Tuesday, July 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊትኩረት የሚሹ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች

ትኩረት የሚሹ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች

ቀን:

በዓለም በአሁኑ ጊዜ ከሚከሰቱት ሞቶች መካከል ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች 70 ከመቶ ድርሻ ሲኖራቸው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ 44 ከመቶ ድርሻ እንዳላቸው ይገመታል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚከሰቱ ሞቶች ግማሽ ያህሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መሆናቸውንም ያስቀምጣል፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ቡድን መሪ ዶ/ር ብስራት ደሳለኝ እንደገለጹት፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በዓለም ላይ በአራት፣ በአገራችን ደግሞ በሰባት ይከፈላሉ፡፡ አራቶቹም ልብና ከልብ ሥር ጋር የተያያዘ ተላላፊ ያልሆነ በሽታ፣ ካንሰር፣ ሥር የሰደዱ የመተንፈሻ አካል ሕመሞች ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ደግሞ አራቱን በሽታዎች ጨምሮ የሥነ አዕምሮ በሽታ፣ ትራኮማና የዓይን ሞራ ግርዶሽ እንዲሁም አደጋ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ውስጥ እንደተካተቱ አስረድተዋል፡፡

ሰባቶቹን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ያካተተ አንድ መሪ ዕቅድ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በዚህም ፕላን በአሁኑ ጊዜ ያለውን የ44 በመቶ የሞት ድርሻ በ2017 ዓ.ም. ወደ 25 በመቶ ዝቅ ለማድረግ ታቅዷል፡፡ ሥራውም በአራት ክፍሎች በመከፋፈል እየተከናወነ ሲሆን፣ ለዚህም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ማስተዳደር፣ መከላከያ መንገዶቹ ላይ ማተኮር፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግና ጤናማ አመጋገብ እንዲኖር መሥራት ትኩረት የተሰጣቸው ተግባራት ናቸው፡፡

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ ‹‹ትኩረት የተሰጠበት የተቀናጀ የሕክምና አገልግሎት›› ለመስጠትም ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ካለው በጀት ውስጥ 15 ሚሊዮን ብር መድቧል፡፡ በጀቱን የሚያንቀሳቅሰው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ቡድን እንደሆነ፣ ነገር ግን የተመደበው በጀት በቂ እንዳልሆነና በዚህም ሳቢያ ታካሚዎች የሚፈልጉትን ሕክምና በበቂ ሁኔታ እንደማያገኙ ተገልጿል፡፡ ክልሎች በዚህ በጀት እንደማይጠቀሙ በተረፈ ለዚህ ሕክምና ከራሳቸው በጀት እንዲመደቡ መደረጉንም ዶ/ር ብስራት አመልክተዋል፡፡

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በባህርያቸው ረጅም ጊዜ በሕክምና ላይ ሰዎች እንዲቆዩ የሚያደረጉ ናቸው፡፡ ለዚህም ሕክምና ታካሚዎች ከኪሳቸው አውጥተው የመሸፈን አቅም የላቸውም፡፡ መድኃኒቶቹ አብዛኞቹ ከውጭ የሚገቡ መሆናቸውና በአሁኑ ጊዜ ያለው የውጪ ምንዛሪ ከፍ ማለቱ የታካሚዎችን የመግዛት አቅም ፈትኗል፡፡

ይህንንም ችግር ለመቅረፍ የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ጨረታ አውጥቶ ከሚገዛው መድኃኒት ሌላ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ‹‹አስትራሊዘኒካን›› እና ‹‹ኖቫርቲስ›› የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ጋር የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል፡፡ በመግባቢያ ሰነዱ መሠረት ሁለቱ አምራች ኩባንያዎች ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ፈውስ የሚውሉና ጥራታቸው ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟሉ መደኃኒቶችን ያቀርባሉ፡፡

ይህም ማለት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታ ያለበት አንድ ታካሚ ለአንድ ወር የሚያገለግለውን መድኃኒት በአንድ ዶላር ሒሳብ እንዲገዛ የሚያደርግ ነው፡፡

ከዚህም ሌላ ስፔሻሊስት ሐኪሞች ከሚያከናውኗቸው ሙያዊ ሥራዎቸ መካከል ግማሽ ያህሉን በመካከለኛ ደረጃ ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎች በአቅም ግንባታ ሥልጠና አማካይነት ለማሸጋገር ለሚያስችለው የአቅም ግንባታ ሥልጠና የሚያስፈልገውን ወጪ  ሁለቱ መድኃኒት አምራች ኩባንያዎቹ ለመሸፈን ውል ገብተዋል፡፡

ከተጠቀሱት ኩባንያዎች መካከል አስትራዘኒካን የተባለው ኩባንያ 60 የጤና ድርጅቶች ላይ የሙከራ ሥራ በማካሄድ ላይ ሲሆን፣ እስካሁንም በተከናወነው የሙከራ ሥራ ከእያንዳንዱ ጤና ደርጅት ለተውጣጡ 60 የጤና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ሰጥቷል ተብሏል፡፡

አገልግሎቱ መስጠት ከተጀመረ አንድ ዓመት ገደማ ሲሆን፣ ውጤቱም እየታየና መረጃዎቹም እየተሰበሰቡ ነው፡፡ ውጤቱ ይበል የሚያሰኝ ከሆነ አገልግሎቱ በመላ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄድ ይሆናል፡፡

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በተለይ የስኳር ሕክም እስከ ጤና ጣቢያ ድረስ ባሉት የሕክምና ተቋማት እንደሚሰጥ፣ ሆኖም በሚገባ የተደራጀ እንዳልሆነ ዶ/ር ብስራት ጠቁመው፣ የማደራጀቱም ሥራ የሚከናወነው የአቅም ግንባታ ሥልጠና የወሰዱ የጤና ባለሙያዎችን በመመደብ፣ በቂ ግብዓቶችን በማቅረብ፣ ያለውንም ግብዓት አቀናጅቶ በትክክል በመጠቀም መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...