‹‹የምስክሩ ቃልና ትርጉሙ ሳይመረመር ሊታሰሩ አይገባም››
ተከሳሾች
‹‹አማርኛ የሚሰሙ ቻይናዊት ከማስቀመጣችን በተጨማሪ በሞባይል ቀርፀናል››
ዓቃቤ ሕግ
ግብርና ታክስ በማጭበርበር ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው የነበሩ የቻይናዊው ባለሀብት ድርጅት በሆነው ‹‹ሲሲኤስኮም ሰርቪስ ሶሉዩሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሠራተኞችን ክስ ለማቋረጥ፣ አምስት ሚሊዮን ብር ጉቦ ተቀብለዋል ተብለው ክስ በተመሠረተባቸው ተከሳሾች ላይ በምስክርነት የቀረቡ ቻይናዊ ምስክርነት ቃልን በአግባቡ አልተረጎሙም የተባሉ አስተርጓሚ ታሰሩ፡፡
ፍርድ ቤቱም ሆነ ዓቃቤ ሕግ የቻይና ቋንቋ (ማንዳሪን) ወደ አማርኛ የሚተረጉም በመጥፋቱ፣ በተከሳሾች በኩል ቢቀርብ እንደማይቃወም ዓቃቤ ሕግ በመስማማቱ፣ ተከሳሾች ከሕጋዊ ትርጉም ቤት አንድ አስተርጓሚ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምደብ 18ኛ ወንጀል ችሎት አቅርበው ነበር፡፡
ታኅሳስ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. አስተርጓሚው ለመታሰር ያበቃቸው የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሥራ ባልደረቦች በነበሩት ዓቃቢያነ ሕግ አበበ ብርሃኔና ጌታሰው ተሰማ፣ በግል ሥራ ላይ መሠማራታቸው በተገለጸው አቶ በላይነህ ፈንታና አቶ አክሊለ ብርሃን አባቡ፣ እንዲሁም በጠበቃው አቶ አብዮት ተስፋዬ ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክር ሆነው ለቀረቡት ቻይናዊ ግለሰብ አስተርጓሚ ሆነው በመቅረባቸው ነው፡፡
ቻይናዊው ምስክር ቃለ መሐላ ከፈጸሙ በኋላ የቻይንኛ ቋንቋን ወደ አማርኛ የሚተረጉሙትም ግለሰብ ቃለ መሐላ ፈጽመው ምስክርነቱ ተጀመረ፡፡ ዓቃቤ ሕግ ዋና ጥያቄ በማቅረብ ቻይናዊው ምስክርነታቸውን ለፍርድ ቤት ሲያስረዱ፣ ተርጓሚውም ቻይናዊው ምስክር ምን እንዳሉ በአማርኛ ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡
የዓቃቤ ሕግ ዋና ጥያቄ ተጠናቆ መስቀለኛ ጥያቄ ሳይቀጥል ችሎቱ የጠዋት ክፍለ ጊዜውን በማጠናቀቁ ለከሰዓት በኋላ ቀጠሮ ይዞ ተነስቷል፡፡
ችሎቱ ከሰዓት በኋላ የሚሰየም ቢሆንም ዳኞች ባለመሟላታቸው ሳይሰየም ከመቅረቱ በተጨማሪ፣ በአስተርጓሚነት ቀርበው የነበሩ ግለሰብ ዓቃቤ ሕግ እንደሚፈልጋቸው ተነግሯቸው ወደ ጽሕፈት ቤት መሄዳቸውን ተከሳሾች በአዳር ሲቀርቡ ሐሙስ ታኅሳስ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡ በዓቃቤ ሕግ ተጠርተው የሄዱት አስተርጓሚ ቻይናዊው ምስክር የመሰከሩትን በአግባቡ እንዳልተረጎሙ ተነግሮዋቸው፣ በፖሊስ ተይዘው ታስረው ማደራቸውን የተከሳሾች ጠበቃና አስተርጓሚው ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡
አስተርጓሚው በአግባቡ መተርጎም አለመተርጎማቸውን ዓቃቤ ሕግ እንዴት ሊያውቅ እንደቻለ በፍርድ ቤቱ ሲጠየቅ፣ ምስክሩንና አስተርጓሚውን በሞባይል መቅረፁን፣ እንዲሁም አማርኛ ቋንቋ የሚችሉ ቻይናዊትን ማስቀመጡን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ትርጉሙ በአግባቡ እንዳልተተረጎመ ያወቀበትን መንገድ ሲያስረዳ የሰሙት ተከሳሾች፣ የተቃውሞ አቤቱታቸውን ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡
ተከሳሾቹ በራሳቸውና በጠበቆቻቸው አማካይነት እንዳስረዱት፣ ዓቃቤ ሕግ በሞባይሉ መቅረፁ ሕገወጥ ነው፡፡ ከፍርድ ቤቱ በስተቀር የከሳሽንም ሆነ የተከሳሾችን ድምፅ ማንም መቅረፅ አይችልም፡፡ የተመሠረተባቸው ክስ ሕግን የተከተለ አይደለም፡፡ ምስክር ሆነው የቀረቡት ቻይናዊ ፎቶ ሲያነሷቸውና ሲቀርጿቸው እንደነበር አስረድተዋል፡፡
የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ባልደረባ የነበሩት ተከሳሽ ዓቃቤ ሕግ አበበ እንደገለጹት፣ በፍርድ ቤት ሥራ ላይ እያሉ እንደሚፈለጉ ተጠርተው ሲሄዱ፣ ወደ ፍሬንድሺፕ ወስደዋቸው እጅ ከፍንጅ እንደተያዙ ተደርጎ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እንደተነገረ አስረድተዋል፡፡
ሌላኛው ተከሳሽ አቶ አብዮት ደግሞ እየደረሰባቸው ያለውን በደል ፍርድ ቤቱ እንዲሰማቸው ጠይቀው፣ መጠቀስ የሌለበት የሰበር ውሳኔ ተጠቅሶ ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና መብታቸውን እንደተነፈጉ አስረድተዋል፡፡ በተለያየ ቦታ በፖሊስ ተይዘው ሁሉም ከእሳቸው መኪና ውስጥ እጅ ከፍንጅ እንደተያዙ ተደርጎ በመገናኛ ብዙኃን መነገሩም ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የምንፈልገው ፍትሕ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በመሀል ምንም ይባል ምንም የሚዳኙት እንደ ማንኛውም ዜጋ መሆኑን በመግለጽ እንዲረጋጉ አሳስቧል፡፡
የተከሳሾቹ ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ ደንበኞቻቸው በተለያየ ምክንያት ለሰባት ጊዜ መቀጠራቸውን አስታውሰው፣ ዓቃቤ ሕግ አስተርጓሚ በማጣቱ ተከሳሾች ቢያቀርቡ ተቃውሞ እንደሌለው መግለጹን በመናገር በቀረቡት ምስክር ላይ እምነት እንደሌለው መግለጹ ተገቢ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡
አስተርጓሚው በአግባቡ አለማስተርጎማቸውን ዓቃቤ ሕግ ከተጠራጠረ ወዲያውኑ ‹‹በሚሰጡት ትርጉም አልስማማም፤›› ብሎ ማስቆም ሲችል፣ ምንም ዓይነት የሕግ ድጋፍ በሌለበት ሁኔታ አስተርጓሚውን እንዲታሰሩ ማድረጉ ከሕግ ውጪ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አስተርጓሚው የተረጎሙትና ቻይናዊው ምስክር የመሰከሩት ቃል ከመቅረፀ ድምፅ ወጥቶና በሌላ አስተርጓሚ ተተርጉሞ ከተለያየ፣ ሕጋዊ መንገዱን ጠብቆ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ በማቅረብ ተርጓሚው ተጠያቂ ማድረግ ሲገባቸው፣ ያላግባብ እንዲታሰሩ ማድረጉ ተገቢ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ በዕለቱ አስተርጓሚው ችግር ፈጥረዋል ቢባል እንኳን፣ መዝገቡን በያዘው ችሎት በችሎት መድፈር ወይም በሌላ በመዝገቡ ላይ ሊጠየቁ ሲገባ፣ ወደ እስር ቤት መወሰዳቸው አግባብ እንዳልሆነ ጠበቆቹ ተከራክረዋል፡፡ በተጨማሪም ዓቃቤ ሕግ በሕገወጥ መንገድ በሞባይል የምስክሩንና አስተርጓሚውን ከመቅረፁ በተጨማሪ፣ አማርኛ የሚሰሙ ቻይናዊት ማስቀመጡ ለቀሪ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ሊያስጠኑ የሚችሉ መሆናቸውንም አስረድተው፣ በቀጣይ ችሎቶች እንዳይገቡ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው አመልክተዋል፡፡ የተረጋገጠ ነገር በሌለበት አስተርጓሚውም ሊታሰሩ እንደማይገባና መፈታት እንዳለባቸው አክለዋል፡፡
ጠበቆቹ ስለቀጣይ የምስክርነት አሰማም በሰጡት አስተያየት፣ የዓቃቤ ሕግ ምስክር በዋና ጥያቄ ላይ ምላሽ ሰጥተው ካጠናቀቁበትና በቀጣይ ከመስቀለኛ ጥያቄ እንዲጀምሩ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡ ገለልተኛ አስተርጓሚ ፍርድ ቤቱ እንዲመድብላቸውም አሳስበዋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ፣ አስተርጓሚው የሰጡት ትርጉም ለትክክለኛ ፍትሕ ስለማያግዝ ምስክርነቱ ከመጀመርያው ጀምሮ እንዲሰማ ጠይቋል፡፡ ገለልተኛ አስተርጓሚ ቢቀርብ እንደሚስማማ ወይም ተከሳሾችም ቢያቀርቡ እንደማይቃወም ተናግሯል፡፡ ሊያስተረጉም የቀረበው ሰው እጅ ከፍንጅ ወንጀል ሲፈጽም የተያዘ በመሆኑ፣ በሕጉ በተቀመጠው አግባብ መጠየቅ ስላለበትና ዓቃቤ ሕግም እንዲጣራ የማድረግ ኃላፊነት ስላለበት ያንን ማድረጉን ገልጿል፡፡ ቻይናዊቷ አማርኛ እንደማይችሉ (ቀደም ብሎ ይችላሉ ብሏል) ገልጾ፣ በችሎት እንዳይገቡ መከልከል እንደሌለባቸው አስረድቷል፡፡ ተከሳሾች በእስር ላይ ስለሆኑ ብዙ ሊናገሩ እንደሚችሉ ጠቁመው፣ ግን ምስክር ያስጠናሉ፣ ቪዲዮ ይቀርፃሉ የተባለው አግባብ አለመሆኑን በመግለጽ፣ ተከሳሾች ጓደኞቻቸው የነበሩ መሆናቸውን በመጠቆም፣ በእነሱ ላይ የማይሆን ነገር በማድረግ የሚያገኙትም ሆነ የሚያጡት ነገር እንደሌለ አስረድተው፣ ሥነ ምግባርን በጠበቀ ሁኔታ መከራከር ስለሚገባ ፍርድ ቤቱ ሥርዓት እንዲያስይዝ አሳስቧል፡፡
ታስረው የሚገኙት አስተርጓሚ መናገር እንደሚፈልጉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀው ሲፈቅድላቸው እንደተናገሩት፣ ከከሳሽም ሆነ ከተከሳሽ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም፡፡ ሲተረጉሙ ስህተት መሆኑን ዓቃቤ ሕግ ማስቆም ሲችል መታሰራቸው ተገቢ አይደለም፡፡ ዓቃቤ ሕግ እንደሚፈለጉ ጠርቷቸው ቢሮ ከሄዱ በኋላ፣ አብረዋቸው ወደ ቢሮ ከሄዱት ቻይናዊያን ጋር ዓቃቤ ሕግ በቢሮ ውስጥ ተነጋግረው ሲጨርሱ፣ ምንም ሳይጠየቁ በፖሊስ ወደ እስር ቤት መላካቸውንና እዚያም ምንም እንዳልተጠየቁ ገልጸዋል፡፡ የተረጎሙትና ቻይናዊው ምስክር የተናገሩት ተተርጉሞ እንዲነፃፀር ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ለሁለቱም ወገኖች እንደገለጸው፣ አስተርጓሚ ስለማያገኝ ሁለቱም ወገኖች ተመካክረው አስተርጓሚ እንዲያቀርቡ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ ሁለቱም ወገኖች ስላልተስማሙ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተርጓሚ እንዲልክ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ተከራካሪዎቹ ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተርጓሚ ያቅርብ ብሏል፡፡ አማርኛ ይችላሉ ወይም አይችሉም የተባሉት ቻይናዊት በሌላ ቀጠሮ ችሎት እንዳይገቡ የቀረበውን አቤቱታ እንዳልተቀበለው አስታውቋል፡፡ ከችሎቱ መቅረፀ ድምፅ ውጪ ማንም መቅረፅ እንደማይችልም አስጠንቅቆ፣ ዓቃቤ ሕግ መቅረፁ ተገቢ አለመሆኑን ገልጿል፡፡ ምስክሩ የተናገሩትና አስተርጓሚው የተረጎሙትን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጂውን ወስዶ ካዳመጠ በኋላ፣ ጥር 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርቦ በችሎት እንዲያስረዳ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ቀጣይ የምስክርነት ጊዜ ወደፊት እንደሚነገር አስታውቋል፡፡