Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናዋና ኦዲተር ታክስና ግብር መርምሮ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን እንዳልተሰጠው ለፍርድ ቤት ተነገረ

ዋና ኦዲተር ታክስና ግብር መርምሮ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን እንዳልተሰጠው ለፍርድ ቤት ተነገረ

ቀን:

ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የኩባንያዎችን ሒሳብ መርምሮ የግብርና የታክስ ውሳኔዎችን ለመስጠት ሥልጣን እንደሌለውና ግብር ከፋዩ በግብር አዋጅ ላይ የተሰጡትን መብቶች እንዳይጠቀም የሚያግድ መሆኑን፣ አንድ የተፈቀደለት የሒሳብ አዋቂና የታክስ አማካሪ ኤክስፐርት ለፍርድ ቤት ተናገሩ፡፡

ኤክስፐርቱ አቶ አማረ ላቀው ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ግብርና ታክስን በሚመለከት መርምሮ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን እንደሌለው የገለጹት፣ በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የክስ መዝገብ ቁጥር 141352 ተካተው ክስ ለተመሠረተባቸው ኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና ለድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ከተማ ከበደ መከላከያ ምስክር ሆነው፣ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ታኅሳስ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀርበው ነው፡፡

የተከሳሾቹ ጠበቆች መከላከያ ምስክር ሆነው የቀረቡት አቶ አማረ፣ የተፈቀደለት የሒሳብ አዋቂና የታክስ አማካሪ በመከላከያነት የሚያስረዱት፣ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የግብርና የታክስ ከፋይ ኩባንያዎችን ሒሳብ መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት፣ በሕግ የተሰጠው ሥልጣን እንደሌለውና ዋና ኦዲተር ኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ላይ ያደረገውን የሒሳብና የታክስ ምርመራና ያስተላለፈውን ውሳኔ ከሕጉ ጋር እያነፃፀሩ ለፍርድ ቤቱ እንደሚያስረዱ በጭብጥነት አስይዘዋል፡፡

ዋናው ኦዲተር መሥሪያ ቤት የኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ላይ ባደረገው የግብርና የታክስ ምርመራ፣ ድርጅቱ ለመንግሥት ገቢ ማድረግ የነበረበትን 32,217,578 ብር ተጨማሪ እሴት ታክስ አለመክፈሉን፣ 17,869,941 ብር ግብር አለመክፈሉን፣ ወደ አገር ውስጥ ያስገባቸውን የተለያዩ ዕቃዎች በሕጉ በተቀመጠው ታሪፍ አመዳደብና ዋጋ ተመን መሠረት ከሕግና መመርያ ውጭ 9,543,391 ብር ያላግባብ ተጠቃሚ መሆኑን በምርመራው ማረጋገጡን ዓቃቤ ሕግ በድርጅቱ ላይ ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡ በመሆኑም ከላይ በተጠቀሱት የገንዘብ መጠኖች ለመንግሥት አለመክፈሉ ተገልጾ በፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ክስ ተመሥርቶበታል፡፡ የኬኬ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅና ከፍተኛ ባለድርሻ አቶ ከተማ ከበደ ደግሞ፣ ግብርና ታክስን አሳውቆ ባለመክፈልና አሳሳች መረጃ በማቅረብ ወንጀሎች መከሰሳቸው በክሱ ተብራርቷል፡፡

ምስክሩ እንዳብራሩት፣ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የተዘጋጀው የግብር አወሳሰንና ኦዲት ማንዋል አለ፡፡ በኦዲት ስታንዳርድ መሠረት አንዱ የኦዲት ሥርዓት የመግቢያና የመውጫ ኮንፈረንስ በሕግ ሥልጣን ከተሰጠው የግብርና የታክስ መርማሪ ጋር ይደረጋል፡፡ በመግቢያ ኮንፈረንስ ሲጀመር ድርጅቱ የሚከተለውን የሒሳብ አያያዘ ዘዴ፣ የሒሳብ መዝገቦችና ሰነዶች የሚገኙበት ሁኔታ በተመለከተ ተገቢውን ማብራርያ መስጠት የሚችለውን ኃላፊ ለማወቅ እንደሚረዳ አስረድተዋል፡፡ በመውጫ ኮንፈረንስ ደግሞ ኦዲተሮቹ ያገኙትን ግኝት ለተመርማሪ ድርጅት ለሒሳብ ባለሙያዎች በመግለጽ፣ የተሠራው የኦዲት ሥራ ትክክለኛነት እንዲረጋገጥላቸው፣ ሊታረሙ የሚገቡ ነጥቦች ላይ በመወያየትና ተገቢውን ማስረጃ በማቅረብ እርምት እንዲደረግ እንደሚደረግ ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡

ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ግን የኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርን የግብርና ታክስ ሒሳብ የመመርመርና ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን ባይኖረውም፣ ያዘጋጀው የግብርና ታክስ ሪፖርት የኦዲት ሥርዓትን ያልተከተለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የመግቢያና መውጫ ኮንፈረንስ አለማድረጉንም ጠቁመዋል፡፡ የኦዲት ሥራው ከመጠናቀቁ በፊት ውይይትና ማስረጃና ሰነድ ላይ ማብራርያ ቀርቦላቸው ሊታረሙና ሊስተካከሉ የሚችሉ የኦዲት ግኝቶች ሳይታረሙ መታለፋቸውንም አክለዋል፡፡ በገቢ ግብር አዋጅና በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ መሠረት በግብር ከፋይ ላይ የሚፈለግ ተጨማሪ ግብርና ታክስ ካለ በሕጉ መሠረት ሒሳቡ ተመርምሮ ከተወሰነ በኋላ፣ የግብርና የታክስ ውሳኔ ማስታወቂያው ለግብር ከፋዩ ኬኬ ድርጅት ሊሰጠው የሚገባ ቢሆንም፣ እንዳልተሰጠው መስክረዋል፡፡ ምስክሩ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ኦዲት ምርመራን በሚመለከት አጠቃላይ የኦዲት ግኝትን በሚመለከት፣ ተጨማሪ እሴት ታክስን በሚመለከት፣ የንግድ ትርፍን በሚመለከት ዝርዝር ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡ ድርጅቱ ሕጉንና አዋጁን በመከተል በአግባቡ የሠራ መሆኑንም በመግለጽ ምስክርነታቸውን አጠቃለዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በመስቀለኛ ጥያቄው ለመላከያ ምስክሩ ጥያቄዎችን አቅርቧል፡፡ መከላከያ ምስክሩ የጠቀሱትን መመርያ በሚመለከት ተፈጻሚነቱን ጠይቋቸው፣ ምስክሩ ግራ በመጋባት ለማነፃፀሪያ እንደተጠቀሙበት ገልጸዋል፡፡ የጠቀሱት መመርያ ስህተት መሆኑን ዓቃቤ ሕግ ጠቁሞ ‹‹ስህተት ሠርተዋል አልሠሩም?›› የሚል ጥያቄ በማንሳቱ ምስክሩ ሊመልሱ ባለመቻላቸው በጠበቆቻቸው በኩል ተቃውሞ በመቅረቡ፣ ፍርድ ቤቱ በምርመራ እንደሚመለከተው በመግለጽ ታልፏል፡፡ የዓቃቤ ሕግ መስቀለኛ ጥያቄ ባለመጠናቀቁም ለጥር 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

የአቶ ከተማና የኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አንደኛ መከላከያ ምስክር ሆነው የቀረቡት ደግሞ የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢና አባል ሆነው እንደሚሠሩ የተገለጸው አቶ ኃይለ ሥላሴ ሐጎስ ናቸው፡፡ ምስክሩ የሚያስረዱት የኬኬን ድርጅት አቋምና አደረጃጀት መሆኑን ጠበቆቹ ጭብጥ አስይዘው ምስክሩ መስክረዋል፡፡ ኬኬ በስድስት መምርያዎች የተዋቀረና በልዩ አደረጃጀቱ ከሌሎች ድርጅቶች የተሻለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የግል ድርጅቶች ቦርድ እንዲያቋቁሙ በሕግ የማይገደዱ ቢሆንም፣ አሠራሩን በአግባቡ ለመቆጣጠርና በጥንቃቄ ለመሥራት በማለት አቶ ከተማ ቦርድ እንዲቋቋም ማድረጋቸውንና በኢትዮጵያም የመጀመርያው ድርጅት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የንግድ፣ የፋብሪካ፣ የሒሳብ፣ የሰው ኃይልና የማሽነሪ መምርያዎች እንዳሉትም አስረድተዋል፡፡ ቦርዱ ከማኔጅመንቱ የሚደርሰውን ሪፖርት ተመልክቶ መስተካከል ያለበት እንዲስተካከል፣ የተስተካከለው ተሻሽሎ እንዲቀጥል እንደሚያደርግም አስረድተዋል፡፡

የውስጥ ኦዲተር የሒሳብ ክፍሉን ሌሎች ወጪና ገቢዎችን እየመረመረ እንደሚቆጣጠርና በየዓመቱ በውጭ ኦዲተር አጠቃላይ አሠራሩ እንደሚመረምር አስረድተዋል፡፡ ኬኬ ታክስም ሆነ ግብር ወቅቱን ጠብቆ የሚከፍልና ለሌሎች ድርጅቶች አርዓያ እንደሆነም አክለዋል፡፡ ከፍተኛ ባለድርሻው አቶ ከተማ ሲሆኑ ልጃቸው ትዕግሥት ከተማ ሌላዋ ባለድርሻ ናት ብለዋል፡፡ ቦርዱ ተጠሪነቱ ከፍተኛ ባለድርሻ ለሆኑት አቶ ከተማ ቢሆንም፣ ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት እንደሌለ ምስክሩ አስረድተዋል፡፡ የመከላከያ ምስክሩ ስለድርጅቱና አሠራሩ በዝርዝር አስረድተው ሲያጠናቅቁ፣ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበላቸው መስቀለኛ ጥያቄ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ በሕግ የተጣለበትን ኃላፊነት ስለማወቃቸው ተጠይቀው ‹‹አውቃለሁ›› ብለዋል፡፡ ድርጅቱ ግብርና ታክስ በወቅቱ ስለመክፈሉ ማወቃቸውን ተጠይቀውም እንደሚያውቁ ገልጸዋል፡፡ ቦርዱ መቼ መቼ እንደሚሰበሰብ ተጠይቀው በየሦስት ወሩ እንደሚሰበሰብ ተናግረዋል፡፡ ድርጅቱ በዋና ኦዲተር ተመርምሮ መክፈል የሚገባውን ሳይከፍል መቅረቱን እንደሚያውቁ ተጠይቀው፣ ‹‹አላውቅም›› ብለዋል፡፡ ኬኬ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ነው ያሉት ከእነማን ጋር ተወዳድሮ እንደሆነ በስም ጠቅሰው እንዲያስረዱ ሲጠየቁ፣ ‹‹እከሌ እከሌ ብዬ ድርጅቶቹን መጥቀስ አልችልም፡፡ ምክንያቱም የማማክራቸውን ድርጅቶች ሚስጥር ጠብቄ፣ የሚሻሻሉበትንና ተወዳዳሪ የሚሆኑበትን መንገድ ለማሳየት ቃል ገብቼ የተፈራረምኩ በመሆኑ የሥነ ምግባር ሕጉም አይፈቅድልኝም፤›› ብለዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ መጥቀስ እንዳለባቸው ለፍርድ ቤቱ ሲያመለክት ጠበቆች ተቃውመዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የሁለቱን ወገኖች ተቃውሞና ክርክር ከሰማ በኋላ፣ በአብላጫ ድምፅ ምስክሩ ያነፃፀሩባቸውን ድርጅቶች መጥቀስ እንዳለባቸው ብይን ሰጥቷል፡፡ ምስክሩ ግን የፍርድ ቤት ትዕዛዝን ለመጋፋት ሳይሆን የድርጅቶቹን ሚስጥር ከመጠበቅ አንፃር መግለጽ እንደማይችሉ ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡ ችሎቱ ለደቂቃዎች ዕረፍት ወስዶ ሲመለስ በአቋሙ ፀንቶ፣ ምስክሩ የማይጠቅሱ ከሆነ ኬኬ ከሌሎች ይሻላል ያሉት ምስክርነት ከጭብጥ እንዲወጣ እንዲወስኑ ለጠበቆቹ ዕድል ሰጥቷል፡፡ ጠበቆቹም ምስክሩ የደንበኞችን ሚስጥር መጠበቅ እንዳለባቸው ገልጸው፣ ምስክሩ የሰጡት ማነፃፀርያ ምስክርነት ከነጭብጡ እንዲሰረዝ ተስማምተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም እንዲሰረዝ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...