Sunday, April 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መሰቦ ሲሚንቶ የ70 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ስምምነት ተፈራረመ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የጂብሰምና ቀለም ፋብሪካዎች ለመገንባት አቅዷል

በኤፈርት ሥር ከሚተዳደሩት በርካታ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው መሰቦ ሲሚንቶ የግንባታ ዕቃዎች የሚያመርት ኩባንያ በ70 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ለማቋቋም፣ ኩስቶ ግሩፕ ከተሰኘ የሲንጋፖር ኩባንያና ፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ ከተባለ የአሜሪካ ኩባንያ ጋር ስምምነት ተፈራረመ፡፡

ስምምነቱን የኤፈርት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አዜብ መስፍን፣ የኩስቶ ግሩፕ የሕግ ክፍል ኃላፊ ሃይደር ጉላምና የፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ ሊቀመንበር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ታኅሳስ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ፈርመዋል፡፡

በስምምነቱ መሠረት መሰቦ ሲሚንቶ፣ ኩስቶና ፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ በጋራ ኤምኬኤፍ ቢዩልዲንግ ማቴሪያልስ ፕሮዳክሽን የተሰኘ ኩባንያ ያቋቁማሉ፡፡ በሽርክና የሚመሠረተው ኩባንያ በዋናነት የጣሪያ ክዳን ጡብ የሚያመርት ሲሆን፣ መሰቦ ሲሚንቶ 60 በመቶ፣ ኩስቶና ፌርፋክስ በጋራ 40 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡

ኤምኬኤፍ በመቐለ አቅራቢያ የጣሪያ ክዳን ጡብ ፋብሪካ እንደሚገነባና ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸው ምርቶች በማምረት ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብ ወ/ሮ አዜብ ተናግረዋል፡፡

‹‹መሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የግንባታ ዕቃዎች አምራች ኩባንያ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ወ/ሮ አዜብ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የጣሪያ ክዳን ፋብሪካ ግንባታ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል፡፡ ‹‹የአዋጭነት ጥናቱ ተሠርቷል፡፡ ሁሉም ነገር ዝግጁ ነው፡፡ ስንጠብቅ የነበረው የስምምነቱን መፈረም ነው፤›› ብለዋል፡፡

የመሰቦ ሲሚንቶ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ክብረአብ ተወልደ፣ የሚገነባው ፋብሪካ በዓመት 3.6 ሚሊዮን ካሬ ሜትር የጣሪያ ጡብ የማምረት አቅም እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ ‹‹በግንባታ ዕቃዎች ምርት የረዥም ጊዜ ልምድ ካለው ኩስቶና ሰፊ የኢንቨስትመንት ተሞክሮ ካለው ፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ ጋር አብረን በመሥራታችን ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል፤›› ብለዋል አቶ ክብረአብ፡፡ ኩስቶ በቬትናም፣ በካዛክስታንና በእስራኤል በግንባታ ዕቃዎች ምርት የተሰማራ ግዙፍ ኩባንያ ሲሆን፣ ዓመታዊ ገቢው ሦስት ቢሊዮን ዶላር ይገመታል፡፡ ኩባንያው 50,000 ሠራተኞች አሉት፡፡

ሚስተር ጉላም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፍጥነት በማደግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፣ በአዲስ አበባ ባዩዋቸው የግንባታ ፕሮጀክቶች ብዛት መደመማቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከመሰቦ ሲሚንቶና ከፌርፋክስ ጋር አብረን ሠርተን የኢንቨስትመንት ዕቅዳችንን እንደምናሳካ እርግጠኛ ነኝ፤›› ብለዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1997 በ240 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተመሠረተው መሰቦ ሲሚንቶ በዓመት ሁለት ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም አለው፡፡ ከፍተኛ ጥራት ያለው የሲሚንቶ ምርት በማምረት የሚታወቀው መሰቦ ለግልገል ጊቤ ሦስትና ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ለግድብ ግንባታ የሚሆን ልዩ ሲሚንቶ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ በቅርቡ 200 ጀርመን ሠራሽ ማን የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች በ700 ሚሊዮን ብር ወጪ ገዝቶ በመስፍን ኢንጂነሪንግ ተገጣጥመው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡፡

አቶ ዘመዴነህ ኩስቶና ፌርፋክስ በርካታ ኩባንያዎች ሲያጠኑ ከቆዩ በኋላ ቀዳሚ ከሆነው መሰቦ ሲሚንቶ ጋር ለመሥራት መወሰኑን ተናግረዋል፡፡ ኤፈርት በቀጣይ ሌሎች ኢንቨስትመንቶች በመመልከት ላይ እንደሆነ ታውቋል፡፡

እንደ አቶ ክብረአብ ገለጻ በቀጣይ መሰቦ ከኩስቶና ከፌርፋክስ ጋር በጋራ የጂፕሰም ፋብሪካ ለማቋቋም ድርድር ተጀምሯል፡፡ በመቐለ አቅራቢያ ከፍተኛ ጥራት ያለው የጂብሰም ማምረቻ ጥሬ ዕቃ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ክብረአብ፣ ክምችቱ ለመቶ ዓመት እንደሚበቃ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ናሙናዎችን ወደ ሲንጋፖር ልከን በላቦራቶሪ ተመርምረዋል፡፡ የኩስቶ ባለሙያዎች መጥተው የክምችቱን ጥራት እንዲያረጋግጡ እየጠበቅን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሚስተር ጉላም በበኩላቸው የጂፕሰም ኩባንያ መመሥረቻ ረቂቅ ስምምነት ዝግጁ መሆኑን ገልጸው፣ የቴክኒክ ሥራው እንደተጠናቀቀ ስምምነቱ እንደሚፈረም ተናግረዋል፡፡ የጂፕሰም ፋብሪካው በመሰቦ፣ በኩስቶና በፌርፋክስ ባለቤትነት የሚቋቋም ይሆናል፡፡

መሰቦ ሲሚንቶ የቀለም ፋብሪካ ለመገንባት ጥናት በማካሄድ ላይ እንደሆነ ታውቋል፡፡ በዓለም ታዋቂ  የቀለም አምራች ከሆነው ታምቡር ከተሰኘ ኩባንያ ጋር ንግግር መጀመሩን ወ/ሮ አዜብ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ታምቡር ተቀማጭነቱ በቴላቪቭ እስራኤል ሲሆን፣ የኩባንያው ባለቤት ኩስቶ ግሩፕ ነው፡፡

ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነውን የእስራኤል የቀለም ገበያ የተቆጣጠረውን ታምቡር ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ወ/ሮ አዜብ ጠቁመዋል፡፡

አዲስ የሚመሠረተው የቀለም ፋብሪካ ላይ መሰቦ፣ ኩስቶና ፌርፋክስ በጋራ ኢንቨስት እንደሚያደርጉ ታውቋል፡፡ ኤፈርት በሥሩ 14 ኩባንያዎች የሚያስተዳድር ሲሆን፣ ለ18,000 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠሩ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች