Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትሪዮ እና ዝግጅቷ

ሪዮ እና ዝግጅቷ

ቀን:

በደቡብ አሜሪካ ብራዚል ለመጀመርያ ጊዜ የሚካሄደው 31ኛው ኦሊምፒያድ ከሁለት ሳምንት በኋላ በይፋ ይጀመራል፡፡ የሪዮ ደጂኔሮ ከተማ የማንነቷ መገለጫ እንደሚሆን የሚጠበቀውና ከ207 አገሮች 10,293 በላይ አትሌቶች በ28 የስፖርት ዓይነቶች ሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ ለመግባት ከሚያደርጉት ትንቅንቅ ጎን ለጎን ዚካ ቫይረስና የፀጥታ ችግሮች ትኩረትን የሚይዙ ትዕይንቶች እንደሚሆኑበትም ይጠበቃል፡፡ በውድድሩ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ ሐምሌ 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ወደ ሥፍራው ያመራል፡፡
በአውስትራሊያ ሜልቦርን ከአምስት አሠርታት በፊት በተከናወነው ኦሊምፒክ በ12 አትሌቶች በየአራት ዓመቱ አንድ ጊዜ የሚካሄደውን የኦሊምፒክ ጨዋታዎችን የተቀላቀለችው ኢትዮጵያ ያለምንም ሜዳሊያ መመለሷ ይታወቃል፡፡ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያን ጥቁር ሕዝቦች በፈር ቀዳጅነቱና በኦሊምፒክ መድረክ ስሙን በወርቅ መዝገብ ያሰፈረው አበበ ቢቂላ፣ ጣሊያን እ.ኤ.አ. በ1960 ባስተናገደችው ሮም ኦሊምፒክ የተወዳዳሪዎችን ጽናት በእጅጉ በሚጠይቀው ማራቶን በኦሊምፒክ የመጀመርያውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኘ፡፡ ኢትዮጵያ በወቅቱ አሥር አትሌቶችን ማሳተፏም ይታወቃል፡፡ ‹‹የሯጮች ምድር›› በመባል የምትታወቀው ኢትዮጵያ በካዳና ሞንትሪያል በ1976፣ በአሜሪካ ሎሳንጀለስ በ1984 እና በደቡብ ኮሪያ ሲኦል በ1988 በተከናወኑት ኦሊምፒኮች በጊዜው አገሪቱ በምትከተለው ርዕዮት ዓለም ምክንያት ባትካፈልም፣ በተቀሩት ግን በሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ በመግባት ከጥቂት የዓለም አገሮች አንዷ ሆና እስከ ለንደኑ ኦሊምፒክ ዘልቃለች፡፡
በጃፓን ቶኪዮ በ1964 በተከናወነው ኦሊምፒክ በ12 አትሌቶች ተሳትፋ አንድ ወርቅና አንድ ነሐስ፣ ሜክሲኮ 1968 ባስተናገደችው ኦሊምፒክ በ18 አትሌቶች ተወክላ አንድ ወርቅና አንድ ነሐስ፣ በጀርመን አስተናጋጅነት በ1972 በተከናወነው ሙኒክ ኦሊምፒክ በ31 አትሌቶች ሁለት የነሐስ ሜዳሊያ፣ በሩሲያ አስተናጋጅነት በ1980 በተካሄደው ሞስኮ ኦሊምፒክ በ42 አትሌቶች ሁለት ወርቅና ሁለት ነሐስ፣ በስፔን አስተናጋጅነት በ1992 በተካሄደው ባርሴሎና ኦሊምፒክ በ20 አትሌቶች አንድ ወርቅና ሁለት ነሐስ፣ በአሜሪካ በ1996 በተካሄደው አትላንታ ኦሊምፒክ በ18 አትሌቶች ሁለት ወርቅና አንድ ነሐስ፣ በአውስትራሊያ በ2000 በተካሄደው ሲድኒ ኦሊምፒክ በ26 አትሌቶች አራት ወርቅ፣ አንድ ብርና ሦስት ነሐስ፣ በግሪክ በ2004 በተካሄደው አቴንስ ኦሊምፒክ በ26 አትሌቶች ሁለት ወርቅ፣ ሦስት ብርና ሁለት ነሐስ፣ በቻይና በ2008 በተከናወነው ቤጂንግ ኦሊምፒክ በ27 አትሌቶች አራት ወርቅ አንድ ብርና ሁለት ነሐስ እንዲሁም በ2012 በተከናወነው ለንደን ኦሊምፒክ በ35 አትሌቶች ተወክላ ሦስት ወርቅ፣ አንድ ብርና ሦስት ነሐስ በማስመዝገብ የኦሊምፒክ ተሳትፎ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡
ሜዳሊያውን ካስመዘገቡት 12 አትሌቶች ጥሩነሽ ዲባባ ሦስት የወርቅና ሁለት ነሐስ፣ ቀነኒሳ በቀለ በተመሳሳይ ሦስት ወርቅና አንድ የነሐስ ሜዳሊያዎች በስማቸው አስመዝግበው ሲጠቀሱ፣ መሠረት ደፋር ሁለት ወርቅና አንድ ነሐስ፣ ምሩፅ ይፍጠር ሁለት ወርቅና አንድ ነሐስ፣ ደራርቱ ቱሉ ሁለት ወርቅና አንድ ነሐስ፣ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ሁለት ወርቅ፣ አበበ ቢቂላ ሁለት ወርቅ፣ ማሞ ወልዴ አንድ ወርቅ፣ አንድ ብርና አንድ ነሐስ፣ ሚሊዮን ወልዴ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ገዛኸኝ አበራና ቲኪ ገላና አንድ አንድ የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገቡ ናቸው፡፡ ጌጤ ዋሚ አንድ ብርና ሁለት ነሐስ፣ ስለሺ ስሕን ሁለት ብር፣ እጅጋየሁ ዲባባና ደጀን ገብረመስቀል አንድ አንድ ብር በማስመዝገብ በኦሊምፒክ ስማቸውን በሜዳሊያ ሰንጠረዥ ያሰፈሩ አትሌቶች ናቸው፡፡
የነሐስ ሜዳሊያ ያስገኙት ደግሞ መሐመድ ከድር፣ እሸቱ ቱራ፣ አዲስ አበበ፣ ሶፍያ አሰፋና ታሪኩ በቀለ ናቸው፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ በይፋ እንደሚጀመር የሚጠበቀው 31ኛው ኦሊምፒያድ የሚከናወንበት ሪዮ ደጂኔሮ ምንም እንኳ ዝግጅቷን እንዳጠናቀቀች ብታስታውቅም፣ በአገሪቱ የተከሰተው የዚካ ቫይረስና የፀጥታዋ ጉዳይ ግን ከዝግጅቷ ባልተናነሰ መነጋገሪያነቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ ያም ሆኖ አስተናጋጇ ብራዚል ከ20 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት በመመደብ ለሚቀርብባት ወቀሳና ትችት አፀፋዊ ምላሽ በመስጠት ዝግጅቱን ያላንዳች ሥጋት ማጠናቀቅ የሚያስችላትን ሁሉ ማጠናቀቋን እየገለጸች ትገለኛለች፡፡
በ28 የስፖርት ዓይነቶች ለተከታታይ 17 ቀናት የሚዘልቀው የሪዮ ኦሊምፒክ በአጠቃላይ ከ306 በላይ ውድድሮች ይካሄዳሉ፡፡ የውድድሩ መርህም ‹‹አዲሲቷ ዓለም›› ተብሎ ተሰይሟል፡፡ የመወዳደሪያ ማዕከላቱ ደግሞ በሪዮ ደጂኔሮ 33 ቦታዎች ሲኖሩ፣ በሌሎች አምስት ከተሞች ማለትም በሳኦፖሎ፣ ቤሎ ሆሪዘንቶ፣ ሳልቫደሬ፣ ብራዚሊያና ማኑስ በተመሳሳይ ውድድሮች የሚደረጉባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡ ሪዮ ዲጄኔሮ በአጠቃላይ 17,000 ኦሊምፒያኖችንና ልዑካኖቻቸውን ታስተናግዳለች፡፡ የመክፈቻና የመዝጊያ ፕሮግራሞች በአገሪቱ በትልቅነቱ በሚጠቀሰው ማራካኛ ስታዲየም ይሆናል፡፡ የኦሊምፒክ መንደሯ 3,604 አፓርትመንቶች ሲኖሩት፣ በውስጡም ለኦሊምፒያኖችና ልዑካኖቻቸው አስፈላጊ የሚባሉ ቁሳቁሶች የተሟሉለት ስለመሆኑ ተነግሯል፡፡ ከ7.5 ሚሊዮን በላይ ትኬቶች ተዘጋጅተው የሚፈለገውን ያህል ሽያጭ ላይ አለመዋሉም እየተነገረ ይገኛል፡፡
የቴሌቪዥን ሥርጭት ከአጠቃላይ የኦሊምፒክ ገቢ 47 በመቶው ድርሻ እንደሚኖረውና ከ40,000 በላይ የሰዓት ሽፋን እንደሚያገኝም ይጠበቃል፡፡ ከመላው ዓለም የተውጣጡ ከ26,000 በላይ ጋዜጠኞች፣ ከ5,000 በላይ ቱሪስቶች በሪዮ ዴጀኔሮ ይታደማሉ፡፡ 31ኛውን ኦሊምፒያድ ሁለት አዳዲስ ስፖርቶች ማለትም ጎልፍና ራግቢ ውድድሮች ለመጀመርያ ጊዜ ይከናወኑበታል፡፡ ለሪዮ ደጂኔሮ ኦሊምፒክ 306 የወርቅ ሜዳሊያዎች የተዘጋጁ ሲሆን፣ ይዘታቸውም አንድ በመቶ ወርቅ፣ ሁለት በመቶ የብርና 68 በመቶ የመዳብ ቅይጥ መሆኑም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
31ኛው ኦሊምፒያድ እንደ ጎልፍና ራግቢ ስፖርቶች ሁሉ ስደተኛ ስፖርተኞች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመወከል ለመጀመርያ ጊዜ የሚታደሙበት ይሆናል፡፡ የተወዳዳሪዎቹ ብዛትም አሥር ናቸው፡፡
ከተወዳዳሪዎቹ አንዱ ዮናስ ክንዴ የተባለው ኢትዮጵያዊው አትሌት ይገኝበታል፡፡ የተቀሩት ደግሞ አምስቱ ደቡብ ሱዳናውያን፣ ሁለቱ የዲሞክራቲክ ኮንጎና ሁለት ሶሪያውያን ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...