Wednesday, February 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአገሪቱ የተከሰተውን ቀውስ ለማስቆም የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ ተጠቆመ

በአገሪቱ የተከሰተውን ቀውስ ለማስቆም የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ ተጠቆመ

ቀን:

በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰና በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለውን ቀውስ ለማስቆም፣ በርካታ የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ ተጠቆመ፡፡

የአገር መከላከያ ሚኒስትርና የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ጸሐፊ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ዓርብ ታኅሳስ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የፌዴራልና የክልል የፀጥታ ምክር ቤቶች የተካሄደው የጋራ ስብሰባ ከተጠናቀቀ በኋላ በሰጡት መግለጫ ነው ይህንን ያሉት፡፡ ከአንድ ወር በፊት በአገሪቱ ያለውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት በፌዴራልና በክልሎች የጋራ ምክር ቤት ዕቅድ ወጥቶና መግባባት ተፈጥሮ ወደ ሥራ በመግባት በርካታ ለውጦች ቢመዘገቡም፣ ሕገወጦችን በቁጥጥር ሥር ከማዋል አኳያ የሚቀሩ ሥራዎች አሉ ብለዋል፡፡

አቶ ሲራጅ እንደገለጹት፣ አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄዱ ሕገወጥ ሠልፎችና ግጭቶች አሉ፡፡

በአገሪቱ የሚታየውን የፀጥታ ችግር ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ያልተቻለበትን ምክንያት ምክር ቤቱ እንዴት ነው የገመገመው? የሚል ጥያቄ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ በየቦታው ለሚፈጠሩ የመንገድ መዘጋትና ሌሎች ችግሮች መሠረታዊ የሚባል ምክንያት ሊቀመጥላቸው እንደማይችል ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከመልካም አስተዳደርና ከልማት ጥያቄዎች ጎን ሆነው የሚገፋፉና በዘረኝነትና በተለያዩ ጉዳዮች ቅስቀሳዎች በመኖራቸው እንደሆነ ነው ማየት የተቻለው፤›› ብለዋል፡፡

አገሪቱ ካለችበት የፀጥታ ችግር ለመውጣት ከአንድ ወር በፊት በፌዴራልና በክልሎች የጋራ የፀጥታ ምክር ቤት የፀደቀው ዕቅድ እንደተገመገመ ተናግረው፣ አሁን  የተሻሉ አፈጻጸሞች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡

በዕቅድ ተይዘው ሲሠራባቸው ከነበሩ ጉዳዮች መካከል ዋነኛዎቹ በዋነኛ መንገዶች ላይ የነበሩ የመንገድ መዝጋት ችግሮች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ሰዎች በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ አንዳንዴም ዘርን በመለየት ጥቃት የሚፈጸምባቸው ቦታዎች ነበሩ፤›› ብለዋል፡፡ በዚህም የፌዴራልና የክልል የፀጥታ አካላት ተቀናጅተው በመሥራታቸው በዋና ዋና መስመሮች ላይ መሻሻሎች መታየታቸውንና ውጤት ማሳየታቸውን አስረድተዋል፡፡

በኦሮሚያ፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ተከስተው የነበሩ የፀጥታ ችግሮችን በፌዴራልና በክልሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም በአገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች አማካይነት የማስተማር ሒደቱ እንዲቀጥል መደረጉን አቶ ሲራጅ ጠቁመዋል፡፡ ይሁንና ሦስት ዩኒቨርሲቲዎች አሁንም ድረስ የማስተማር ሥራ እንዳልጀመሩ ተናግረዋል፡፡ የማስተማር ሥራቸውን ያልጀመሩ ዩኒቨርሲቲዎች እነማን እንደሆኑ ግን ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት የሁለቱ ክልሎች አመራሮችና የፀጥታ አካላት እጅ እንዳለበት የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ‹‹በተሠራው ከፍተኛ ሥራ በአንፃራዊነት የተሻለ ሰላም መፍጠር ተችሏል፤›› ብለዋል፡፡

የፌዴራልና የክልል የፀጥታ የጋራ ምክር ቤት ከአንድ ወር በፊት በአገሪቱ የተከሰተውን ቀውስ ለማስቆም ዕቅድ ማውጣቱንና በየአካባቢው የሚከሰተውን ግጭት ለማስቆም ለክልል አመራሮች ኃላፊነት መሰጠቱን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ጥቁር የመልበስ ውዝግብና የእምነት ነፃነት በኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኅዳር ወር ላይ በፓርላማ...

የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚቆጠጠር ገለልተኛ ተቋም ለመመሥረት እንቅስቃሴ ተጀመረ

ከ70 በላይ አዳዲስ የፋይናንስ ተቋማት ዘርፉን ሊቀላቀሉ ነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ...

እስቲ አንገፋፋ!

እነሆ መንገድ። ጊዜና ሥፍራ ተጋግዘው በውስንነት ይዘውናል። መፍጠን ያቃተው...