Tuesday, October 3, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

አገርም ሕዝብም ተንፈስ ይበሉ!

አገርን እንደ ንፋፊት ቀስፎ የያዛትን ውጥረት የሚያረግብ ተስፋ ሲሰማ ሕዝብ  ተንፈስ ይላል፡፡ ሰሞኑን ከገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ አመራሮች የተሰማው ራስን መውቀስና ወደ ትክክለኛው ጎዳና የመመለስ ተስፋ አገርንም ሕዝብንም ተንፈስ ያደርጋል፡፡ የኢሕአዴግ አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ በውስጣቸው የነበረውን ፀረ ዴሞክራሲ አስተሳሰብና አሠራር በማስወገድ አገርንና ሕዝብን የሚያስቀድም ዴሞክራሲያዊ አሠራር ለማስፈን በቁርጠኝነት መነሳታቸውን አስታውቀዋል፡፡ ምንም እንኳ ይህ ዓይነቱ የተስፋ ቃል ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሲነገር የነበረ ቢሆንምና አሁንም መጠራጠር ቢኖርም፣ ካሁን በኋላ ወደ ቀድሞ አላስፈላጊ ድርጊቶች መመለስ አደገኛ መሆኑን አፅንኦት መስጠታቸው በበጎ ጎኑ ሊታይ ይገባል፡፡ የአገሪቱን የተበላሸ የፖለቲካ ምኅዳር ለማስፋትና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ለማስጀመር፣ በፖለቲካ ምክንያት የታሰሩ ዜጎችን ለመፍታትና በብዙዎች ዘንድ በጭካኔ ድርጊቱ የሚታወቀው ማዕከላዊ የምርመራ ቢሮ ተዘግቶ ሙዚየም እንዲሆን ውሳኔ ላይ መደረሱ በራሱ አንድ ጅማሬ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በዚህ ምክንያት እንኳን አገርም ሕዝብም ተንፈስ ይላሉ፡፡

ለዓመታት በአገሪቱ ውስጥ የተገኙ መልካም አጋጣሚዎችን ለመጠቀም ባለመቻሉ ምክንያት ብቻ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሰናከሉ፣ ለሕዝብ ምሬት መጨመር ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ተዘጋግቶ ምርጫ መቀለጃ መሆኑ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተንኮታኩተው መውደቃቸው፣ በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና የተሰጣቸው መሠረታዊ መብቶች ሥራ ላይ መዋል አለመቻላቸው፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መብዛታቸው፣ ዜጎች በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት የጥቃት ሰለባ መሆናቸው፣ ፍትሕ መጥፋቱ፣ ኢፍትሐዊ የሆኑ ብልሹ አሠራሮች መንሰራፋታቸው፣ እኩልነት ጠፍቶ ጥቂቶች እንዳሻቸው መሆናቸው፣ ወዘተ. አገርን እንደ ውጋት ቀስፈው የያዙ በሽታዎች ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ድርጊቶችን አሽቀንጥሮ በመጣል በሕግ የበላይነት ሥር የሚተዳደር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ዋናው መሠረቱ፣ በችግሮቹ መሠረታዊ መንስዔዎች ላይ መተማመንና የጋራ መፍትሔ መፈለግ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሰሞኑን የኢሕአዴግ አመራሮች እንዳሉት መጀመርያ ድርጅታቸው ዴሞክራሲን ይላበስ፡፡ ውስጠ ድርጅት ዴሞራክሲው መልክ መያዝ ካልቻለ ዴሞክራሲን ማስፈን ከቶውንም አይቻልም፡፡ ስለዚህ የተናገሩትን በተግባር ለማረጋገጥ የሚችሉት ዴሞክራሲን ከእነ ሙሉ ክብሩ ሲላበሱ ነው፡፡ ያኔ ሕዝብና አገርን ቀስፎ የያዘው ውጋት ይለቃል፡፡ 

ኢሕአዴግ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱና እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን ሙሉ በሙሉ ማስቆም የሚችለው፣ በውስጡ የተፈጠረውን ሽኩቻ በዴሞክራሲያዊ መንገድ መፍታት ሲችል ብቻ ነው፡፡ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ቡድን ድረስ የሚታዩ አላስፈላጊ ድርጊቶችን በፍጥነት በማስወገድ፣ ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅም ሥራ ማከናወን ይጠበቅበታል፡፡ በውስጡ የነበሩ መጠራጠሮችና አለመተማመኖች የተፈጠሩት ሕገወጥ ድርጊቶች በመብዛታቸው መሆኑን ማመን ይገባል፡፡ ከሥልጣን በላይ አገር አለ፣ ከጥቅም በላይ ሕዝብ አለ፡፡ ሥልጣንና ጥቅምን ብቻ ማዕከል ያደረጉ ለሕዝብና ለአገር የማይበጁ ድርጊቶች፣ ግጭት በመቀስቀስ ንፁኃንን ሰለባ ከማድረግ ውጪ የፈየዱት የለም፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖችን ከማፈናቀል በተጨማሪ በርካቶችን የአካል ጉዳተኛ ነው ያደረጉት፡፡ የደሃ አገርን ሀብት ነው ያወደሙት፡፡ በዚህ ምክንያት የአገር ህልውና አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ወድቆ ሕዝብ ለከፍተኛ ሥጋት ተዳርጓል፡፡ የአገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የብሔር ግጭት መቀስቀሻ መሆናቸው ደግሞ ሌላው ራስ ምታት ነበር፡፡ ዴሞክራሲ በሌለበት ቀውስ መከተሉ አይቀርም፡፡ የአገሪቱ ፖለቲካ አቅጣጫ መጠቆሚያ እንደሌለው ጀልባ በወጀብ እየተገፋ ብዙዎች ተስፋ ቆርጠዋል፡፡ መንግሥት የሌለ ይመስል በየቦታው ሥርዓተ አልበኝነት እየነገሠ ከፍተኛ ጥፋት ደርሷል፡፡ አገርና ሕዝብም ውጥረት ውስጥ ከርመዋል፡፡ ይህ ውጥረት ረግቦ መተንፈስ ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ ቀደም በስፋት ይታይ የነበረው ፀረ ዴሞክራሲ አመለካከት ወደ አክራሪ ብሔርተኝነት ተለውጦ፣ ዜጎች በገዛ አገራቸው ውስጥ ባዕድነት የሚፈጥርባቸው ስሜት በስፋት እንዲሠራጭ ተደርጓል፡፡ ለዴሞክራሲያዊና ለሰብዓዊ መብቶች ትኩረት በመነፈጉ በርካታ ጉዳቶች ደርሰዋል፡፡ ተቃውሞን በሠለጠነ መንገድ ማስተናገድ አቅቶ ብዙዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ብዙዎች  ተሰደዋል፡፡ በዚህ የተነሳም አገሪቱ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ብዙ ጊዜ ተወንጅላለች፡፡ ሕዝብ የሚያዳምጠው መንግሥት በማጣቱ በተለይ ላለፉት ሁለት ዓመታት አገሪቱ ነውጥ ውስጥ ገብታለች፡፡ የደረሰውን ጥፋትም እናውቀዋለን፡፡ አሁን ወደ ኋላ መመለስ አይቻልም፡፡ በነበሩ ችግሮች ላይ ተማምኖ በአስቸኳይ አገሪቱንና ሕዝቧን ከማጥ ውስጥ ማውጣት ይገባል፡፡ በተለይ የመንግሥትና የገዥው ፓርቲ ሚና መደበላለቅ ማብቃት አለበት፡፡ መንግሥታዊ ተቋማት ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ሆነው መደራጀት አለባቸው፡፡ የፀጥታ ኃይሎች የፓርቲ ተቀጥላ መሆን የለባቸውም፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማት በነፃነት እንዲሠሩ መደረግ አለበት፡፡ የሲቪክ ማኅበራት ማበብ አለባቸው፡፡ ሕግ አውጪ ፓርላማው አስፈጻሚውን መንግሥት በብርቱ መቆጣጠር አለበት፡፡ ሕግ ተርጓሚው በነፃነት ሥራውን እያከናወነ ፍትሕ እንዲሰፍን መደረግ አለበት፡፡ ካሁን በኋላ በጉልበት ሳይሆን የሕግ የበላይነት ብቻ ነው መከበር ያለበት፡፡ ይህ ሲሆን አገርና ሕዝብ በነፃነት ይተነፍሳሉ፡፡

የአሁኑ በጎ ጅምር የመላው ሕዝብ ድጋፍ ሊቸረው ይገባል፡፡ የተገባው የተስፋ ቃል ባክኖ እንዳይቀር ሕዝብ ግፊት ማድረግ አለበት፡፡ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ አዛውንት፣ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አዲሱ ጅማሬ በተግባር ጎልብቶ ውጤት ያፈራ ዘንድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበርክቱ፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት ሐሳባቸውን የሚያካፍሉ ዜጎች ከጨለምተኛ አስተሳሰቦች በመላቀቅ ጠቃሚ ምክሮችንና ልምዶችን ያጋሩ፡፡ በተለያዩ ጎራዎች በመሠለፍ የቡድን ጥቅምን ታሳቢ ያደረጉ ጭቅጭቆችና ውዝግቦች ለአገርም ሆነ ለሕዝብ ፋይዳ የላቸውም፡፡ በእልህና በግትርነት ላይ የተመሠረቱ ጉንጭ አልፋ ክርክሮች ሳይሆኑ የሚጠቅሙት፣ ወደፊት የሚያራምዱ የለውጥ ሐሳቦችን ማፍለቅ የተሻለ ነው፡፡ በተቃውሞ ጎራ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላትና አመራሮችም ለአዲሱ ጅማሬ የሚጠቅሙ ነገሮች ላይ በማተኮር ከአረንቋ ውስጥ መውጣት አለባቸው፡፡ ወቅቱ አገርን ከውድቀት የመታደጊያ እንጂ፣ የቆዩ ቁስሎችን እያነካኩ ማመርቀዝ ለማንም አይጠቅምም፡፡ በተለይ ከተበላሸው የፖለቲካ ግንኙነት ጋር የተያያዙ ችግሮችን በማስወገድ፣ ለአዲሱ ጅማሬ የሚጠቅሙ ግንኙነቶችን ለመፍጠር ራሳቸውን በብቃት ያዘጋጁ፡፡ ሌሎችን ከመውቀስ ባልተናነሰ ራሳቸውንም ይፈትሹ፡፡ አገርና ሕዝብ ተንፈስ እንዲሉ ከተፈለገ ዋናው ቁም ነገር ከዘመኑ ፍላጎት ጋር መጣጣም መቻል ነው፡፡ አሰልቺው ስህተት ላይ ተቸክሎ ለውጥ መጠበቅ ጊዜ አልፎበታል፡፡

በአጠቃላይ ይህች ታሪካዊ አገርና ይህ ኩሩ፣ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ መከበር አለባቸው፡፡ ከሥልጣን በላይ የአገርና የሕዝብ ህልውና ይቅደም፡፡ ከጥቅም በላይ አገርና ሕዝብ ይከበሩ፡፡ በጎራዎች ተቧድኖ አገርን ማፍረስ ይቁም፡፡ ሕዝብን ማሳቀቅ ይብቃ፡፡ ዴሞክራሲን እያነበነቡ ፀረ ዴሞክራሲ አዘቅት ውስጥ መዘፈቅ ኋላቀርነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ የሚታወቀው በመከባበር፣ በመረዳዳትና በመተሳሰብ ተምሳሌትነቱ ነው፡፡ ችግር ሲፈጠር እንደ ባህሉ የሚፈታበት አርዓያነት ያለው ልምድ አለው፡፡ ከአገሩ በላይ ምንም ስለሌለው አገሩን ለጥቅም አሳልፎ ሰጥቶ አያውቅም፡፡ ይልቁንም ለአገሩ በፍቅር መስዋዕትነት ሲከፍል የኖረ አንፀባራቂ ታሪክ ያለው ጀግና ሕዝብ ነው፡፡ ይህንን ሕዝብ አክብሮ ማገልገል አለመቻል የትውልድና የታሪክ ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ኢሕአዴግም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ከምንም በላይ ሕዝብን አክብሩ፡፡ ለሕግ የበላይነት ዋጋ ስጡ፡፡ በሰጥቶ መቀበል መርህ ተነጋገሩ፡፡ ዴሞክራሲ በተግባር እንዲሰፍን ውስጣችሁ ያለውን ፀረ ዴሞክራሲ አመለካከት ሙልጭ አድርጋችሁ አራግፉ፡፡ ይህንን ማድረግ ሲቻል አገርና ሕዝብ ይተነፍሳሉ፡፡ በተለይ ኢሕአዴግ የገባውን ቃል ያክብር፡፡ ከተለመደው አሰልቺና አደናጋሪ ፕሮፓጋንዳ በመላቀቅ ሕዝባዊነትን ይላበስ፡፡ ቃሉን በተግባር ያረጋግጥ፡፡ ይህ ቃል እንዲከበር ዜጎች በሙሉ ድጋፍ ያድርጉ፡፡ በዚህም አገርም ሕዝብም ተንፈስ ይበሉ!  

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የባለሥልጣናትና የባለሀብቶች ግንኙነት ሥርዓት ይኑረው!

በሕዝብ ድምፅ ሥልጣን የያዘ ፓርቲ የሚመሠርተው መንግሥት ከምንም ነገር በፊት ለሕግና ለሥርዓት መከበር ኃላፊነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንን ኃላፊነት በሚገባ ሊወጣ የሚችለው ሥራውን በግልጽነትና በተጠያቂነት...

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...