Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ተጨማሪ የአውሮፕላን ማቆሚያ ሊገነባ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የአዲሱ ኤርፖርት ግንባታ የመንግሥት ውሳኔ እየጠበቀ ነው

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የተፈጠረውን መጨናነቅ ለማስተንፈስ፣ ተጨማሪ የአውሮፕላን ማቆሚያ ሥፍራ ሊገነባ ነው፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ታኅሳስ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. እንደተናገሩት፣ የአዲስ አበባ ኤርፖርት በፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኘውን አየር መንገድ ፍላጎት ማሟላት ተስኖታል፡፡

በዓመት በአማካይ 20 በመቶ በማደግ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየወሩ ሁለት አዳዲስ አውሮፕላኖች በመረከብ ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ ተወልደ፣ በቂ የአውሮፕላን ማቆሚያ ቦታ ማግኘት ፈታኝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ኤርፖርቱ በከተማዋ በመከበቡ ለማስፋፊያ የሚሆን በቂ ቦታ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ ዳዊት የአዲስ አበባ ኤርፖርት 53 አውሮፕላኖች ማቆሚያ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ አየር መንገዱ ያሉት አውሮፕላኖች ብዛት ከ100 በማለፍ ላይ በመሆኑ፣ ተጨማሪ የአውሮፕላን ማቆሚያ ሥፍራ መገንባት እንዳስፈለገ አቶ ቴዎድሮስ አስረድተዋል፡፡

አቶ ቴዎድሮስ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች የአውሮፕላን ማቆሚያ ሥፍራ የሚገነቡ ኮንትራክተሮች ለመቅጠር ከሁለት ሳምንት በፊት ጨረታ አውጥቷል፡፡ ጨረታው የዲዛይንና የግንባታ ሥራ አካቶ የያዘ ሲሆን፣ ለ45 ቀናት ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች የአዲስ አበባ ኤርፖርት የመንገደኞች ማስተናገጃ ሕንፃ በ345 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማስፋፋት ላይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አቶ ተወልደ እንደተናገሩት የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ በተለያዩ ምክንያቶች ዘግይቶ የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ሥራው በመፋጠን ላይ ነው፡፡ ግንባታውን የሚያካሂደው ቻይና ኮሙዩኒኬሽን ኤንድ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ሥራውን በታኅሳስ 2008 ዓ.ም. መጀመሩ ይታወሳል፡፡ ፕሮጀክቱ በጥር 2010 ዓ.ም. እንደሚጠናቀቅ የታቀደ ቢሆንም፣ በፍላጎትና በዲዛይን ለውጥ ምክንያት በተፈጠረ መዘግየት የማጠናቀቂያ ጊዜው ለጥር 2011 ዓ.ም. መተላለፉን አቶ ቴዎድሮስ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹የመጀመርያውን ክፍል በመጪው ሰኔ እንዲያስረክበን ለኮንትራክተሩ ጥያቄ አቅርበናል፤›› ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ የሚጠናቀቀው በጥር 2011 ዓ.ም. እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ግዙፍ የሆነ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ከአዲስ አበባ ውጪ የሚገነባ በመሆኑ፣ በአዲስ አበባ ኤርፖርት የሚደረጉ ግንባታዎች አዲሱ ኤርፖርት እስከሚገነባ ያለውን የአየር መንገዱን ፈጣን ዕድገት መሸከም እንዲችል ታስቦ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ለመገንባት ያቀደው የኤርፖርት ከተማ የመንግሥት ውሳኔ እየጠበቀ እንደሆነ ታወቀ፡፡

በአማካሪነት የተቀጠረው ኤዲፒአይ የተሰኘው የፈረንሣይ ኩባንያ የቦታ መረጣ ጥናት ሲያካሂድ ቆይቶ፣ አሥር ቦታዎች ተመርጠው ለመጨረሻ ውሳኔ ለመንግሥት መቅረቡን የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፣ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ለመሸጋገር የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች