርፈው ምርጫው ካለፈ ከጥቂት ወራት አንስቶ መሆኑ ነው፡፡

ለአብነት ያህል ባሳለፍነው በጀት ዓመት በኦሮሚያ ክልል የልተገመተ የሕዝብ ቁጣ ቀስቅሶ ሥርዓቱን ጥያቄ ውስጥ ያስገባው ጣጣ የመጣው በሕዝብ ውይይት ባልዳበረው የ‹‹ጋራ ማስተር ፕላን›› ጉዳይ ነው፡፡ ራሱ የክልሉ መንግሥት ባለሥልጣናትና የኦሕዴድ ካድሬዎች ባላመኑበትና በጥርጣሬ ባዩት ፕላን ‹‹ትግበራ›› ስም ሕዝቡ እስከ መገንፈል ደርሷል፡፡ ሕይወትና ንብረት ጠፍቷል፡፡

በተመሳሳይ ወቅቶች በአዲስ አበባ ከተማና ዳርቻ የሚገኙ ሕገወጥም ይባሉ ሕጋዊ ነዋሪዎችን የማስነሳቱ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በተለይ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በተወሸቁ ቀማኞች ጭምር ተታለው በሕገወጥ መሬት ላይ ግንባታ ያከናወኑና ሀብታቸውን ያፈሰሱ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሁኔታ አሳሳቢ ነው፡፡ በእርግጥ መንግሥት ሕገወጥነትን የመከላከል ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበት ይታወቃል፡፡ ግን ገና በእንቁላሉ ጊዜ ሕዝቡን እያሳተፈ ሊያርመው በተገባ ነበር፡፡

ከቅርብ ወራት ወዲህ በሰሜን ጎንደርና በትግራይ ክልል ድንበርተኛ ሕዝቦች መካከል የተነሳው የ‹‹ወልቃይት ጉዳይ››ም ቢሆን የተፍታታ ምክክርና መተማመን የተደረገበት አይመስልም፡፡ ከዚያ ይልቅ የፖለቲካ ትርፍ ያስገልኛል ያለው ሁሉ እየተነሳ ላገኘው ማኅበራዊ ድረ ገጽና ሚዲያ ሲረጨው የሚውለው ‹‹ወሬ›› የሕዝቡን ቀልብ እየሰነገው ይገኛል፡፡ ወልቃይትና አካባቢውን አንድ የልማት ኮሪደር አድርጎ የትግራይም ይሁን የአማራ ክልል ሕዝብ በጋራ እንዲጠቀሙበት ማድረግ ሲቻል፣ ‹‹በእኔ ነው›› ንቁሪያ ይኼ ሁሉ መከራር የሥርዓቱን አደጋ ላይ መውደቅ አመላካች ነው የሚሉም እየበዙ ነው፡፡

አገሪቱ ባፀደቀችው ሕገ መንግሥት መሠረት የሚከናወን የማንነት ጥያቄ፣ የፖለቲካ ምኅዳር ማስፋት፣ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ፣ የሐሳብ ነፃነት፣ የመደራጀት ጉዳይ … መመለስ ያለባቸው በሕገ መንግሥቱ መሠረት ብቻ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ክልል ከክልል የጋራ አረዳድና ውሳኔም ያለ አይመስልም፡፡ ጣልቃ ገብነትና ተፅዕኖ ያለበት አካሄድም እንዳይኖር ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲን የማሳደጉ ጉዳይ የህልውና ጉዳይ ነው›› ሲባል አፍአዊ ሊሆን አይገባም፣ መሆንም አይችልም፡፡ ከ80 በላይ ብሔሮችና ቋንቋዎች፣ በርከት ያሉ የሃይማኖት ዓይነቶች፣ ብትንትኑ የወጣ አመለካከትና ፍላጎት እንዲሁም የታሪክ መጓተት በረበበበት ሁኔታ ብድግ ብሎ ‹‹ቻይናን›› ልሁን ማለት የሚመከር አይደለም፡፡ ያውም ባለፉት 25 ዓመታት ዴሞክራሲን እየተለማመደ የመጣ ዜጋ ባለበት፣ የዓለም መረጃ ሁኔታም ሁሉን እንደ ወንፊት የሚያንዠቀዥቅ በሆነበት አግባብ ፈጽሞ ሊታሰብም አይችልም፡፡

ይህ ቢሆንም ልማትን ለማምጣት በመታተር ብቻ የዴሞክራሲ መረጋገጥን ማሰብ ያዳግታል፡፡ ገንዘብና መሣሪያ ያለው መንግሥትና ገዢው ፓርቲ ብቻ ‹‹ይደመጥ›› ወደሚል ዝንባሌ እንዳይኬድም ዙሪያ ገባውን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ በየጥጋጥጉ ያለውን አስተሳሰብ ንፋስ እንዲመታው ማድረግ፣ ሕዝብ አቋሙን እንዲገልጽበት ማስቻል ከሥርዓት መሻገት ያድናል፡፡ የፖለቲካ መታደስና የመነቃቃት አማራጭ መኖር አለበት፡፡

ሕዝብ በሚከፍለው ግብር፣ ለልማት በሚያወጣው ገንዘብ፣ ጉልበትና ዕውቀት ላይ ሁሉ እየተማመነ መኖር ይገባዋል፡፡ ‹‹የግዳጅ ቋንቋ›› የተቀላቀለባቸው የአንዳንድ የመንግሥት ኃላፊዎች ንግግርና ተግባራት ‹‹የደርግነት›› ባህሪዎች ናቸው፡፡ ተሳዳቢነትና ኃይል መድረሻቸው ጥላቻና መቃቃር ነው፡፡ ፍቅር፣ አንድነት፣ ሰላምና እኩልነትን መስበክ ብቻ ሳይሆን በተግባር ማሳየት የቻሉ መንግሥታትና የመንግሥት መሪዎች ይበልጥ ሕዝባዊና ተፈላጊ ናቸው፡፡ ከእነዚያ መማር ሕዝብ አድማጭና አሳታፊነትን ያጎናፅፋል፡፡

የአገር ሉዓላዊነትና ቀጣናዊ ጉዳይ

አገራችን ያለችበት ቀጣና ለሽብርተኝነት አደጋ የተጋለጠ፣ በቀይ ባህር አካባቢ ለጦር የታጠቁ አገሮች የፍጥጫ የስበት ማዕከል፣ የዓባይ ተፋሰስ የቅርብ ጊዜ ትኩሳት፣ አገሪቱን እንቅልፍ የማያስተኛ መሆኑ ተደጋግሞ ተወስቷል፡፡ ከዚህ አንፃር ከመካከለኛው ምሥራቅ እስከ ምዕራባውያን፣ ብሎም ከሩቅ ምሥራቅ እስከ ሰሜን አፍሪካ አገሮች በበጎም ሆነ በመጥፎ ትኩረት የሚስብ አካባቢ ውስጥ ነው ያለነው፡፡

ኢትዮጵያ ደግሞ ካላት ስትራቴጂካዊ ጂኦፖለቲካ ባሻገር እስከ 100 ሚሊዮን እየተቃረበ ባለው ሕዝቧ፣ እስከ ትሪሊየን ብር አጠቃላይ ምርት ማካበት የጀመረች መሆኗ ትኩረትን ይስባል፡፡ ለ15 ዓመታት ባለሁለት አኃዝ ብቻ ሳይሆን ከዓለም ፈጣን ዕድገት ተርታ የተመደበው የኢኮኖሚ ጉዞ አባባሉን ያረጋግጣል፡፡ አገሪቱ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በቱሪዝም መስክ ሌላውን ዓለም ለመሳብ የምትከተለው ሥልትም ሆነ በአብዛኛው ‹‹በሰጥቶ መቀበል›› መርህ የሚመራው ዲፕሎማሲ፣ ከየአቅጣጫው ብዙዎችን የመሳቡ ሚስጥርም ይኼው ነው፡፡

ይህን ብሩህ የሚመስል ተስፋ የሚያደበዝዙ በቅርብ ርቀት ቀውሶች ግን አሉ፡፡ አንደኛው የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ፍጥጫና መቆራቆስ ነው፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ ተንታኞች ደጋግመው እንደሚወተውቱት ከኤርትራ መንግሥት ጋር የተፈጠረው አለመግባባት ዘላቂ መፍትሔ ሊያገኝ ይገባል፡፡ ካልሆነ ግን ‹‹እኔ ከሞትኩ …›› ባዩ ሻዕቢያ ኢትዮጵያን እንደ ጠላት ለሚመለከት የትኛውም ወገን መሸጋገሪያና አጋር እየሆነ አገሪቱን ከማድማት የሚቆጠብ አይደለም፡፡ ይኼንን በተለያዩ ጊዜያት ከሳዑዲ ዓረቢያና ከኢራን ጋር ባሳየው ሽርክና ብቻ ሳይሆን በዚህ ክፍለ ዘመን ሥርዓቱን በነፍጥና በኃይል ለማውረድ የሚፋለሙ ዜጎችን በማስታጠቅና በማሰማራት አሳይቷል፡፡ የፊት ለፊት ትንኮሳ የሞከረባቸው፣ የዕገታና የዘረፋ ድራማዎችን የተወነባቸው ጊዜዎች እንደነበሩም በመንግሥት በኩል ተገልጿል፡፡ ስለዚህ በቀዳሚነት ይህ ‹‹ተከድኖ ይብሰል›› የተባለ የኢትዮ-ኤርትራ አጀንዳ ሊቋጭ ይገባል፡፡

ሌላኛው ተግባር የኢትዮ-ሶማሊያ ጉዳይ ነው፡፡ እርግጥ ነው ኢትዮጵያ በሶማሊያ በኩል እየመጣ የነበረውን ግብረ ሽብርና ጥቃት ለመመከት ብሎም የሶማሊያን የሽግግር መንግሥት በእግሩ ለማቆም ላለፉት ስምንት ዓመታት ገደማ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍላለች፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በአፍሪካ ኅብረት ዕውቅና ጭምር ጦሯን አስገብታም እስካሁንም አላወጣችም፡፡

ይህ ታሪካዊ ሁነት ግን መቋጫ ሊያገኝ ይገባል፡፡ አንደኛው የአገራችን ወታደሮች እስካሁንም ካልቆመው ጥቃትና ግብረ ሽብር ጉዳት መጠበቅ አለባቸው፡፡ ሌላው ግን ለዓመታት በአንቀልባ ተይዞ በእግሩ ያልቆመው የዚያች አገር ሰላም ሕዝቡን በንቃት ባሳተፈ መንገድ እንዲፈታ ዕድሉን ለእነሱው መስጠት አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ሸማቂውን ወገን የሚደገፉ ሶማሊያውያን መኖራቸውም አይቀርምና ከአገራችን ጋር ቂምና ቁርሾ እንዳይዙ አድርጎ ፋይሉን መዝጋትና ጦሩ በአገሩ ሆኖ ሉዓላዊነቱን እንዲያስከብር መታሰብ ይኖርበታል፡፡

የደቡብ ሱዳን ውስጣዊ ትርምስ ማገርሸቱም ለኢትዮጵያ መንግሥት ሌላ የቤት ሥራ ይዞ መጥቷል፡፡ አንደኛው ከወራት በፊት በድንበር አካባቢ በሚኖሩ ዜጎች ላይ የደረሰው ዓይነት የግድያና የዘረፋ ተግባር እንዳይፈጸም ጥበቃ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሌላኛው ግን የደቡብ ሱዳን መንግሥት ወደተበታተነና የከሰረ ‹‹መንግሥት›› ደረጃ ከወረደ ሕገወጥ ስደት፣ ሕገወጥ መሣሪያ ዝውውርና ተዛማጅ ወንጀሎች መናኸሪያ የመሆን ዕድል ነው ያለው፡፡

ይህንን ችግር ለመቅረፍ የኢትዮጵያ መንግሥት የጀመራቸው የዲፕሎማሲና የሰላም ማስከበር ጥረቶች አሉ፡፡ ግን ከዚህም በላይ ዓለም ችግሩን እንዲያውቀው ማድረግና የጋራ ድንበሩን በተጠናከረ አኳኋን መጠበቅ ያስፈልገዋል፡፡ በነገራችን ላይ ‹‹ኢትዮጵያ የአፍሪካ ትልቋ የስደተኞች መሰብሰቢያ›› ከሚለው ሞገስ ጀርባም ከየአገሩ የሚመጣው ስደተኛ ጎርፍ በአገር ደኅንነት፣ በኑሮ ውድነትና በሕዝቦች የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ያለው ተፅዕኖ ሊፈተሽና ሊጤን ይገባዋል፡፡

የመጨረሻው መመለስ የለበት የጎረቤት አገር የቤት ሥራ የኢትዮ-ሱዳን ድንበር አጀንዳ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ተቃዋሚዎች ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ለሱዳን መሬት ሰጠ፣ ለመልካም ወዳጅነት ሲባል የአገር ጥቅም አሳልፎ ሰጠ…›› ሲሉ ይደመጣል፡፡ ይህን አባባል መንግሥት ‹‹ሐሰት ነው›› ቢልም ሱዳን ትሪቡንን የመሳሰሉ የካርቱም ጋዜጦች ግን ብዙ ሐተታዎችና ዜናዎችን ጽፈውበታል፡፡ የሁለቱ አገሮች የጋራ ድንበር ኮሚሽንም ያዝ ለቀቅ እያደረገ ጉዳዩን ለዓመታት እየፈተለው መጥቷል፡፡

ምንም ተባለ ምን ግን መንግሥት በታሪክ የሚያስወቅሰውን ብቻ ሳይሆን፣ የአገሪቱን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ ዕርምጃ ሊወሰድ እንደማይችል ይታመናል፡፡ ሥራው የሚፈልገውን ጥንቃቄ ማድረግም ተገቢ ይሆናል፡፡ ከዚህ ተነጥሎ የማይታየው የታላቁ ህዳሴ ግድብና የኢትዮ-ሱዳን-ግብፅ ከላይ ከላይ ለስላሳ የሚመስል ግንኙነት እንደ ዓሳ አበላል በብልኃትና በዕውቀት መያዝ ይኖርበታል፡፡ ይኼኛው የቤት ሥራም ቢሆን ቀላል ግምት የማይሰጠው ከባድ የአገር ሸክም ነው፡፡

በአጠቃላይ መንግሥት የቤት ሥራዎቹ ብዙ ናቸው፡፡ ዋና ዋናዎቹን ጠቅልለን ያነሳናቸው ብቻም አይደሉም፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ግን ብቻውን ለመወጣት መሞከር በአንድ እጅ ማጨብጨብ ነው፡፡ ስለሆነም በየደረጃው ሕዝቡ በአገሩ ጉዳይ ይሳተፍ፣ ይምከር፣ ይወስን፡፡ ራሱን ካሸሸውና ከቀበረው ፖለቲከኛ በስተቀር ወደ ውይይት መምጣት የሚሻውም ይደመጥ፡፡ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና ወዳጅ አገሮች ምክርም በፋይዳው ልክ ይተግብር፡፡ ግን እነዚህን ሁሉ ተግባራት በአግባቡ ማከናወን የሚቻለው መንግሥት ራሱን ሲያፀዳ ብቻ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው Lzerugmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles