Wednesday, July 17, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የ‹‹እናውቅልሃለን›› ፖለቲካዊ ፍልስፍና ከያ ትውልድ እስከ እኛ ትውልድ

በዮሴፍ ሙሉጌታ ባባ (ዶ/ር) 
‹‹የሕዝባችን ብሶትና የድሆች አሰቃቂ ሁኔታ እስከ አጥንታችን ድረስ ዘልቆ ተሰምቶናል›› ያሉን ‹‹ምርጥ የኢትዮጵያ ልጆች››፣ የ‹‹እናውቅልሃለን›› ፖለቲካዊ ፍልስፍና ማራመድ ከጀመሩ እነሆ 44 ዓመት አስቆጠሩ። ከዚያ ጊዜ ወዲህ የ‹‹እናውቅልሃለን›› ፖለቲካዊ ፍልስፍና በአገራችን ባህል ሆኖ ቆይቷል። (1) ያ ትውልድ በአንድ በኩል፣ አብዮታዊ መንግሥትን የመሠረቱ ‹‹ቡዳዎች›› ተነስተው ለሰፊው ሕዝብ መቆማቸውን አበሰሩን። የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ አብዮታዊው መንግሥት ከፊውዳሉ መንግሥት ፈጽሞ የተለየ መሆኑን ሲሰማ፣ ጮቤ መርገጥ ጀመረ። እነኝህ ግለሰቦች፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንደሚኖር ለሰፊው ሕዝብ ቃል የገቡት፣ በሥላሴ ስም ምሎ ሳይሆን፣ ‹‹የአብዮቱ ሰይፍ አንገታችንን ይቀንጥስ›› በማለት ነበር። የአብዮቱ ሰይፍ ወድያውኑ መቀንጠስ የጀመረው ግን፣ የሕዝቡን አንገት እንጂ የ‹‹ቡዳዎቹ››ን አልነበረም፡፡ የ‹‹እናውቅልሃለን›› የፖለቲካ ፍልስፍና ከቀመሩ ‹‹ቡዳዎች›› መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ጅቦች ነበሩ። አብዮቱ በጅቦች እንደ ተጠለፈ የገባት ሄለን መሐመድ፣ ትዝብቷን እንዲህ ስትል አስፍራ ነበር፡፡ አብዮት አብቦ ጎምርቶ አሽቶ የሚዘነጥፈው የሚቆርጠው ጠፍቶ ጅቡ በላው አሉ፤ ሌት ከማሳው ገብቶ አብዮቱን ከጅቦች ማጥራት አልተቻለም ነበር። ሆድና ጅብ የአንድ ስሙኒ ሁለት ገጽታ በመሆናቸው፣ ለድሆች አሰቃቂ ሁኔታ ቁብ የሰጠ አልነበረም። የ‹‹እናውቅልሃለን›› የፖለቲካዊ ፍልስፍና ‹‹የግል ጥቅምን ብቻ ማሳደድ›› በሚል የጅቦች አስተሳሰብ ተተካ። ‹‹የሕዝብን ገንዘብ ለግል ጥቅም ማዋል ወንጀል ነው›› የሚሉትን ሰዎች በጥይት እንደ ንፍሮ ቀቀሏቸው። እንደ ንፍሮ ከተቀቀሉት አንዱ በዓሉ ግርማ ነበር። ወንጀል ስለሠራ ሳይሆን፣ ‹‹በሕዝብ ስም ከሚነግዱ ነጋዴዎች አብዮቱን ማጥራት ያስፈልጋል፤›› ብሎ ስለጻፈ ብቻ ነበር። ከበዓሉ ‹‹አንደበት›› እንስማ፡- ‹‹ . . .ለግል ጥቅማቸውና ፍላጎታቸው ሥልጣን የሚያሳድዱ ሰዎች በዝተዋል። አደገኛ አዝማሚያ ነው፤ የተንኮል ገበያ ደርቷል። ከዚያ እንግዲህ ምናለ? መኪናና ቪላ ማማረጥ፣ ጥሩ መብላት፣ መጠጣት፣ መልበስ፣ መሽቀርቀር፣ በየዕለቱ የበሰለ ብርቱካን እየመሰሉ መሔድ፣ እንዲያም ሲል ቆንጆ ቆንጆዎችን እያማረጡ ሕይወትን መቅጨት። በስልክ ሀሎ! እያሉ ቤት ለምትፈልገው ቤት፣ ሥራ ለምትፈልገው ማለፊያ ሥራ፣ የደመወዝ ጭማሪ ለምትፈልገው ማለፊያ ጭማሪ፣ ተጠቅሞ መጥቀም፣ በልቶ ማብላት፣ ማብላትና መብላት። በሥልጣን እየተጠቀሙ ጥቅሞችን ለወደዱትና ለፈለጉት እንደ ጠበል ማርከፍከፍ። ይህ ሁሉ እየታየ ነው። እኔ የምሠጋው በሕዝብ ስም ተነስተን ከሕዝብ እየራቅን፣ ለሕዝብ ባዳ እየሆን እንዳንሄድ ነው። ጥራት! ጥራት! በሕዝብ ስም ከሚነግዱ ነጋዴዎች አብዮቱን ማጥራት ያስፈልጋል። ለግል ታሪክ፣ ለግል ዝና ይበልጥ ስለምንጨነቅ ኅብረት ጠፍቶ ግላዊ ሩጫና ጀብደኝነት ይነግሣል። እኔ ከጠላት ይልቅ በጣም የሚያሠጋኝ ይህ ነው።›› (ኦሮማይ፣ ገጽ 298-299) መቼም ሆዳም ሰው እምብርት የለውም፣ ጅብ ነዋ! ሰውየው ‹‹ድንቁርናና ሥልጣን ሲጋቡ ውጤቱ አደገኛ ነው›› ብሎ የተነበየው ነገር ለካስ ትክክል ነበር! አብዮታዊው መንግሥት ለዘለዓለሙ ላይመለስ ተሰናብቶን የሄደው ከ27 ዓመት በፊት ነበር! ነፍሱን ይማር! (2) የእኛ ትውልድ በሌላ በኩል፣ ከ17 ዓመት የትጥቅ ትግል በኋላ የ‹‹እናውቅልሃለን›› ፖለቲካዊ ፍልስፍና ከአብዮታዊው መንግሥት ‹‹የተረከበው›› ልማታዊ መንግሥት፣ ‹‹በሕዝብ ስም ከሚነግዱ ኪራይ ሰብሳቢዎች ልማቱን ማጥራት ያስፈልጋል፤›› ብሎ ከተነሳ 25 ዓመታትን አስቀጥሯል። ከኢሕአዴግ ‹‹አንደበት›› እንስማ፡- ‹‹የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ የበላይነት ባገኘበት አገር የመንግሥትን ሥልጣን መቆጣጠር ከሞላ ጐደል ብቸኛው የመበልጸግያ መሣሪያ ይሆናል። ሥልጣኑን የያዘና ሥልጣኑን ከያዘው ጋር በቅርብ የተሳሰረው ሁሉ ኪራይ መሰብሰቡን በሰፊው በማስኬድ እንደሚከብርና መንግሥት ሁሉንም እንደ ልማት አስተዋጾኦ እኩል ማስተናገድ ሳይሆን እንደ ቅርበቱ የኪራይ መሰብሰብ ዕድል እንደሚከፍትለት ስለሚታወቅ ሥልጣን መቆጣጠር የሞትና የሽረት ጉዳይ ይሆናል። ኪራይ ሰብሳቢነት የፖለቲካ ትግሉ የአመለካከት ሳይሆን በዋናነት የኪራይ መሰብሰብ ዕድሎችን በሞኖፖል በመያዝ ወይም በመጋራት ጥያቄዎች ዙሪያ የሚከናወን ነው። የሠለጠነና የተረጋጋ ትግልና የሥልጣን ሽግግር ሳይሆን የኑሮ መሠረትን በመገንባትና በመከላከል ዙሪያ የሚከናወን ፍልሚያ የሚካሄድበት ዴሞክራሲ ይሆናል።›› (ኢሕአዴግ፣ ልማት፣ ዴሞክራሲና አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ አዲስ አበባ፣ 1999፣ ገጽ 83…) ይሁን እንጂ፣ ኢሕአዴግ በሕዝብ ስም ከሚነግዱ ነጋዴዎች ልማቱን ማጽዳት አልቻለም። ያላግባብ መበልጽግ (ሙስና) ባህል ሆኗል፣ የመልካም አስተዳደር እጦት ሰፍኗል፣ የውሸት ባህል ነግሧል፣ ለሆዱና ለፍትወት ብቻ ያደረ ትውልድ ተፈጥሯል፣ አድሏዊነት፣ ጥላቻ፣ ዘረኝነት፣ ጨቋኝነት ተንሰራፍቷል፣ ብሔርተኝነት ከመጠን በላይ ተለጥጧል፣ በሰላምና በፍቅር አንድ ላይ መኖር አልተቻለም፣ ሕዝብና መንግሥት የጥይት ጨዋታ ውስጥ ገብቷል፣ ወጣቱ ተስፋ ቆርጧል፣ መግባባት፣ መደማመጥና መነጋገር ጠፍቶ መናናቅ ብቻ ሆኗል፡፡ የአብሮነት መንፈስ የሚባል ነገር ጠፍቷል፣ ለምዕራቡ ዓለም የአጎብዳጅነት መንፈስ ሰፍኖ ሕዝቡ ስሜቱ ተሰለቧል፣ ደሃው በኃይልና በጉልበት ከተወለደበት ቀዬ ተፈናቅሏል . . .ወዘተ። በአጠቃላይ፣ እንደገና ተመልሰን የቆንጨራ ጨዋታ ውስጥ ገብተናል፣ ይህ የማይካድ ሐቅ ነው። ዞረም ቀረ፣ መንግሥት በሕዝብ ብሶትና ዕንባ ማትረፍ የሚሹትን ሰዎች አያውቅም ማለት አይቻልም። ስለዚህ፣ በሕዝብ ስም የራሳቸውን ኑሮ ያመቻቹና የሕዝብን ገንዘብ በጆንያ የሚዘርፉት ግለሰቦችን ወደ ፍርድ ለምን እንደማያመጣቸው ፈጽሞ ግልጽ አይደለም። በአሁኑ ጊዜ በሥርዓቱ ውስጥ ተሰግስገው ያሉ አብዛኞቹ ግለሰቦች (ሁሉም አይደሉም) ስለሆዳቸው እንጂ ስለሕዝቡ አሰቃቂ ሁኔታ የሚያስቡበት ሰዓትም የላቸውም። የሚከተለው የሞገስ ሀብቱ ግጥም የእነኝህን አድርባይ ግለሰቦችን የ‹‹እናውቅልሃለን›› ፖለቲካዊ ፍልስፍና ውጤት በትክክል ይገልጻል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ 
‹‹መቶ ሺህ ብር ይውጣ 
ሰው ጠግቦ እንዲወጣ 
ውስኪም ብዙ ብዙ 
ቢራም ብዙ ብዙ 
ምግብም ብዙ ብዙ 
ሁሉም በገፍ ይምጣ 
ሰው ጠግቦ እንዲወጣ
እየበላህ ብላ፣ እየጠጣህ ጠጣ 
ከሕዝብ ነው እንጂ ካንተ ኪስ አይወጣ፤››
ይህ ነው እንግዲህ ሰውየው ‹‹በሕዝብ ስም ተነስተን ከሕዝብ እየራቅን ለሕዝብ ባዳ እየሆን እንዳንሄድ›› ያለው!
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ‹‹የመንግሥት ሌቦች እጅና እግራችንን አሰሩ›› ሲል፣ ‹‹መንግሥት ሌባ እየሆነ መጥቷል›› ማለቱ ነበር እንጂ ሌላ ሚስጥር የሌውም። መንግሥት ሙስና የሚሉት ካንሰር አገሪቷን ከመግደሉ በፊት አስቀድሞ መድኃኒቱን ካላፈላለገለት መዘዙ አደገኛ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም። በሕዝብ ስም እየነገዱ ከፍተኛ ሀብት ያካበቱትን ግለሰቦች እያጣራ ፍርድ ፍትሕ የማቅረብ ሞራላዊ ግዴታ አለበት። በሙስና ምክንያት 20 ሚሊዮን የናጠጠ ሀብታምና 80 ሚሊዮን መናጢ ድሃ ይዘን የምንቀጥልበት ምንም ዓይነት መለኮታዊም ሆነ ምድራዊ ምክንያት ሊኖር አይገባም። ‹‹በቅርብ ጊዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ እንሠለፋለን›› የሚል ትንቢት ግቡን እንዲመታ ከተፈለገ፣ መንግሥት የሙሰኞች እጅ እንዴት መቀንጠስ እንዳለበት ከአሁኑ በደንብ ልያስብበት ይገባል! ይህ እስካልተደረገ ድረስ፣ ‹‹መጀመሪያ ሙስና ነበረ፣ ሙስናም በሥልጣን ዘንድ ነበረ፣ ሙስናም ሥልጣን ነበር፤›› የሚል ‹‹የሙስና ወንጌል›› በኢትዮጵያ ምድር እየተሰበከና እየተተገበረ ይቀጥላል! ለነገሩ ሙስና በሃይማኖት ተቋማት ውስጥም እጅጉን አድማሱን እያሰፋ መጥቷል። ያም ሆነ ይህ ለገንዘብ ብሎ እግዚአብሔርን የሚያገለግል ቄስ፣ ካህን፣ ፓስተር፣ ሼክ፣ ብዙ ቢከፈለው ሰይጣንንም ያገለግላል! ባለፉት 44 ዓመታት፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ችግሮቻችንን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት አልተቻለም። የ‹‹እናውቅልሃለን›› የፖለቲካዊ ፍልስፍና ከጥይት ጨዋታ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ማምጣት አልተቻለም። ችግሮች ሲፈጠሩ ሰላም እንዲወለድ የሚያስችል ባህል የለንም። አሁን በተጨባጭ እየሆነ ያለውን ነገር ስመለከት፣ ‹‹ኦሮማይ›› እንድል አስገድዶኛል። ዳግም ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንዳንገባ ትልቅ ሥጋት አለኝ። እንደ አንድ ወጣት ዜጋ ግራ ገብቶኛል! ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ከባድ የቤት ሥራ ይጠብቃቹሃል። በተለይ፣ የሃይማኖት አባቶች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው! ሕዝቡ በቆንጨራ እየተጨራረሰ ዝም የሚሉ ከሆነ፣ በፈጣሪና በሕግ ፊት ተጠያቂዎች ናቸው። እምነትና ጸሎት ብቻ በቂ አይደለም። ሰይጣንም እኮ እግዚአብሔር የዘለዓለም ኗሪ መሆኑንና ታላቅ አምላክ መሆኑን ያምናል። ግን መልካም ሥራ የለውም፡፡ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው! የሃይማኖት አባቶች ሆይ! ‹‹አዲስ አማኝ ከጳጳሱ በላይ ለቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ ነው›› እንደማትሉኝ ተስፋ አለኝ። ምንም ዓይነት መልካም ሥራ ሳይኖረው ያንን ለማለት የሚደፍር የእግዚአብሔር አገልጋይ ካለ ግን፣ ‹‹ፂም በማሳደግ ቢሆን ፍየል ትሰብክ ነበር›› የሚል ተመጣጣኝ ምላሽ ስለሚሰነዝር ላንደማመጥ እንችላለን! ይልቅ፣ በልጅነት መንፈስ እናንተን ማሳሰብ የፈለግኩት ነገር ቢኖር፣ ፍትሕ ሲጓደል አይታችሁ ዝም አትበሉ ነው። የእግዚአብሔር ቃልም የሚላችሁ ይህንኑ ነውና፣ ‹‹ዓመት በዓላችሁን ጠልቼዋለሁ፣ ተጸይፌውማለሁ፡፡ የተቀደሰውም ጉባዓያችሁ ደስ አያሰኘኝም። የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁና የእህሉን ቁርባናችሁን ብታቀርቡልኝም እንኳ አልቀበለውም፡፡ ለምስጋና መሥዋዕት የምታቀርቡልኝን የሰቡትን እንስሶች አልመለከትም። የዝማሬህንም ጩኸት ከእኔ ዘንድ አርቅ፣ የመሰንቆህንም ዜማ አላደምጥም። ነገር ግን ፍርድ እንደ ውኃ፣ ጽድቅም እንደማይደርቅ ፍሳሽ ይፍሰስ፡፡›› (አሞጽ 5፡ 22-24) ይህ ማለት አንድም፣ የምትሰብከውን ኑር እንጂ ፈሪሳዊ አትሁን፣ ሁለቱም፣ ‹‹ከመጠምጠም መልካም ሥራ ይቅደም›› ማለት ነው። ከምሁራንና ከአገር ሽማግሌዎችም ተመሳሳይ ተልዕኮ እንጠብቃለን፣ ተማርኩ ብሎ ጥሩንባ መንፋት በቂ አይደለም፡፡ ትልቁ ነገር ዕውቀትን ወደ ተግባር መቀየሩ ነው! የአስተሳሰብ ለውጥ ሳይኖር ተማርኩ ብሎ መንጠራራት፣ በፍልስፍናው ዓለም ምሁራዊ ውስልትና ወይም የአስተሳሰብ ሽርሙጥና ይባላል! የአንድ ግለሰብ ዕውቀት (ሥልጠና) ብዙኃኑን ካለጠቀመ፣ የፕሮፌሰርነት ማዕረጉ ለሕዝቡ አንድ ኪሎ ሽንኩርት ወይም ድንች ሊሆን አይችልም። በተግባር ያልተገለጠ ዕውቀትና ከመልካም ሥራ የተለየ እምነት አንድ ነው። ሰው መከበር ያለበት በተግባሩና በአስተሳሰቡ እንጅ በማዕረጉ አይደለም፣ ከባለጌ ክቡር የድሃ ሥልጡን ይሻላልና! ጥሩንባ የሚነፉ ሰዎች አላጣንም! ጋንዲ ‹‹ከአንድ ኩንታል ወሬ አንድ ኪሎ ተግባር›› ብሎ የለ! መንግሥትና ሕዝብ ከታረቁ ብሔራዊ እርቅ ላይ እንደርስ ይሆናል፡፡ ካልሆነ መበታተናችን ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ከማንኛውም እልቂት ፈጣሪ እንዲጠብቀን ግን አጥብቀን መሥራት አለብን። ከሁሉም በላይ፣ ለዚች አገር የሚያስፈልጋት ሰላም ነው፡፡ ሰላም! ሰላም! ሰላም! ዘላቂ ሰላም! ሮናልድ ሬገን ያለውን ግን እንዳንረሳ ‹‹ሰላም የግጭት አለመኖር አይደለም፡፡ ግጭትን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት አቅም ነው፡፡›› 
ስለዚህ፣ ከራሷ ጋራ ሰላም የፈጠረች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በአንድነት እንሥራ። ማርቲን ሉተር ኪንግ እንደሚለን፣ ‹‹ጦርነትን ማወጅ የለብንም ማለት ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ሰላምን መውደድና መስዋዕትነት መክፈልም ይኖርብናል፡፡›› ስስታምነት ይብቃን፣ የንጹሐን ደም መፍሰስ የለበትም፣ አድሏዊነትን አጥብቀን እንዋጋ፣ ሰውን በሰውነቱ ብቻ እናከብር፣ የመጠላለፍ ፖለቲካ ይብቃን፣ በአጠቃላይ በባህልና በታሪክ በተሳሰሩ ሕዝቦች መካከል የቆንጨራ ፍልስፍናን ማቀንቀን፣ ለዚች አገር የሚበጅ አይመስለኝም። በኃይለመለኮት መዋዕል ግጥም ልሰናበታችሁ፡፡ 
     ‹‹ምን ጠቀመው ቃየል የመሣሪያ ቋንቋ 
ሰጠመ ጠፋ እንጂ በአቤል ደም አረንቋ
መኢኑም አባተ ሰመረ መረሳ 
ኦቦንግ አብዱል ከሪም ጋቸኖ ቶሎሳ 
አብረኸት ምንትዋብ ኛዳክም ጋዲሴ 
በላህ በነቢዩ በሦስቱ ሥላሴ 
ሰይፉም ዶማ ይሁን ሞርታሩም አንካሴ፡፡››
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በፍልስፍና የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸውና በካፑቺን ፍራንቸስካና የፍልስፍናና የነገረ መለኮት ተቋም (CFIPT) የአፍሪካ ፍልስፍና መምህር ሲሆኑ፣ በአገራዊና በአፍሪካ ፍልስፍና ዙርያ በእንግሊዝኛና በአማርኛ መጻሕፍትን አሳትመዋል፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡
 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles