Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅየአዲስ አበባው ድባብ

የአዲስ አበባው ድባብ

ቀን:

የዘንድሮውን የልደት በዓል ለማክበር በአዲስ አበባ ከዋዜማ ቀናት ጀምሮ ከነበሩት ሽርጉዶች መካከል በቦሌ አካባቢ የሚገኙ መደብሮች የበዓሉን ገጽታ በልዩ ልዩ መገለጫዎች ሲያስተዋውቁ ቆይተዋል፡፡ ከነዚህም ሁለቱ የገና ዛፍና ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁለት ሺሕ ዐሥር ዓመታት በፊት በቤተልሔም በበረት ውስጥ መወለዱን የሚያሳይ ተምሳሌታዊ በረት ከመንገድ ዳር የተተክሉት ይጠቀሳሉ፡፡ በሌላ በኩል ከታች የሚታየው ፎቶ  ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ (1884-1967) በጃንሜዳ የገና ጨዋታን ሲያስጀምሩ የተነሡት ነው፡፡

ዘላለምሽ፤ ዘላለሜ፤ ዘላለምነቱ

ትንሽ፤ አራት መስመር ግጥም

የእጥረትሽ ቃጠሎ ሲጥም

ንዑስ የበረሃ አበባ

ልስልስ የጉንትቶ ቆዳ

ነፋሻ የገብስ ገለባ

ፈንጂ የወረቀት ኰዳ

ይህ ነው፤ የፍቅር እውነቱ

ዘለዓለምሽ ዘለዓለሜ ዘላለምነቱ፤

ኃላፊ እንደ ጉንፋን

በጥባጭ፤ የነፋስ እባጭ

ታራቂ፤ ለጋ ደጋን፡፡

ጉንትቶ የፈረጠመ የቆንጆ ጡት

  • ሰሎሞን ዴሬሣ (መነን መጽሔት)

*****

የልደት በዓል ከ59 ዓመት በፊት

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አከባበር ምንም እንኳን በተለያዩ ቀኖች አከባበሩ ቢውልና ቢነገርም ዞሮ ዞሮ የምዕራባውያንም ሆነ የምሥራቃውያን ወይም የአፍሪካውያን ፍላጎት የክርስቶስን መወለድ በማይናወጥ እምነት ላይ ማሳረፍ ነው፡፡ ዘንድሮም በአሥራ ዘጠኝ አምሳ አንድ ዓመተ ምሕረት እንደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ደንብና ሕግ ልማድ ታኅሣሥ 29 ቀን ረቡዕ በመላ ኢትዮጵያ በዓሉ ተከብሮ ውሏል፡፡

በዋዜማው ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ የሐረር ጳጳስ ቃለ ቡራኬ አሰምተዋል፡፡ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ግርማዊት እቴጌ ከሌሊቱ 8 ሰዓት ሲሆን በመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው አስቀድሰዋል፡፡ ከንጋቱ 12 ሰዓት ሲሆን መድፍ ተተኩስዋል፡፡

ከጠዋቱ በ3 ሰዓት ላይ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥትና ግርማዊ እቴጌ እንኳን አደረሳችሁ ለማለት ወደ ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት የመጡትን ልዑላን መሳፍንትን ብጼዓን ጳጳሳትን ክቡራን ሚኒስትሮችንና መኳንቶችን ከፍተኛ የጦር አለቆችን፣ ወይዛዝሮችንና በከተማዋ የሚኖሩ ታላላቅ ሰዎችን ተቀብለው እጅ አስነስተዋል፡፡

በአዲስ አበባ የሚገኙት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ በየተመደበላቸው በር ገብተው ስጦታቸውን ተቀብለው በየትምህርት ቤቱ ስም በተመደበላቸው ሥፍራ ተሠልፈው በልደት መስክ የግርማዊንና የግርማዊትን መምጣት ይጠባበቁ ነበር፡፡ ልክ 4 ሰዓት ተኩል ሲሆን ግርማዊ ንጉሠ ነገሥትና ግርማዊ እቴጌ እዚያው ደርሰው ተማሪዎቹን በመካከል ገብተው እየተዘዋወሩ ጎበኙ፡፡ ጉብኝቱም እንደ ተፈጸመ ቲያትርና ጨዋታ ለመመልከት በተሰናዳው ሉአላዊ ሥፍራ እንደተቀመጡ የአምኃ ደስታ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እሰይ ተወለደ የተባለውን መዝሙር አሰሙ፡፡ ከመዝሙሩም በኋላ የትምህርትና የሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ልጅ እንዳልካቸው መኰንን እንኳን አደረሳችሁ በማለት በግርማዊና በግርማዊት ፊት ንግግር አደረጉ፡፡

ከንግግሩም በኋላ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ተማሪዎች መዝሙርና ቅኔ አበረከቱ፡፡ ቀጥሎም የአምኃ ደስታ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በበገና ድምፅ እየተመሩ በዓሉን የሚመለከት መዝሙር አሰምተዋል፡፡ ከእነሱም ቀጥሎ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስኮላርሺፕ ከልዩ ልዩ የአፍሪካ አገሮች የመጡት የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪዎች አፍሪካ የተባለውን መዝሙር አሰሙ፡፡

እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሚማሩ የህንድ ተማሪዎች የአገራቸውን ውዝዋዜ አሳይተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ የዳግማዊ ምኒልክና የሽመልስ ሀብቴ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በአንድነት ተቀላቅለው በሀገር ልማድ ሽለላና ፉከራ አሳዩ፡፡

ቀጥሎም በደጃዝማች ወንድ ይራድ ትምህርት ቤት የሚማሩ ሱማሌዎች ደስ የሚያሰኝ የሱማሊኛ ዘፈን አሰምተዋል፡፡

የልደት በዓል ከ59 ዓመት በፊት

 

ታላቅ ግብዣ በልደት አዳራሽ

በዚህ ቀን ስለልደት በዓል ክብር ግርማዊ ንጉሠ ነገሥትና ግርማዊት እቴጌ ለልዑላን መሳፍንት ለሚኒስትሮችና መኳንንቶች ለወይዛዝር ለመምህራን ለሹማምንት ታላቅ የምሣ ግብዣ አድርገዋል፡፡ ከእኩለ ቀን በላይ ወደ ኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት ሄደው በተለይ ጥሪ ለተደረገላቸው ተማሪዎች የገና ስጦታ አድለዋል፡፡

ወደዚያው ልክ 9 ሰዓት ሲሆን ጨዋታና ልዩ ልዩ ትርዕይት መታየት ጀመረ፡፡ 11 ሰዓት ሲሆን ጥሪ ለተደረገላቸው ሕፃናት በሙሉ የገና ስጦታ ተደረገና የበዓሉ ፍጻሜ ሆነ፡፡ የተማሪዎቹም ብዛት 42 ሺሕ ነበር፡፡

በዚሁም ጊዜ ከተማሪዎቹ በስተቀር የቀረው ሕዝብ ሁሉም የለበሰው ፀዓዳ የአገር ልብስ ስለነበር ያ የልደት አዳራሽ በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ በብዙ ዓይነት የሚቆጠሩ አበባዎች የፈነደቁበትን ተራራ መስሎና ተንቆጥቁጦ ሲታይ የቱን ያህል የዓይን ደስታ አበርክቶ ነበር ተብሎ ለመወሰን አይቻልም፡፡

  • መነን መጽሔት ታኅሣሥ – ጥር 1951

*******

የአውሮፓውያን ገና

ታኅሣሥ 15 ቀን 1951 ዓ.ም. ከእኩለ ቀን በላይ በ12 ሰዓት የጌታን ልደት በዓል ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ የሚኖሩ አሜሪካውያን በክቡር የአሜሪካን አምባሳደር አማካይነት ቀርበው ግርማዊ ንጉሠ ነገሥትንና ግርማዊ እቴጌን እጅ ነስተዋል፡፡ የሻምፓኝም ግብዣ ተደርጎላቸዋል፡፡ አሜሪካውያኖቹ በኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት ቅጥር ግቢ ውስጥ ገብተው እንደቆሙ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥትና ግርማዊ እቴጌ ልዑል አልጋ ወራሽን፣  ልዑል ሳህለ ሥላሴን፣ ልዕልት ተናኘ ወርቅን፣ ልዕልት መድፈሪያሽ ወርቅን፣ ልዕልት ሳራ ግዛውን፣ ክቡራን ሚኒስትሮችን አስከትለው በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ብቅ ብለው በታዩ ጊዜ አሜሪካውያኖቹ ደስታቸውን በጭብጨባ ገልጠው እጅ ነሱ፡፡ ከዚህም አያይዘው ደስ የሚያሰኝ መዝሙር አሰሙ፡፡

ግርማዊ ንጉሠ ነገሥትም ለአሜሪካውያኖቹ መልካም ልደት ሜሪ ክሪስማስ ይሁንላችሁ ብለው ደስታቸውን በበኩላቸው ከገለጡላቸው በኋላ ወደ ቤተ መንግሥቱ ገብተው የሻምፓኝ ግብዣ ተደረገላቸው፡፡ የሻምፓኙም ግብዣ እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት ድረስ ቆይቶ አሜሪካውያኖቹ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥትንና ግርማዊ እቴጌን እጅ እየነሱ ተመልሰዋል፡፡

******

ሐሙስ የገባው በጋ

ሐሙስ፥ በፀሐይ ታኅሣሥ 26 ቀን 7510 ዓመተ ዓለም፣ 2010 ..፤ በፀሐይና ጨረቃ ጥምር አቆጣጠር ጥር 16 ቀን 2018 ዓ.ም. (በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አቆጣጠር) ረቢ ሰኒ (በግእዝ ረቢ ዳግማይ) 16 ቀን 1439 ዓመተ ሒጅራ (በኢትዮጵያ እስልምና አቆጣጠር) ተቬት 17 ቀን 5778 ዓመተ ፍጥረት (በቤተ እስራኤል አቆጣጠር) የበጋ ወቅትን (ሐጋይ) ተቀብለናል። ሐሙስ ታኅሣሥ 25 ቀን የአበባና የነፋስ ወቅት የሆነው መፀውን ሸኝተናል።

ሐጋይበጋ የፀሐይ፣ የድርቅ (ደረቅ) ወቅት ነው፡፡ ፀሐይ የምትበረታበት ወቅቱ እስከ መጋቢት 25 ይዘልቃል። በጋ በመፀው ያሸተውና ያፈራው መከሩ የሚታጨድበት የሚሰበሰብበት ወዘተ. ነው።አንተ የምድርን ዳርቻ ሁሉ ሠራህ። በጋንም ክረምትንም አንተ አደረግህእንዲል መዝሙረኛው። እንኳን አሸጋገራችሁ፣ ሠናይ በጋ ይሁንልን። መጋቢት 26 ለሚብተው የፀደይ ወቅት ኤሎሂም ያድርሰን።

  • ሔኖክ መደብር

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...