Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልበዓል እና ገፀ በረከት

በዓል እና ገፀ በረከት

ቀን:

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለች፣ ጓደኞቿ ለልደት በዓል ስጦታ መለዋወጥ እንደሚፈልጉ ነገሯት፡፡ የጓደኛሞቹ ስም በወረቀት ይጻፍና ተጠቅልሎ ዕጣ ይወጣል፡፡ ከመካከላቸው ማን የማን ስም የተጻፈበት ወረቅት እንደደረሰው ዕጣው በወጣበት ዕለት አይነጋገሩም፡፡ በሚስጥር ይያዛል፡፡ ወ/ሮ ቤተል ዓባይ እንደምትለው፣ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አንድ ወይም ሁለት ቀን ሲቀረው ስጦታ ይለዋወጣሉ፡፡ የትኛው ሰው ለማንኛቸው ስጦታ እንደሚሰጥ ከበዓሉ በፊት አለመታወቁ፣ ስጦታ የመለዋወጥ ሒደቱን አጓጊና አስደሳች ያደርገዋል ትላለች፡፡

ሐሳቡ ከምዕራባውያኑ ‹‹ሲክሬት ሳንታ›› (ምስጢራዊ ሳንታ እንደማለት) የስጦታ መለዋወጥ ባህል የተወረሰ ነው፡፡ ብዙ የሁለተኛ ደረጃና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በዚህ መንገድ ስጦታ ይለዋወጣሉ፡፡ ወ/ሮ ቤተል፣ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለች ፖስት ካርድ፣ ጌጣ ጌጥ፣ ሻማ፣ የእስኪርቢቶ ማስቀመጫና ሌላም የተማሪ አቅም የሚፈቅደውን ገዝታ ለጓደኞቿ ስጦታ ሰጥታለች፡፡ ዩኒቨርሲቲ ከገባች በኋላ ያፈራቻቸው ጓደኞቿም በ ‹‹ሲክሬት ሳንታ›› ቀጥለውበታል፡፡

ከዓመታት በፊት ከዩኒቨርሲቲ ተመርቃ ወደ ጎንደር ለሥራ አቀናች፣፡፡ የልደት በዓልም ተቃረበ፡፡ ጓደኞቿ እንደተለመደው ዕጣ ለማውጣት ተሰባሰቡ፡፡ በቦታው አለመኖሯ ልማዱን እንዳያስተጓጉል፣ የአንድ ካፌ አስተናጋጅ በሷ ስም ዕጣ እንድታወጣ ተስማሙ፡፡ በዕጣው መሠረት ስሙ ለደረሳት ጓደኛዋ የአፄ ቴዎድሮስ ምስል ያለበት ካናቴራ ገዝታ ለበዓሉ ላከችላት፡፡ ‹‹ስጦታ ለሰጪውም ለተቀባዩም ያስደስታል፡፡ ለአንድ ሰው ያለንን ዋጋ የምናሳይበት መንገድ ነው፤›› ትላለች፡፡

በሥራና በሌሎችም ኃላፊነቶች ምክንያት ከዩኒቨርሲቲ ጓደኞቿ ጋር በየዓመቱ ለልደት ስጦታ መለዋወጥን አልገፉበትም፡፡ ለበዓል፣ ለልደት፣ ልጀ ሲወለድ፣ ለሠርግ ወይም በሌላ ምክንያትም ስጦታ መስጠት በሰዎች መካከል ያለውን ትስስር እንደሚጠብቅ ታምናለች፡፡ መዋደድና መከባበርን ያሳያልም ብለ ታምናለች፡፡ ‹‹ሰው የሚፈልገውን ነገር አውቆና ገዝቶ መስጠት ጥሩ ስሜት ይፈጥራል፤ አሁን ካለው በበለጠ ለበዓል ስጦታ መለዋወጥ ቢዘወተር በዓልን ያጎላዋል፤›› ትላለች፡፡

ስጦታ የመለዋወጥ ሐሳብን ብትደግፍም፣ አሁን ላይ ሆና ወደ ኋላ ስትመለከት የምዕራባውያኑን ‹‹ሴክሬት ሳንታ›› መውረስ ላይ ጥያቄ አላት፡፡ በሉላዊነት ምክንያት ወደ አንድ መንደርነት እየተጠጋጋች በምትገኝ ዓለም፣ መልካም ሐሳብን ከሌሎች አገሮች በመውረስ ታምናለች፡፡ ሆኖም የልደት በዓል ሲከበር ‹‹ሳንታ ክላውስ ስጦታ ይሰጣል›› የሚለው የባህር ማዶ ሐሳብና ሌሎች ባህሎችም ቀስ በቀስ በኢትዮጵያ መለመዳቸውን አትቀበልም፡፡

አፀደ ሕፃናት የምትማር ልጇ፣ ትምህርት ቤት ልደትን ለማክበር ቀይ በቀይ ለብሰውና ኩኪስ ይዘው እንዲሄዱ መጠየቃቸውን ስትነግራት መገረሟን ትገልጻለች፡፡ ልጇ ጎድ ኢዝ ማይ ሴቭየር (God Is my Savior) የሚል እንግሊዝኛ መዝሙር እንድትለማመድም ተደርጓል፡፡ ‹‹በሁሉም አገር ስላለው የልደት አከባበር ተማሪዎችን ማስተማር ይቻላል፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ ስላለው የልደት አከባበር አንዳች መረጃ አንኳን አይሰጣቸውም፤›› ትላለች፡፡

ልጆች ከቤተሰባቸውና ከትምህርት ቤት ውሏቸው የሚማሩት ነገር በወደፊት ማንነታቸው አሉታዊ ወይም አወንታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀርም፡፡ ዛሬ ዛሬ የልደት በዓል በትምህርት ቤቶች የሚከበርበት መንገድ፣ ምን ዓይነት አመለካከት ያለው ትውልድ ለመቅረጽ እንዳለመ ግራ እንደምትጋባ እንግዳ ባይሆንም ትገልጻለች፡፡ ስጦታ መለዋወጥ ለኢትዮጵያውያን እንግዳ ባይሆንም የምዕራባውያኑ መንገድ መከተል የብዙዎች ምርጫ ሲሆን ይስተዋላል፡፡

‹‹ሌላ አገር የተደረገ ነገር በሙሉ እኛ አገርም መደረግ የለበትም፡፡ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፤›› ትላለች፡፡ ልደት፣ ሃይማኖታዊ በዓል መሆኑ እስኪዘነጋ ድረስ የተለያዩ አገሮች ልማዶች ወጣቱን እንደወረሱት ታምናለች፡፡ በቅርቡ ያነበበችውን ጥናት እንደ ማሳያም ትጠቅሳለች፡፡ ወደ 60 በመቶ ገደማ የሚሆኑ አሜሪካውያን ልደት የሚከበርበትን ትክከለኛ ምክንያት እንደማያውቁ ጥናቱ ያሳያል፡፡ ‹‹ልደት፣ አዲስ ዓመት አንድ ሳምንት ሲቀረው የሚከበር በዓል ነው፤›› ብለው ስለ በዓሉ የተናገሩ ነበሩ፡፡

ለልደት የሚለበሰው ልብስ፣ ስጦታ የመለዋወጫ መንገዱና ሌሎችም የበዓሉ መገለጫዎች አገርኛ መሆን እንዳለባቸው ትናገራለች፡፡ ችግር ያለባቸው የማይመስሉ እንደ ‹‹ሲክሬት ሳንታ›› ያሉ ልማዶችን ከመውረስ በፊት፣ አመጣጣቸውን ማስተዋል እንደሚገባም ታክላለች፡፡ ‹‹ተማሪዎች የአገር ባህል ልብስ እንዲለብሱ ቢደረግ፣ አገርኛ ዜማን ቢማሩ፣ የገና ጨዋታ ወይም ሌላ የበዓሉን መገለጫዎች ቢያውቁ መልካም ነው፤›› ስትልም አስተያየት ትሰነዝራለች፡፡

በዓልን ጨምሮ በተለያየ ምክንያት ስጦታ የመለዋወጥ ባህል ከሰው ልጆች ታሪክ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ በጥንታዊ ሥልጣኔ፣ የጎሳ መሪዎች ከሕዝቡ መካከል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ሰዎች ስጦታ ይሰጡ ነበር፡፡ መልካም ዕድል እንዲገጥም ለመመኘት፣ አክብሮት ለማሳየት፣ በጦርነት ወቅት በነገሥታት መካከል እርቅ ለማውረድና በሌሎችም መሰል ሁነቶች ስጦታ ይበረከታል፡፡

በዚህ ዘመንም በማኅበረሰብ መካከል የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማጠናከር ስጦታ ይሰጣል፡፡ ሠራተኞችን ማበረታቻ መንገድም ይሆናል፡፡ ብዙ መሥሪያ ቤቶች ለበዓል የደመወዝ ጭማሪ ወይም ጉርሻ ይሰጣሉ፡፡ በግ፣ ዶሮ አልያም ሌላ ስጦታ ለሠራተኞቻቸው የሚሰጡም አሉ፡፡ መሥሪያ ቤቶች ለደንኞቻቸው ውስኪና ሌላ ስጦታም ያበረክታሉ፡፡ ለልደት፣ ለሠርግ፣ ለምርቃትና በሌሎችም መሰናዶዎች ስጦታ ይዘወተራል፡፡ የእናቶች፣ የአባቶች፣ የፍቅረኞች ቀንም ስጦታ ለመለዋወጥ መልካም አጋጣሚ ናቸው፡፡

የሥነ ልቦና ተመራማሪዎች፣ ስጦታ መስጠት ሰዎችን ከሚያስደስቱ ተግባሮች አንዱ መሆኑን ደርሰውበታል፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ስጦታ መስጠት ከመቀበል በበለጠ ሐሴት ያጭራል፡፡ በአንድ ጥናት፣ ሰዎች ስጦታ እንዲሰጡና እንዲቀበሉ ተደርጎ፣ የሰጪዎቹ የደስታ መጠን ከተቀባዮቹ በልጦ ተገኝቷል፡፡ አንድ ሰው ስጦታ ሲያበረክት፣ ‹‹ኢንዶርፊንስ›› የተባለ ደስታ ሲሰማ የሚለቅ ኬሚካል በሰውነቱ እንደሚሰራጭም ተመልክቷል፡፡

ባለፉት ዓመታት በነገሥታት መካከል የተደረጉ ትልልቅ የስጦታ ልውውጦች መነጋገሪያ ሲሆኑ ታይቷል፡፡ የከበሩ ድንጋዮችን ስጦታ የሚለዋወጡ ፍቅረኛሞችም ከወጣው ገንዘብ አንፃር መወያያ ሆነዋል፡፡ በሌላ በኩል ‹‹የስጦታ ዋጋ አይጠይቅም›› ሲሉ ስጦታ የፈሰሰበት ገንዘብ መነጋገሪያ መሆኑን የሚቃወሙም አሉ፡፡

በኢትዮጵያም ይሁን በሌሎች አገሮች ያሉ የገፀ በረከት መደብሮች ገበያ ከሚደራበት ወቅት አንዱ የልደት በዓል ነው፡፡ በመላው ዓለም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የስጦታ ሸመታ የሚካሄድበት ወቅት እንደመሆኑ፣ ሁሉም እንደአቅሙ ለወዳጅ ዘመድ ስጦታ ይገዛል፡፡ አንዳንዶች ከልደት በዓል ውጪ ካለው ስጦታ የመለዋወጥ ባህል በተለየ በዓሉን አይመለከቱትም፡፡ በሌላ በኩል ልደት ሲባል ቀድመው ስጦታን የሚያስቡም አይታጡም፡፡

ሠራዊት ክንፈ ስጦታ መስጠትም መቀበልም ከማይወዱ መካከል ነው፡፡ ‹‹ስጦታ በመስጠት አላምንም፡፡ ዋነኛው ምክንያቴ ለአንድ ሰው ስጦታ ሲሰጥ፣ መልሶ እንዲሰጠኝ የማስገድደው ስለሚመስለኘ ነው፤›› ሲል ያስረዳል፡፡ ስጦታ ከመቀበል ጀርባ ‹‹ውለታ መመለስ›› እንዳለ ስለሚገምትም ስጦታ ከመስጠት ይቆጠባል፡፡ የልደት በዓል ስጦታ በብዛት የሚሰጥበት ቢሆንም፣ መልካም ምኞትን የሚገልጹ በጎ ነገሮች ማድረግን ይመርጣል፡፡

እንደ ምሳሌ የሚጠቅሰው በቅርቡ በኤግዚቢሽን ማዕከይመወክል ያየውን ነው፡፡ የኮካ ኮላ ድርጅት ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን የከብቶች በረት በሚመስል ድንኳን ውስጥ ሰዎች ፎቶ እንዲነሱ ይጋብዛል፡፡ ሰዎቹ በበረቱ ፎቶ ተነስተው ከመልካም ምኞት መግለጫ ጋር ይሰጣቸዋል፡፡ በዓል ነክ ጥያቄ ተጠይቀው ከመለሱም በግ ይሸለማሉ፡፡ ሠራዊት እንደሚለው፣ በሃይማኖታዊው መንገድ ሲታይ፣ የክርስቶስ መወለድ ከስጦታዎች የላቀ ስጦታ መሆኑን ምሳሌ በማድረግ ሰዎች ስጦታ ይለዋወጣሉ፡፡

የልደት በዓል ከሃይማኖታዊነቱ ጎን ለጎን የተለያዩ ባህላዊ ክንውኖች የሚካሄዱበት መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ የገና ጨዋታን እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል፡፡ በየዓመቱ ጃንሜዳ የሚካሄደው የፈረስ ጉግስ ጨዋታም ተያይዞ ይነሳል፡፡ ‹‹ልደት ከሌሎች በዓሎች በተለየ ስጦታ ለመለዋወጥ የተመቸ ነው፡፡ እኔ ባልሳተፍም ሃይማኖታዊ ዳራውን  አከብራለሁ፤›› ይላል ሠራዊት፡፡

‹‹ያለ ስጦታ የልደት በዓል ምሉዕ አይሆንም›› ያለን አንድ አስተያየት ሰጪ፣ የቅርብ ለሚላቸው ሰዎች ባጠቃላይ በየዓመቱ ስጦታ መስጠት ከጀመረ ወደ 20 ዓመት ገደማ አስቆጥሯል፡፡ ከቴሌቨዥን እስከ ብዕር ድረስ ስጦታ አበርክቷል፡፡ ለቤተሰቦቹ፣ ለጓደኞቹና ለሥራ ባልደረቦቹም እንደየአስፈላጊነቱ ስጦታ ይሰጣል፡፡

‹‹ልደት ሁለት ሳምንት ሲቀረው የገፀ በረከት መሸጫ መሄድ እጀምራለሁ፡፡ ስጦታ ልሰጠው ያሰብኩትን ሰው የሚያስደስተውን ነገር መርጬም እገዛለሁ፤›› ይላል፡፡ የልደት በዓል እስከሚደርስ ለወዳጅ ዘመዶቹ የሚሰጠውን ያሰላስላል፡፡ ‹‹ይሄ ነገር ቢኖረኝ›› ወይም ‹‹ይኼንን ነገር ወድጄዋለሁ›› ሲሉ ከሰማ በማስታወሻ ደብተሩ ይመዘግባል፡፡ በዓል ሲደርስም ይገዛላቸዋል፡፡

በዓሉ ሲቃረብ ለስጦታ የሚሆን ገንዘብ ይመድባል፡፡ የሚገዛው ነገር ውድ ቢሆን እንኳን ገንዘብ ይበደራል እንጂ ከመሸመት ወደ ኋላ አይልም፡፡ በእሱ እምነት፣ ስጦታ የሚሰጠው ሰው በሕይወቱ ለሚያበረክተው አስተዋፅኦ የሚያመሰግነው ለልደት በዓል ነው፡፡ ብዙ ጊዜ መገልገያ ቁሳቁሶችን በስጦታ ማበርከት ይመርጣል፡፡ ‹‹በዓሉን በማስታከክ የምወዳቸውን ሰዎች ማስደሰት እፈልጋለሁ፤›› ይላል፡፡

ስጦታ የመስጠት ልማዱን ያዳበረው ከቤተሰቦቹ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ልጅ ሳለ፣ ለልደት ገንዘብ አጠራቅሞ ለቤተሶቦቹ ስጦታ እንዲገዛ ይበረታታ ነበር፡፡ አድጎ ደመወዝተኛ ከሆነ በኋላም አላቋረጠም፡፡ ለ2010 ዓ.ም. የልደት በዓል ከገዛቸው ስጦታዎች መካከል ለእህቱ ስልክና ለጓደኛው ልጅ የእንግሊዝኛ አማርኛ መዝገበ ቃላት ይገኙበታል፡፡

ሌላዋ አስተያየት ሰጪ፣ ‹‹የምሰጠውን ስጦታ የማዘጋጀው ቤቴ ነው፤›› ትላለች፡፡ ስጦታ የመቀራረብ ስሜትን ይፈጥራል ብላ የምታምነው፣ ሰጪው ስጦታውን ለማዘጋጀት በሚያፈሰው ጊዜ ነው፡፡ ፖስት ካርድ፣ ጌጣ ጌጥ፣ የእጅ ቦርሳና ሌሎችም መገልገያዎች ቤቷ አዘጋጅታ ሰጥታለች፡፡ ከሁሉም ስጦታዎቿ የማትዘነጋው ለአምስት ዓመታት በተለያዩ አገሮች ስትዘዋወር የተለያዩ ጠጠሮችና ቅጠሎች ሰብሰባ ለዕጮኛዋ የሰጠችው ነው፡፡

ሰዎች እንደሷ ቤታቸው ስጦታ አዘጋጅተው ባይሆንም ገበያ ያፈራውን ገዝተው ያበረክቱላታል፡፡ ‹‹የስጦታ ትንሽ የለውም›› ብላ ስለምታምን ሁሉንም በደስታ ትቀበላለች፡፡ ከተሰጧት ስጣታዎች መካከል እጮኛዋ ያሠራላትን መጽሐፍ መደርደሪያ አትዘነጋውም፡፡

በየአገሩ ያለው የስጦታ ግንዛቤ የተለያየ እንደመሆኑ፣ የሚሰጠው ስጦታና የሚያበረክትበት ወቅትም ይለያያል፡፡ ጥንት ሮማውያን ስጦታ መስጠትን እንደ መልካም ምኞት መግለጫ ይወስዱ ነበር፡፡ ለግብፅ ፈርኦኖች የሚሰጡ ውድ ስጦታዎች በፒራሚዶቻቸው አብረዋቸው ከተቀበሩ ቁሳሶች መካከል ይገኙበታል፡፡

የኢትዮጵያ ስጦታ የመለዋወጥ ባህል ከአክሱም ዘመን አንስቶ ዘመናትን ያስቆጠረ ነው፡፡ በወርኃ መስከረም ‹‹ተቀፀል ጽጌ›› (የአበባ በዓል) መስከረም 25 ቀን (በኋላ መስከረም 10) ሲከበር አደይ ይበረከታል፡፡ ስጦታ የመስጠት ባህልን ከዚህ አንስቶ በተለያየ ገጽታ መመልከትም ይቻላል፡፡ እንደየአካባቢው ባህልና ሃይማኖት የተለያየ የስጦታ አሰጣጥ አለ፡፡ ለአዲስ ዓመት ልጆች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የያዘ ሥዕል ማደላቸው አንዱ ነው፡፡ ለልደት በዓል ልጆች ለቤተሰቦቻቸው ጠቦት ይሰጣሉ፡፡ በገጠርና በከተማም ስጦታ የመስጠት ልማድ ዘመናትን የተሻገረ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...