ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ሁሉን ዓይነት አገልግሎቶች የሚሰጡ ግዙፍ ግንባታዎችን ለማካሄድ የወጣው ጨረታ፣ የኢትዮጵያ ደረጃ አንድ ሥራ ተቋራጮች ማኅበርን አስቆጣ፡፡
ግዙፍ አገር በቀል ኮንትራክተሮች የሚገኙበት የኢትዮጵያ ደረጃ አንድ ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ለተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ታቃውሞውን እየገለጸ ሲሆን፣ ማኅበሩ ለሪፖርተር እንዳስታወቀው ጨረታው የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን ያገለለና አገሪቱንም ለኪሳራ የሚዳርግ ነው ብሏል፡፡
ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ ታኅሳስ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ሁለቱ ምክር ቤቶች የሚገለገሉባቸውን የተለያዩ ግንባታዎች የሚያካሂዱ ኮንትራክተሮችን ለመምረጥ ዓለም አቀፍ ጨረታ አውጥቷል፡፡
ጨረታው ለአንድ ወር ከቆየ በኋላ ጥር 8 ቀን 2010 ዓ.ም. በይፋ ይከፈታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በባለሙያዎች ግምት እስከ አራት ቢሊዮን ብር ይፈጃል የተባለው ግዙፍ ግንባታ የሚካሄደው፣ አራት ኪሎ አካባቢ ከታላቁ ቤተ መንግሥት ዋናው በር ፊት ለፊት በሚገኝ መሬት ላይ ነው፡፡
በጨረታ ሰነዱ ላይ እንደተገለጸው ቦታው 69,232,40 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ የተለያዩ አገር በቀር አማካሪዎች ተሳትፎ ያደረጉበት ቅድመ ዲዛይን ተሠርቶለታል፡፡ በጨረታ ሰነዱ በግልጽ የተቀመጠው ዲዛይንና ግንባታን በአንድ ላይ የሚያካሂድ ኮንትራክተር መምረጥ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ደረጃ አንድ ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ግዙፍ መንግሥታዊ ተቋማት ለአብነት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ኢትዮ ቴሌኮም የሚያስገነቧቸው ግዙፍ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃዎች ዲዛይንና ግንባታ በአንድ ላይ በማድረግ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን አቅም ያላገናዘቡ መሥፈርቶችን በማውጣት የውጭ ኮንትራክተሮችን መቅጠራቸው፣ አሁን ደግሞ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ታሪካዊ ዳራ ያለውን ግዙፍ ግንባታ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ሊያሳትፍ የማይችል፣ ይልቁንም ለውጭ ኮንትራክተሮች የተመቻቸ ጨረታ ይፋ መደረጉ አሳስቦአቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ደረጃ አንድ ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ቦርድ ጸሐፊ አቶ ሙሉጌታ ገሠሠ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው መንግሥታዊ ተቋማትና የግል ኩባንያዎች ለሚያካሂዷቸው ግዙፍ ግንባታዎች የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች የማግለል አዝማሚያ ነው፡፡
አቶ ሙሉጌታ ሦስት ነጥቦችን አንስተው የማኅበራቸውን አቋም አብራርተዋል፡፡ የመጀመርያው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ራሱን የቻለ የግንባታ ተቋም እንደመሆኑ የአሠሪዎቹ ወኪል ሊሆን አይገባም፡፡ ሁለተኛው በአሁኑ ወቅት እየተለመደ የመጣው የዲዛይንና የግንባታ ሥራን አንድ ላይ ለአንድ ኩባንያ መስጠት በኢትዮጵያ ሕጋዊ መሠረት የሌለው መሆኑ ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ አሠሪው አንድ ጊዜ መቶ በመቶ ክፍያ የሚፈጽም በመሆኑ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች በዋጋ ልዩነት ችግር ውስጥ የሚያስገባቸው ይሆናል የሚል ነው፡፡
በጨረታ ሰነዱ የወጡት መሥፈርቶች ለአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ፈታኝ በመሆናቸው፣ የውጭ ድርጅቶች በተለይ የቻይና ኮንትራክተሮች ሥራዎችን እየተቀራመቱ አገር በቀል ኮንራክተሮቹ ደግሞ በአንፃሩ ከጨዋታ ውጪ እየተደረጉ ነው ተብሏል፡፡
ይህ በመንግሥት ተቋማትና በግል ኩባንያዎች እየተዘወተረ የመጣ አዲስ አዝማሚያ ለኮንትራክተሮች ብቻ ሳይሆን ለአርክቴክቶችም ሥጋት መሆኑ ተገልጿል፡፡
ውሂብ ከበደና ተባባሪዎቹ አርክቴክቶችና አማካሪ መሐንዲሶች ባለቤትና ዋና ዳይሬክተሮች አቶ ውሂብ ከበደ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የዲዛይንና የግንባታ ጉዳይ ለሁሉም ነገር መፍትሔ ይመስል እየተዘወተረ መጥቷል ይላሉ፡፡
‹‹ዲዛይንና ግንባታ በኢንዱስትሪያል ምደባ ውስጥ በኢትዮጵያም ሆነ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አልተጠቀሰም፡፡ አንድ ድርጅት በሌለ ጉዳይ ይህን ለማድረግ ማሰቡ ልክ አይደለም፡፡ ሕገወጥ ነው፤›› ሲሉ አቶ ውሂብ ገልጸው፣ ‹‹ዲዛይንና ግንባታ በአንድ ለማካሄድ ማሰብ እብሪት ነው፤›› ሲሉ አቶ ውሂብ የአዲሱን አዝማሚያ አደገኛነት አስገንዝበዋል፡፡
በተለይ ለሕንፃ ግንባታዎች አማካሪ ድርጅቶች መኖር ወሳኝ ነው በማለት፣ መንግሥት ይህንን ጉዳይ በፅሞና ሊመረምር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከግዙፍ ግንባታዎች በተለይ ከሕንፃ ግንባታዎች ዘርፍ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች እየወጡ፣ በአንፃሩ የቻይና ኩባንያዎች እየተተኩ መሆናቸው አደገኛ መሆኑንና አገሪቱን አቅም እያሳጣና ከፍተኛ ሀብትም ከአገር እንዲወጣ እያደረገ መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡