Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርለቤት ኪራይ ተመን የተረቀቀው ሕግ የት ገብቶ ይሆን?

ለቤት ኪራይ ተመን የተረቀቀው ሕግ የት ገብቶ ይሆን?

ቀን:

የቤት ኪራይ ተመንን በተመለከተ በከተማዋ ከሚያወጡት ዋጋ በላይ የሚከራዩ ቤቶች በመብዛታቸው ኅብረተሰቡም በአማራጭ እጦት ክፈል የተባለውን እየከፈለ፣ ጨምር የተባለውን እየጨመረ እንደሚኖር ይታወቃል፡፡ የዚህን አቤቱታ መሠረት በማድረግ የቤት ኪራይን ተመን በተመለከተ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ረቂቅ መቅረቡን በጋዜጣችሁ አንብቤ ነበር፡፡ ከተለያዩ የሬዲዮ ጣቢያዎችም ስለዚሁ መስማቴን አስታውሳለሁ፡፡

ሕጉ ሳይፀድቅ ግን ከእሱ በኋላ የመጡ ሌሎች ሕጎች እየፀደቁ ይታያል፡፡ ሕጉ የማይፀድቅበትንና የዘገየበትን ምክንያት አጣርታችሁ በዜና አምዳችሁ እንድታቀርቡ ስል እጠይቃለሁ፡፡ ለአንድ ክፍል የጭቃ ቤት 1500 እስከ 2000 እየከፈልን ነው፡፡ እባካችሁ አስታውሱልን በፈጣሪ፡፡

(ሰለሞን አበበ፣ ከአዲስ አበባ)

**********

የተሰጠው መግለጫ ከእውነት የራቀ ነው

ሰኔ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. በሪፖርተር ጋዜጣ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኤርፖርቱን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ‹‹ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባልተወጡ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ላይ ዕርምጃ መወሰዱንና ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ኃላፊዎችና ሠራተኞች አሉ፤›› በማለት ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠታቸውን ተመልክተናል፡፡

እውነታው ግን ይህ ሳይሆን፣ ዕርምጃ ተወሰደባቸው የተባሉት የድርጅቱ ኃላፊዎች የአሠራር ግድፈቶችን፣ ብልሹና ፈር የለቀቁ አሠራሮችን፣ ሠራተኞችን ከመመርያና ደንብ ውጭ መቅጣት እንዲሁም ቅጥር ከመመርያ ውጭ የመፈጸሙ ተግባራትን በሚቃወሙ ሠራተኞች ላይ የተወሰደ የማን አለብኝነት ዕርምጃ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በአጠቃላይ በጋዜጣው ላይ ከዋና ሥራ አስፈጻሚው የተሰጠው መግለጫ ከእውነት የራቀ ነው፡፡ ይልቁንም ከማኔጅመንት ውስጥ ተጠያቂ መሆን የሚገባቸው ነገር ግን ከዋና ሥራ አስፈጻሚው ጋር ቀረቤታና ትስስር ያላቸው ኃላፊዎች ታቅፈው ሌሎች ላይ ዕርምጃ መውሰድ የሚያሳፍር እንደሆነ ታዝበናል፡፡

(ታዛቢ እውነቱ ይውጣ፣ ከአዲስ አበባ)

*************

ክፉ ክፉውን ለማረም እንተባበር

ቦሌ ድልድዩ ሥር ትክክለኛ መንገዴን ይዤ ከባለቤቴ ጋር ስንጓዝ አንድ ከባድ መኪና ከኋላችን ድንገት በመምጣት የመኪናዬን ግራ ፈረፋንጎ በመግጨት ወደ ምሥራቅ ታመራ የነበረችውን መኪና መቶ በመቶ ወደ ደቡብ ካዞራት በኋላ በግምት ከሁለት እስከ ሦስት ሜትር ገፈተረን፡፡ በመንገደኛው ጩኸት ብዛት፣ በእግዚአብሔር ኃይል መኪናው በመቆሙ ሕይወታችን ተርፏል፡፡ ሾፌሩ በብዙ ምስክሮች ፊት እንደተናገረው አንድ ጥቁር መኪና ከኋላው በግራና በቀኝ ሲያዋክበው ስለነበር የእኔን መኪና እንዳላየና ከገጨኝ በኋላ ድምፅ በመስማት ብቻ ፍሬን መያዙን፣ በሁኔታውም እንደተደናገጠ ከማስረዳቱም በላይ ፕላን ላነሳውም ፖሊስ ጥፋተኛ መሆኑን ራሱ አረጋጋጦና ከምሽቱ 2፡15 ሰዓት ላይ ለደረሰው አደጋ ጥፋቱ የእርሱ መሆኑ ጥርጥር ሳይኖረው ተረጋገጠ፡፡

መንጃ ፈቃዴ ተመልሶልኝ መኪናዋንም መውሰድ ትችላለህ ተብዬ ከሄድኩና ሰዓታት ካለፉ በኋላ በግምት ከምሽቱ አራት ሰዓት ከሩብ ገማ ፕላን አንስቶ ጥፋተኛ እንዳልሆንኩ አረጋግጦ ያሰናበተኝ ፖሊስ፣ በምን ምክንያት እንደሆነ ሳላውቀው፣ እኔ በተጎዳሁ ጥፋተኛ ነህ ተብዬ መኪናዬ እንድትቆም፣ የመንጃ ፈቃዴንም ለመርማሪው ፖሊስ እንዳስረክብ ታዘዝኩ፡፡ የትናንቱን ውሳኔህን በምን ምክንያት ለወጥክ ብዬ ብጠይቀው፣ በበላይ ትዕዛዝ ነው አለኝ፡፡ አዛዧ አጠገቡ ነበረችና ጥፋቱ የእርስዎ ነው፣ መኪናው የተገጨው ከፊት ፍሬቻው ላይ ነው ብላ ተከራከረችኝ፡፡ ይህ ግን ፈጽሞ ትክክል አልነበረም፡፡ ካስፈለገ አብረን ሄደን እንድታይ ብጠይቃትም ፈቃደኛ አልሆነችም፡፡ ከብዙ ልመናና ጉትጎታ በኋላ ሄዳ የተከሰተውን ብታይም አሁንም ግጭቱ ከፊት ነው ብላ ተከራከረችኝ፡፡ እኔም እንዳልሆነ ስሟገታት እንዲያውም በወንጀል እከስዎታለሁ ብላ ያላልኩትን አፍ እላፊ ራሷ ፈጥራ ልትከሰኝ አዛዥ ወደ ሆኑት ሻምበል ዘንድ አቀረበችኝ፡፡ ምስክር ያደረገቻቸውም ሁለት የሥራ ባልደረቦቿንና የገጨኝን ሾፌር ነበር፡፡ ሻምበሉ ጉዳዩን በጥሞና ከተመለከቱና ካጣሩ በኋላ በሰላም አሰናብተውኛል፡፡

ለመሆኑ ግን አንድ የሕግ ምስክር በአለቃ ትዕዛዝ የምስክርነት ቃሉን የሚለውጥበት አገር ይኖር ይሆን? ሳጅኑም ትናንት ያነሳሁትን ፕላን በአለቃዬ ትዕዛዝ ለወጥኩ ማለቱስ ላለበት ቦታ የሚመጥን ሰው ስለመሆኑ ያሳይ ይሆን? በዚህ ዓይነት ሁኔታ በየአደጋው ሕይወታቸው ያለፈ ወገኖች ስንት ይሆኑ? ትክክለኛ ፍትሕ ያላገኙትን ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ ይህንን ካየሁ በኋላ ሽንጤን ገትሬ ጥፋተኛ ያለመሆኔን ካስረዳሁና ለሻምበል አዛዡ ባመለከትኩት መሠረትም በዕለቱ የተነሳው ፕላን ታይቶ ቃላችንም ተመሳክሮ እኔ ያላጠፋሁ መሆኔ፣ የገጨኝ ሰው ጥፋተኛነቱ ተረጋግጦና ያለምንም ቅሬታ ጥፋቱን አምኖ ተለያይተናል፡፡ በዚህ ዓይነት መከራከር አቤት ማለት ያልቻለ ስንቱ ኢትዮጵያዊ ይሆን የሚበደለው?

ይህ ሁኔታ እንዲያውም ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮ ነበር፡፡ ፖሊስ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ስንት ዓመት ነድተህ ነው የመንጃ ፈቃድ ያወጣኸው? ለመንጃ ፈቃድ የወሰድከውስ ሥልጠና አለ ወይ? ብሎ በመጠየቅ ሌላ ጉዳት በንብረትም ሆነ በሰው ሕይወት ላይ ከማድረሱ በፊት ማስቆም ሲቻል፣ እንደ ሳጅኑና አለቃው ያሉ ኃላፊዎች ነገሩን በዋዛ ፈዛዛ እያለፉት በሰውና ንብረት ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ እንደዋዛ እየታየ ነው፡፡ የገጨኝም ሾፌር በ400 ብር ቅጣት በነፃ ተሰናብቷል፡፡

ይህ የኅብረተሰባችን የፍትሕ ችግር መሆኑ ታውቆ፣ ጥንቃቄ እንዲደረግበት በማሰብ ጉዳዩን ለአዲስ አበባ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ዘንድ ሰኔ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ቢሯቸው ባቀናም ስላልነበሩ ለቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ የጻፍኩትን የደብዳቤ ግልባጭ ለሌላ ለሚመለከታቸው ኮማንደር አስረክቤ፣ እርሳቸውም ለመዝገብ ቤት መርተውልኛል፡፡ ሌላ ጊዜ ብሔድ ምክትል ኮሚሽነሩን እንደማገኛቸው ገልጸውልኝ ተለያየን፡፡ በተነገረኝ መሠረት ምክትል ኮማንደሩ በነበሩበት ዕለት ጊዜ ሳላጠፋ ቢሯቸው ጠዋት አራት ሰዓት ገደማ ሰኔ 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ብደርስም፣ አንድ ሰዓት ያህል ከጠበቅሁ በኋላ ስብሰባ ላይ ናቸው በመባሌ ተስፋ ቆርጬ ተመለስኩ፡፡

ምክትል ኮሚሽነሩ ለማንም ሕጋዊ ሰው ቢሮዬ ክፍት ነው ብለው በሬዲዮ ቃለ ምልልስ ሲሰጡ በሰማሁት መሠረት ነበር የሄድኩት፡፡ እውነትም ቢሯቸው ክፍት ነው፡፡ እርሳቸውን በአካል ማግኘቱ ግን እጅግ ከባድ ነበር፡፡

ዓይቼ ማለፍ ስችል ላይ ታች ያልኩበት ምክንያት ሁላችንም ከተባበርንና አገራችንን ለሚጠቅም ነገር ዘብ ከቆምን ሁሉ ነገር ይስተካከላል በማለት እንጂ እነኚህን የዋህ ሰዎች ለማጥቃት ብዬ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፡፡

የሕግ አስከባሪ፣ የዳኝነታችን ጠባቂ የተሰጣትን አደራ መልሳ እኛኑ ለማጥቃት መነሳቷ ተገቢ ስላልሆነ፣ እንደኔ ይህንን ጉዳይ ሊከታተልና መብቱን ለማስከበር የማይችል ግለሰብ በዚህች ወጣት ሳጅን እንዳይጠቃ እጅግ አድርጌ እፈራለሁና የሚመለከተው አካል አስፈላጊውን ዕርምጃ ቢወስድ መልካም ነው እላለሁ፡፡ ሁሉንም በአሉባልታ ብቻ ከሚሉ፣ ያየነውን ክፉ፣ ክፉ ነገር ለማረም እንተባበር እላለሁ፡፡

(አሰፋ አደፍርስ፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...