Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበልጆች ተፅዕኖ ሥር የወደቀ የበዓል ሸመታ

በልጆች ተፅዕኖ ሥር የወደቀ የበዓል ሸመታ

ቀን:

የሚተዳደሩት በላዳ ታክሲያቸው መንገደኞችን አመላልሰው በሚያገኙት ገቢ ነው፡፡ ለዚህም እየሰለቻቸውም ቢሆን በ1980ዎቹ መጀመሪያ የገዙትን ላዳ ታክሲ ይዘው አምባሳደር አካባቢ ደንበኛ መጠባበቅ ይዘዋል፡፡

በሩን ገርበብ አድርገው ከነላስቲኩ ፊታቸው ያስቀመጡትን ጫት ይቅማሉ፡፡ ‹‹ይሄ ባይኖር ቁጭ ብሎ ሰው መጠበቅ በጣም ያሰለቻል›› አሉ ተሳፋሪ አግኝተው ሞተሩን ሲያስነሱ፡፡

ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት የሆኑት የ45 ዓመቱ አቶ አዲስ አሰፋ የሸራተንን ዳገት ጨርሰው፣ ወደ ካዛንቺስ የሚወደስደውን መንገድ ሲይዙ እንደነገሩ ሆኖ ከፈታቻው የተቀመጠውን ጫት ከነፌስታሉ አንስተው ወደ ኋላ ደበቅ አደረጉት፡፡

- Advertisement -

በየ ሱቆቹና የገበያ ማዕከላቱ ደጃፍ ላይ ያሉትን የፕላስትክ የገና ዛፎች፣ ማስዋቢያዎች፣ በመልክ በመልኩ የተሰቀሉትን ፊኛዎች ሲያዩ ‹‹ካለ ሁሌም በዓል ነው›› አሉ በዓል በመጣ ቁጥር በየመንገዱና በየቤቱ የሚኖረውን ግርግር በመተቸት ዓይነት፡፡

ለበዓል ብዙም ግድ የሌላቸው የሚናገሩት አቶ አዲስ፣ ዓውደ ዓመት ሲመጣ እንኳን አደረሰን ብሎ ቡና አፍልቶ፣ ቄጠማ ጎዝጉዞና ተሰባስቦ አብሮ መብላቱ ግን ብዙም እንደማይከፋቸው ይናገራሉ፡፡ የገና በዓል በመጣ ቁጥር ግን የገና ዛፍ ማዘጋጀት ማስጌጥና የመሳሰሉት ለሳቸው ትርጉም የለውም፡፡ እንዲያውም ቢቀር ደስታቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ለ14 ዓመት ሴት ልጃቸው ግን ይኼ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው፡፡ እንዲያውም የገና በዓል በመጣ ቁጥር ቤት የማጽዳት፣ የገና ዛፍ የማዘጋጀት ኃላፊነቱን ወስዳ ወደ ሥራ የምትገባው በዓሉ ቀናት ሲቀሩት ነው፡፡ ከተገዛ ዓመታት ያስቆጠረው ፕላስቲክ የገና ዛፍ ከተወሸቀበት ይወጣል፡፡ ዛፉ ላይ የሚሰቀሉ ብልጭልጭ ኳሶች፣ ደወሎችና ሌሎችም ጌጣጌጦች ካሉበት ይወጣሉ፡፡ በቆይታ ብዛት የተበላሹ ካሉ አለምንም ቅድመ ሁኔታ በሌላ ይቀየራሉ፡፡ ‹‹ገንዘቡን ራሱ ከየት እንደሚያመጡ አላውቅም፡፡ ከውጪ ስገባ ቤቱ ተንቆጥቁጦ ነው የሚጠብቀኝ፤›› የሚሉት አቶ አዲስ ናቸው፡፡ የገና ድባብ የሚያስደስታት ሴት ልጃቸውን ማስከፋት አይፈልጉምና ከመከልከል ዝምታን መርጠዋል፡፡ ዕድሜዋ ከፍ ሲል እንደምትተወውም ይገምታሉ፡፡

ሰዎች በአንድነት የሚደሰቱበት፣ ለጋስ የሚሆኑበት፣ አምረውና ደምቀው የሚታዩበት አጋጣሚ ቢኖር ዓውደ ዓመት ነው፡፡ በየሃይማኖቱ ያሉ በዓላት እንደየሃይማኖቱ ሥርዓት እንደየ አገሩ ባህል በተለያየ ሁኔታ በድምቀት ይከበራሉ፡፡ ከእነዚህ በዓላት መካከልም ገና በአከባበሩና ባለው የተለየ የድምቀት ድባብ ይታወቃል፡፡ ገና ሲነሳ በብዙዎች ዓይነ ህሊና የገና ዛፍ ይመጣል፡፡

የገና በዓል ሌላኛው ገጽታ የሆነው የገና ዛፍ ከምዕራባውያን የተቀዳ እንደሆነ ተደርጎ ይነገራል፡፡ በግሪክ የተሰሎንቄ አርስቶትል ዩኒቨርሲቲ የቤዛንታይን አርኪዬሎጂ ፕሮፌሰር የነበሩት ኮንስታንቲን ኪሎኪርስ በአንድ ጥናታቸው በክርስቲያን ቲኦሎጊያና አምልኮ ውስጥ ዛፍ ዕውቀትን፣ እንደሚያመለክትና በሃይማኖቱ ውስጥ ልዩ ትርጉም ያለው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

የገና ዛፍ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ ሩብ ውስጥ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቤተ መንግሥት እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በተጨማሪም የገና ዛፍ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ውስጥ ካሉ ትውፊቶች ጋር የሚዛመድበት ሁኔታ መኖሩንም ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡ እነዚህና መሰል መረጃዎች የገና ዛፍ ከምዕራባውያን የተቀዳ ሳይሆን በክርስትና እምነት ውስጥ ቦታ ያለው መሆኑን ያሳያሉ፡፡

ከምዕራባውያን የተቀዳ ባህል ነው አይደለም የሚለው ክርክር እንዳለ ቢሆንም ገና እና የገና ዛፍ ግን ተነጣጥለው አያውቁም፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያም ከቤት አልፈው ወደ አደባባይ ወጥቷል፡፡ በዓሉ ሊገባ ቀናት ሲቀሩት ጀምሮ በከተማው የሚገኙ የገበያ ማዕከላትና ሆቴሎች በረንዳና እንግዳ መቀበያዎች በገና ዛፍ ያሸበርቃሉ፡፡ ከዚህ ሲያልፍም በየሕንፃዎቹ መግቢያ ላይ የገና አባቶች ቆመው ለልጆች ከረሜላ ይሰጣሉ፣ አቅፈዋቸው ፎቶ ይነሳሉ፡፡ በየቤቱም በድምቀት ይከበራል፡፡ እንደ አቶ አዲስ ያሉ የልጆቻቸውን ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ ሳይወዱ በግዳቸው የማይፈልጉትን የአከባበር ሥርዓት የሚከተሉና ላልተፈለገ ወጪ የሚዳረጉም አሉ፡፡

በዓላት በልጆችና በወላጆች ላይ የሚፈጥረው ስሜት የተለያየ ነው፣ ልጆች ደስታውን ፈንጠዝያውን እንጂ ከበስተኋላ ያለውን ወጪ አያውቁም የሚሉት በሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ መምህሩ አቶ አስጢፋኖስ አበራ ናቸው፡፡

ብዙውን ጊዜም የወላጆች የመሸመትና የመግዛት ውሳኔም በልጆች ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ እያደጉ ሲሄዱ ነገሮችን የማገናዘብ አቅማቸው ስለሚጨምር ይህ ሊቀንስ ቢችልም፣ በተለይ ከ5 እስከ 12 ዕድሜ ክልል ያሉ ታዳጊዎች ገንዘብ ምን እንደሆነና እንዴት እንደሚገኝ አይረዱም፡፡ የሚጠብቁት በአካባቢያቸውና በጓደኞቻቸው ቤት የሚያዩትን ነገር በእነሱም ቤት መደረጉን ብቻ ነው፡፡

በአገራችን የበዓል አከባበር በአብዛኛው ከመብላትና ከመጠጣት ጋር የተያያዘና እስካሁንም ለውጥ ያላመጣ ነው የሚሉት አቶ እስጢፋኖስ፣ በውጭ አገር ከአካባቢያቸው ርቀው በመውጣት፣ በጎ ሥራ በመሥራት የሚያከብሩበት ሁኔታ እዚህም ቢለመድ ይመክራሉ፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ የተለመደ ባለመሆኑ አከባበሩ ከዓመት ዓመት የተለየ ነገር አይታይበትም፡፡ አንዳንዶች ግን ወደ መረዳጃ ተቋማት በመሄድ በዓላትን ትኩረት ከሚሹ ወገኖቻቸው ጋር የማሳለፍ ባህል እያዳበሩ ይገኛሉ፡፡

ለመብላትና ለመጠጣት የሚያስፈልጉ ነገሮች በአብዛኛው በዋጋ ደረጃ ከፍተኛ ይሆናሉ፡፡ ከዚህ ባሻገርም በጎረቤቶችና በዘመዳሞች መካከል የፉክክር ስሜት ይታይበታልም፡፡ ይኼ የፉክክር ስሜት የሚመነጨው ደግሞ በአብዛኛው ከልጆች ፍላጎት በመነሳት ነው፡፡ በተለይ ለእርድ የሚቀርበው በግ ከሆነ የመጓጓትን ስሜት በልጆች ላይ ይፈጥራል፡፡ ስለሆነም ወላጆች ያልሆነ ሸመታ ውስጥ ይገባሉ፡፡

በአገራችን በተለይ በከተማ አካባቢ በልጆች ተፅዕኖ ሥር የወደቀ ሸመታ ይበዛል፡፡ በዚህም ብዙ ወላጆች እጅግ ያልተፈለገ ጫና ውስጥ ይገባሉ፡፡ ወላጆች ልጆቻቸው የሰው ቤት እንዳያዩ ከአቅማቸው በላይ ወጪ በማውጣትም የልጆችን ያህል ይደሰታሉ ለማለትም ይከብዳል፡፡ በተለይ እንደ አቶ አዲስ ያሉ ሰዎች በዓልን እንዲጠሉ የሚያደርጋቸውን ወጪ ለማውጣት ይገደዳሉ፡፡

የገንዘብ አያያዝ እውቀት አለመኖር ወላጆች ላይ ለሚፈጠረው ጫና ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ ወላጆች ለልጆች ስለገንዘብ እያወቁ እንዲሄዱ አያደርጉም፡፡ ሳይኖራቸው ለልጆች ከአቅማቸው በላይ የሆኑ ነገሮችን ያደርጋሉ፡፡ ይኼ ለበዓል ብቻ ሳይሆን በሌላ ጊዜም የተለመደ ነው፡፡ የልጆችን ፍላጎት በቀላሉ የሚወጡት አይሆንም፡፡ ገደብ የሌለው የልጆች ፍላጎት የወላጆችን አቅም ካለማወቅ የሚመጣም ሊሆን ይችላል፡፡

እንደ አቶ እስጢፋኖስ፣ ገንዘብ እንዴት ይገኛል፣ ይያዛል፣ ይጠፋል የሚለው በአብዛኛው በአገራችን አይታወቅም፡፡ ልጆች ስለገንዘብ እንዲያውቁ አይደረግም፡፡ ይኼንን ስለማያውቁ ሁሉ ነገር በገንዘብ እንደሚገዛ፣ ወላጆች ደግሞ ሁሉን የመግዛት አቅም እንዳላቸው ያምናሉ፡፡

ወላጆች ልጆቻቸውን ማስጨነቅ ስለማይፈልጉም ምን ያህል እንደሚያገኙ፣ ለምን እንደሚያውሉት ምስጢር ያደርጉታል፡፡ ልጆች ግን ይኼንን በግልጽ እየተረዱ ቢያድጉ በእቅድ የሚመሩና የሚያስቡ ይሆናሉ፡፡ ይኼ አብሯቸው ቢያድግ መልካም ሰብእና ይኖራቸዋል፡፡

ለምሳሌ የገና ዛፍ ከነማስጌጫው ለመግዛት ከሺሕ ብር የበለጠ ዋጋ ይጠይቃሉ፡፡ ምግቡ ተጨምሮ ወጪው በሺዎች ይደርሳል፡፡ ይኼንን ደግሞ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አይችለውም፡፡ በመሆኑም አላስፈላጊ ወጪ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ይህም ወላጆችን ከደስታ ይልቅ ለጭንቅ ይዳርጋቸዋል፡፡ 

ሆኖም ልጆች ለገንዘብ ሊኖራቸው ስለሚገባው ግንዛቤ በቤት ውስጥ በወላጆች፣ ከቤት ውጪ ደግሞ በትምህርት ቤት ከሥር ጀምሮ ቢማሩ፣ ያዩትን ነገር ሁሉ የመሰብሰብ፣ የመጠየቅና የአልጠግብ ባይነት ባህሪያቸውን ይተውታል፡፡ የገንዘብ እውቀታቸው ከዳበረ በወደፊት ሕይወታቸው ሌሎች እንደ ሙስና ያሉ ችግሮችንም መፍታት ይችላሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...